Tidarfelagi.com

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ስምንት)

ክፍል ስምንት፡ በወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት መርህ

ባለፈው ትረካችን የጠቀስናቸው ሶስት አውሮፕላኖች በተጠለፉበት ዕለት (መስከረም 6/1970) ለይላ ኻሊድም በሌላ የጠለፋ ኦፕሬሽን እንድትሳተፍ ታዝዛ ነበር። ለይላ ጠለፋውን እንድታከናውን የታዘዘችው ከሁለት ፍልስጥኤማዊያን እና ፓትሪክ አርጌሎ ከሚባል የኒካራጓ ተወላጅ ጋር ነበር። ፓትሪክ አርጌሎ ከደቡብ አሜሪካ መጥቶ የግንባሩ ታጋይ የሆነው “ወዝአደራዊ ዓለም አቀፋዊነት” በሚባለው የሶሻሊስቶች መርህ በጥብቅ ያምን ስለነበረ ነው።

ለይላ የመጀመሪያውን ጠለፋ ካከናወነች ዓመት እንኳ አልሞላትም ነበር። ሆኖም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዋ ከፍተኛ በመሆኑ ለሁለተኛ የጠለፋ ኦፕሬሽን እንደተመረጠች ተነገራት። ለይላ ማንኛውንም መስዋዕነት ለመክፈል ወስና ነው ወደ ትግሉ የተቀላቀለችው። በመሆኑም የግንባሩ መሪዎች በዓመቱ ውስጥ በሚካሄዱት ጠለፋዎች እንደምትሳተፍ ሲነግሯት ወዲያውኑ መዘጋጀት ጀመረች። በቀደመው ዓመት በነበራት ተሳትፎ በቴሌቪዥንና በመጽሔቶች ተደጋግሞ የታየው ፊቷ እንዳይታወቅ በሚልም የፕላስቲክ ሰርጀሪ ተጠቅማ ገፅታዋን ለዋወጠች።

ኒካራጓዊው ፓትሪክ አርጌሎ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ አምስተርዳም ከተማ ገባ። ለይላ ኻሊድ እና ሁለቱ ፍልስጥኤማዊያን ደግሞ በመስከረም 1/1970 ወደ አውሮጳ ተሻግረው ከኒካራጓዊው ታጋይ ጋር ተገናኙ። መስከረም 6/1970 ከአምስተርዳም ወደ ኒውዮርክ የሚበርረውን አንድ የእስራኤል አየር መንገድ አውሮፕላን ለመጥለፍ ተሰማሩ።

አራቱ ጠላፊዎች ወደ አየር ማረፊያው ሲቃረቡ በሁለት ቡድን ተከፋፍለው ወደ ውስጥ ለመግባት ወሰኑ። በዚሁ መሠረትም በቅድሚያ ለይላ እና ኒካራጓዊው ፓትሪክ እንደ ባልና ሚስት ሆነው በመግባት የአየር ማረፊያውን የደንበኞች መቆጣጠሪያ ካውንተር አለፉት። ሁለቱ ፍልስጥኤማዊያን የርሱን መግባት ሲያረጋግጡ በተራቸው ካውንተሩን ለማለፍ ሞከሩ። ይሁንና በአየር ማረፊያው አሳላፊዎች ተጠርጥረው እንዳያልፉ ተከለከሉ። ፍልስጥኤማዊያኑ በዚህ ገጠመኝ ሳይደናገጡ አሳላፊዎቹን ለማሳመን ሞከሩ። ነገር ግን አሳላፊዎቹ በጥርጣሬአቸው ፀኑ።

እነዚያ ፍልስጥኤማዊያን ከጓዶቻቸው መነጠላቸው ቢያናድዳቸውም በእቅድ ያልተያዘ ሌላ ኦፕሬሽን ለመፈጸም ወሰኑ። ወዲያውኑም በክፍል ስምንት በጠቀስነው የPan Am አየር መንገድ አውሮፕላን ወደ ኒውዮርክ ለመሄድ የሚያስችላቸውን ትኬት በመቁረጥ ወደ አውሮፕላኑ ተሳፈሩ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም አውሮፕላኑን ጠልፈው ቀደም ብለን በገለጽነው መንገድ ወደ ዮርዳኖስ ወሰዱትና ከሳምንት በኋላ አቃጠሉት።

ለይላ ኻሊድ እና ፓትሪክ አልጌሮ ደግሞ ወደ እስራኤሉ አውሮፕላን እንደገቡ የጠለፋ ኦፕሬሽናቸውን ጀመሩት። ይሁንና ይህኛው የጠለፋ ሙከራ እንደተጀመረ ነበር የከሸፈው። ለክሽፈቱ መንስኤ የሆነው የእስራኤል አየር መንገድ ከወትሮው በዛ ያሉ የጸረ-ጠለፋ ኮማንዶዎችን በአውሮፕላኑ ውስጥ መመደቡ ነበር። በዚህም መሠረት ሁለቱ ተጣማሪዎች አውሮፕላኑን የሚጠልፉበትን ኦፕሬሽን እንደጀመሩ የኒካራጓው ተወላጅ በኮማንዶዎቹ ተገደለ። ለይላ ኻሊድ ደግሞ ቁስለኛ ሆና ተማረከች። አውሮፕላኑ ለንደን እንደደረሰም ለይላ ወደ እንግሊዞች እስር ቤት ገባች።

እስራኤልና የምዕራብ ሀገራት በለይላ ኻሊድ መማረክ በእጅጉ ፈነደቁ። የፍልስጥኤማዊያን ደጋፊዎችና በሶሻሊዝም ፍልስፍና የሚያምኑ የግራ ኃይሎች ግን በጣም ተበሳጩ። ብዙዎችም ቁጭታቸውን በይፋ ገለፁ። በዚሁ መሀል አንድ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ። የለይላ ኻሊድን መታሰር በሬድዮ የሰሙ እና የፍልስጥኤም ህዝብ ትግልን የሚደግፉ ሁለት የአውሮጳ ተወላጆች ህይወቷን ለመታደግ ተንቀሳቀሱ።

ለይላ ከታሰረች ከአምስት ቀናት በኋላም ሁለቱ አውሮጳዊያን ከህንዷ የቦምቤይ ከተማ ወደ ለንደን ይበር የነበረውን አንድ የእንግሊዝ አውሮፕላን በመጥለፍ ወደ ዮርዳኖስ ወሰዱት። አውሮፕላኑ በዳውንሰን የአየር ማረፊያ ላይ እንዳረፈም ጠላፊዎቹ “እንግሊዝ ዜጎቿ እንዲለቀቁላት የምትፈልግ ከሆነ ለይላ ኻሊድን በአስቸኳይ መፍታት አለባት” የሚል ቅድመ ሁኔታቸውን አሰሙ። ከብዙ ድርድር በኋላም እንግሊዝ ጥያቄውን ተቀብላ ለይላ ኻሊድን ለቀቀች።

ከዚያ በማስከተል ደግሞ ጠላፊዎቹ “የሌሎች ሀገራት ዜጎች እንዲለቀቁ ከተፈለገ በእስራኤል እስር ቤቶች ያሉ በርካታ ፍልስጥኤማዊያን ታጋዮች ይለቀቁ” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። እስራኤል በጠለፋው ዜጋዋ ስላልተያዘባት ጥያቄውን ለመቀበል አንገራገረች። በኋላ ግን ከአሜሪካ የመጣባትን ጫና ለመቀበል ተገደደች። በመሆኑም በነገሩ ላይ ኦፊሴላዊ መግለጫ የተወሰኑ ፍልስጥኤማዊያንን ፈታች። ጠላፊዎቹም አውሮፕላኑንና ተሳፋሪዎቹን ለቀቁ።

የለይላን ህይወት ለመታደግ የእንግሊዙን አውሮፕላን የጠለፉት አውሮጳዊያን ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸውን ምክንያት እንዲናገሩ ሲጠየቁ የሰጡት አንድ አጭር መልስ ነበር። እንዲህ የሚል!
“ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት ነው ያነሳሳን!”
(ይቀጥላል)
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 7/2010
በሸገር ተጻፈ።

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ዘጠኝ)

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...