Tidarfelagi.com

“የማርያም ልጅ ነኝ”

ታክሲ የከተማችን መሲህ ይመስለኛል፣ አስራ ሁለት ሐዋርያቱን ይዞ የሚጓዝ በእግር ከመኳተን፣ በፀሐይ ከመጠበስ ሊያድነን የመጣ መሲህ።

ታክሲ ውስጥ ነኝ፣ ጋቢና። ታስበው ይሁን ተሰብስበው የማይገቡኝን ጥቅሶች እያፈራረኩ ማየት ጀመርኩ _ እንደልማዴ። ጋቢናው በብዙ መላዕክት ስዕል ስለተሞላ መለስተኛና ተንቀሳቃሽ ቤተመቅደስ መስሏል።

ከጥቅሶቹ መካከል አንዱን አይቼ ክው አልኩ።
በቀይ ቀለም
“የማርያም ልጅ ነኝ!” ይላል ።

የማርያም ልጅ?
እየሱስ?
የማርያም የብቻ ልጅ ክርስቶስ?
እንዴት ሆኖ?

” ጌታዬ! ” ብዬ እግሩ ላይ መውደቅ ዳዳኝ። የልብሱን ጫፍ መንካት፣
ማረኝ ማለት አማረኝ።

ጥቅሱ ላይ እንዳፈጠጥኩ ቆየሁ።
የማርያም ልጅ ነኝ!
ሹፌሩን (የማርያምን ልጅ) ዞር ብዬ ማየት (ፈራሁ ። ልቤ በሃይል ይመታል። የፍርድ ቀን ደረሰ? የምመጣበትን ቀን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ ሲለን የነበረው እንዲህ እንደ ሐዋሪቱ አስራ ሁለት አድርጎ ይዞን ሊሄድ? ትዛዙን ስተን ባንቀላፋን ሰዐት ከች አለ?

” ኦ የማርያም ልጅ ሆይ ማረኝ!” አልኩ በውስጤ።
***

እንደምንም እራሴን አደፋፍሬ ቀስስስ… ብዬ ሹፌሩን አየሁት… ምኑም የማርያምን ልጅ አይመስልም።
ወጣዛሁዙዘ
ተረጋጋሁ።
ቀጥሎ ተበሳጨሁ። ፌስቡኬ ላይ አቀረቀርኩ።
አንዲት የፌስ ቡክ ስሟ “የማርያም ልጅ ” የሆነች ሴት የለጠፈችው (ማርያም ከልጇ ጋር) ፎቶ፣ ከሞባይል የስክሪኔ መጠን የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ቁጭ ብሏል። ከፎቶው ስር

“አንቺ የትኛዋ ነሽ? “ብዬ ኮመንት ፅፌ ወጣሁ ።

ቆይ! ማርያም ስንቱ ልጆች ነው ያሏት? ይህን ቀልድ ማነው የጀመረው? መቼ ነው የተጀመረው?

የማርያም ልጅ አንድ ሆኖ ሳለ እንዴት ማንም እየተነሳ አፉን ሞልቶ የማርያም ልጅ ነኝ ይላል? ዛሬ የማርያም ልጅ ነን ብለው ጀምረው አደል ነገ፣
“እኔ እኮ እየሱስ ነኝ” የሚሉት?
ያቺ “ማርያም ነኝ” ብላ ስታጭበረብር የነበረችው ሴትዮ፣ ምናልባት ለረጅም አመታት የማርያም ልጅ ነኝ ስትል የቆየች ሳትሆን ትቀራለች?

ከዛ በጊዜ ዝግመት እራሷን ከማርያም ልጅነት… ወደ ማርያምነት ያሳደገች…

አሁን እኔ በሹፌሩ ድርጊት ተሳስቼ፣
እግዚሐር እረኛዬ ነው በማለት ፋንታ፣
እግዚሐር ሹፌሬ ነው ብል ይፈረድብኛል?
ስተው ያሳስቱናል።

በዚህ ለምዶ እኮ ነው ስንቱ ነገ እየተነሳ ፣ ያልሆነውን ነኝ እያለ ተሰለፉልኝ የሚለው።

ንጉሡ የሰለሞን ዘር ነን አሉን… አመንን
ቀጥለው የሰፊው ሕዝብ አዳኞች ነን አሉን… አመንን

ነፃ አውጪዎች ነን አሉን… አመንን
ማመናችንን ያዩ የሌላቸውን ዶክትሬት አለን፣ ፒ ኤች ዲ አለን… ብለው መጡ… አመንን (ማመናችን ባይዘልቅም)
ያልሆኑትን ነን እያሉ ጥላችንን እንኳ መጠራጠርን ይከትቡናል።

ይኸው ዛሬም ማመናችንን ያዩ ብለው ብለው የማርያም ልጅ ነን ይሉን ገቡ፣
እንዲህ እንደቀልድ ከእየሱስ ጋር እናት መጋራት እንደሚቻል አልገባኝም ነበር።

ይበሉ የማርያም ልጅ ነን ካሉ ሕዝቡን ያድኑት?
የማርያም ልጅ ነን እያሉ፣ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉን እነሱ አይደሉም?
ይበሉ፣
የማርያም ልጅ ነን ካሉ፣ መሄዱን እንጂ መሄጃውን የማያውቀውን ሕዝብ እረኛ ሆነው ይምሩት

እንግዲህ የማርያም ልጅ ነን ካሉ፣ በባህሪም ሊሆኑ ግድ ነው።
ንግድ ማጧጧፊያ የሆነ ቤተመቅደሶችን ይሂዱና ያበታትኑ።
የሕዝቡን የብሶት መስቀል ይሸከሙለት።

አዳሜ ሶፋዋ ላይ ተጋድማ፣ በስማርት ፎኗ በኩል የማርያም ልጅ ነኝ ስላለች ልናምናት ኖሯል ታዲያ?

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

3 Comments

 • የብቻ ተስፋዬ commented on September 15, 2016 Reply

  ታላቅ ማስተዋል

 • zeruethiopi@gmail.com'
  Zerihun commented on November 28, 2017 Reply

  Kezhi yetazebekute negre benore gna chenekelathi alebesleme ….beka

 • የማርያም ልጅ አቦ commented on January 14, 2021 Reply

  ጥሩ አባባል ነው በጣም ደስ ይላል ቀጥልበት?

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...