Tidarfelagi.com

የሆነ ምሽት

ይሄ ንፍጣም ቫይረስ ወደ አገራችን ከመግባቱ ሁለት ወር አስቀድሞ የነበረውን ጊዜ እንደ ጉድ ጨፈርኩበት! ዛሬ እንዲህ ተጨማድጄ ልቀመጥ ያኔ እየዞርኩ የክለብ ምንጣፍ በዳንስ ሳጨማድድ አመሽ ነበር!

የዚያን ቀን ምሽት ከጊድዮን ጋር ነበርሁ፤ ባለትዳር ነው፤ የሚስቱና (ዛዮን) የሶስት ልጆቹ ፎቶ በስልኩ ስክሪን ላይ ወለል ብሎ ይታያል ፤ እኔ ስለጎተጎትኩት ፤ ሚስቱም “ እስቲ ዛሬ ወንድ ይውጣህ ! አምሽተህ ና” ብላ ስለገፋፋችው ነው እንጂ ጌድዮን በተፈጥሮው’ መዝናናት የተሳነው’ ሰው ነው፤
“ምን ላምጣላችሁ?” አለችን አስተናጋጂት ኤደን!
“ዘፈን የለም እንዴ ዛሬ?” ስል ጠየቅሗት የምንፈገውን ካዘዝኳት በሗላ።
“አራት ሰአት ላይ እንጀምራለን’
“እነማን አሉ?
“ኩኩ ሰብስቤ ! አለማየሁ ! ወንድሙ ጂራ “
“ አሹስ ?”
አሹ የታወቀ ተወዛዋዥ ነው፤ የሰማንያ አራቱን ብሄረሰቦች ውዝዋዜ አሳምሮ ይችላል ፤( ሶስቱ ብሄሮች ከኤርትራ ናቸው)፤ ‘ “ሰውነቱ አጥንት ያለውኮ አይመስልም ይሉታል ‘ አድናቂዎቹ!!
“ አሹ እንደታመመ አልሰማህም እንዴ?” አለችኝ በትካዜ፤
“ምን ገጠመው?”
‘’ በቀደም እለት አቶ ወርቁ አይተነው አምስት መቶ ሺ ብር ሲሸልሙት በድንጋጤ ከመድረክ ወድቆ ፤ አሁን ሼክ አላሙዲን እያሳከሙት ነው”
ጉዋደኛየ ጊድየን ሚስቱን ስልክ ለማናገር መሸተኞችን እየጣሰ ወጣ፤ ባልና ሚስቱ የሚያወሩትን መገመት አያቅተኝም ፤
“ ዛይየ” ይላታል
“ወይ አባቱ”
“ ሶስተኛ ቢራ ልጨምር ነበር ፤ይደብርሻል ?”
“ እንዴ ልትዝናና አይደል እንዴ ከቤት የወጣኸው? እንዲያውም ከስምንት በታች ጠጥተህ ከመጣህ እዚች ቤት አትገባትም ”
የጌድዮንና የዛየንን ጋብቻ እንዲሰጣችሁ እየትመኘው ታሪኩን ልቀጥል፤
ትንሽ ቆይቶ የክለቡ ፀጥታ አስከባሪ አቦሌ ወደ ተቀመጥንበት ጠረጴዛ መጣ፤
“ ስራ እንዴት ነው” አልኩት፤
“ ” አሼወይና ነው፤ “
“ አንተ እዚህ ቤት ከተቀጠርክ ጊዜ ጀምሮ ያጥንት ህክምና ክሊኒኮች ስራ እንደበዛባቸው ሰምቻለሁ “ ብየ አሟሟቅሁለት።
አቦሌ መጠነ -ሰፊ ፈገግታ አሳየኝ “ እንዴት ባለ ብቃት እየሰራሁ እንዳለሁ ለመታዘብ ከፈለግህ ትንሽ መጠበቅ አለብህ፤ ዋናው የጥሎ ማለፍ ድብድብ የሚጀምረው ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ ነው” አለኝ፤
“ እስከዚያ እንኳን የምንቆይ አልመሰለኝም ”
አቦሌ ቅር አለው፤ ግን ወድያው ዞር ብሎ አዳራሹን ከዳር እስከዳር ቃኘው ፤ወድያው ፊቱ በደስታ በራ “ ኦኬ! ያን ኤደንን ካልሳምኩ እያለ እሚወራጨውን ረጅም ሰውየ አየኸው?” አለኝ።
“ አው”
“ አንድ ጥፊ አይነስቡ ስር በስሱ እገባለታለሁ ፤ ሶስቴ ተሽከርክሮ ወደ ምስራቅ ከወደቀ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ጥጋብ ይሆናል ”
አራት ተኩል ላይ እኔና ጌድዮን ከክለቡ ወጥተን በቅርቡ ወደ ተከፈተ ሌላ ክለብ ሄድን ፤ መንፈቀሌሊት ገደማ ያልጠበቅነው ነገር ተከሰተ ! መደበኛው መብራት ጠፋና ባለህብረቀለም መብራት ክፍሉ ውስጥ መንቀዥቀዥ ጀመረ፤ አንዲት ገላዋ በሁሉም አቅጣጫ ሞላ ሞላ ያለ ቆንጅየ ሴትዮ ከሙታንታ በቀር እርቃን ሆና ወደ መድረክ ወጥታ ምሶሶውን እየታገለች መወረግረግ ጀመረች ፤ ደንበኞች ማውካት ማጨብጨብ ጀመሩ! ፤ እኔም ግራ እግሬን በቀኝ እግሬ ላይ ጭኜ ትእይንቱን ለማጣጣም ተሰናዳሁ ፤ ጉዋደኛየ ግን አልተመቸውም፤ ኮሌታየን ጭምድዶ እያካለበ ይዞኝ ወጣ፤ ጥቂት ጨዋ ታዳሚዎች እያጉረመረሙ ተከተሉን!
በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ቢራ እየጠጣን ስናወራ ፤አንድ ሽማግሌ ከክለቡ ወጡ፤በጣም ተናደዋል፤ በሽበት የተሞላውን የእርጎ ጣባ የመሰለውን ራሳቸውን እየነቀነቁ ከፊታችን ትንሽ ተንቆራጠጡ ፤ ሲጃራቸውን አቀጣጠሉና አንዴ ስበው ጭሱን ወደ ሰማይ ተኮሱት ‘በእድሜየ ማምሻ ላይ እንዲህ ያለ ጉድ ታሳየኝ !’ የሚሉ መሰለኝ! ትውልዱን ወክየ ግብዳ ድንጋይ ተሸክሜ እግራቸው ላይ ለመውደቅ ከጀለኝ
“ ዘገነነዎት አይደል አባት?”
አላቸው ጉዋደኛየ፤
“ በጣም እንጂ !” አሉ ሽሜው” ስንት ሽንኩር ሽንኩር የመሳሰሉ ኮረዶች እያሉ ይቺን ደባደቦ ፈትተው ይለቁብናል ? ”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...