Tidarfelagi.com

የቤተሰባችን ፎቶ

….አቤት የቤተሰብ ፎቶዋችን ማማሩ! የጥርሳችንንጣቱ! የሳቃችንድምቀቱ!
አባዬ እበርበት ይመስል እኔን ጥብቅ አድርጎ አቅፏል፡፡
እማዬ ይበርባት ይመስል ናሆምን ጥብቅ አድርጋ አቅፋለች፡፡
እኔ እና ናሆም ያለን ጥርስ ሁሉ እስኪታይ ስቀን ከእናትና አባታችን ስር እንደጉልቻ ቁጭ ቁጭ ብለናል፡፡
የሚያስቀና አራት ጉልቻ፡፡
እዩት የእማዬን ሳቅ!
አባዬ ሚስቱን ከመደብደብ ቀናት በአንዱ በቦክስ ሲነርታት ያወለቀው ጥርሷ የት እንደገባ እንጃ የሚታየው እህል ነክቶ የማያውቅ የሚመስለው ነጫጭ ጥርሷ ብቻ ነው፡፡
ለወትሮው አይኖችዋን እንደ አጥር የሚከበው ደማቅ ጥቁር ብልዝ ፎቶው ላይ የለም፡፡
አባዬ ‹‹ደሞ ምን ለመሆን ነው ልጅ ከወለዱ እንዲህ አይነት ልብስ መልበሱ!›› እያለ ስለሚቆጣት ብዙ ጊዜ የማትለብሰውን እጅጌው ጥሩምባ አበባን የሚመስል መአት አበበቦች የፈሰሱበት ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ቀለሙ አይን የሚያደነቁር ቀይ ነው፡፡
ከእድሜዋ ፈጥኖ ለእርጅና እና ማዲያት እጅ የሰጠው ፊትዋ በእጅ ስራ ቆንጅቷል፡፡
እማ ፍክት ብላለች፡፡ እማ አበባ ነገር ሆናለች፡፡
አባዬን እዩትማ!
ከእማዬ ጥርስ ድምቀት ጋር የሚፎካከረው የወርቅ ቀለበቱ ብልጭታ እጁ ላይ ትንሽ ፀሃይ ያለ አስመስሎታል፡፡
ይሄ አብረቅራቂ የጋብቻ ቀለበቱ ከማያልቀው
ጭቅጨቃቸው ባንዱ ቀን
‹‹እንዲያውም ያውልሽ! ካንቺ ጋር ያለኝ ትዳር በዚህአብቅቷል!›› ብሎ ሽንትቤት የወረወረው ነው፡፡ እማዬ በምልጃና በልመና ጎትታ አወጣችው እንጂ!
የለበሰው ደማቅ ሮዝ ሸሚዝ ከጥቁር በሮዝ መስመር መስመር ከረቫቱ ጋር ፍፁም ተቀናጅቷል፡፡ ይሄን ከረቫት ‹‹ካንቺ የማያልቅ ጭቅጭቅ ለመገላገል በዚህ ተንጠልጥዬ በሞትኩ!›› እያለ እማዬን የሚያስፈራራበትና አብዝቶ የሚለብሰው ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማታ ማታ ፣ ያውም በተመሳሳይ ሰአት ፤ ትልቅ ስልኩን ይዞ እየተንሾካሾከ እያወራ ወደ ሽንትቤት ሲሮጥ ሲሮጥ ብቻ የማውቀው ሳቁ ያምራል፡፡
ናሆምዬ፣
ቀኝ እጁ ፎቶው ከመነሳቱ ሰከንዶች በፊት የተቀማውን ‹‹ሎሊፖፕ›› ለመያዝ እንደተስተካከለ ተንከርፍፎ ቀርቷል፡፡ የአባዬን ስልክ ነካክቶ እየከፈተ ለእማዬ መስጠት ከጀመረ ወዲህ አባዬ ሊደልለው በየቀኑ የሚገዛለትን ሎሊፖፕ ነበር የያዘው፡፡ እማዬ ፎቶ ውስጥ አይገባም ብላ እስክትነጥቀው፡፡
ክንፍ እስከሚያካክሉት ትልልቅ ጆሮዎቹ በተዘረጋው ሰፊ ፈገግታው መሃል በቅርብ የወለቀው ጥርሱ ትቶት የሄደው ክፍተት ይታየኛል፡፡ የእማዬን ወላቃ ጥርስ በጥበቡ የደፈነው ፎቶ አንሺያችን የናሆምን መርጦ መተዉ ገረመኝ፡፡
‹‹ይሄን ሳተላይት ጆሮ የወረስከው ከአባትህ ነው.. እሱንጠይቀው››፤ ትለዋለች እማዬ ትምህርት ቤት በጆሮዬ ትልቀት ሳቁብኝ ብሎ እያለቀሰ ሲነግራት፡፡ ያለችውን አምኖ አባዬን ሲጠይቅ የናሆም ጆሮ የዘር ግንድ አዲስ የጭቅጭቅ ማገዶ ይሆናል፡፡
እነሱ በጩኸት ሲጨቃጨቁ የሳሎኑን ጥግ ይዞ ሲያለቅስ የማየው ልብ ሰባሪ ፊቱ እዚህ የለም፡፡
እኔ፣
አርቴፊሻል ፈገግታዬ ለፊቴ እንግዳ የሆነበት አይመስልም፡፡ ጥርሴ እንኳን ከአመት ጀምሮ ከትምህርት ቤታችን ሶስት አጥር ዘልሎ ካለው መርኬ ጫት ቤት እየሄድኩ ከብዙ ጎረምሶች ጋር ታጅዬ ጫት ሳሻምድና ሺሻ ሳጨስ እንደምውል አያሳብቅም፡፡
አገጬን ሊነካ ምንም ያልቀረው ቢትልስ ሹራቤ ትላንት መርኬ ጓዳ፣ ጥግ ያለው ፍራሽ ላይ፣ የሰሞኑ ጓደኛዬ መሳይ በአንገቴ ላይ የሰራውን ገድል ማስታወሻ ሸፍኖታል፡፡
አቀማመጤ እንደጨዋ ልጃገረድ ሰብሰብ፣ ቆጠብ ያለ እና ከረጅም ቀሚሴ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ አባዬ፣ ድሮ ሁሉን ነገር እነግረው በነበረ ጊዜ ያቅፈኝ እንደነበረው ስላቀፈኝ፣ ከአስተቃቀፉ ጋር የድሮን ፅህናዬን ለማምጣት ባደረግኩት ከፍተኛ ጥረት ያመጣሁት አቀማመጥ አይመስልም፡፡
ያቀፈኝ እጁን አያያዜ ጥብቅ ያለና አትልቀቀኝ የሚል ይመስላል፡፡ ‹‹አባዬ መልሰኝ..አባዬ ልጠፋ ነው መልሰኝ›› የሚል፡፡ ከቤታችን ሰላም ጋር አብሮ የጠፋውጨዋነቴን በአባቴ እቅፍ ውስጥ እፈልግ ይመስል የምለምነው ይመስላል፡፡
….አቤት የቤተሰብ ፎቶዋችን ማማሩ! የጥርሳችን ንጣቱ! የሳቃችን ድምቀቱ!
የምፈልገው ቤተሰብ ፎቶአችን ላይ ያለውን ነው፡፡
የምመኘው ቤተሰብ ፎቶአችን ላይ ያለውን ነው፡፡
አሁን አሁን የምፀልየው ፎቶው ላይ እንዳለው ያለ ቤተሰብ እንዲሰጠኝ ብቻ ነው፡፡

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...