Tidarfelagi.com

የቀይ ልክፍት

 “ጥሬ ስጋ በቀይ ወይን ምሳ ልጋብዝሽ” ብሎ ነው የጀመረኝ።
“በደስታ” አልኩኝ። ጥሬ ስጋ ነፍሴ እንደሆነ ማንም ያውቃል።……
“ምሳ በልቼ አሁን መጣሁ” ብዬ ከቤት ወጥቼ የሚቀጥለውን ቀን ምሳ በልቼ ተመለስኩ።
በቁርጥ ሰበብ ስንቋረጥ ዓመት ሆነ።……
“ሜዬ ገብቶልሻል ይሄ ልጅ! “ይሉኛል ጓደኞቼ……
በፍፁም! በጠዋት ደውሎ ካላሳቀኝ ደህና ዋዪልኝ ካላለኝ ደህና አልውልም እንጂ ፍቅር አልያዘኝም። ደሞ ምሳ ሰዓት ላይ ደውሎ “የት ነሽ? እ? ልይሽ? ” ካላለኝ እህሉን እንደቀሙት ህፃን እነጫነጫለሁ እንጂ ፍቅር አልያዘኝም። ማታ ደውሎ ደህና እደሪ ካላለኝም አድራለሁ እንቅልፍ በዓይኔ አይዞርም እንጂ……
“ኸረ ሜዬ ገብቶልሻል! ” ይሉኛል ጓደኞቼ ለወትሮው ስንገናኝ አዲስ ስለወጣ መፅሃፍ በመጨቃጨቅ የምናጠፋውን ቅዳሜ ከሰዓት እኔ አዲስ ስለሆነው የኔ ታሪክ፣ የነገረኝን ቀልድ ፣ የሄድንበትን ቦታ…… እያጎረሰኝ የበላነውን ምግብ… ስቀድላቸው ማታ 2 ሰዓት ሆኖ ስለተለያየን እኮ ነው። እኔ ልጅት በፍፁም!
“ኤጭ አሁንስ ተጃጃልሽ! “ይሉኛል ደግሞ። አዲስ ጫማ ልጦኝ ከአራት ኪሎ ፒያሳ በለሊት ቼቼ አድርጎ እንዳደረሰኝ ልነግራቸው የትከሻውን ስፋት… የአንገቱን ስር ጠረን… ላስረዳቸው አንድ ሰዓት ከ59 ደቂቃ ስለወሰደብኝ።
“ማፍቀርስ እንዳንቺ ከሆነ አይፈቀር! ” ይሉኛል። እሱ እወዳለሁ ያለውን ቀይ ጥፍርቀለም ፍለጋ 16 ተኛ ቀይ ጥፍርቀለሜን እያጋዙኝ በቀደም ለት የእግሬን ጥፍሮች ሊቀባልኝ ብሎ እንዴት እንዳበለሻሸው ስነግራቸው ብቻዬን እየሳቅኩ ስሽኮረመም እኮ ነው። እስኪ አሁን ይሄ ማፍቀር ነው? እነሱ ሳያዩ የገዛሁትን 10 ቀይ ጥፍር ቀለም ቢያውቁ ምን ሊሉ ነው?
“አይ እንግዲህ በቃሽ አንቺ ከሰሙሽ እንዴት እንዳደረገኝ አድርጌ ላሳያችሁ ትያለሽ! ” ይሉኛል ደግሞ። እሱ የሚወደውን ቀይ ፒኪኒና ጡት ማስያዣ ቁጥሩን ለማላውቀው ጊዜኛ ለመግዛት ቡቲክ ባየሁ ቁጥር እያስቆምኳቸው በቀደም ለት እንዴት እንዳገላበጠኝ ስነግራቸው።
(እህእ ቺኮች ከልጁ ፎንቃ ሊይዛችሁ ነው እንዴ? ኸረ ተበተኑ አግብቷል)
“አዎን አፍቅሬዋለሁ! “
በሁለተኛው ዓመት የሆነ ቀን እቤቴን ከሳሎን መኝታ ቤት፤ ከጓዳ ሳሎን እየተዘዋወርኩ እያየሁት እኔ የምወደው ሳይሆን እሱ የሚወደው ቤት እንደሆነ ሳይ…… ሶፋዬ እሱ በሚወደው ግራጫማ ቀለም ሶፋ ተቀይሯል። ምንጣፉ እሱ የሚወደው ብርማ ቀለም… የቤቱ ግድግዳ ቀለም… ሌላው ቀርቶ የጓዳ እቃዎቼ…… ሁሉም እሱ እወዳቸዋለሁ ያላቸው ናቸው። አንድ ሎከር ሙሉ ቀይ ፒኪኒና ጡት ማስያዣ.… ሺቲ የምትለብስ ሴት አልወድም ማለቱን ተከትሎ የነበሩኝን 6 ሺቲዎች የሰፈራችን ልብስ ሰፊጋ ቁምጣና ቦላሌ ማስደረጌን ታዝቤ……
“አዎን አፍቅሬዋለሁ።” አመንኩ።
በምንም ምክንያት የማይሰረዘውን ለዓመታት የኖረ የጓደኞቼን የቅዳሜ ከሰዓት ስብስብ ከሱ ጋር ለመሆን ስሰርዝ፤ የቤቴን አንድ ቁልፍ ስሰጠው……
“አዎ ተጃጅያለሁ።” አመንኩ
ይህችኛዋ ሰራተኛሽ ወጧ አይጣፍጥም ቀይሪያት ሲለኝ የምወዳትን ልጅ ደመወዟን ሰጥቼ ሳሰናብታት፤ ይሄ ጓደኛሽ አይነውሃው አላማረኝም ሲለኝ ጓዴን የአይንህን ቀለም ካልቀየርክ ብዬ ስተጋተግ……
“አዎ ነፍዣለሁ።” አመንኩ።
በሶስተኛው ዓመት የሆነ ቀን ላይ……
“ቀይ ሴት በጣም ነው የምወደው! ” አለኝ…… ቀይ ሚስቱን ፍለጋ ከቤቴ ወጣ… የሚወደውን ነገር እየፈለግኩ ሳደርግለት አይደል ሶስት ዓመት ያለፈው? ልቤ ሌላ ስራም ልምድም አልነበረውም አይደል? ልቤ ተከትሎት ቀይዋን ሚስቱን ሊያፋልገው እንደወጣ አልተመለሰም ። ቀይ ወንድ ላግባለት ይሆን?
“አሁን ጅልም እብድም ነው የሆንሽው! “አሉኝ ጓደኞቼ
፠፠. ፠፠. ፠፠፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...