Tidarfelagi.com

የመታወቂያው ጉዳይ

የቀድሞው ቀበሌያችን አሁን አድጎ ወረዳ ሆኗል።
ከጠዋት ጀምሮ እስከ አሁን መብራት የለም ስለተባለ የመታወቂያ እድሳት ጉዳይ ለዛሬ አይሳካም ተብሎ ተመልሻለሁ።

ጥያቄዬን ግን ለተረኛው ሹም “ብሔር – ኢትዮጵያዊ የሚል መታወቂያ ይሰጠኝ” ስል አቅርቤ በፈገግታ እና በአግራሞት ሳቅ “ቅፁ ላይ ካለው ወይ ከአባትህ ወይ ከእናትህ ከአንዳቸው ብሔር መርጠህ መታወቂያው ይሰጥሀል እንጂ አንተ ያልከው መመሪያው አይፈቅድም” የሚል መልስ ከረዥም ሳቅ ጋር ተሰጥቶኛል። “ነገር ግን ነገ መብራት ይምጣና ጥያቄህን እናየዋለን” ብሎ በሳቅ እየተፍለቀለቀ አሰናብቶኛል።

ይህን ዛሬ አስቂኝ የመሰለ ጥያቄ ለወረዳው ሹም ሳቀርብ አስደሳች መልስ ማግኘት እንዲሁ በቀላሉ የሚሳካ እንዳልሆነ ገብቶኛል። ነገር ግን “መመሪያ” የተባለውስ ሳንካ ለምን አይቀየርም? የሚል ቅንነት ይዤ ነገም ቢሆን በድጋሚ ልሞክር በተስፋ ተመልሻለሁ።

የዛሬን ልፋቴን ያላሳካው መብራት ሀይል ይሆን ወይንስ መመሪያው?

 

“መረጃ ኦክሲጅን ነው” የግርግዳው ላይ መፈክር

መታወቂያዬ ላይ ያለውን ብሔር ወደ ‘ኢትዮጵያዊ’ ለማስቀየር የቀድሞው ቀበሌ ያሁኑ ወረዳችን ጋር ለሁለተኛ ቀን ተመልሻለሁ።

እስከ ምሳ ስራዬ ላይ ቆይቼ ሰባት ሰዓት ገደማ ሲሆን ሄድኩ። ሁሉም ቢሮዎች ዝግ ናቸው። ትላንትና የገባሁበት ሰፊ ክፍል በር አንኳኳሁ የሚከፍት የለም። ነገር ግን ገርበብ ብሏል።
እራሴው ከፍቼ ገባሁ። በርካታ ሰው በሚያስተናግደው ቢሮ ውስጥ ልክ እንደ ባንክ ቤት ሌላ የመስታወት ክፍልፋይ ክፍል አለው። ከመስኮቱ ባሻገር ያሉ የቢሮው ሰራተኞች ቡና አፍልተው ቁርሱን እየጎረደሙ በመዝናናት ላይ ናቸው።

ትላንትና ያስተናገደኝ ፍልቅልቁ ሰው ሲያየኝ ወዲያው አወቀኝ። መሳቁን ጀመረ።
“እሺ መጣህ ተመልሰህ”
“አዎ መጣሁ ያው ነገ ና ብለኸኝ ስለነበር ነው”
አልኩት
“መብራት ዛሬም የለም። ከጠዋት ጀምሮ አልመጣም” አለኝ
“ጉዳዬን ላናግረው የምችለው ሰው ካለ ምራኝና ላናግር”
አልኩት
“ምኑን ነው የምታናግረው?” ሲለኝ
“ያው ብሔር የሚለውን ኢትዮጵያዊ እንዲባልልኝ ወይንም ደግሞ ምንም እንዳይፃፍብኝ ነዋ!”
“ውይ እሱማ አይቻልም እኮ። ትላንት ነግሬህ የለ እንዴ?” የሱን ፈገግታ እኔም ተውሼ ለስለስ ብዬ

“ነግረኸኛል። ነገር ግን ነገ ና እና እንመካከርበታለን ብለኸኝ ነበር እኮ”
አልኩት። ከቡና ጠጪዎቹ ሰራተኞች መሀል እንዲሁ እድሜ ልኳን ሰው ስታመናጭቅ የኖረች የምትመስል ግንባሯ የማይፈታ ሴትዮ፡-
“ምንድነው የምትመካከሩት አይቻልም ተባልክ አይደለም እንዴ”

“ለምንድነው የማይቻለው?”
“መመሪያው አይፈቅድማ የምን መጨቃጨቅ ነው።”
“መመሪያውን ልታሳዪኝ ትችያለሽ?
“በኋላ ተመለስ አሁን ምሳ ሰዓታችን ነው”
“የስራ ሰዓታችሁ ስንት ሰዓት ነው የሚጀምረው?” አልኳት በእርጋታ።
“ሰባት ሰዓት ተኩል” ተመለስ አለችኝ
ሰዓቴን አየሁ “7፡18” ይላል። አስራ ሁለት ደቂቃ ይቀረዋል።
“እሺ እጠብቃለሁ” አልኳት
“ውጪ ሆነህ ጠብቅ” ብላ በአይኗ አስወጣችኝ።

አስራ ሁለት ደቂቃ ብዙ መሆኑ የገባኝ ዛሬ ነው። እንዳያልፉት የለም እንዲል ታጋይ። ሰዓቱ ደርሶ በሩን ከፍቼ ገባሁ። ገና እንደገባሁ መመሪያ የተባለውን ለማየት ስጠብቅ ፍልቅልቁ ሰውዬ፡-

“ያንተን ጉዳይ የሚመለከተው የወረዳው ስራ አስፈፃሚ ነው ስለዚህ አራተኛ ፎቅ ላይ ሄደህ አቶ እከሌን አነጋግር” ብሎኝ የስራ አስኪያጁን ስም ነግሮ ከሰትዮዋ የሚጉረጠረጡ አይኖች ገለል አደረገኝ።

እንደ ኮንዶሚንየም ቤት አይነት የተሰራውን ህንፃ ሽቅብ አራት ፎቅ በሚውረገረገው የብረት ደረጃ ወጥቼ ቢሮው ደረስኩ። ስራ አስፈፃሚው ቢሮዋቸው ውስጥ የሉም። እታች ያሉ ሰዎች ገለል ሊያደርጉኝ ወደ ላይ እንደሰቀሉኝ ባውቅም ትዕግስት እንደሚያስፈልገኝ አምኜ ንዴት ብዙም አይታይብኝም።

የዚህን ፎቅ ደረጃ እየወጣሁ ሳለ የአስተያየት መስጫ ሳጥን አይቼ ነበር። ነገር ግን ሳጥኑ ቁልፍ የለውም። ቁልፍ አልባ አስተያየት መስጫ፥ ምን ማለት ይሆን? ስል እያሰብኩ የስራ አስፈፃሚው የእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ቁጭ አልኩ።

በግርግዳው ላይ አስቂኝ ጥቅሶች አሉ አንደኛው እንዲህ ይላል። “መረጃ ኦክሲጅን ነው”

እንግዲህ ሰባት ሰዓት ተኩል የተቀመጥኩ እስከ አስር ሰዓት ድረስ ስራ አስፈፃሚው ቢሯቸው የሉም። ደጋግሜ ፀሀፊያቸን ስጠይቅ “ይመጣል። ለምሳ ወጥቶ ነው። ዛሬ ረቡዕ ስለሆነ እንግዳ ማስተናገጃ ቀኑ ነው።፡ሰኞ ረቡዕና አርብ እንግዳ ማስተናገጃ ቀን ስለሆነ ይመጣል። ጠብቀው”

ፀሀፊዋ ትሁት ስለሆነች መቀመጥ ብዙም አልጨነቀኝም። እግረ መንገዴንም ጉዳዬን ለሷ ባስረዳት መንገዱን ትጠቁመኝ ይሆናል ብዬ አዋየኋት።
“የመጣሁት መታወቂያዬ ላይ የተፃፈውን ብሔር ለማስቀየር ነው”
“ምን በእናትህ ተጽፎብህ ነው?”
“አይደለም። ብሔር ኢትዮጵያዊ እንዲባልልኝ ወይም ምንም እንዳይፃፍብኝ ነው የመጣሁት”
“ምን!”
እግሯን እያነሳች ሳቀችብኝ።

“ምን አይነት ጥያቄ ነው?” አለችኝ ከሳቋ እንደ መመለስ እያለችኝ። በዝርዝር አስረዳኋት።

ትንሽ ልትረዳኝ ሞክራለች “ሀሳብህ ገብቶኛል። ግን መመሪያው የሚፈቅድ አይመስለኝም። ለማንኛውም [አለቃ] ይምጣና ታናግረዋለህ” አለችኝ።

አንድ ‘የፍትህ ባለሙያ’ ነው ያለችኝ ወጣት ወደ ቢሮው ድንገት ሲመጣ የኔን ጥያቄ በደፈናው “መታወቂያ ላይ ብሄር አለማፃፍ ይቻላል ወይ?” ብላ ጠየቀችው። ወጣቱ የፍትህ ባለሙያ ቀልጠፍ ያለ መልስ ሰጠ “ብሔር ሳይሆን እንዴት ዜጋ መሆን ይችላል? አይቻልም። ብሔር ግድ ነው”

ከኔ ጋር ክርከር ገጠምን። በሂደት በሀሳቤ በከፊል ተስማማ። ችግሩ መመሪያ መሆኑን ነገረኝ። “እስኪ መመሪያ የተባለውን ነገር ማየት እችል ይሆን?” አልኩት። ከአራተኛ ፎቅ ቁልቁል አንደኛ ፎቅ ይዞኝ ተመልሰን ዝነኛውን መመሪያ አገኘሁት።

መመሪያውን የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነቶትና የነዋሪዎች አገልግሎት ጽህፈት ቤት የተባለ ተቋም ነው። “የነዋሪዎች መታወቂያ አሰጣጥ መሟላት ያለባቸው” የሚል የመመሪያው አካል ላይ ብሔር እና ሀይማኖት መታወቂያ ላይ መፃፍ እንደ መስፈርት ተቀምጧል።

ወጣቱን ባለሙያ ጠየቅኩት
“ለመሆኑ እዚህ ላይ ያሉ በሙሉ ግዴታ መፃፍ አለባቸው?” ስለው “አዎ!” አለኝ
“እስኪ መታወቂያህን ላስቸግርህ” አልኩት። ሰጠኝ።
“አሁን እዚህ ላይ የተፃፉ መስፈርቶች በሙሉ እዚህ መታወቂያ ላይ አሉ ነው የምትለኝ?” አልኩት
“አዋ” አለኝ። “ሀይማኖት የሚል ታዲያ የታለ?”

ሀይማኖት የሚለውን በመታወቂያው ላይ መኖር አለመኖሩን እያገላበጠ መፈለግ ጀመረ። “እውነትህን ነው የለም። ግን እኮ ሰው ሀይማኖት ላይኖረው ስለሚችል መፃፉ ብዙም ጥቅም የለውም” ሲለኝ
“መመሪያው ግን ያዛል” አልኩት።

በቃ በንግግር የሚያምን ሰው ስለነበር “ልክ ነህ” አለኝ። ከዚያም ቀጠል አደረግኹና “እኔም ብሔር የለኝም። ነገር ግን ብሔር አለኝ ለሚል ሰው ብሔሩን እንዲጽፍ ይፈቀድለት ለኔ ደግሞ ኢትዮጵያ በቂዬ ስለሆነች ብሔር የሚለው ቦታ ላይ ኢትዮጵያዊ የሚል እንዲጻፍልኝ ወይንም ምንም እንዳይፃፍ ብጠይቅ መመሪያው አይፈቅድም መባሉ በሎጂክ ፋላሲ አይሆንም ወይ?” ስል አጠናከርኩለት።

ከወረዳው ይልቅ የክፍለ ከተማው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሀላፊ ጋር ሄጄ እንዳሳምነው መክሮኝ ሰላምታ ተለዋውጠን ተለያየን።

በኋላ ላይ “በፕሮሲጀር የወረዳውን ሀላፊ መዝለል ልክ አይደለም” የሚል ምክር ስለተመከርኩ ስራ አስፈፃሚውን ለመጠበቅ ሽቅብ አራተኛ ፎቅ ተመልሼ ሄድኩ።

ስራ አስፈፃሚው አቶ እከሌ አስር ሰዓት ሲሆን መጡ።

ልጅ እግር ስለሆኑ አስፈቅጄ ‘አንተ’ እያልኩ ማናገር ጀመርኩ። ጥያቄዬን አቀረብኩለት። አልሳቀብኝም። ግን “መመሪያው የሚፈቅድ አይመስለኝም” ሲል ተመሳሳይ መልስ ሰጥቶኝ፥ ከመደርደሪያው መሀል ያለውን ሰነድ ያገላብጥ ጀመር። አዲስ የተባለውን የ2008 መመሪያ እና እነሱ የሚጠቀሙበትን የ2005 መመሪያ ሰጠኝ ሁለታችንም እያገላበጥን ካየን በኋላ የክፍለ ከተማው ሀላፊ ጋር በስልክ ደውሎ አናገረው።

ስልኩን ሲጨርስ “የሚቻል አይመስለኝም ነገር ግን ክፍለ ከተማ ሄደህ እሱን አሳምነውና ደውሎ በስልክ ከነገረኝ መታወቂያውን እንሰራልሀለን” የሚል መልስ ሰጠኝ።

አሁን የኔ ጉዳይ ከፍ እያለ ወደ ክፍለ ከተማ ስለደረሰ ጥሩ ለውጥ ነው ብዬ አመስግኜ ወጣሁ።

የስራ ሰዓት ሳያልፍ ተጣድፌ ክፍለ ከተማ ደረስኩ።

ሀላፊው የሉም። ሌሎች ሶስት ትልልቅ ሰዎች (ኤክስፐርት ይላል ማዕረጋቸው) ነገኘሁ። አንደኛዋ እመቤት ቀድመው አናገሩኝ።

“ስራ አስኪያጁ የሉም የዛሬ ሳምንት ሰኞ ወይንም ማክሰኞ ተመለስ” አሉኝ። “ኣረ አሁን ከወረዳው ሀላፊ ጋር በስልክ ሲያወሩ ሰምቻቸዋለሁ”
“ልክ ነህ ግን በህመም ምክንያት ነው የሌሉት በሚቀጥለው ሳምንት ሊገቡ ይችላሉ። ሰኞ ወይ ማክሰኞ ተመለስ”

“የወከሉት ሰው ይኖር ይሆን?” አልኳቸው። እስኪ እሱን አናግረ ብለው ትንሽ ፈንጠር ብሎ የተቀመጠ ኤክስፐርት አሳዩኝ። ኤክስፐርቱ ምስኪን ይመስላል። “ምን ልታዘዝ አለኝ” ጉዳዬን አስረዳሁት።

“መታወቂያዬ ላይ ያለውን ብሔር ኢትዮጵያዊ ለማስባል ነው የመጣሁት” አልኩት
በፈገግታ “ለምን?”
“ምክንያቱም እኔ በታፃፈብኝ ብሔር አላምንም። ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው። ሀገሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ስለሆነች ለዚህ ነው” አልኩት በትሁት አንደበት።

ኤክስፐርቱ ተደሰተብኝ “ፓ ምነው ሁሉም እንዳንተ ቢሆን። ጎበዝ” ፈገግታው አስደሰተኝ።
“ግን መመሪያው አይፈቅድም” አለኝ። ኩም አልኩ።
“ታዲያ ምን ይሻለኛል?”
“ፓስፖርት የለህም?”
“አለኝ”
“ታዲያ በፓስፖርትህ ተጠቀማ”
“እንደሱ አስቤያለሁ ግን ያው ፓስፖርት የመጨረሻ ምርጫዬ ነው። ነገር ግን ኪስ ውስጥ በቀላሉ ይዞ ለመሄድ አይመችም”
“ታዲዲ ለሱማ ጥሩ መፍትሔ አለ እኮ”
“ምን?”
አጠገቡ ያስቀመጠውን ብዙ መዛግብትና የምሳ እቃ የመያዝ አቅም ያለውን የቆዳ ቦርሳ እያሳየኝ፡-
“እንደዚህ አይነቱን ግዛና በዚህ መያዝ ትችላለህ”

የቅንነት አስተያየቱ ስለሆነ አሳዘነኝ። ዋናውን ጉዳዬን በድጋሚ ተመለስኩበት።
“በስራ ጉዳይ ኢትዮጵያን ስለምዞር ሁሉም ቦታ ፓስፖርት ማሳየት ትንሽ ቶሎ ሊያስረጀው ይችላል። በዚያ ላይ ደግሞ የወረዳውን መታወቂያ ቀልጠፍ ያለ ስለሆነ እሱ ይሻለኛል”
“እንግዲህ ሀሳብህ ጥሩ ነው። ግን ሀላፊውን ከሳምንት በኋላ ተመልሰህ ና እና ለማሳመን ሞክር” አለኝ።

እኒያ ፈገግ ብለው ውይይታችንን ሲያዳምጡ የነበሩ ኤክስፐርቷ እመቤት፡-
“ይሄ አንተ ያልከው እኮ ልክ ነው። ብሄር ምናምን ድሮ ያልነበረ ነገር ነው። አሁን እንዲህ የሆነው። እስኪ ሰኞ ማክሰኞ መጥተህ ሀላፊውን በደንብ ታናግረዋለህ። ግን ቆይ ስራህ ሾፌር ነህ እንዴ? ለምን በመንጃ ፍቃድህ አትጠቀምም ብዬ ነው”

“አይ ሾፌር አይደለሁም”
“እ ምንድነው ስራህ?”
“የፊልም ባለሙያ ነኝ”
“ውይ እንዴት ነው ቃና በጣም ጎዳችሁ አይደል?”

የዛሬው ውሎዬ ይሄን ይመስል ነበር። እንግዲህ ሰኞ እና ማክሰኞ ደግሞ ሶስተኛ ሙከራዬ ይቀጥላል።

ሠላም ለኢትዮጵያ!!

የመታወቂያው ጉዳይ – ሦስተኛው ሙከራ

6 Comments

 • atetefmelaku29@gmail.com'
  አተረፍ መላኩ commented on September 22, 2016 Reply

  ጥያቄህን እንዳታቆም እኔም ስጠይቅ ነበር አሁንም እጠይቃለሁ. ብሔር ማለት ሀገር ነው ሀገር ደግሞ ኢትዬጵያ. በነገራችን ላይ አንተ ያነሳሀው አመክንዮ ለሌሎችም መነሻ ሀሳብ ና ማሳመኛ ይሆናል.

 • tamiratbekelee@gmail.com'
  Tamirat commented on October 1, 2016 Reply

  why u don’t go? are you giving up

 • desubizu@gmail.com'
  Dessalegn Bizuneh commented on October 8, 2016 Reply

  ሸገሮች በምትፍፏቸው ፅሁፎች እየተማርኩባቸው እና እየተዝናናሁባቸው ስለሆነ አመሰግናችሁአለሁ። በርቱልኝ።

 • commented on November 20, 2016 Reply

  በጣም ደስ ይላል

 • asbe2015@gmail.com'
  አስበ commented on April 11, 2017 Reply

  ሸገር ብሎግ ወዝ ያለው መረጃ ድርቅ ባሰቃየን ወቅት የተከሰተ ድንቅ ብሎግ ፤ ያሬዶ በምትጽፋቸው ጽሁፎች ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን አንድነትን መስበክህ ሁሌም ይደንቀኛል ። እግዜር ጽጋውን ያብዜህ

 • asbe2015@gmail.com'
  አስበ commented on April 11, 2017 Reply

  ሸገር ብሎግ ወዝ ያለው መረጃ ድርቅ ባሰቃየን ወቅት የተከሰተ ድንቅ ብሎግ ፤ ያሬድ በምትጽፋቸው ጽሁፎች ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ፣አንድነትን መስበክህ ሁሌም ይደንቀኛል ። እግዜር ጽጋውን ያብዛልህ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...