Tidarfelagi.com

የማይነጋ የሚመስል ሌሊት…

ቅድም ከምሽቱ 3ሰዓት ገደማ ሰፈሩ ድንገት በአንዲት ሴት እሪታ ተደበላለቀ። ከተቀመጥኩበት ብትት ብዬ ተነስቼ በመስኮት ወደ ውጭ ማተርኩ- አንዲት የተደናገጠች ሴት እጆቿን እያወራጨች ትተረማመሳለች…
.
ሌላዋ ሁለት እጆቿን ጭኖቿ መሃል ከታ አንዴ ጎንበስ አንዴ ቀና እያለች… ‘ደውሉ በናታችሁ! ስልክ ደውሉ!’ ትላለች፣ የሚታዩኝ እንደመስመር በተዘረጋ የበረንዳ መብራት ነው።
”እሳት ተነስቶ ይሆን?”
(ሽንቴ ከየት መጣ?)
.
ተንደርድሬ መታጠብያ ቤት ገባሁ።
እንደገና የቅድሙ የ’ሪታ ድምጽ ህንጻውን ድጋሚ አናጋው… <አረ ኡኡኡኡ!!!!>
(ሽንት እንዲህ ይረዝማል? ላቋርጠው? አረ እለቅቅ!!!)
.
በ’ሬን ከፍቼ በደረጃው ቁልቁል ተንደረደርኩ…
(ልብስ ደርቤአለሁ? እሳት ቢሆን ወደላይ እመለሳለሁ? ምንም ሳልይዝ የት ነው የምሄደው ግን?)
.
.
መሬት ስደርስ እንደኔው የተደናገጡ ሰዎች ፈሰውበታል… ጋቢ የደረቡ፣ ልጅ ያዘለች፣ በፒጃማ ያለች፣ በካልሲና በቁምጣ ያለ.. የተሸበሩ ሰዎች!
<ምንድነው?> (ማን ሰምቶኝ!?)
””ሞተ እንዴ፣ ልብ ድካም ነው፣ ወይኔ ሙሌ” ብዙ አይነት ንግግሮች።
.
የቅድሟ ሴት ጸጥ ብላለች። ስገባና ስወጣ ታክኬ ከማልፋቸው የምድር ቤቶች የአንዱ መስኮት… መጋረጃው ተገልጧል። ከውስጥ ብዙ የቆሙ ሰዎችና… ሶፋ ላይ እንደዋዛ ዘፍ ያለ ጎልማሳ… በቆሙት ሰዎች እግሮች መሃል የተጨነቁ አይኖቻቸውን የሚያቁለጨልጩ ቢበዛ 13 ሚሆነው ታዳጊና ከ8 የማትበልጥ ሌላ ሴት ልጅ ይታዩኛል።
.
.
እየተፈራረቁ አንገቱ ስር፣ አውራ ጣቱን፣ የእግሮቹን ጣቶች ጨበጥ ጨበጥ ያደርጋሉ… የሚተነፍሱት ቃል ግን የለም።
.
”ሞቷል” ብሎ መናገር ”ይሙት በቃ!” እንደማለት የከበዳቸው ይመስላሉ።
.
.
እንደኔው በመስኮት ሚያዩ በርክተዋል። ምን ያህል ቆሜ እንዳየሁ እንጃ… አፋፍሰው ወደ መኪና ማቆሚያው ወሰዱት። <አፋፍሰው> የሚሉት ቃል ለካ ቀላል ቃል አይደለም። እንደው ‘ብድግ አርገው’ ማለት አይደለም። ሰቅስቀው ሲያነሱት እጁ ሲያመልጥ፣ አንድ እጁን ሲያፍሱ ጭንቅላቱ ሲወድቅ…. ብቻ አፋፍሰው ይዘውት ሄዱ። እንደፈሰሰ ውሃ 🙂
.
.
ቀን ቤቴ ሆኜ ዛፎች ሲቆረጡ ሰምቼ በመስኮት ብቅ ብዬ ነበር። አራት ብሎኮች ጀርባ ተሰጣጥተው ያበጁት ስኩዌር ሜዳ ባለሳር ሆኖ በጥድ ዛፎች የተከበበና ህጻናት የሚቦርቁበት ነው። የጥድ ዛፎቹ ሲቆረጡ… ቁብም ሳልሰጥ ”ምናልባት የተሻሉ ዛፎች ሊተከል ታስቦ ይሆናል” ብዬ ነው ያለፍኩት (የግቢው ኮሚቴ የተጠናከረ ስለሆነ የግቢውን ውበትና ድህንነት በጥብቅ ይከታተላል)።
እና ይህ ሰው የብሎኮቹን ነዋሪዎች ወክሎ ዛፎቹን ሲያስቆርጥ አምሽቶ ነበር ገብቶ ጋደም ያለው- አመሻሽ ላይ።
.
.
ቤቴ ስመለስ የሊቨርፑልና ሪያል ማድሪድ ጨዋታ ጀምሯል። ሃሳቤን በሱ ለመያዝ ሞከርኩ… በሳይበሩ chat እያደረግን ከነበርን ጓደኞቼ ጋር ወሬዬን ቀጠልኩ፣ በመስኮት ብቅ አልኩ.. እታች የሚተራመሱ ሰዎችን አየሁ። ተቁነጠነጥኩ።
.
.
ትንሽ እንደመረጋጋት ስል ሰፈሩ ድጋሚ በእሪታ ተናጋ። የመኖሪያ ህንጻዎቹ የገደል ማሚቱ አበጅተው ድምጽ ስለሚቀባበሉ እና ግቢውም ከሚሯሯጡ ህጻናት ጫጫታ የጎላ ድምጽ ስላልለመደ…. ጩኸቱ ሙሉ ግቢውን ነው ሚያነቃንቀው።
.
ወደመስኮቱ ሄጄ ሳይ የሰውየው በድን አካል ነጭ ለብሶ በሸክም ከመኪና ይወርዳል። ‘እንደው ለምናልባት’ ብለው እንጂ የወሰዱት ቤት ውስጥ ነበር ነፍሱ ከስጋው የተለየችው።
ምናባቴ ላድርግ?
ወርጄ ላልቅስ?
ሄጄ ቤት ሚያደርጉትን ላግዝ?
.
እንኳን እታችኛው ወለል የሶስተኛ ፎቅ ጎረቤቶቼም አያውቁኝም – መንፈቅ ከሁለት ወር ኖሬም አልተግባባንም። ከኔ በፊት ኖረውበትም ጎንለጎን አይተዋወቁም። (ያለሁበትን የነገርኩት የልቤ ሰው በmessenger ሊያረጋጋኝ ይሞክራል)
.
ድምጽ ጎላ ባለ ቁጥር ወደ መስኮቴ ሄዳለሁ…
ብዙ የስልክ ብርሃን ይታየኛል፣ ገሚሱ ይንቀሳቀሳል።
(ዘመድ ቤተሰብ እየተጠራ ነው) (የአንዳንዱ ምልልስ ያሳቅቃል) (ምን ሆነሽ ነው ስልክ እማታነሺው? ሙሌ የ**ባል ሞቷል መኪና ይዘሽ ነይ)(እግዚዖ!)
.
ወገቧን ያሰረች ቀጭን ሴት በረንዳው ላይ ተደፍታ ሸክላውን መቀጥቀጥ ጀመረች…
ሌላ ደርበብ ያለች ሴት ደረቷን እየደቃች ዘለል ዘለል…
ተመልሼ ቁጭ አልኩ። ስልኬ ላይ መልእክት እየመጣ ነው…
”ሰሙዬ ሞ ሳላ መውጣቱ አያናድድም?”
”ውይ ወጣንዴ? ለምን?”
”ተጎዳኮ”
.
የብዙ ወንዶች ዋይታ አንዴ ድብልቅልቅ አደረገው…
”ወንድሜ ወንዴሜ”
አንድ የሴት ድምጽ ተከትሎ አስተጋባ ”ሙሌ ጓደኞችህ መጡ አንዴ ቀናበል”
(ሽንቴ በድጋሚ መጣ።)
.
.
የዋንጫው ጨዋታ 1-0 ለረፍት ተቋረጠ። ለቅሶውም አብሮ ሚቋረጥ መሠለኝ ልበል? ግን አልተቋረጠም…
እዛ ልሂድ?
እዚሁ ቁጭብዬ የሰው ሰቆቃ ላዳምጥ… ኡፍፍፍ!!
.
”ልጄ ምን ነካህ ልጄ ምነካህ”
”ሙሌ ጉድ ሰራኸኝ ለማን ትተኸኝ”
”ልጆችህን ምን ላረጋቸው ነው? አላደጉምኮ!”
.
ወይ አብሬ አላለቀስኩ: ወይ አልሸሸሁ…
ቁና ቁና ትንፋሼን እየዘረገፍኩ ይሄው 8:15ከሌሊቱ
ይነጋ ይሆን?

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...