Tidarfelagi.com

“ዐልቦ” – (ክፍል ሁለት)

(መነሻ ሃሳብ- ዘሚድል ተከታታይ ፊልም)

‹‹ቤቷ ብቻ ስንት ካሬ እንደሆነ ታውቃለህ…ሁለት መቶ ሃምሳ ! ሁለት መቶ ሃምሳ ካሬ አስበው…ከዚህ እስከ ደብረወርቅ ህንጻ ማለት ነው…ቤቷ ከእኛ ቤት እስከ ደብረወርቅ ህንጻ ነው….በዛ ላይ እቃዎቿ…ሶፋ ብትል…የእኛን አልጋ ሶስት እጥፍ የሚሆን ሶፋ…ፍላት ስክሪን ተቪ…የውጪ በር የሚያክል ፍላት ስክሪን ቲቪ አላት… ምንጣፉ… እዚያ ሁሌ የማየው…ሁሌ የምመኘው …ሁሌ ግዛልኝ የምልህ ኮምፈርት ትዝ ይልሃል…ያ ሳሪስ ያለው ቤት…እሱን ነው የሚመስለው…እሱን ነው የሚረግጡት…እ…››
እየተስገበገብኩ ነው የማወራለት- ለቤሪ። እስኩ ጋር አምሽቼ መምጣቴ ነው። የአሜሪካው ቤቷን በስልክ ላይ ፎቶ እና ቪዲዮ አይቼ መምጣቴ ነው። በቢራ እና በቅናት ተሞልቻለሁ።
‹‹ፍቅር….›› አለኝ ቤሪ።
‹‹ወዬ…!ገና አልጨረስኩልህም እኮ…መኝታ ቤቷ..ባርኮን ይሙት….››
‹‹በልጅሽ አትማይ! ከመቼ ወዲህ ነው በልጃችን የምትምይው?››
‹‹አይደለም እኮ…››
‹‹ኡፍ…በቃኝ ስለሷ ቤት መስማት…አንቺም ይበቃሻል…መሽቷል። እንተኛ…ልጄንም እንዳትቀሰቅሺው››
አኮረፈኝ መሰለኝ።
‹‹ለምን ታኮርፈኛለህ›› አልኩት ወደ መኝታ ስንሄድ እጁን ጎትቼ አስቁሜው። ለብታዬ ወደ ሞቅታ እያደገ መሰለኝ።
‹‹አላኮረፍኩም ፍቅር…ግን ሰለቸኝ…እኛ ብዙ የምናስበው ነገር አለ…ልጆች አይደለንም ….ልጆች አሉን…››
‹‹ጥሩ ነገር …ጥሩ ነገር ማውራት ይሰለቻል…?እኛ ባይኖረን ሌላው ያለውን ማውራት ይበዛብናል?›› አልኩት አልጋው ውስጥ ሲገባ ቆሜ እያየሁት።
‹‹ምን ሆነሻል…ሌላ ሰው ሆንሽብኝ…አራት ቢራ እና ነገር አጠጥታ ላከችብኝ ሚስቴን …ቀንተሻል…?በድሮ ጓደኛሽ ኑሮ ቀናሽ?››
ቤሪ እንዲህ ነው። ዙሪያ ጥምጥም አያውቅም። ነገር ማለሳለስ አያውቅም። መሸፋፈን፣ መጀቧቦን፣ በስውር ማውራት አይችልበትም።
በዚህ እወደው ነበር። ደስ ይለኝ ነበር። ዛሬ ግን አበሳጨኝ።
‹‹ብቀና ሃጥያት ነው?…››አልኩት ድምፄን ከፍ አድርጌ።
‹‹አትጩሂ…ባርኮን ይነሳል። ደግሞ አዎ…ቅናት ሃጥያት ነው››
‹‹ባክህ አትመፃደቅብኝ…ጥሩ ነገር መመኘት ሃጥያት አይደለም…እኔስ ሰው አይደለሁም…?ጥሩ ነገር አያምረኝም …አይገባኝም…?ዘልአለም እንዲህ ያለ ጉረኖ ውስጥ እየኖርኩ፣ እህል ቅጠል የማይል ወጥ ቀቅዬ እንድበላ፣ የልጅ ቅርሻት ስጠርግ እንድኖር የተፈረደብኝ ይመስልሃል…?ደህና ነገር አይወድልኝም….?›› አልኩት። የራሴ የምሬት ድምፅ ይሆን ያልለመድኩት ቢራ አፌን ሲመረኝ ይሰማኛል።
ቤሪ ቅስሙ ሲሰበር አየሁት። በሚታይ ሁኔታ ቅስሙ ስብር አለ።
እንደሚያስብ ሰው ትንሽ ዝም አለና፤
‹‹ ይሄ ሁሉ የታየሽ ዛሬ እሷ ስትመጣ ነው…?የሌለሽን ነገር እንኪ እይው ብላ ፊትሽ ላይ ስትወረውረው ነው ኑሮሽ ያስጠላሽ….? ፍቅር…ሰክረሻል…የምትይውን አታውቂም…እንተኛ…ነገ እናወራለን…›› ብሎ እጁን ዘረጋልኝ።
ዝም ብዬ አየሁት።
‹‹ፍቅር..ነይ አልጋ ውስጥ ግቢ…የኔ ሰካራም…አቅፌ አስተኛሻለሁ…ነይ›› አለኝ የተዘረጋ እጁን ሳያጥፍ።
አልጋውን አየሁት። ሲያስጠላ።
ክፉሉን አየሁት። ሲቀፍ።
የተቦረቦረ ግድግዳችንን፣ የተበሳሳ ጣሪያችንን፣ ምንጣፍ አልባ ወለላችንን፣ ቁምሳጥን የለሽ ርካሽ ልብሶቻችንን፣ መስኮት አልባ፣ የሚሰነፍጥ እና የሚያፍን ሕይወታችንን አየሁት።
ሁሉንም ተጠየፍኩት።
ባሌን አየሁት። ደጅ ድንጋይ ላይ ቁጢጥ ብሎ፣ በግራው ሚጢጢ መስታወት ይዞ በቀኝ እጁ ራሱ የሚከረክመውን ፂሙ እና ፀጉሩን አየሁት።
በላብ የሚያበራ ጎስቋላ ፊቱን ተመለከትኩት።
የለበሰውን የወንድሙን ውራጅ ፒጃማ አየሁት።
የምወደው ቤሪንም ከቤቴ እና ከቅራቅነቦዬ ጋር ደምሬ ተጠየፍኩት።
‹‹ ነይ እንጂ የኔ ሰካራም…ነይ›› አለኝና ገብቶ ከነበረበት አልጋ ተነስቶ ወደ እኔ መጣ።
ልሄድ ፈለግኩ ግን እግሬ አልሄድ አለ። እግሮቼ ዝናብ ከመታው ግንድ ከበዱኝ።
የሞት ሽረቴን ልጠጋው ስሞክር እና ቤቢ ፊያት የምታህል አይጥ በባዶ ቀኝ እግሬ ላይ ስትሄድ አንድ ሆነ።
ከተበሳሳው ጣሪያችን በላይ ጮህኩ።
‹‹ምነው ምን ሆንሽ…?›› ብሎ ተስፈንጥሮ አቀፈኝ።
ከእቅፉ ለማምለጥ እየሞከርኩ፤ ‹‹ኤጭ አሁንስ! ወይኔ አሁንስ …ኤጭ….! ኤጭ!›› እያልኩ መጮሄን ቀጠልኩ-
‹‹ምንድነው ፍቅ..ር…?ምንም አላየሁም እኔ…ሳትተኚ ቅዠት ጀመርሽ እንዴ!›› አለኝ ሊይዘኝ እየሞከረ።
‹‹ከዚህ በላይ ቅዠት አለ… ? ቅዥት ከዚህ ኑሮ በላይ አለ…የማይባንኑበት ቅዠት!››
‹‹ምንድነው ምታወሪው…?››
‹‹እግሬ ላይ የሄደችውን ግብዲያ አይጥ አላየሁም ለማለት ነው?›› አልኩት የረገበ አልጋችን ላይ ብቻዬን እየወጣሁ።
ልጄን ለማባበል ነው የሄድኩት።
ልጄ በጩሐቴ ተቀስቅሶ ማልቀስ ጀምሯል።
‹‹እና አይጥ አዲስ ነገር ነው እዚህ ቤት….?ስም ሁላ አውጥተንላቸው የለ…ማናት የሄደችብሽ ዘርትሁን ወይስ ባንቺ ይርጉ….?›› እያለ መሳቅ ጀመረ።
እጄ ውስጥ ያለው ልጄ ባይሆን ወርውሬ ጥርሱን ብሰብረው ደስ ይለኝ ነበር።
‹‹በርሄ አያስቅም። በዚህ አትሳቅ…አባዬ ይሙት አታናደኝ››
‹‹በርሄ ደሞ ማነው….? ሃ ሃ ሃ! አረ ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው በአይጦቻችን መሳቅ ያቆምነው?››
‹‹ከዛሬ ጀምሮ›› አልኩት የልጄን ለቅሶ ለማስቆም ከግራ ወደ ቀኝ – ከቀኝ ወደ ግራ እየወዘወዝኩት።
‹‹ለምን?››
‹‹ስለመረረኝ…ስለታከተኝ…ከአይጥ ጋር መኖር ስለታከተኝ…አንተም ሊመርህ ይገባል…ከአይጥ ጋር መኖር የሚፈልገው ድመት ብቻ ነው። ድመትም ቀለቡ ስለሆኑ ብቻ …እኔ ምኔ ድመት ይመስላል! ››
‹‹ ወይ ጉዴ…እኮ ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው እንዲህ ባንዴ የተለዋወጥሽው!›› አለ በስጨት ብሎ።
ዝም አልኩት።
ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው አስቤዛ እየተሰፈረላቸው የኖሩት አብሮ አደጎቼ አይጦች እንዲህ ያማረሩኝ…ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው የምወደው እና የሚወደኝ ባሌ እንዲህ ቱግ ቱግ የሚያሰኘኝ…ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው የማርፍበት ቤቴ እረፍት የነሳኝ…
‹‹እስከዳርን ስታገኚ ህይወትሽ አስጠላሽ….?እኛ አስጠላንሽ አይደል ፍቅር›….›› አለ በተሰበረ ድምፅ ወደ እኔ እየመጣ።
ዝም አልኩት።
‹‹ ልጄን ስጪኝ…እንዲህ ሆነሽ ማልቀስ አያቆምም›› አለና ባርኮንን ተቀበለኝ። ሳላንገራግር አቀበልኩት።
ቤሪ ልጃችንን በለመድነው ወጉ፣ በእሹሩሩ ዜማ ለማስተኛት ሲያባብል፣ በለመደው ወጉ ጥሩ አባት ሲሆን እያየሁ ራሴን እንዲህ አልኩት።
‹‹እውነት ግን ምን ሆኜ ነው?››

 

ዐልቦ – (ክፍል ሶስት)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...