Tidarfelagi.com

የሚጠይቁና ለጥያቄያቸው መልስ የሚሹ ሰዎች በደንብ የሚያስቡ ናቸው!

አባቶቻችን የመጠየቅን አስፈላጊነት ሲያሰምሩበት ‹‹ካለመጠየቅ ደጅ አዝማችነት ይቀራል›› ይሉናል። ፈረንጆቹም ‹‹ካልጠየቅክ አታገኝም! (If you do not ask, you will never get)›› ይላሉ። ሊቃውንቱም ‹‹መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ›› በማለት መጠየቅ የሕይወት በርን፣ የአዕምሮ ደጃፍን፣ የልቦና መስኮትን ወለል አድርጎ ከፍቶ ከጥበብ ማማ ላይ እንደሚሰቅል ያስረዱናል። ከራሳቸው ጋር የማይጠያየቁ ለምንም ነገር መልስ አያገኙም። የሚጠይቅ ሕሊና መልሱን ለማግኘት ብዙ ያስባል። ብዙ የሚያስብ አዕምሮ ያሰላስላል። የሚያሰላስል ሕሊና አንድን ሃሳብ ጥቅሙን ብቻ ሳይሆን ጉዳቱንም፤ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን ነገ ይዞት የሚመጣውን ጣጣና ፈንጣጣ አልያ ደግሞ ሲሳይና መልካም አጋጣሚ ቀድሞ እንዲረዳ ያደርጋል። አሰላሳይ ሕሊና፣ ሃሳብ ፈጣሪ አዕምሮ፣ ስሜት አመዛዛኝ ልቦና በጥያቄና በመልስ ይበስላል እንጂ በጥያቄ ብቻ ጥሬ ሆኖ አይቀርም። ጥሬ ስጋ ካልበሰለ ለሆድ እንደማይስማማው ሁሉ ተጠይቆ ያልተመለሰ ጥያቄም ለሕይወት የሚስማማ መልካም ነገር አያተርፍም። በተግባር ያልተመለሰ ጥያቄ በደንብ ያልታሰበ ነው።

በርግጥ ነገ ሙሉ በሙሉ ርግጠኛ የማንሆንበት ቀን ነው። ምን ነገ ብቻ! ከደቂቃዎች በኋላ በሕይወታችን ላይ ሊከሰት የሚችለውን ነገር ማወቅ የማንችል መሃይማን ነን። ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም ብለን ግን ስለነገ ማሰብ አንተውም። የምንችለውን ሁሉ ጠይቀንና መልሱን ፈልገን ነገን የእኛ ለማድረግ እንጥራለን እንጂ በደመነፍስ ያለሃሳብ አንጠብቀውም። ሳናስብ፣ ሳንጠይቅና መልሱን አዘጋጅተን የማንጠብቀው የነገ ሕይወታችን በእኛ ምሪት ሳይሆን በራሱ መንገድ ይዞን ይጠፋል። ከየት አንስቶ ወዴት እንደሚያደርሰን አናውቅም። በመሆኑም በመጠየቃችንና ጥያቄያችንን መሠረት አድርገን በማሰባችን ነገን ለመገመት አንቸገርም። ነገን ቀድሞ ለመዘጋጀት ዛሬን ማሰብ፣ ትናንትን ደግሞ እንደመነሻ ልምድ በመውሰድ ለነገ የተሻለ ዝግጅትና አዲስ አስተሳሰብ ይዘን እንድንጠብቅ ያደርገናል።

ቻይናዊው ፈላስፋ ኮንፊሽየስ፡-

‹‹ጥያቄ የሚጠይቅ ለዛች ለጠየቀባት ደቂቃ ሞኝ ነው። ጥያቄ የማይጠይቅ ግን ሕይወቱን በሙሉ ሞኝ ይሆናል። (The man who asks a question is a fool for a minute, the man who does not ask is a fool for life)›› … ይለናል።

እውነት ነው! ጥያቄ የማይጠይቅ ሰው ሁልጊዜ ሕይወቱን በሙሉ በቀላሉ እንደሚታለል ሞኝ ልጅ ነው። ሌሎች ጠይቀው በቀየሱት የሕይወት መንገድ ይረማመዳል እንጂ የራሱን የሕይወት ጎዳና ፈልጎ በማግኘት ለራሱ የሚስማማውንና የሕይወት ውጣ ውረዱን የሚሸጋገርበትን የሃሳብ ድልድዩን ሠርቶ አይቀርፅም። የጥልቅ አሳቢዎች ተመልካች እንጂ ጠልቆና ረቅቆ ለማሰብ ራሱን ጠይቆ ራሱን ለማግኘት አይሞክርም። አንዳንድ ሰዎች ህፃናት የሚጠይቁትን ጥያቄ አሳንሰው ያያሉ። ነገር ግን የልጆችን ጥያቄ ተረድቶ መልሱን ለማግኘት የሞከረ እምብዛም ነው። ቢሞክር የጥያቄውን ከባድነት ይረዳል። የሚጠይቁ ሰዎች የሚያስቡ ናቸው። ለማሰብ ለማሰላሰል፣ አዙሮ ለማየት የማይፈልጉ ሰዎች አይደለም ሊጠይቁ ቀርቶ ሲጠየቁ ይሸሻሉ። ጥያቄን የሚፈሩ ሰዎች የአዕምሯቸውን አቅም አሟጠው መጠቀም የማይችሉ ናቸው። ዛሬ ዛሬ በሐገራችን የምናያቸው ጥቂት ምሁራን፣ ያልበሰሉ ባለስልጣናትና ዝነኛ ነን ባዮች ጥያቄ ሲጠየቁ ያልባቸዋል። ጠያቂውን እንደጠላት ያያሉ እንጂ ለማሰብ እድል እንደሰጣቸው ሰው አይቆጥሩትም። ጥያቄን መፍራት ባሕላችን ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይሄም ራሳችንን መጠየቅ ባለመለማመዳችን ምክንያት ሌሎች የሚጠይቁንን ጥያቄ መሸከም የሚችልና መልስ ማመንጨት ብቃት ያለው አዕምሮ ማበጀት እንዳንችል አድርጎናል።

የሆኖ ሆኖ የጠየቀ ሁሉ አሳቢ ነው የሚል ድምዳሜ ውስጥ አንገባም። አንዳንዶች መጠየቅ እንጂ እንዴት እንደሚጠየቅ ዕውቀቱ የላቸውም። አጠያየቃችን በራሱ መልሱን ለማወቅም ይሁን ላለማወቅ መንገድ ጠራጊ ነው። እውነት ነው! መጠየቅ የለመደ ነገ እንዴት መጠየቅ እንዳለበት የአጠያየቅን ልምድን ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ነገር ግን መጠየቁ በራሱ አሳቢነቱን አያሳይም። ወደአሳቢነት ጥበብ የሚወስደው ጥያቄው ብቻ ሳይሆን አጠያየቁም፤ አጠያየቁም ብቻ ሳይሆን አመላለሱም ነውና። የሆነው ሆኖ ጠይቀው መልሱን የማይፈልጉ ጠያቂዎችም ከማይጠይቁት መሻላቸው ምኑ ላይ ነው? በመጠየቅ ማሰብና ማሰላሰል ቢኖርም መልሱን በመፈለግ ሂደት ውስጥ ደግሞ በሃሳብ ባህር መስመጥ፣ መርቀቅና መጥለቅ አለ። በሃሳባቸው የጠለቁና የረቀቁ ጥልቅ አሳቢዎች ዕውን የሚሆኑት የጥያቄአቸውን መልስ ፈልገው መልሱን የሚያገኙት ብቻ ናቸው። ራስን፣ ሕይወትን፣ ዓለሙን መጠየቅና ምላሹን ፈልጎ ማግኘት የጥበቦች ሁሉ ጥበብ ነው!

ራሱን መጠየቅ የለመደ ሌሎች ቢጠይቁት አይደነግጥም። ይልቁንም በሌሎች ጥያቄ ሃሳቡንና ራሱን እንዲገልፅ ያደርገዋል እንጂ። በመሆኑም ራሳችንን፣ ሕይወታችንን፣ ፊታችንን፣ ኋላችንን እየጠየቅንና መልሱን እየፈለግን ራሳችንን በሃሳብ ከፍ ከፍ እናድርግ። እንመራችኋለን የሚሉትንም ባለስልጣኖቻችንንም አልያም ደግሞ እንወክላችኋለን የሚሉን የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንም ቢሆን በመጠየቅ እናብስላቸው፤ በመጠያየቅና መልስ በመፈለግ ራሳችንንና ሃሳባችንን እናክም የዛሬው መልዕክት ነው!

ቸር የሕይወት ጥያቄና መልስ!

________________________

እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

አርብ ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

One Comment

  • Anonymous commented on August 16, 2021 Reply

    ደስ የሚል እይታ ነው።ራሴን ከመተየክ ልጀምር

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...