Tidarfelagi.com

የሴቶች ካቴና!

ይህች ፅሁፍ ባለፈው ዓመት “በአዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ወታ ነበር፡፡ በጊዜው ትንሽ ተነካክታ ስለነበር ኦርጅናል መልኳን እንዲህ አቅርበናል፡፡

የሴቶች ካቴና!

ሰልችተውኛል፡፡ አንዷ ከአንዷ በቁመት፣ በመልክ፣ በሰውነት ቅርፅ ቢለያዩ እንጂ በአዕምሮ አንድ ሆነውብኛል፡፡ ብዙ ሴቶችን አይቻለሁ፡፡ ያው ናቸው፡፡
ለፍቅር ስሱ ነኝ፡፡ ቶሎ እወዳለሁ፡፡ በፍቅር ውስጠጥ እንዳለሁ ልታቆኝ የምትችል ሴት ግን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ወድጃት፣ ወዳኝ…. ሙዳችንና ኮከባችን እና ከንፈራችን ገጥሞ ባለንበት ሰዓት መሳሳማችንን አቋርጣ፤ “ትወደኛለህ?” ትለኛለች፡፡ ብስቅ!! ደሜ ይፈላል፡፡ አንዲት ሴት እንዲህ ካለችኝ በቃ ጠላኋት፡፡ አብሬያት መቆየት ይቀፈኛል፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉም ሴቶች “የወል በሽታ” ነው፡፡ ሄደው ሄደው “ትወደኛለህ?” ከሚል የጥያቄ አጥር የማላተም ተፈጥሮ!

ከሳምኳት፣ ካቀፍኳት፣ ጊዜዬን ከሰጠኋት አይበቃም? ምን ማለት ነው ትወደኛለህ፣ አትወደኝም እየተባባሉ እንደማይተማመን ባልንጀራ በየመሳሳሙ መሃል መማማል??

ብዙ ሴቶች በህይወቴ መጥተዋል፡፡ ግን፣ አንድ ሴት ያወቅኩ ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡ ምክንያት- ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እግዜሩ አንዲት “ሴት ነብስ” ብቻ ፈጥሮ ለሁሉም ሴቶች ያብቃቃት ይመስለኛል፡፡
“እውነት ትወደኛለህ?” የቀሽሞች ቀሽም ጥያቄ፡፡ እንዴት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ይጠየቃል? እሺ ልውደዳት፣ እሷን መውደድ የእኔ እንጂ የእሷ ጉዳየይ ነው እንዴ? ብወዳት` ባልወዳት ምን ያገባታል? እኔ መች ትወጅኛለሽ ወይ ብዬ ጠይቄ አውቃለሁ? በመጃጀመሪያ ሰው እንዴት ይፈቀራል? ነገ የሚፈርስ፣ ጠፊ፣ ስስ፣ ደካማ ፍጥረት እንዴት መወደድን ይሻል? በመወደድ መሙላት የሚፈልጉ ስንኩላን ምኞት ነው ይሄ፡፡ ወንድና ሴት መሳሳም፣ መደሰት መዋለድ ነው ያለባቸው፡፡ የ “መ” ህጎች በሉት ስትፈልጉ፡፡ መሆን ያለበት ይሄ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው የሌለውን ፈልጎ ይቀበላል እንጂ እንዴት ካልተወደድኩ ይባላል፡፡

“ከልብህ ትወደኛህ?” ይሄ ለኔ ጥያቄ አይደለም፡፡ ካቴና ነው፡፡ የሴቶች ካቴና! እኔ ደግሞ ነፃነቴን እወዳለሁ፡፡ ያለምንም ወንጀል… ባቀፍኳት፣ ሙቀቴን በሰጠሁ፣ የወጣትነት ውበቴን ባጋራሁ ታሰር እባላለሁ እንዴ? ይህ ጥያቄ፣ በሆነ ድርጅት ውስጥ ግለሂሀስ አውርድ የተባልኩ ያህል ምቾት ይነሳኛል፡፡ ሰዉ ግን እንዴት ነው በፍቅር መሰል ግምገማ ውስጥ እስችሎት የሚዘልቀው? ምነው አምላክ ይሄን ጥያቄ የማትጠይቅ ሴት ፈጥሮ ሃያልነቱን ቢያሳየኝ…

* * * * * * * * * * *
በዚህ ስሜት ውስጥ እያለሁ ሶስና ወደ ህይወቴ ገባ፡፡ እንደሌለሎቹ፣ ትወደኛለህ ብላ እስክትጠይቅ አብሪያት አሪፍ ጊዜ እንደማሳልፍ አሰብኩ፡፡ የመጬ ውብ ናት፡፡ እኔ ነኝ ያለች ቆንጆ፣ ለሰዓታት ተኳኩላ… ሶሲ ከእንቅልፏ ስትነሳ ያላት ወበት ጋር እንኳ አትደርስም፡፡ በዛ ላይ አስተሳሰቧ! እንደ ሌሎች ሴቶች ጭኗ ብቻ ሳይሆን ጭንቅላቷም ውብ ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው፣ የሆነ ሰዓት ላይ “ትወደኛለህ?” የሚለውን ጋግርታም ጥያቄ መደንቀሯ አይቀርም፡፡ ደስ የሚለው…. እስካሁን አላለችኝም፡፡ ባለችኝ ቅፅበት የመለያያ ደውላችን መደወሉ አይቀርም፡፡

….ጊዜያት አለፉ፡፡ ያን የተረገመ ጥያቄ እስካሁን አልጠየቀችኝም፡፡ ደስስስስ አለኝ፡፡ ሶሲ ደስ አለችኝ፡፡ ከኔ ጋር ብዙ ጊዜ የመቆየትን ክብረ-ወሰን ሰበረች፡፡ የሚያሳዝነው….. በቅርብ ጊዜ ውስጥ መጠየቋ አይቀርም፡፡ እንደጠበኩት ግን አልሆነም፡፡ የለመዱትን የመነጠቅ አይነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ ቢሆንም ደስ ብሎኛል፡፡

አንድ ቀን አልጋ ውስጥ ሆነን… እቅፌ ውስጥ እንዳለች አስተውዬ አየኋት፡፡ የሷም አስተያየት የፍቅር ነው፡፡ታሳሳለች፡፡ ልዩ ሴት መሆኗ ተሰማኝ፡፡ ያን ቀፋፊ ጥያቄ ከደሟ ውስጥ መደምሰስ ብችል ተመኘሁ፡፡ እንዳትጠይቀኝና እንዳንለያይ ፈራሁ፡፡ በጣም ፈራሁ፡፡ በጣም ፈራሁ፡፡ የማጣት የማጣት መሰለኝ፡፡ ውስጤ ተረባበሸ፡፡ ልቤ አካባቢ ምቾት የሚነሳ ስሜት ሰቀዘኝ፡፡ይሄን ስሜት ለማባረር ከእሷ ጋር ማውራት ፈለኩ፡፡
“ሶሲ?” ጠራኋት፡፡
“ እ….እ…?” አለችኝ ዓይን ዓይኔን እያየች፡፡ ምን ላወራት እንደፈለኩ አላውቅም፡፡
“ወዬ” አለችኝ ዝምታዬ ሲረዝምባት፡፡ እንዴት እንደሆነ አላውቅም….. “ትወጅኛለሽ?” አልኳት፡፡ ለራሴ ደነገጥኩ፡፡
“እ…” አለችኝ በቀዘቀዘ ድምፅ፡፡
“ትወጅኛለሽ ወይ?” ….. እንደ ድምፅዋ የፍቅር አተያይዋም ቀዘቀዘ፡፡ ዐይኖቿ ቀዘቀዙ፡፡ ልቧም የቀዘቀዘ መሰለኝ፡፡ ክው አልኩ! አተነፋፈሴ ተዛባ፡፡ፀጥታ ሆነ፡፡ የልቤ ድው ድው የሚል ድምፅ ብቻ ይሰማል፡፡ ድው…..ድው….ድው…..ድው…..

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • HUSEN commented on November 17, 2017 Reply

    YAMRAL

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...