Tidarfelagi.com

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ሰባት)

ክፍል ሰባት፡ ተከታታዮቹ ኦፕሬሽኖች

PFLP በዚያው ዓመት (በ1969) ውስጥ ጥቃቱን በማስፋት “የወራሪዋ እስራኤል ተባባሪዎች ናቸው” የሚላቸውን ሀገራት በሙሉ ዒላማ ማድረግ ጀመረ። በዚሁ መሠረት “ፊዳይን” የሚባሉ ኮማንዶዎቹን በብሪታኒያና በሌሎች የምዕራብ ሀገራት በማሰማራት ልዩ ልዩ ጥቃቶችን ፈጸመ። “ወዝ አደራዊ ዓለም አቀፋዊነት” በሚባለው የሶሻሊዝም መርህ የሚያምኑ የልዩ ልዩ ሀገራት ዜጎችም ግንባሩ በሚፈጽማቸው የአውሮፕላን ጠለፋዎችና ሌሎች ጥቃቶች ይሳተፉ ጀመር።

የአውሮጳዊያኑ 1970 ግን በPFLP ታሪክ ውስጥ የተለየ ዓመት ሆነ። በዚያ ዓመት ግንባሩ “ለወራሪዋ እስራኤልም ሆነ የርሷን ህገ-ወጥነት ለሚያበረታቱት የኢምፔሪያሊስት ሀገራት ኃይላችንንና አቅማችንን ማሳየት አለብን” የሚል ውሳኔ አስተላለፈ። በመሆኑም የግንባሩ ወታደራዊ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ የነበረው ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ በአንድ ጊዜ በርካታ አውሮፕላኖችን ለመጥለፍ ያቀረበውን ሐሳብ አመራሩ ተቀበለው። ዶ/ር ዋዲ ሀዳድም ኦፕሬሽኖቹን እንዲመራ መመሪያ ተላለፈለት።

ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ መመሪያውን ተቀብሎ ለዘመቻው የሚያስፈልጉ ፈዳይኖችን መለመለ። ሰላሳ ያህል የግንባሩ አባላትንም ለዘመቻው አዘጋጀ። በመስከረም ወር 1970 አስራ ስድስት ፈዳይኖችን ለጠለፋው ወደ አውሮጳ አሰማራ። ፈዳይኖቹም መስከረም 6/1970 በተመሳሳይ ሰዓት ባካሄዷቸው ኦፕሬሽኖች ንብረትነታቸው የትራንስ ወልድ አየር መንገድ፣ የፓን አሜሪካ አየር መንገድ እና የስዊትዘርላንድ አየር መንገድ ንብረት የነበሩ ሦስት አውሮፕላኖችን ጠለፉ። የፓን አሜሪካው አውሮፕላን ወደ ቤይሩት ተወስዶ ተጨማሪ የPFLP አባላትን አሳፈረ። በማስከተልም ወደ ካይሮ ተወሰደ። ተሳፋሪዎቹ በካይሮ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ከወረዱ በኋላም አውሮፕላኑ ተቃጠለ።

የትራንስ ወርልድ አየር መንገድና የስዊስ አየር መንገድ ንብረት የነበሩት አውሮፕላኖች ደግሞ ወደ ዮርዳኖስ ተወስደው የእንግሊዝ ጦር ኃይል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይጠቀምበት በነበረውና ከከተማ ራቅ ባለ ስፍራ በተሰራው የዳውሰን የአየር ማረፊያ ላይ እንዲያርፉ ተደረጉ። በአውሮፕላኖቹ ውስጥ የነበሩት ተሳፋሪዎችና ሰራተኞች በአማን ከተማ ወደሚገኘው የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ከተወሰዱ በኋላ አውሮፕላኖቹ ተቃጠሉ።

የምዕራብ ሀገራት በግንባሩ ጥበቃ ስር ይገኙ የነበሩ ተሳፋሪዎችን ማስለቀቅ ከፈለጉ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ፍልስጥኤማዊያን እስረኞችንና የPFLP ደጋፊዎችን መልቀቅ እንደሚኖርባቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን ነገሩን ሲሰሙት “ከአሸባሪዎች ጋር አንደራደርም” በማለት መልስ ሰጡ። በፍልስጥኤማዊያኑ እጅ የሚገኙትን ምእራባዊያን ዜጎች በወታደራዊ ኃይል ለማስለቀቅ ወሰኑና የመከላከያ ሚኒስቴራቸው ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ሚስጢራዊ ትእዛዝ ሰጡ።

ይሁን እንጂ የመከላከያ ሚኒስትራቸው “አሁን ባለው የአየር ሁኔታ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የተሳፋሪዎቹን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል” በማለት ትእዛዙን ተቃወሙት። በመሆኑም አሜሪካም ሆነች ሌሎች ምዕራባዊያን ከፍልስጥኤማዊያኑ ጋር መደራደር ግድ ሆነባቸው። በምዕራባዊያኑ ጠቋሚነት ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ ተጠራ።

የቀይ መስቀል ወኪሎችና የPFLP መሪዎች ለሳምንት ያህል ከተደራደሩ በኋላ ከስምምነት ላይ ደረሱ። በስምምነቱ መሠረት በርካታ ፍልስጥኤማዊያን ከእስራኤል እስር ቤቶች ተለቀቁ። እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ሰዊትዘርላንድና ኔዘርላንድም በእስር ቤቶቻቸው የሚገኙ ፍልስጥኤማዊያን ታጋዮችን ለቀቁ። በPFLP እጅ የወደቁት የአውሮፕላኖቹ ተሳፋሪዎችና የአቪዬሽን ሰራተኞችም ነፃ ወጥተው ወደየሀገሮቻቸው ተሸኙ።
—-
እስከ አሁን ድረስ በጻፍነው ትረካ ከለይላ ኻሊድ በስተቀር የጠላፊዎቹን ማንነት በስም አልገለጽኩም። ታዲያ ይህ ክፍተት የተፈጠረው ስለሰዎቹ ማንነት የሚገልጹ መረጃዎችን ለማግኘት ባለመቻሌ እንዳይመስላችሁ። ግንባሩ ሰዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችን በሚስጢር ይዞአቸው ስላቆያቸው ነው ክፍተቱ የተፈጠረው። እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ከለይላ በስተቀር በኦፕሬሽኖቹ የተሳተፉ ሌሎች ሰዎች ማንነት በግንባሩ ይፋ አልተደረገም።

በሌላ በኩል ኮማንዶዎቹ ወደ አውሮፕላኖቹ ገብው ጠለፋውን በሚጀምሩት ወቅት ፊታቸውን በጭምብል ይሸፍኑ ነበር። ከጠለፋው በኋላ ተሳፋሪዎችን አግተው በሚቆዩበት ጊዜም ጭምብላቸውን አያወልቁም። ስለዚህ ፊታቸው ለውጪ አካላት አይታወቅም ማለት ነው። ታዲያ የጠለፋዎቹ ማንነት ሚስጢር ሆኖ የሚቆየው ጠለፋዎቹ ከተሳኩ ብቻ መሆኑን ልብ በሉ። ጠለፋው ከከሸፈ ግን የሰዎቹ ማንነት በፀጥታ ኃይሎች መታወቁ አይቀሬ ነው።

ለይላ ኻሊድ ጭምብል ሳታጠልቅ በኦፕሬሽኑ የተሳተፈችው ባለፈው ክፍል የጠቀስነውን የግንባሩን ዓላማ ለማሳካት ስለተፈለገ ነው። ይህም ማለት ጠላፊዋ ሴት መሆኗ አትኩሮትን የሚስብ መሆኑ ስለታመነበት ነው። ይህንንም ለማጠንከር ሲባል ለይላ እውነተኛ ፓስፖርቷን እንድትጠቀም ተደርጓል (ለይላ በወቅቱ በሊባኖስ ፓስፖርት ትጠቀም ነበር። አሁን ግን የዮርዳኖስ ፓስፖርት ነው የምትይዘው)። ሌሎች ጠላፊዎች ግን በሐሰት ፓስፖርት ነበር የተጠቀሙት።
—–
የPFLP ታጋዮች ሶስቱን አውሮፕላኖች በጠለፉበት ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃ ሌላ ጉልህ ድርጊትም ተከስቷል። ይህም ድርጊት ከለይላ ኻሊድ ጋር የተያያዘ ነው። በድርጊቱ ሳቢያ ሚሊዮኖች “ይህቺ ወጣት ማን ናት? ፍላጎቷስ ምንድነው? ለምንድነው ስሟ ተደጋግሞ የሚነሳው?” በማለት ለመጠየቅ ተነሳስተዋል። የዓለም ህዝብ በሶስቱ አውሮፕላኖች መጠለፍ ተገርሞ ሳያበቃ ይህኛው ድርጊት በመከሰቱ በጣም ነበር የተደነቀው። በድርጊቱ ሳቢያም ከዚያ በፊት ባልታየ መልኩ ስለፍልስጥኤም ህዝብ ጥያቄና የዘመናት ሰቆቃ በስፋት መነጋገር ጀምሯል።

ለመሆኑ በወቅቱ የተከሰተው ድርጊት ምንድነው? በተከታዩ ክፍል እናዳስሰዋለን።
(ይቀጥላል)
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 8/2010
በሸገር ተጻፈ።

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ስምንት)

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...