Tidarfelagi.com

ዝክረ- ኳራንታይን (ክፍል ሁለት)

ውበት

የውበት ሳሎኖች እንደ መድሃኒት መደብሮች፣ የምግብ መሸጫ ሱቆች እና የህክምና ጣቢያዎች ሁሉ ‹‹አንገብጋቢ አገልግሎት አቅራቢ›› ተብለው መመደብ እንደነበረባቸው ያየንበት ጊዜ ነው- ኳራንታይን። የሴቶች ትክክለኛ የጠጉር ቀለም (በአብዛኛው ሽበት) ፣ ትክክለኛው ኪንኪ ጠጉርን (ሂውማንሄር ለረጅም ጊዜ በካውያ ሳይሰራ ሲቀር ተሳስሮ እዚህ ራስ ቅል ላይ አለመብቀሉን ያገልጣልና)፣ ያልተኳሉ እና በአርቴቪሻል ሽፋሽፍት ጎላ ጎላ ያላሉ አርበ ጠባብ አይኖችን፣ ሜካፕ ያልተለደፈባቸው ፊቶችን፣ ልጎንጉንህ ቢሉት የሚመች ያልተቀነደበ ቅንድብን በስንት ጊዜያችን አየንበት?

ምስጋና ለኳራንታይን እና የዛሬዎቹ የአዲስባ ሴቶች ሜሪ አርምዴ የሴቶችን ጠጉር በካውያ ማለስለስ ከመጀመሯ በፊት ያሉትን እስኪመስሉ ድንግል የተፈጥሮ ጠጉራቸው ሁለት አራት ቦታ ተጎንጉኖ፣ አምፖሎ ስታይል ሸብ ተደርጎ አደባባይ ሲወጡም ውብ እንጂ ሌላ እንዳይደሉ አይተናል። ይህን አይተው በውበት ሳሎኖች የሚባክነው ጊዜና ጉልበት ተገቢ አይደለም ብለው የሚደመድሙም አይጠፉም።

ይሁንና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ከዜሮ እስከ ሶስት በሆነባቸው ቀናት ተስፈኛ የሆኑ ሴቶች ደጃፍን ከበረንዳዬ ሆኜ ስመለከት በርካታ ሂውማን ሄሮች ታጥበው መሰጣታቸውን አስተውዬ ነበር። አስራ እና ሃያ ቤት ሲገባ ደግሞ እዚያው ገመድ ላይ ሙታንታና ሻሽ ተሰጥቶበት አያለሁ።

ጉርብትና እና ማህበራዊ ኑሮ
ኳራንታይን ቤት ካሸገን ጀምሮ በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ለምንኖር ሰዎች ምንም እንኳን ኑ ቡና ጠጡ ተባብለን በእርስ በርሳችን ቤት ባንታደምም፣ ሰብሰብ ብለን ቆሎ ባንዘግን ቂጣ ባንቆርስም፣ በግድግዳ በሚያልፍ ድምፃቸው (አንዳንዴ አሽኮረማሚ ድምጾች) ብቻ የምናውቃቸውን ጎረቤቶቻችንን በአይነ ስጋ እንድናይ፣ ብሎም በየእለቱ ከበረንዳችን የሩቅ ሰላምታ እንድንለዋወጥ እድሉን ሰጥቶናል።

ለምሳሌ እነዚያ ትላንት እንደተገናኙ አፍላ ፍቅረኞች ከጣሪያ በላይ እየጮሁ ፍቅር የሚሰሩ ጎረቤቶቻችን በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ጎልማሶች መሆናቸውን ሳይ ትን ሊለኝ ነበር። ሁሌም በፍቅራቸው ድግስ ማለቂያ ላይ ‹‹አሁን…አሁን….አሁን..›!›› እያለች እጅጉን ስለምትጮህ ‹‹አሁን›› የሚል መጠሪያ የሰጠናት ሴት የተቀዳደደ ጂንስ ሱሪ በቲሸርት የምታደርግ ልጃገረድ ሳትሆን ኪትን ሂል በጉርድ ቀሚስ እና ሹራብ የምታዘወትር ደርባባ እመቤት መሆኗን ማወቅ አያስደነግጥም?

ቤት መቀመጡ በተጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠዋት ሁለት ሰአት ሳይሞላ ፣ በአንድ እጄ ሃደሮ ቡናዬን፣ በሌላኛው ላፕቶፔን ይዤ ወደ በረንዳዬ መውጣትና መቀመጥ፣ስራዬን ማቀላጠፍ አዲሱ ጠባዬ ሆነ።
ፊትለፊቴ ካሉት እጅብ ብለው ከበቀሉ ዛፎች ላይ ያሉ ወፎች ውብ ዜማቸውን ይለቃሉ፣ አንዳንዶቹ ትናንሽ የበረንዳ የአበባ መደቦቼ ድረስ መጥተው እንዲመጡ ብዬ ያስቀመጥኩላቸውን ፍርፋሪ ፈራ ተባ እያሉ ለቅመው ብ—–ር ይላሉ። ዛፎቹን አልፎ በሚገኘው ሌላ ህንፃ ላይ በየበረንዳቸው የተሰየሙ ከዚህ በፊት በመልክም የማላውቃቸው ጎረቤቶቼ የራሳቸውን የማለዳ ሕይወት ጀምረዋል።

ጥቂቶቹ ልጆቻቸውን እኔ ህንፃ ላይ ካሉ ልጆች ጋር በርቀት አኩኩሉ ሲያጫውቱ አንጀቴ ተላወሰ። እዚያ በረንዳ ላይ ያሉት ልጆች ቤታቸው ተደብቀው ሳለ እዚህ ህንጻ ላይ በበረንዳቸው ያሉት ልጆች በምናብ በቀር እንዴት ሊያገኙዋቸው እና ሊነጋ ይችላል ብዬ ሳስብ ፈገግ አልኩ። ግን ደስ ይል ነበር።

አንድ ባለትዳር እንደሆኑ የምጠረጥራቸው ጥንዶች በረንዳቸው ላይ ተቀምጠው የቤት ሰራተኛቸውን ቡና እያስፈሉ ፣ እጣን እያስጨሱ፣ ቁርስ እየበሉ እኔ እንደማያቸው ያዩኛል። የእጣኑ ጭስ ሂድ- ሽተታት የተባለ ይመስል ተንቦልቡሎ አፍንጫዬ ሲደርስ ሴትዮዋ ጮህ ብላ ‹‹ይቅርታ…ረበሸሽ እንዴ!?›› አለችኝ። ‹‹አረ በጭራሽ…እጣን በጣም ነው የምወደው….ደስ ይላል….››አልኳት እኔም ጮህ ብዬ።

‹‹መጥፎ ዘመን ሆነ…ጎረቤት ቡና ጠጡ የማይባባልበት›› አለች መልሳ። ፈገግ ብዬ አየኋትና ወደ ስራዬ ስመለስ እማዬ ከሰሞኑ ያለችን ትዝ ብሎኝ የባሰ ፈገግ አልኩ።

‹‹እኛስ ኖረነዋል! ይብላኝ ለእናንተ….ያልታደላችሁ ትውልድ ናችሁ..አንዴ ኮንዶም አንዴ ማስክ አድርጉ የምትባሉ›› ነበር ያለችኝ።
እንዳሻን የማንኖር ትውልድ መሆናችንን አሰብኩ።
በእነዚህ በረንዳ ላይ ወጥቶ በመተያየት ጊዜያት በፍጥነት ወዳጅነት ያበጀሁት ግን ከ‹‹ብዙ የሚያጨሰው ሰውዬ›› ጋር ነበር። ስሙን ሰለማላውቀው ስጠራው እንዲህ ብዬ ነው – ብዙ የሚያጨሰው ሰውዬ።
መጀመሪያ ሰሞን እኔም ቡናዬን እሱም ሲጃራውን ሲል በአይን እንተያይ ነበር። ቀናት ሲያልፉ የእጅ ሰላምታ መሰጣጠት ጀመርን። ከሳምንታት በኋላ – እንዴት አደርሽ- እንዴት አደርክ- ትላንት ምነው ሳትወጣ- በደህና ነው- ሰሞኑን ጠፋሽ- ወሬ ጀመርን። ይሄ የርቀት ጉርብትናችን ከሳምንታት በኋላ ጎልብቶ ትላንትና ምን አልኩት ‹‹ይሄን ሲጋራ ግን ምናለ ብትተው….በናትህ ተወው….?››….እንዲህ ካለመተዋወቅ ወደ መተሳሰብና መመካከር በሳምንታት ያደረሰን መገናኘት፣ የጊዜ ፀጋ አይደለምን?

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
ቤት መቀመጡ ካመጣቸው ብዙ ጣጣዎች አንዱ ፈጣን ውፍረት ነው። ለምን ለሚል መልሱ ቀላል ይመስለኛል። የምግበ ሰአት የለንም። ብዙዎቻችን ሲደብረን፣ ሳይርበንም እንበላለን። እርምጃችን በቤታችን ስፋት፣ እንቅስቃሴችን በጉብዝና እና ስንፍናችን ልክ ነው። ይሄ ሁሉ ሲደመር ስብ ይሆናል።
‹‹ካሮት ለማምጣት ፍሪጅ ሄጄ የሙልሙል ኩኪስ ይዞ መመለስ ነው …ስኳር አፌ ውስጥ መገጎስጎስ ነው እንዲህ ያበላሸኝ› ትለኛለች አንድ ጓደኛዬ- ስምንት ኪሎ እንደ ጨመረች እየተማረረች ስትነግረኝ።
እኔ የስፖርት ሰው አይደለሁም። በዛፍ የተከበበ መንገድ ላይ፣ በአበቦች ያጌጠ ስፍራ ላይ ግን ለሰአታት በእግሬ መጓዝ እችላለሁ። ሩጪ፣ ዝለይ፣ ተወራጪ፣ ተሳቢ፣ ፑሽ አፕ ስሪ፣ ቁጭ ብድግ በይ የሚለኝ ግን ጠላቴ ነው። ለዚህ ነበር ወዳጄ ዳግማዊት (ቀንደኛ የስፖርት አፍቃሪ) ‹‹ ስሚ ሁላችንም ኦንላይን ሆነን እየተያየን ዩቱዪብ ላይ ያለ ቀላል እንቅስቃሴ እንስራ…ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ›› ስትለኝ ሃሞቴ የፈሰሰው።

እንዳልኳችሁ ከቤት ወጥቼ ግቢውን ካልዞርኩ እና ጥላ ሲመጣ ለአንድ ሁለት ሰአት የእግር ጉዞ ካልወጣሁ የማደርገው ብቸኛ እንቅስቃሴ በፊልሞች መሃከል በምትገኘው የማስታወቂያ ክፍተት ኩሽና ሄጄ ምግብ የማመጣባት እርምጃ ናት። እና ጨነቀኝ።:
ግን ስትነተርከኝ እሺ ብዬ ገባሁበት። ስህተት ነበር።
ሞት ሞት ነበር ያለኝ። ከዝላይ በኋላ ሶፋዬ ላይ ልቀመጥ ስል ስለምታየኝ ትቆጣኛለች። እሺ ብዬ ቀጠልኩ። ቀጥሎ ምን መጣ? ልክ ‹‹ትሬድ ሚለ›› ላይ እንዳለን ሁሉ በፍጥነት መሮጥ? ስፖርትን ለደስታ በሚሰሩ ሰዎች ተደነቅኩ። ሰው እንዴት ይሄ ያስደስተዋል?
ካቅሜ በላይ ሲሆን ሩጫዬ ወደ ሶምሶማ፣ ሶምሶማዬ ወደ ርምጃ ሲቀየር ጓደኛዬ
‹‹ሕይወት…እያዘገምሽ ነው ወይስ ኢንተርኔትሽ ሰሎው ሆኖ ነው?›› ስትለኝ መውጫ ቀዳዳዬን እንዳገኘሁ ገባኝና፣
‹‹ኢንተርኔቴ ነው….እንደውም ሊቋረጥ ነው መሰለኝ›› ብዬ ኦፍላይን ሆኜ ሶፋዬ ላይ ዘርፍጥ!
ኳራንታይ ብዙ አጉድሎብናል። ግን ጥቂትም ሰጥቶናል። ለራስ የሚሆን ጊዜ። ለጥሞና የሚያመች ወቀትን።
ያጎደለብን ሲያመዝን አስተውያቸው የማላውቃቸው በሕይወቴ ውስጥ ደስታን ይሰጡኝ የነበሩ፣ ዛሬ ግን በቫይረሱ ምክንያት የተነጠቅኳቸውን ጥቃቅን እና የአፍታ ደስታዎችን አሰብኩ። አለ አይደል…
ሰፈር ውስጥ እየሄድኩ ድምቡሽቡሽ ያለ ህፃን ሳይ ጠጋ እና ጎንበስ ብዬ ‹‹አውይ…አንቺ ማነሽ? ቡቡቱጡቡጡ….›› ብዬ አቅፌ የምስመውን።

ፊልም ቤት ገብቼ ፈንዲሻውን እዛው ከተዋወቅኩት ሰው ጋር የምጋራውን።
ባሻኝ ሰአት ትግራይ ሽሮ ቤት ሄጄ በአለም አንደኛውን ሽሮ ላፍ አድርጌ የምበላውን።
ከጓደኞቼ ጋር የተጨናነቀ ካፌ ቁጭ ብዬ ወሬ በቡና የማንቃርረውን።
የሰው ልደት ሄጄ እፍፍ…. ያሉበትን ኬክ ቆርሼ የምጋራውን።
ለቅሶ ቤት ሄጄ ሃዘን የደረሰበት ወዳጄን እቅፍ ድግፍ አድርጌ የማፅናናውን።
ባንክ እጄን ሳልታጠብ፣ ማስክ ሳላደርግ የምገባውን።
ኤቲኤምን ካለ ስቲኪኒ የምጠቀመውን።

ከቢጃማ ውጪ ያሉ ዘናጭ ልብሶቼን ለብሼ ያሻኝ ቦታ የምሄደውን። ….ሌላም ሌላም….
የሆነው ሆኖ ያለንበት ጊዜ ይሄ ነው። ‹‹የኮንዶም አድርጉ…ማስክና ጓንት አጥልቁ›› ትውልዶች ነን እና ፈጣሪ ይሄን ጊዜ በቸር አሳልፎ ወደ መደበኛ ሕይወታችን እስኪመልሰን…ባላችሁበት በርቱ፣ በነገራችሁ ሁሉ ተጠንቀቁ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...