Tidarfelagi.com

የመውሊድ ትዝታዎቼ

የመውሊድ በዓልን እያከበርነው ነው።
በዚህ ጽሑፌ ስለበዓሉ አከባበር የማወጋችሁ ነገር የለም። ከዚያ ይልቅ ያኔ በልጅ ወኔአችን ከሰራናቸው “አድቬንቸሮች” አንዳንዶቹን አጋራችኋለሁ።
*****
በህዳር ወር 1980 ነው። በወቅቱ እኔ (አፈንዲ)፣ መሐመድ አብደላ (ማመኔ)፣ ጆሀር ሀጂ ዩሱፍ (ጀዌ)፣ አድናን ዑመሬ (አግሽ)፣ እና አሕመዶ ሙሄ የምንባል ልጆች በሼኽ ዑመር አሊዬ ሀድራ (እስላማዊ ማዕከል) በሚከበረው የመውሊድ በዓል ለመታደም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ከሀድራው ተገኝተናል። በሁሉም ስፍራ ተዟዙረን መንዙማውንና ዚክሪውን ካየን በኋላ “ቤይቱል ሀድራ” ከሚባለው ቤት ታዛ ስር (ከውጪ በኩል) አርፈን መጨዋወት ጀመርን። በዚያን ጊዜ ጫት ስለማንቅም ዋነኛ መዝናኛችን “ቀደዳ” እና “ለከፋ” ነው። ስላየናቸው የህንድ ፊልሞች እናወራለን። ተረት የሚያውቅ ካለ ተረት ያወጋናል። የእግር ኳስ ወሬም እንጋራለን። ወሬ ማውራቱ ከሰለቸን ደግሞ እርስ በራሳችን እንተራረባለን። በዚያ ዘመን አንዳንዶች “እንካ ሰላንቲያ” እያሉ የብልግና ለከፋ ይላከፋሉ። እኔ በነበርኩበት ቡድን ውስጥ ግን ከመበሻሸቅ በስተቀር በብልግና ቃላት አንሰዳደብም። ደግሞም ለከፋው ከራሳችን አልፎ ወደ ቤተሰብ አይሻገርም።

በዚያች ምሽት “አግሽ” የተባለው ልጅ ድሮ የምናውቀውን አንድ ተረት ያጫውተን ጀመር። ተረቱ “Waman ajaa’iba” (አንድ ነገር ይገርመኛል) እያሉ ስርቆት ስለሚያካሄዱ ሁለት ሌቦች ነበር የሚተርከው። አግሽ ተረቱን ተርኮ ካበቃ በኋላ በዚያችው ቅጽበት ወደ ለከፋ ዞረ። እናም “Waman ajaa’ibaa” እያለ ሁላችንንም መተረብ ጀመረ። በአግሽ ለከፋ እየሳቅን ስንቀጥል ጭራሽ ለከፋው ወደ መንዙማ ስልት ተቀየረ። አግሽ አዝማቹን ገጥሞ በዜማ ለቀቀው። እርሱን ተከትሎ ደግሞ ጆሀር ሀጂ ዩሱፍ (ጀዌ) ከአዝማቹ የሚለጥቁትን ግጥሞች እዚያው ማፍለቅ ጀመረ። ጀዌ ግጥሞቹን ሲለቅ እኛ በመንዙማ ዜማ መቀበሉን ተያያዝነው።

ከዚያን ጊዜው ግጥሞች መካከል የሚበዙትን አሁን አላስታውሳቸውም። ሆኖም ሁሉም “Waman ajaa’ibaa… Waman ajaa’iba” በሚል ሀረግ ነው እንደሚጀምሩ አልዘነጋም። በግጥሙ ውስጥ አንዱን ጓደኛችንን የሚያበሽቁ ስንኞች ይደረደራሉ። በመጨረሻው ላይ መሪው ግጥሙን ደርድሮ ሲጨርስ እኛ አዝማቹን እንዘምራለን። ጀዌ ከገጠማቸው ግጥሞች አንዱ ይህ ነው።
Waman ajaa’iba waman ajaa’iba (2)
Akkuma Maammanneen daabboo madaan tuqatee tii nyaatune ajaa’iba.

ይህ የኦሮምኛ ግጥም በአማርኛ ቢፈታ ጥሩ ስሜት አይሰጥም። በጨዋ ደንብ ሲታይ “ነውር” የሚባል ዐይነት ነው። ሆኖም መፍታት ግዴታዬ ነውና ለጊዜው ነውሩን ጥሼ ልተርጉመውና ላሳያችሁ።

“ አንድ ነገር ይገርመኛል፤ አንድ ነገር ያስገርመኛል!
ማመኔ ዳቦውን በመግል እያጠቀሰ የሚበላበት ሁኔታ ይገርመኛል።”

በዚህ ግጥም ውስጥ የተሰደበው ማመኔ ነው። ይሁንና በጊዜው ሲተረብ የነበረው እርሱ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ተራው ሲደርሰው የመጣለትን ሐሳብ በግጥም እየደረደረ ሌሎች የቡድኑን አባሎች ይለክፋል። የሚያሳዝነው ነገር ግን በአዝማቹ ውስጥ የሚተረበው “ማመኔ” ብቻ መሆኑ ነው። ይህንንም ያደረገው “አግሽ” ነው። አዝማቹ በመንዙማ ደንብ መሰረት “አላሁማ ሰሊ ዓላ ሙሐመዲን” ብሎ ይጀምራል። በማሰሪያው ላይ ደግሞ በተረብና በለከፋ ይቋጫል። እስቲ ሁሉንም እዩት።

Allahumma Salli alaa Muhammadin (አላሁማ ሰሊ ዓላ ሙሐመዲን)
Maammanee mukha ija hinqabnee (ማመኔ ፍሬ የሌለው ዛፍ ነው)
Goggogaa dirqoosha maxxannee (እንዲያውም እንደ ድርቆሽ የደረቀ ነው)።

ታዲያ በዚያች ሌሊት በጣም ያስቀን የነበረው እያንዳንዱ ሰው የሚፈጥረው የለከፋ ግጥም አይደለም። በጣም ሲያስፈነድቀን ያመሸው “አግሽ” የፈጠረው አዝማች ነው። ምክንያቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ? ሌሎቻችን በግጥም ስንለከፍ ምንም ሳይሰማን እናሳልፍ ነበር። ማመኔ ግን በታወቀው ንጭንጩ “እኔን ብቻ ነው እንዴ የምትችሉት? አግሽ ለምን መንዙማውን በጀዌና በአፈንዲ ስም አያደርገውም?” እያለ እርሪ ይላል። እኛም ማመኔ ብሽቅ ብሎ ሲነጫነጭልን አንጀታችን ቅቤ ይጠጣል። እስኪበቃን ድረስ ስቀን ስናበቃ ባለተራው ግጥሙን ይገጥማል። እኛ ግን ከተረኛው ግጥም ጉዳይ አልነበረንም። ግጥሙ አልቆ አዝማቹን በህብረት የምናዜምበትን ቅጽበት እንጠባበቃለን። ከዚያም ግጥሙ ሲያልቅ ሁላችንም ወደ ማመኔ እየተመለከትን “Maammanee… Mukha ija hinqabnee” እያልን እንዘምራለን። ማመኔ “እኔን ብቻ ነው የምትችሉት?” እያለ መማረሩን ይቀጥላል። እኛም መሳቃችንን እንቀጥላለን።

በዚያች የመውሊድ ምሽት የተፈጠረው ኪነታዊ ቅንብር በሀድራው ግቢ ተወስኖ አልቀረም። በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማው ተስፋፍቶ ሁሉም የሚደጋግመው ህብረ-ዜማ ለመሆን ችሏል። ማመኔም በዜማው የሚያበሽቁትን ልጆች እያሳደደ ሲማታ ከረመ። ዜማው መረሳት የጀመረው ማመኔ ጎርምሶ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ከሆነ በኋላ (በ1983) ይመስለኛል።

እዚህ ዘንድ አንዳንዶቻችሁ “ሰለዋትን ከተረብ ጋር መቀላቀላል ሐጢአት አይደለም እንዴ?” ልትሉኝ ትችላላችሁ። በርግጥም እኛ እናደርግ እንደነበረው ሰለዋትን ለብሽሽቅ መጠቀም ሐጢአት ነው። ይሁንና በዚያ ዘመን በመላው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር በነበረው ባህል በመንዙማ የሚወዱትን ማድነቅና የሚጠሉትን ማንኳሰስ በጣም የተለመደ ነገር ነበር። ባል ሚስቱ ካስከፋችው በመንዙማ እያስመሰለ ስሜቱን ይገልጻል። ሚስትም የባሏ ጸባይ ካላማራት በመንዙማ ትታረባለች። በስራ ጊዜም መንዙማን ለወኔ መቀስቀሻ የመጠቀም ልማድ በሰፊው ይታወቃል። የደርግ መንግሥትን በመንዙማ የሚያወግዙ ሼኾች ነበሩ። በ1982-83 የሰሜኑ ጦርነት እየተጠናከረ ሲመጣ ደግሞ ወያኔና ሻዕቢያን የሚያወግዙ መንዙማዎች ተደርሰው ነበር (በሀረር ሬድዮ ጣቢያ የኦሮምኛ ስርጭት ፕሮግራም ይቀርቡ እንደነበርም አስታውሳለሁ)። በ1984 ደግሞ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ይካሄድ በነበረው የጦፈ ፉክክር ምክንያት ድርጅቶቹን በመንዙማ ስልት ማድነቅና ማጥላላት በስፋት ይካሄድ ነበር። በዚህም የኦነግ እና የኦነእግ (የኦሮሞ ነጻነት እስላማዊ ግንባር) ደጋፊዎች የአንበሳ ድርሻ ነበራቸው።
*****
ትልቁ የገለምሶ መውሊድ ባበቃ በአስራ አምስተኛ ቀን ሌላ የጦፈ መውሊድ “ደረኩ” በሚባል የገጠር መንደር ይከበራል (ይህ ቀበሌ ከገለምሶ ከተማ በስተደቡብ በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል)። በዐረፋ ወር ደግሞ ቀጣይ የመውሊድ በዓል ሎዴ በሚባል ስፍራ ይከበራል (የሚከበረው የአረፋ በዓል ቢሆንም አከባበሩ በመንዙማና በዚክሪ በመሆኑ ህዝቡ “መውሊድ” እያለ ነው የሚጠራው)። በደረኩ የሚከበረው መውሊድ በጣም ደስ የሚለው ለበዓሉ የመጣ ማንኛውም ሰው እራት እንዲበላ የሚደረግ በመሆኑ ነው። የተኙ ልጆች እንኳ እየተቀሰቀሱ እንዲበሉ ይደረጋል። በገለምሶና በሎዴ በሚከበሩት በዓላት ግን ብዙ ጊዜ “በዓሉን ለመበጥበጥ የመጣችሁ ዱርዬዎች ናችሁ” በሚል በከተማ ልጆች ላይ ማዕቀብ ይጣላል። ስለዚህ ወደ ገለምሶው ሀድራ የሚሄድ ልጅ በአብዛኛው እራቱን ከቤቱ በልቶ ነው የሚሄደው። በሎዴ ደግሞ በልዩ ልዩ ዘዴ ካላጭበረበሩ በስተቀር የከተማ ልጆች እራት አያገኙም።

የገጠር ሰዎች “በዓሉን ለማክበር አልመጣችሁም” ለሚለው ክሳቸው እንደ ማስረጃ የሚቆጥሩብን ትልቁ ነጥብ አንድ ቦታ ቁጭ ብለን መንዙማ የማንዘምር መሆናችን ነው። እውነታቸውን ነው። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እኛ መንዙማውን ትንሽ ከነካካንለት በኋላ ወደ አንድ ጥግ ሄደን የራሳችንን ጨዋታ መጫወቱን እንመርጣለን። በምሽቱ መጀመሪያ ላይ በየቦታው የሚዘመረውን መንዙማ ካዳመጥን በኋላ አንድ ቦታ መርጠን ቁጭ እንልና ተረብና ለከፋ እንጀምራለን። ለከፋው ከሰለቸን ተረት እናወጋለን። ወይ ደግሞ እንቆቅልሽ እንጠያየቃለን። አስተናጋጆቹ እራት ማብላት ሲጀምሩ (ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ሲሆን) ልዩ ልዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን እየተጠቀምን እራት ለማግኘት እንሞክራለን።

ከምናጭበርብርባቸው ዘዴዎች መካከል በጣም የተለመዱት “ከአዋሽ የመጣሁ እንግዳ ነኝ”፣ “እኔ እኮ የሸሪፍ መሐመድ ዘመድ ነኝ” (ሸሪፍ መሐመድ የሀድራው መሪ ናቸው) የመሳሰሉ ማስተዛዘኛዎችን ለአስተናጋጆቹ መንገር ነው። ይሁንና እነዚህ ዘዴዎች ለአንድ ሰው ወይም ለሁለት ሰው ብቻ ነው እራት የሚያስገኙት። ስለዚህ ሁላችንንም የሚመግብ ዘዴ መፍጠር ግድ ይለናል። በዚያን ጊዜ ካጭበረበርንባቸው ዘዴዎች መካከል ሁለቱን ላጫውታችሁ።

በ1982 መጨረሻ ላይ ይመስለኛል። እንደተለመደው የሎዴ ሀድራ አስተናጋጆች “እራት አትበሉም” በማለት ማዕቀብ እንደሚጥሉብን እርግጠኛ ሆነን ነበር። በመሆኑም አንድ ሰው “ለምን መንዙማ የምንዘምር አናስመስልም” አለን። ሁላችንም በነገሩ ስለተስማማን ማስመሰል ጀመርን። ሆኖም መንዙማውን በግጥም የሚመራልን ሰው ጠፋ። በዚህም የተነሳ ተጨነቅን። ምን እንደምናደርግ ግራ ገባን። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ሌላ ልጅ “ለምን ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆን አምጥተን አናስዘምረውም” አለን።

እኛም “ድንቅ ብልሃት ነው፤ ነገር ግን ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆ እዚህ ለመምጣቱ እርግጠኛ ነህ?” በማለት ጠየቅነው። ልጁ “እርግጠኛ ነኝ፤ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ አይቼዋለሁ” በማለት መለሰልን (ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆ የታወቀ እብድ ነው፤ ነገር ግን ከማበዱ በፊት ሼኽ የነበረ በመሆኑ መንዙማና ሰለዋት ሲያደርግ ነው የሚውለው)።

ሁላችንም ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆን ፍለጋ ጀመርን። ከብዙ ልፋት በኋላ ለማኞች በተሰበሰቡት ቦታ ጫቱን ሲያመነዥክ አገኘነው። በለሰለሰ አንደበት “ሼኽ ሙሐመድ፤ እኛ የርስዎ ጀመዓዎች እያለን ከዚህ ወራዳ ስፍራ ምን ያደርጋሉ? እሳት አንድደን ሞቅ አድርገን እየጠበቅንዎት ስለሆነ የዛሬዋን ምሽት ከኛ ጋር ያሳልፉ” አልነው።

ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆ ኮተቱን ሰብስቦ ተነሳና ተከተለን። በመንገዳችንም ላይ ሳንቲም አዋጥተን ሲጋራ፤ ሰንደል (ነድ) እና ስኳር ገዛንለት። ከዚያም በመንዙማ አጀብ እኛ ወደነበርንበት ቦታ ወሰድነው። ሼኽ ሙሐመድ ለትንሽ ጊዜ ጫቱን ቃም ቃም ካደረገ በኋላ መንዙማውን ይለቀው ጀመር። እኛም በጋለ ስሜት መቀበሉን ተያያዝነው። አላፊና አግዳሚው “ከየት የመጣ ሼኽ ነው?” እያለ ይመለከተው ገባ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የዱርዬ ስብስብ የተባለው ጀመዓ በሼኽ ሙሐመድ ሻንቆ መሪነት በሚያወርደው መንዙማ የሌሎች ተፎካካሪ ለመሆን በቃ። በዚህም የተነሳ በፊት “ቦዞኔ” እያሉ ሲያባርሩን የነበሩ አስተናጋጆች ከአምስት ያላነሰ ማዕድ አመጡልን። እኛም ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆን እያመሰገንን እራታችንን ጥስቅ አድርገን በላን። ከዚያም ሼኻችንን አሰናብተን ወደ መደበኛ ጨዋታዎቻችን ተመለስን።
*****
በሌላ ዓመት ነው። መውሊድን ለማክበር በዚያው የሎዴ ሀድራ ተገኝተናል። በዚህኛው ዙር እራት እንድናገኝ የፈጠርነው ዘዴ ሰርጎ ገብነት ነው። ይህኛውን ጉዳይ ባስታወስኩት ቁጥር እስቃለሁ። የሆነው እንዲህ ነው።

በመውሊድ ወቅት ምግብ የሚያድሉ አስተናጋጆች እርስ በራሳቸው አይተዋወቁም። ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ናቸው በፍላጎታቸው አስተናግዳለሁ ብለው የሚነሱት። እነዚህ አስተናጋጆች ምግቡ ከሚወጣበት ማዕድ ቤት እስከ መድረሻው ድረስ በሰልፍ ነው የሚጓዙት። ማንኛውም ሰው ከደከመው ለማንም ሳይናገር አስተናጋጅነቱን ትቶ ማረፍ ይችላል። በተጨማሪም ለአቅመ አዳም የደረሰ ማንኛውም ሰው በፈለገው ሰዓት ከመሬት ተነስቶ (የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቅ) አስተናጋጅ መሆን ይችላል። በዚያ ቦታ ስርቆት አይታሰብም። በዘመኑ ስርቆት መስጊድ፤ ሀድራና ቤተክርስቲያን አልገባም። በመውሊድ በዓልም ይኸው ስነ-ምግባር ይከበራል። እንግዲህ ይህንን ጥብቅ ስነ-ምግባር ጥሰን ነው ስርቆት የፈጸምነው። እንዴት? አሁንም ትረካዬን ልቀጥልላችሁ።

ከገለምሶ በመጣነው ቡድን ውስጥ “ባቼ” (ጃዕፈር ሙሐመድ በከር) የሚባለው ልጅ ተከትሎናል። ይህ “ባቼ” ከሁላችንም ይተልቃል። እድሜው ከአስራ አምስት ይበልጣል። ሰውነቱም በጣም ወፍራም ነው። ባቼ በዚህ ቁመናው በመጠቀም አንድ ማዕድ እንደሚያስገኝልን ቃል ገባ። በጨለማ ቦታ እንድንጠብቀው ከነገረን በኋላ በሰልፍ ምግብ የሚያመላልሱትን አስተናጋጆች ተቀላቀለ። እኛም እንደተነገረን አደረግን።

ባቼ አንድ ሁለቴ ምግቡን በስነ-ስርዓቱ አመላለሰ። በሶስተኛው ላይ ግን ቀስ እያለ ከአስተናጋጆቹ ሰልፍ ወጣና ጨለማ ውስጥ ሆነን እንጠብቀው ለነበርነው ጓደኞቹ አስረከበን (ለራሱ እንዳይያዝ ግን ከሰፊው የበዓሉ ታዳሚ መሀል ገብቶ ተሰወረ)። እኛም ምግቡን ጥግ ሄደን እየተሻማን በላነው። ይሁንና ብዙ ስለነበርን አንድ ማዕድ ሊበቃን አልቻለም። እንዲያውም ትንንሽ ልጆች ምንም ሳይቀምሱ ነው ያለቀብን። ስለዚህ ተጨማሪ ማዕድ መዝረፍ ግድ ሆነብን። ይህኛውን ግዳጅ እንዴት እንደምንወጣ ስንመካከር ሑሴን ረሺድ (በቅጽል ስሙ “ማይክል”) የሚባለው ልጅ ፈቃደኛ ሆኖ ተገኘ።

ይሁንና ይህ ማይክል በእድሜው ከኛ ብዙም አይርቅም። ስለዚህ ትልቅ ሰው እንዲመስል ማድረግ ነበረብን። በዚህም መሰረት ተረከዙ ረጅም የሆነ ጫማ ፈልገን አለበስነው። ከወገቡ በታች ሽርጥ አሰርንለት። በለበሰው ጃኬት ላይ ሁለት አንሶላዎችን ደራረብንለት። በራሱ ላይ የማመኔን ነጭ ጃኬት እንደ ጥምጣም አሰርንለት። በመጨረሻም ማይክል ትልቅ ሰው መሰለ። (ባይገርማችሁ የያኔው አለባበስ ማይክልን ከሰሜን አፍሪቃ የመጣ የቱአረግ-በርበር ተወላጅ አስመስሎት ነበር። ሌሎቹ አስተናጋጆች ግን አለባበሱን ፈጽሞ አላስተዋሉም)።

ማይክል ራሱን “በርበር” አስመስሎ ከአስተናጋጆቹ ተርታ ተሰለፈ። እርሱም እንደ ባቼ ሁለት ጊዜ ያህል ምግቡን ካመላለሰ በኋላ በሶስተኛው ላይ አንዱን ማዕድ ጠለፎ አመጣልን። እኛም እስኪበቃን ድረስ በላነው (አንዱ ማዕድ ከአስር እንጀራ በላይ እንዳለው ልብ በሉ)። በዚህኛው ወቅት ግን የሀድራው ተቆጣጣሪዎች አንድ ማዕድ እንደተሰረቀ ሊነቁ ችለዋል። በመሆኑም ሳናስበው እኛ ወዳለንበት ስፍራ በጥቆማ መጡና የዱላ መአት አወረዱብን። በዚህን ጊዜ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ሆነ። ሁላችንም እንዳንያዝ በየአቅጣጫው ተበታተንን። በወቅቱ ምግቡን የበላነው በጨለማ ቦታ ስለነበር ተቆጣጣሪዎቹ ከአንድ ሰው በስተቀር ሌሎቻችንን በመልክ ሊለዩን አልቻሉም። ከኛ ውስጥ መለየት የቻሉት ማመኔን ብቻ ነው። እርሱ ግን “አልታወቅኩም” በሚል መንፈስ ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ከአንድ ቤት ጥግ ቆሞ ወጪ ወራጁን ይመለከት ነበር። ተቆጣጣሪዎቹ እየተጠቋቆሙ መጥተው “ይህ እኮ ነው ማዕድ የዘረፈው” እየተባባሉ በአርጩሜ የሚበቃቸውን ያህል ዠለጡት።
*****
ከላይ እንደገለጽኩት “ደረኩ” በሚባለው ቀበሌ በሚከበረው የመውሊድ በዓል ለመታደም ስንሄድ የእራት ችግር ገጥሞን አያውቅም። ከዋናው እራት በፊት እንኳ “ለመቆያ ይሆናችኋል” ተብሎ ንፍሮ ይሰጠን ነበር። ታዲያ በ1980 በዚያች ቀበሌ በተከበረው በዓል እስከ ዛሬ የሚያስገርመኝ ነገር አጋጥሞኝ ነበር።

በወቅቱ እኔ፣ ጀዌ፣ ማመኔ እና አሕመዶ ሙሔ አንድ ቦታ ነበር ያደርነው። ትምህርት የምንማረው በጧት ፈረቃ ስለሆነ እራት ከበላን በኋላ ወዲያውኑ ተኛን። ሌሊት ላይ ጀዌ “እናንተ.. ሊነጋ ነው እኮ!… ትምህርት እንዳያመልጠን ቶሎ ወደ ገለምሶ እንሂድ” እያለ ቀሰቀሰን። ምን ያህል እንደተኛን በርግጠኝነት አላውቅም። ሁላችንም ተነስተን ወደ ከተማችን የመልስ ጉዞ ጀመርን። ጥቂት እንደተጓዝን “ወደ ቦኬ ነው የምንሄደው” የሚሉ ሰዎች ገጠሙን (ቦኬ ከገለምሶ በስተደቡብ ምስራቅ በኩል ራቅ ብሎ የሚገኝ ወረዳ ነው)። በዚህን ጊዜ ጀዌ “በአጭር ጊዜ ውስጥ ገለምሶ የሚያደርሰን መንገድ ስላለ ከነዚህ ሰዎች ጋር እንሂድ” አለን። እኛም ሐሳቡን ተቀብለን ከሰዎቹ ጋር ጉዞአችንን ቀጠልን። አንድ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ሰዎቹ “ወደ ገለምሶ የምትሄዱ ከሆናችሁ በዚህኛው መንገድ ብትቀጥሉ ይሻላል” በማለት አንድ ድንጋያማ መንገድ አሳዩን። እኛም እውነት ነው ብለን መንዱን ቀጠልንበት። ሆኖም መንገዱ ወደ ገለምሶ ሊወስደን አልቻለም። ለረጅም ጊዜ በደረቅ ሌሊት ባዘንን። ላይ ታች እያልን ብዙ ለፋን። ነገር ግን አንድም ፍንጭ ሊታየን አልቻለም።

በዚህም የተነሳ በጣም ተማረርን። ጀዌን መሳደብና መዝለፍ ጀመርን። “አንተ ነህ የማታውቀውን መንገድ አውቃለሁ ብለህ ወደዚህ ያመጣህን” እያልን ወቀስነው። እርሱ ግን ስድብና ወቀሳውን ችሎ መንገድ መምራቱን ቀጠለ። “አብሽር! ጥቂት ነው የቀረን” እያለ አስተዛዘነን። በመሀሉ ማመኔ “እነዚያን ሰዎች ጠረጠርኳቸው፤ የሰው ልጆች አይመስሉኝም፤ ጂኒዎች ሳይሆኑ አይቀሩም” አለን። በዚህን ጊዜ ልባችን እንደ መውሊድ ድቤ ይደልቅ ገባ። ፍርሀት አንቀጠቀጠን። የጅብና የቀበሮ ጩኸት ሲጨመርበትማ የባሰውኑ ተርበተበትን። ሶስታችንም ጀዌን ረገምነው። “ጅብ ከበላን ተጠያቂው አንተ ነህ!” አልነው። እርሱ ግን ሁሉንም ታግሶ አሳለፈ። ብዙ ከተንከራተትን በኋላ ከአንድ አነስተኛ ጉብታ ላይ ስንወጣ ከገለምሶ የሚበራው መብራት ጭላንጭል በርቀት ታየን። በዚህም ምክንያት ልባችን ትንሽ መለስ አለልን።

ይሁን እንጂ መብራቱ የሚታይበትን አቅጣጫ እየተመለከትን ብንጓዝ መንገዱ አላልቅ አለን። ወደ ከተማዋ ዳርቻ ለመጠጋት ብቻ ከገለምሶ-ደረኩ ስንሄድ የሚወስድብንን ጊዜ ያህል ፈጀን። ለረጅም ጊዜ እየተንገታገትን ተጉዘን እሁድና ቅዳሜ ከምንዋኘው ለገሃሬ የተሰኘ ጅረት አጠገብ ደረስን። በዚህም እፎይ አልን። (ለገሀሬ ከከተማችን ሁለት ኪ.ሜ. ያህል ይርቃል)።

በዚያች ሌሊት ጀዌ ከእንቅልፋችን የቀሰቀሰን ለኛ አስቦ ነበር። ነገር ግን ሁላችንም ማስተዋል ስለተሳነን በብርድ ተጠለዝን። ለምሳሌ አንዳችንም “ስንት ሰዓት ሆነ?” ብለን ለመጠየቅ አልሞከርንም። ጀዌ “ቶሎ ተነሱ! ሊነጋ ነው” ስላለን ብቻ ተነስተን ተከተልነው። ታዲያ ንጋቱ እርግጠኛ ሆኖ የመጣው ወደ ከተማችን ከገባን በኋላ ነው። ወደ ከተማዋ ዋና መንገድ ስንወጣ ታዋቂው ሙአዚን (ሑሴን ሾሮ) ገና የሱብሒን አዛን እያወጣ ነው። ከዚህ ሁኔታ እንደተገነዘብነው ጀዌ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ሲሆን ነው “ነግቷል” ብሎ የቀሰቀሰን። ከዚያች ሌሊት ገጠመኞቼ አንዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወርዋሪ ኮከብን በአይኔ ማየቴ ነው። ከዚያ በፊት “ኮከብ ይወረወራል” ሲባል ብሰማም ነገሩ ውሸት ይመስለኝ ነበር። በዚያች ደረቅ ሌሊት ባደረግኩት ጉዞ ሲባል የነበረው ሁሉ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ቻልኩ።
——-
ጥር 26/ 2006 ተጻፈ።
ሸገር – አዲስ አበባ
አፈንዲ ሙተቂ

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...