Tidarfelagi.com

የምኒልክና የአድዋ ነገር

የምኒልክና የአድዋ ነገር በዚህ መጣጥፍ አልቆለታል!
/#ዲ_ሳህለማርያም እንደፃፈው/

“ደጃዝማች ፣ ገና ከሰላሌ ስንነሳ ታማኝነቴን በምኒልክ ስም ቃል የገባሁት ላንተ እንጂ ለሽማግሌዎች ወይም ለንጉሱ አይደለም። እኔ ንጉስ አይደለሁም። ተራ ወታደር እንጂ። …. ላንተ ግን አሁንም በምኒልክ ስም ፣ በምኒልክ አምላክ በድጋሚ ቃሌን እሰጣለሁ። ለአንተ እሞታለሁ። ተመለስ ላልከው ግን የት ነው የምመለሰው? ምንስ መመለሻ ቤት አለኝና? እዚህም እዚያም እሳት እየነደደ እንዴት ቁጭ ልበል? ሽማግሌዎቹ ጦር ሊሰዱብኝ አስበው ከሆነ ደግ ምንም ችግር የለም። ግን እኔ ከነሱ ጠብ እንደሌለኝና የሀገሬ ታማኝ ወታደር እንደሆንኩ አስረዳልኝ። ደጃዝማች ስማኝማ! ምናልባት ካልተገናኘን እማማን ደስተኛ እንደነበርኩ ንገራት። በእሳተ ገሞራ መሃል ማለፍ ቢኖርብኝም ወደ ሰላሌ እመለሳለሁ” ይህን ታሪክ የነገረን አዶልፍ ፓርለሳክ (ገጽ፣234)ስለ ኢትዮጵያዊው ተናዳፊ ጦረኛ አብቹ በ’አበሻ ጀብዱ’ ሲተርክልን ነው። አብቹ ጣልያን በ’አድዋ ኮምፕሌክስ’ ዳግም ሊወረን በመጣበት ሰአት ጠላትን መግቢያ መውጫ ያሳጡ ከነበሩ ትንታግ የሸዋ ኦሮሞወች አንዱ ነው። በወቅቱ በርካቶች በምኒልክ ስም መማል እና ቃል መግባታቸውን የታዘበው ፓርለሳክ “አዎ ኢትዮጵያዊ በምኒልክ ስም የገባው ቃል ቅዱስ ነው። ምንጊዜም አይሽረውም” (ገጽ፡236) በማለት ተናግሯል።

ይህ በዘመኑ በሳር ቅጠሉ “እምዬ” የሚባል ፣ ነገስታት የሚርዱለት ፣ ጎበዛዝት የሚወዱት ፣ ሽማግሌዎች በፍቅር የሚከተሉት ከባድ ንጉስ ዛሬ በኛ ጊዜ ደግሞ ስሙ ብዙ ነው። የሚወዱት የመብዛታቸውን ያህል እሱን በማዋረድ ቀልብ መግዛት ከሚፈልጉት ጀምሮ የሱን ፎቶ የያዘ መኪና አንድዱ እስከሚሉ ንኮች ድረስ የምኒልክ ስም የማይፈነቅለው ጂኒ የለም።

ምኒልክ እና ግዛት ማስመለስ/ወሰን ማስከበር

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 50አመታት ተደጋግሞ ከመነገሩ የተነሳ በበርካቶች ዘንድ አመኔታን ያገኘ አንድ ቅጥፈት ቢኖር ‘ምኒልክ የደቡብ ኢትዮጵያን ወሯል’ የሚለው ሸለፈት ትርክት ነው። ይህን ቅጥፈት ባዶ ለማስቀረት ምኒልክ ምን አደረገ ማንስ ነበረ የሚለውን መፈተሽ ያሻል። ምኒልክ ገና ከልጅነቱ ዘመነ መሳፍንት የበላውን የኢትዮጵያን ታላቅነት ወደነበረበት ከፍታ በመመለስ ፍቅር የተያዘ እንዲሁም የሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ህጋዊ ወራሽ ነበር። ምኒልክ የአባቶቹን ወሰን የአምደ ጽዮንን ፣ የዘርዐ ያዕቆብን አገር ወደነበረበት ሲመልስ “ገብር! እምቢ ካልክ ግን ወግቼ አስገብርሃለው” ብሎም የተነሳ ንጉስ ነው። አምደ ጽዮን የደቡብ ኢትዮጵያን ክፍሎች ሃድያ ፣ ደዋሮ ፣ ፈጠጋር ፣ ባሌ የመሳሰሉት ክፍለ ሃገራትን በአንድ ማእከላዊ የኢትዮጵያ መንግስት ስር ይገዛ እንደነበር የታወቀ የተረጋገጠ ሃቅ ነው። ከሱ በኋላ የተነሳው እና የኢትዮጵያን “nation state”ነት አድምቆ ያሰመረው ዘርዐ ያዕቆብ ደግሞ ከአምደጽዮን ኢትዮጵያ የሰፋች ትልቅ አንድ ኢትዮጵያን ይገዛ እንደነበር ሌላ በታሪክ የተመዘገበ ሃቅ ነው። በ1950ወቹ በደቡብ ኢትዮጵያ አንድ የጥናት ቡድን እየመሩ ለረጅም ጊዜ የመስክ ጥናት የሰሩትን ጀርመናዊውን ዶር ሃበርላንድን ዋቢ በማድረግ ዶናልድ ለቪን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከ1434-1468 በነበረው ዘመን ኢትዮጵያን ለገዛው ለንጉስ ዘርዐ ያዕቆብ ያላቸውን ትውስታ እንዲህ ከትበውታል። “His expedition to the south had a profound and lasting impact on the peoples of those regions. Many of them still have legends which recall that period . Among the sidamo, for example, his reign is still remembered as a Golden Age” ዶ/ር ሃበርላንድ በመስክ ጥናታቸው ንጉስ ዘዐአ ያዕቆብ ማጂ በሚባለው ጠረፍ አገር እንኳን ሳይቀር “ሰራቆ” ተብሎ እንደሚታወስ በጥናታቸው መዝግበዋል። ለቪን ትረካቸውን ሲቀጥሉ እንዲህ ይላሉ ‘Even among the remote Maji, who live in thr southwester most part of the greater Ethiopia, he is remembered under the name Seraqo’ (2002, p. 74) ። እርግጥ ነው ዛሬ የማቱኬ ልጅ ሸማውን ለብሶ አርባ ምንጭ ጨንቻ ኮረብታ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲያውለበልብ ስታይ አይግረምህ። የብርብር ማርያሙ ጋሞ ኢትዮጵያዊነቱ ከጥንት ነው።

ምኒልክ ነፍጥ በአለም አቀፍ የሃይል አሰላለፍ እና ሚዛን ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ጠንቅቆ የሚያውቅ ፣ እንደ አያቱ ሳህለስላሴ ነፍጥ እጁ እንዲገባ በዲፕሎማሲም ሆነ በገንዘቡ ከባድ ጥረት ያደርግ የነበረ ፣ የተሳካለትም ፤ እንዲሁም በአጋጣሚ ሳይሆን (!) በብቃቱ እና በብልሃቱ ንግስናውን እና ስኬቱን በእጁ የሰራ ፤ የመሪነት ክህሎቱ እጅግ የረቀቀ ንጉስ ነበረ። እንግሊዞች ከአጼ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ ቴዲ የሰሯቸውንም ሆነ የሰበሰቧቸውን የጦር መሳሪያዎች መቅደላ ላይ እንዳልነበረ አድርገው ማውደማቸውን ፓንክረስት ሲተርኩልን እንዲህ ብለው ነበር ‘Guns in Ethiopia” በተሰኘው የጥናት ጽሁፋቸው ‘Ethiopia’s first major attempt at arming herself adequately, in face of a hostile world, was brought to an abrupt end” ለዚህም ነው ምኒልክ ጠንካራ አገር ያለነፍጥ እንደማይሰራ ፤ ቢሰራም በዚህ ጸበኛ በበዛበት አለም እራሱን ችሎ እንደማይቆም በመረዳት የነፍጥ አቅሙን በማሳደግ ላይ ታትሮ ሲሰራ የነበረው።

ምኒልክ በነፍጥ በሚገባ ከተደራጀ በኋላ ባንድ ወቅት ፓንክረስት “he was imbued with a burning ambition to rebuild the greatness of Ethiopia” በማለት እንደገለጹት የኢትዮጵያን ታላቅነት በማስመለስ ምኞት ውስጡ ይነድ የነበረው ምኒልክ የአገራችንን ግዛት ወደ ነበረበት ለመመለስ ባደረገው ዘመቻ አልገብርም ያሉትን እንደ አርሲ እና ወላይታ የመሳሰሉትን ወግቶ አስገብሯቸዋል። በ16ኛው ክ/ዘ ከተደረገው የኦሮሞወች መስፋፋት በኋላ አርሲ የሚባል መጠሪያ ያገኘው አከባቢ በንጉሰ ነገስት ዘርአያእቆብ ዘመን የሚበዛው የሃዲያ ‘ኪንግዳም’ እንዲሁም የፈጠጋር አከባቢ መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በዘመናችን የምኒልክን ስም በማቆሸሽ የተጠመዱ በርካታ የኦነግ ሰዎች የተገኙበትን የወለጋ አከባቢ ደግሞ ምኒልክ በፍቅር አስገብሮ በራሳቸው ገዥ እና በራሳቸው መንገድ እንዲኖሩ ትቷቸዋል። እርግጥ ነው ያን አከባቢ ከደርቡሽ ጅሃዲስቶች ወረራም የታደገው የምኒልክ እጅ እና ውሳኔ እንደሆነ አሌሳንድሮ ትሩልዚ “Trade, Islam, and the Mahdia in Northwestern Wallagga, Ethiopia” በሚለው የጥናት ጽሁፉ ነግሮናል። ዛሬ በምእራብ ኢትዮጵያ የሚሸለልበት የፕሮቴስታንት እምነትም ሊቆይ የቻለው ምኒልክ ባደረገው የኢትዮጵያን ድምበር የማስጠበቅ እና የማስመር ሃላፊነት ነው ። ስለዚህ ነገራችንን ስንሰበስበው፣ ምኒልክ የነአምደ ጽዮን እና ዘርዐ ያዕቆብ ስርወ መንግስት ወራሽ እንደመሆኑ ፣ ያፈረሰው ዘመነ መሳፍንት እና መንደሬነት እንጂ የወረረው አገርም ሆነ ህዝብ እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል እንላለን።

ምኒልክ እና አዲስአበባ

ክራፍ የሚባለው ጀርመናዊ በምኒልክ አያት ሳህለስላሴ ዘመን ሸዋ ውስጥ ይልከሰከሱ ከነበሩ ሚስዮናዊያን አንዱ ነው። ይህ ሰው ሳህለስላሴ ከአንኮበር ወደሱሉልታ እየመጣ የኦሮሞወችን ጎጆ ያቃጥል እንደነበር ተናግሯል በማለት ሳህለስላሴን የሚያሳቅሉ ሰዎች አሉ። [በሱሉልታ ከI38I-I4IO ኢትዮጵያን በገዛው በአጼ ዳዊት የተሰራ ከተማ ፍርስራሾች መገኘታቸውን እንዲሁም አጼ ምኒልክ ፍርስራሾቹን በማየት “እግዚአብሄር የአጼ ዳዊት ከተማ ፍራሽን እንድናይ ያደረገን የአጼ ዳዊትን ከተማ መልሰን በእንጦጦ ላይ እንድንከትም ነው” በማለት መናገራቸውን የምኒልክን ዜና መዋእል ጸሃፊ ገብረስላሴን ዋቢ አድርገው ፓንክረስት ጽፈዋል] እርግጥ ነው ክራፍ ለንደን ባሳተማቸው ጆርናሎቹ ሳህለስላሴን እየተከተለ ስላየው ነገር ብቻ ሳይሆን ኦሮሞወች የሸሜን ሰዋ ገደል እና ጠርዛማ ኮረብታዎች ባያቆሟቸው ኖሮ ሸዋን ሙሉ በሙሉ ከነባር ነዋሪዎቿ ያጸዷት እንደነበር ተናግሯል። ሳህለስላሴ አዲስአበባ ለምን ይመላለስ ነበር የሚለውን ለመመለስ እንዲሁም ምኒልክ ለምን አዲስ አበባን ለምን መረጠ የሚለውን ለመረዳት ከሪቻርድ ፓንክረት “The foundation of Addis Ababa” ከተሰኘው ጥናታዊ ጽሁፍ የሚከተለውን እንምዘዝ “In the nineteenth century Menelik, while still only King of Shoa, was imbued with a burning ambition to rebuild the greatness of Ethiopia, which had declined in the later Gondar period; he determined to found a capital on one of the sites occupied by his ancestors in the days before Gragni’s invasion and the subsequent advance of the Gallas had thrust the capital northwards to Begemder. Almost half a century earlier, in 1843, his grandfather, Sahle Sellassie, had discovered a ruined church ten minutes’ ride to the west of Filwoha (the site of present-day Addis Ababa) and had conceived a similar idea, but after discussing the matter with his priests had returned to his capital at Ankober. In I878-9 Menelik decided on Lebna Dengel’s old capital which, according to one tradition, had been situated at Entoto, i.e. about eight kilometres to the north of Filwoha.” (1961, ገጽ፣104)
እንግዲህ የሆነው ይሄው ነው። ምኒልክ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታት ከትመውበት በነሩበት በወጨጫ ተራራ ፣ ከዛም በእንጦጦ ቤተመንግስቱን ሰርቶ መኖር ጀመረ። በኋላም የእንጦጦን ብርድ ሽሽት ጣይቱን ተከትሎ ምኒልክ ፍልውሃ ከተመ። ፓንክረስት እንደመዘገቡት ደግሞ ፍልውሃን አለፍ ብሎ የተገኙ መጀመሪያ በግራኝ ኋላም በኦሮሞወች የተናዱ የአብያተ ክርስቲያንት ፍርስራሾች ነበሩ። ታድያ ማነው ምኒልክን በቅድመ አያቶችህ ባድማ የኢትዮጵያን ዋና ከተማ አትከትምም ሊለው የሚነሳ? ጣይቱ ልጅ ስላልነበራት ትጽናናባት ዘንድ ፍልውሃን በከበቡት የአበባ ዛፎች ላይ ተንተርሳ “አዲስ አበባ” የሚል ስያሜ አውጥታላታለች ይላል ፓንክረስት የጠቀሱት በዋቤነት የጠቀሱት የምኒልክ ጆርጅያዊ ሃኪም ዶክተር መራብ አዲስ አበባ እንዴት ስሟን እንዳገኘች ሲናገር። አዲስ አበባን ነዋሪዎቿ እና ጎረቤቶቿ በኦሮምኛ ሸገር ይሏታል። የምኒልክን ያህል ቅርበትም ሆነ ዝምድና የሌላቸው የአርሲ እና የወለጋ ብሄርተኞች ደግሞ “ፊንፊኔ” ሲሏት ሳቃችን ይመጣል።

ምኒልክ እና አድዋ

ምኒልክ የአድዋ ድል ልብ እና ጭንቅላት ነው። ያለ ምኒልክ አድዋም ሆነ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ህልም ነበሩ። አብይ ተክለማርያም የእኛ ዘመን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጂንየስ እና ተንታኝ ነው። እ.ኤ.አ 2014 ላይ 140 ሆሄ በምትይዝ “ትዊቱ” ምኒልክን ሲገልጸው “Menelik’s strategic brilliance has no match in modern Ethio history. An instinctive game theorist who emphatically outmanoeuvred opponents” (28-Feb-2014) ነበር ያለው ። እውነት ነው የምኒልክ ስልታዊ ልቀት እና ብሩህነት በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ወደር የማይገኝለት ነው አብይ እንደመሰከረው ።ምኒልክ አድዋን የሰራ ፣ ሰርቶም በስራው እና በጥበቡ ያሸነፈ እንጂ “21 ሳንታ ማርያ” ሲባል “ቢንጎ” ብሎ ጠርቶ ቁማር የዘጋ ‘እድለኛ’ አይደለም። እንኳን ከመቶ ሺህ ሰው በላይ ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጣበትን ጦር አደራጅቶ የአውሮፓውያንን ሰራዊት ማሸነፍ ይቅርና 100 ሰው የሚጋበዝበት የወይዘሮ አጥቅየለሽ የማርያም ድግስም ከ’እድል’ ያለፈ ስራ እና ብቃት ይጠይቃል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ጆርጅ በርክሌይን ጠቅሰው ወደ 87ሺህ የሚጠጋ ሰው ወደ አድዋ ዘምቷል ይሉና ፤ 25ሺህ ከጎንደር እና ወሎ ፣ 15ሺህ ከጎጃም ፣ 12ሺህ ከትግሬ እንዲሁም 35ሺህ ዘማች ከከሸዋ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ መሆኑን ያትታሉ። እርግጥ ይህ ቁጥር በሌሎች ጸሃፍት ከ120ሺህ በላይ ቢገመትም የተዋጽኦውን ንጻሬ ለመረዳት ግን ጠቃሚ መንደርደሪያ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ FB ላይ ከግርማ ጨብሲ ከሆነ የተማርከው እንዲሁም መመረቂያህን “ህገመንግስቱ ይከበር” በሚል መፈክር ከሆነ የሰራኸው ፣ “የአድዋ ዘማች 2/3ኛው ከመሃል ኢትዮጵያ ነው የሄደው” የሚል ወደል ድፍረት ትዳፈራለህ። ለማንኛውም ወደ ነገራችን ስንመለስ ምኒልክ ይህንን ያህል ብዛት ያለው ሰራዊት ከሸዋ ትግራይ ድረስ መርቶ ፣ አቀናጅቶ እና አደራጅቶ ማሸነፉ ግርርርም ያለው ጃን ማርካኪስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል “’In the battle of Adwa (1896) the Ethiopians mustered a force of more than 100,000 to annihilate an Italian invading force of some 20,000. To field an army of this size required a degree of organization and tactical sophistication which, in this instance at least, out performed a European force sent to colonise Ethiopia’ (2011, p.3)

አድዋ በምኒልክ ያልታከተ ነፍጥ የማግኘት እና የማከማቸት ድካም ፣ ከውጭ መንግስታት ጋር በተደረጉ ያልተቆጠቡ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እና ብዙ ካምፔይኖች እንዲሁም የአገሪቱን ግዛት አስከብሮ ከመንደሬ እና ጎጠኛ አስተሳሰብ አላቆ ለአንድ ብሄራዊ አላማ ማሰለፍ ይህ በአጋጣሚ እና በእድል የተገኘ ሳይሆን እጅግ በላቀ የመሪነት ጥበብ የተገኘ የጥቁር ድል መሆኑን የተረዳው ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጆናስም አድዋን እንዲህ ይገልጸዋል። ‘Adwa deserves to be ranked among the great military campaigns of modern history. Its greatness starts with the fact that it was never just a campaign of guns, blood, and steel. Ethiopia pioneered key “soft power” techniques that would became part of the repertoire of anti-colonial warfare in the new century. By the time the actual military campaign began, Ethiopia had won over a significant portion of enemy public opinion thanks to a well-orchestrated “hearts and minds” campaign’

አድዋ የስኮትላንዱ ዊልያም ዋላስ ከገጠሬዎች ጋር በሳንጃ የተተጋተገበት የሚዲቫል ዘመን ጦርነት አይደለም። በሁለት ሉአላዊ ሃገራት እና በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች መሃል የተደረገ የዘመናዊው ዘመን ጦርነት እንጂ። ስለዚህ ምኒልክ ጎራዴ ይዞ አድዋ ተራራ ላይ እንገፍ እንገፍ እንዲል የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ ወይ ድንቁርና እጅግ ተጭኗቸዋል አልያም በstunting የተጎዳ እና ኮግኒቲቭ አቅሙ የደቀቀ አንጎል ባለቤት ናቸው።

የአድዋ ‘ኮምፕሌክስ’

በአድዋ ኮምፕሌክስ የተመቱ ሶስት ቡድኖች አሉ። የጣልያን ልሂቃን ፣ የትግሬ ብሄረተኞች እና የኦሮሞ ብሄረተኞች።

የጣልያን ልሂቃን ከሞሶሎኒ እስከ ኤንሪኮ ቼሩሊ ድረስ በአድዋ ሽንፈት የተነሳ በጊዜው ህዝባችንን ጨፈጨፉ እንዲሁም ለጎጥ ፖለቲከኞች የሚያገለግል እርሾ አበርክተው ዞር ብለዋል። የአሁኑ የጣልያን ትውልድ እንኳን አድዋን ኢትዮጵያንም የሚያውቃት አይመስለኝም። የትግሬ ብሄረተኞች እና የኦሮሞ ብሄረተኞች ግን የአድዋ ኮምፕሌክስ ናላቸውን በያመቱ ሲያዞር መመልከት አሁን አሁን የተለመደ ክስተት ሆኗል።

የትግሬ ብሄረተኞችን በተመለከተ ገብረህይወት ባይከዳኝን ከራሳቸው ከመጥቀስ ውጭ ሌላ ድካም መድከም አይገባም።

ገብረ ህይወት እንዲህ ነው ያለው። ‘ሁሉም መሬት በሰላም ሲኖር ምስኪኒቱ ትግሬ ግን ሽፍታና ወንበዴ አልተለያትም። ባላባቶቹም ዘወትር እርስ በርሳቸው ሲዋጉ ይኖራሉ። ምስኪኑም የትግሬ ባላገር አጤ ምኒልክ ያጣልዋቸው እየመሰለው በሸዋው ንጉስ ላይ ብዙ ይፈርዳል። አጤ ምኒልክን የሚያውቅ ሰው ግን ይህንን ሃሜት ሲሰማ ይስቃል። የቸሩ ምኒልክን ባህሪ የያዘ ሰው ያፋቅራል እንጅ አያጣላም። ሰውንም ፈጽሞ ሊጎዳ አይችልም። የማያውቃቸው ሰው ግን በብዙ ክፉ ነገር ያማቸዋል …ትግሬ ባጤ ምኒልክ ተጎዳ ቢባል ሃሰት ነው እርስ በርሱ መስማማት ስላጣ ተበላሸ እንጅ’ (ገጽ ፣ 11)

ጤነኛ አእምሮ ላለው ሰው የወለጋ ፣ የጅማ እና የሸዋ ኦሮሞወች እንዴት በምኒልክ ዘመን የተሻለ ኑሮ የኖሩ ሆነው ሳለ እንዲሁም ለየአካባቢያቸውም ገዢ እና ነጂ ሆነው ሳለ እንዴት ከዛ የወጡ ብሄረተኞች የምኒሊክ እና የአድዋ ጠላት ሆኑ የሚለውም ሌላ አስቂኝ ተግባር ነው። ምኒሊክ ከነሰራዊቱ ወደ ሰሜን ሲተም የተመለከተ አዝማሪ ኦሮሞ ለምኒልክ የተቀኘውን ዝማሬ ከቼሩሊ ስብስቦች ጋብዘናቸዋል።

motin bar gama cee
Dano farangi reibe
Waqatti matti ya Dano
dugankieti ya Dano”
የአማርኛው ትርጉም ከእንግሊዘኛው የተቀዳ ነው
“ንጉስ ወንዙን ተሻገረው
ዳኘው ፈረንጁን ሊገርፈው
ለእግዜር ንገረው አባ ዳኘው
እውነት ይዘሃል እና ዳኘው”

እንደ መዝጊያ

ምኒልክ በኢትዮጵያ ከነገሱ ነገስታት ሁሉ እጅግ ቸር የነበረ ፣ የፍርዱም ርትእነት የችሎቱም ፍትሃዊነት የተመሰከረ ፣ አገልጋይ ሚንስትሮቹን ይቅርታ ለመጠየቅ የማይሰንፍ እንዲሁም እጅግ በሚገርም ሁኔታ እውነተኛ ስልጣን እና አቅም በነበራቸው ከተለያየ ዘውግ በመጡ ባለስልጣናት የተከበበ ነበር። ዛሬ ከምእራብ ሃገራት በተገኘ አምስት ገጽ የሂዩማን ራይት ‘ሃንድ አውት’ የምኒልክን ስብእና ለመስፈር እና ለማሳነስ የሚዳዳቸው ኮሜዲያን ሳያቋርጡ በሚለግሱን ሳቅ እየተዝናናን አድዋን መዘከራችን ይቀጥላል።
______
ማጣቀሻዎች

ገብረህይወት ባይከዳኝ (2003) አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ ፣ ገጽ 11
Jonas, R. (2011) The Battle of Adwa : African Victory in the Age of Empire
Levine, D. (2002) ‘Greater Ethiopia : The Evolution of a Multiethnic society 2nd ed., p.74
Markakis, J. (2011) Ethiopia : The Last Two Frontiers, p. 3
Milkias, P. and Metaferia, G. (2005) The Battle of Adwa : Reflections on Ethiopia’s Historic Victory Against European Colonialism, p. 186
Pankhurst, R. (1961) Guns in Ethiopia, pp. 26-33
Pankhurst, R. (1965) ‘Menelik and the Foundation of Addis Ababa’, The Journal of African History, 2(1), pp. 103-117
ተጫነ ጆብሬ (1989) ‘የሃበሻ ጀብዱ’, አአዩ
Triulzi, A. (1975) Trade, Islam, and the Mahdia in Northwestern Wallagga, Ethiopia”, Journal of African History, 16 , p. 68

It’s not about me! it’s not about my life situation either.It’s about life! And in life I trust!

One Comment

  • daniraya1982@gmail.com'
    እንየው ቢ commented on February 27, 2017 Reply

    እናመሰግናለን!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...