Tidarfelagi.com

ዐልቦ – (ክፍል ሶስት)

(መነሻ ሃሳብ- ዘ ሚደል ተከታታይ ፊልም)

“በሱ ቀሚስ ብታስነጥሺ የጡቶችሽ ጫፍ ሳይታዩ አይቀሩም›› አለኝ ቤሪ ከእስኩ ጋር ላለኝ የማታ ቀጠሮ ስበጃጅ።

ትላንት ማታ ከተፈጠረው ነገር በኋላ ለቀልድ የሚሆን ፍቅር ስለቀረው አንጀቴን በላው። ፊቴን ባልለመደው አኳኃን ስቀባ እና ሳጠፋ፣ ስሰራ እና ሳፈርስ፣ አዲስ ሰው ስሆን እያየኝ ለማሳቅ መሞከሩን ሳይ አንጀቴ ተንሰፈሰፈ። ዞር ብዬ አየሁት።

ባርኮንን እያጫወተ ሳይሰርቅ ያየኛል።

‹‹በጣም ጠበበ እንዴ…?ሊያውም እሷ ድሮ ገዝታው ሳትለብስ የቀረችውን እኮ ነው የሰጠችኝ…አሁንማ ተቀዶም…ሌላ ቀሚስ ገብቶበትም አይሆናት›› አልኩት እኔም ሳቅ ለመፍጠር እየሞከርኩ።

‹‹ቢጠብም ያምርብሻል…የኔ ሚስት እንኳን ሶሰት የወለደሽ በልተሸ የምታድሪ አትመስይም እኮ…›› አለኝ ልጁን እንደያዘ እየተጠጋኝ።

ማታ እንዲያ ጥምብ እርኩሱን አውጥቼው ጠዋት ቅዱስ የሚሆን ይሄ ሰው ከምንድነው የተሰራው…?ለምንስ ነው ለኔ የተሰጠኝ…?

ፀፀት ሹክ አለኝ።

‹‹ቂጣምዬ…›› አለኝ ባርኮንን ባልያዘው እጁ ቂጤን ቸብ እያደረገኝ።

‹‹አንተ እረፍ…››

‹‹ምን አገባሽ በኔ ቂጥ…?››

‹‹ሂደደዛ…የኔ ነው…››

‹‹ዞር በይ ወደዛ የኔ ነው….››

በሚጢጢ ቤታችን ውስጥ ብሮጥ ከግድግዳ እጋጫለሁ እንጂ ሮጬ የህንድ ፊልም ነገር ብንሰራ ደስ ይለኝ ነበር። ይሄንን ጊዜ ልሰጠው፣ ይሄንን ጨዋታ ልሸልመው ብችል ደስ ይለኝ ነበር።

‹‹ እረፍ እየጠበቀችኝ ነው አሁን ቶሎ ልሂድ›› ስለው ወደ አሮጌው ፎቴ ተመለሰና ዝርፍጥ አለ።

<‹ቤሪ…?›› አልኩት ሊፒስቲኬን መልሼ እያስተካከልኩ። ከንፈሬ ወሰኑ አይታወቅም። አገጬን እየቀባሁ ተቸገርኩ።

‹‹ወይ ፍቅር…››

‹‹እንዲህ ብዘንጥ ደስ አይልህም ሁሌ…?ማለቴ እንዲህ ቁልትልት ብል..ዝንጥንጥ…?››

‹‹አንቺን ደስ ይልሻል ፍቅር….?›› ያ ሰባራ ድምፁ ተመልሶ መጣ።

‹‹መዘነጥ ማን ይጠላል…?›› ዞር ብዬ ወገቤን ያዝኩና መለስኩለት።

‹‹ለኔ ጆንያም ብትለብሺ ውብ ነሽ…ደስ ካለሽ ግን ዘንጪ….››

————-
ቮድካ በዚህ መጠን ጠጥቼ አላውቅም።

ነገሮች ሁሉ ይበወዙብኝ ጀመር። እስኩ አራት ከንፈር፣ ስድስት ጆሮ እና አራት አይን ያላት ይመስለኝ ጀመር።

የጎደለ ብርጭቆዬን ልትሞላው ስትል በደመነፍሰ ፤‹‹አንቺ በቤሪ ሞት በቃኝ….በቃኝ…›› አልኩኝ የብርጭቆውን አፍ በእጄ ለመክደን እየሞከርኩ። እኔ ይሄን እያልኩ፣ ክዳን ያደረግኩት እጄ ላይ ቮድካውን ስትቀዳ ነገር አለሙን ትተን እንደ ቂል መሳቅ ጀመርን።

‹‹አንቺ እረፊ…ሰካራም›› እላታለሁ፤ ትስቃለች።

‹‹ወይኔ ቤሪ ይሙት….ቤሪ ይሙት ….በቃኝ አልኩሽ እኮ! ›› አልኩኝ እየሳቅኩ።

እጄ ላይ መቅዷቷን ሳታቆም አሁንም ትስቃለች።

የሞት ሞቴን ጠርሙሱን ተቀበልኳት እና ሶፋው ላይ በጀርባዬ ተንጋለልኩ።

ስገባ በብርሃን ተሞልቶ የነበረው ክፍል ጨላለመብኝ። አይኖቼን አሸሁ። አሁንም እንደጨላለመብኝ ነው።

‹‹ውሃ…ውሃ ስጪኝ እስኩዬ …›› አልኳት በተንጋለልኩበት።

‹‹ምን ሆንሽ…?›› አለች። ውፍረቷ እና ጫማ የጨመረው ቁመቷ ተኝተው ሲያዩት ያስፈራል። ቀና ለማለት ሞከርኩ።

‹‹ ተቃጠልኩ እስኩ…ቅጥል አደረገኝ….››

‹‹ጎሽ…የሚያቃጥልሽን አቃጠለው ማለት ነው አሁን…ሰርቷል ማለት ነው…›› አለችና መውደቅን እንደ ፈራ ሰው እየተጠነቀቀች አጠገቤ ቁጭ አለች።

‹‹አረ እኔ በዚህ ሁሉ ሚቃጠል ነገር የለኝም! ›› አልኳት አልታዘዝ ያለኝ አንገቴን አዙሬ ላያት እየሞከርኩ።

‹‹እሰኪ ማይልኝ…›› አለችኝ እግሯን ወደ እጆቼ እየላከች።

ክትክት ብለን ሳቅን።

‹‹ቤሪ ይሙት…›› አልኳት አየሩን በእጄ በመሃላ እየመታሁ።

‹‹ወይ ይሄ ቤሪ ይሙት…እኔ እኮ በባሌ ብምል….›› አለችኝ እየሳቀች

‹‹እ….›› አልኳት

‹‹ይሙት ካልኩ ምኞት ነው እንጂ ምህላ አይሆንም››

‹‹ሃ ሃ..እሰኩ ቀልደኛ ነሽ…››

‹‹ቀልዴን አይደለም…ክልትው ይበል!››

ሳቋ በዚህ ፍጥነት የት ገባ?

‹‹አንቺ በቮድካ የሚቃጠል የለኝም አልሽ አይደል…እኔ ግን አለኝ…ውቂያኖስ የሚያህል ቮድካ አቃጥሎ የማይጨርሰው ነገር ውስጤ አለ ፍቅር….ተቃጠልኩብሽ ….››

በድንገት እንደሚያቅፍም እንደሚደገፍም ሰው በተቀመጥኩበት አፍናኝ ታለቅስ ጀመር።

ወዝገብ አለብኝ።

‹‹እንዴ…!ምን ሆንሽ…ድንገት…?.›› አልኳት ሶፋው ላይ ተመቻችቼ ላመቻቻት እየሞከርኩ። ቆዳ ነኝ የሚለው ጥቁር ፕላክስቲክ ልብሱ መልሶ መላልሶ ያንሸራትታል።

‹‹ኑሮ አቃጠለኝ…ተቃቃጠልኩ አልኩሽ በቃ…ጓደኛዬ…ሕይወቴ አቃጠለኝ…››

ለቅሶዋ ባሰ።

ሁሉ ነገር ድንገቴ ሆነብኝ።

እንባዋ ቮድካዬን የመጠጠው ይመስል ስካሬ ሲበን ተሰማኝ። ቀና አልኩ።

‹‹ምን ሆንሽ…ምን ጎደለብሽ …?ሰክረሽ ነው…አትቀባጥሪ…››

‹‹ምን አለኝ…?ምንም የለኝም እኮ ጓደኛዬ…ባዶ…ባዶ ነኝ እኮ እኔ…ኔፓ…ዚ…ሮ ዚሮ…..››

ለሃጯ እየተዝረበረበ፣ ንፍጧ እየተዝረከረከ፣ እምባዋ እየወረደ ሳያት ቮድካው ሳይሆን እሷ እያወራች መሆኑ ገባኝ።

‹‹ ምን የለሽም..?ቤት… መኪና… ልጅ… ባልሽ….እኔ ምን አለኝ…?ኑሮዬን እያየሽው ባንቺ ኑሮ ትማረሪያለሽ…ቤቴን አይተሽው ምንም የለኝም ትያለሽ…እኔ እኮ መንግስት የሰጠኝ ኮንዶሚኒየምን ቤት አድርጌ መግባት አቅቶኝ እዛ ጉረኖ ውስጥ የምኖር ሰው ነኝ…አንቺ ምን የለሽም….?.›› አልኳት እያቀፍኳት። እንደህፃን ልጅ እያናፈጥኳት። እንደ ባርኮን እያባበልኳት።

‹‹ባሌ…ቴዲ…ባሌ እኮ ጥሎኝ ከሄደ አመት ሞላው ፍቅር…ጥሎኝ ሄደ…ትቶኝ ሄደ…››

ደነገጥኩ።

‹‹እንዴ…መቼ…?››
‹‹አመት አልኩሽ አይደል…?›
‹‹አይደለም…እንዴት ማለቴ ነው…?መቼ ሳይሆን እንዴት….›› ደንበርበር አልኩኝ።

እስካሁን ያልነበረኝ እንግዳ መረጃ ነው። ያን ሁሉ የምቾት ክምሯን በፎቶ ሳይ፣ በቪዲዩ ስመለከት ‹‹ባልሽ የታለ›› ብዬም አልጠየቅኩ። እሷም አልነገረችኝ።

‹‹ይሄውልሽ….›› አለች እየተንፏቀቀች ከተጋደመችበት የሆቴሏ ሶፋ እየተነሳች። ‹‹ይሄውልሽ…ጢቢጢቢ ሲጫወትብኝ ኖሮ…ጥሎኝ ሄደ…››

‹‹እ…ማለት…ምን ብሎ?››

‹‹ ከአንዷ ደጋን እግር ጋር ፍቅር ያዘኝ ብሎ››

ዝም አልኩ። ለእንዲህ ያለው ነገር ምን ተብሎ ይመለሳል? ጓደኛዬ ‹‹ባሌ ጢቢጢቢ ተጫወተብኝ፣ ሌላ ሴት ወዶ ጥሎኝ ሄደ….ተቃጠልኩ›› ብላ ስትል ምን ማለት ነው ያለብኝ..?

‹‹አይዞሽ እስኩዬ…››

ልል የቻልኩት ይህችን ብቻ ነበር።

‹‹አይዞሽ እስኩዬ›› ደገምኩት።

‹‹አውሬ ነበር። የሰው አውሬ። እኔ ጫካ ሆኜለት፣ ችዬው ኖርኩ እንጂ አውሬ ነበር….እላዬ ላይ ሴት ይዞ ይመጣል፣ ልጁን ይክዳል፣ ሌላውን ተይው ፍቅር……እርጉዝ ሆኜ…እርጉዝ ሆኜ እንኳን ፍቅር….›› ለቅሶ አሸነፋት እና መናገር አቆመች።

የምላት ነገር አጣሁ። ግን ቤሪን አሰብኩት። ቤሪ…

ሃሳቤ ወሬዋን ስትቀጥል ተቋረጠ።

‹‹እርጉዝ ሆኜ…እሱ እየነዳ…አብሬው ሆኜ…ትንሽ ካስቆጣሁት…ኢን ዘሚድል ኦፍ ኖ ዌር…ገፍትሮ ያስወርደኛል….ዋን ታይም…አይ ወዝ ሲክስ መንዝስ ፕሬግናንት ዊዝ ብሩህዬ….ጣቱን ሳየው… ቀለበቱን ሳጣው …የት ሄደ ስለው …ሃይዌይ መሃል ካልወረድሽ ብሎኝ…በመከራ ለምኜ ነው…ለምኜ ነው የተረፍኩት ፍቅር….እንዲህ አይነት ሰው ነው››

ለቅሶዋ ያባባል።

ከአምስት ቀን በፊት ሰበር ሰካ እያለች ሰፈሬ የመጣችው እስኩ በዚህ እምባ ብዛት የሟሟች መሰለኝ። ምስኪን አለች። እንስ።

ጎምላላዋ ጓደኛዬ አነሰችብኝ።

ቤሪን ደግሜ አሰብኩት። ባርኮንን እርጉዝ ሆኜ ግማሽ ባልዲ ውሃ ተሸክሜ ስገባ አግኝቶኝ እብደት ቀረሽ ንዴቱ…
ያገኛትን ሳንቲም አገጫጭቶ ስጋ ገዝቶልኝ መምጣቱ…
ሁለት እንቁላል ብዙ አስመስሎ መጥበሱ…

ሆዴን ሌት ተቀን እየዳበሰ ግንባሬን አሳሳሙ

ቤሪ…

‹‹አንዴ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ…?›› ስትለኝ ወደ ሆቴል ክፍሏ ተመለስኩ።

‹‹ምን አለሽ ሆዴ…?››

‹‹አንቺን እኮ ችዬሽ እኖራለሁ እንጂ ወድጄሽ አላውቅም…አይ ቶሌሬት ዩ….ሰው እንደዛ ይባላል ፍቅር…?የልጁን እናት እንዲህ የሚል ሰው አለ…?አንዲህ አይነት ባል አለ…ንገሪኝ እንጂ…ያንቺ ባል እንደዚህ ነው?››

እያባበልኳት ባሌን አሰብኩት።

የኔ ባል ስሜን ባጠራሩ እንደሚወደኝ ይነገረኛል።
ልጆቻችንን በአያያዙ ፍቅሩን ይገልፅልኛል።

የኔ ባል ትሪ የሚያሳይ እንጀራችንን ሳይሰስት እያጎረሰ አፍ አውጥቶ ‹‹አፈቅርሻለሁ›› ሳይለኝ ‹‹አፈቅርሻለሁ››
ይለኛል።

የኔ ባል ከሰል ላቀጣጥል ስጨናበስ ስንጥር ለቃቅሞ አምጥቶ ሲያግዘኝ እንደሚያመልከኝ ይነገረኛል።

የኔ ባል…

እስኩ ዞር አለችና አይን አይኔን እያየች፤
‹‹ ባንቺ እቀናለሁ ፍቅር….በትዳርሽ…በበርሄ….አውቃለሁ ቅናት ሃጥያት ነው ግን…ቀናሁ…በባልሽ ቀናሁ›› አለችኝ።

እምባዬ እየታገለኝ አቀፍኳት።

ሃዘኗን ለመጋራት አልነበረም ለቅሶዬ። የሚያስቀና ባሌን እይው ብላ ስላሳየችኝ፣ በግድግዳ እና በጣሪያ፣ በሶፋ እና በቴሌቪዥን፣ በምንጣፍ እና በአልጋ ጋርጄው የነበረውን የሚቀናበት ባሌን እይው ብላ ስላሳየችኝ በራሴ አዝኜ ስለነበር ነውለቅሶዬ።

ያለኝን ለማወቅ ሰው ስላስፈለገኝ ነው እምባዬ።

ጥብቅ አድርጌ አቀፍኳት።

አይኔን የገለጠልችኝን የልጅነት ጓዴን ጭምቅ አድርጌ አቀፍኳት።

በበነጋው፣ ስካራችንም ነገራችንም በርዶ ወደ ቤቴ ሸኝታኝ ስትሰናበተኝ አጥብቄ ሳምኳት።

ከመኪናዋ ወርጄ ቤቴ ገባሁ።

ከመግባቴ እንደ አዲስ በተገለጠ አይኔ ፣ በፈራረሰ ሰፈር እና ቤት ውስጥ ፀንቶ የቆመውን ትዳሬን፣ ፍቅሬን፣ ባሌን ሳየው ፍፁም በደስታ ተሞላሁ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

2 Comments

  • atetefmelaku29@gmail.com'
    አተረፍ መላኩ commented on September 22, 2016 Reply

    ሚያስቀና ባሌን እይው ብላ ስላሳየችኝ፣ በግድግዳ እና በጣሪያ፣ በሶፋ እና በቴሌቪዥን፣ በምንጣፍ እና በአልጋ ጋርጄው የነበረውን የሚቀናበት ባሌን እይው ብላ ስላሳየችኝ በራሴ አዝኜ ስለነበር ነውለቅሶዬ። እውነት ነው ለባሎችም ለሚስቶችም መልዕክት አለው የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ. ብዙዎቻችን እኛ ያለንን ወርቅ ከእግራችን ስር እየረገጥን መሆኑን አንረዳም ነገር ግን የሌሎች ያላቸው መዳብ ያስቀናናል. ሀሌም የተከለከለን ነገር ለማድረግ እንፈጥናለን ይህም ያስቀጣናል::የራቀ ነገር ይናፍቀናል ደግሞ ቅርብ ያለውን አናይም ነገር ግን ቅርብ የራቀውን አናገኘውም ብናገኝም መጠቀሙን አንችልበትም እልለመድንውማ::የተቀብረውን(የተደበቀ) መዳብ ለማግኘት ስንቆፍር ባወጣንው አፈር እግራችን ስር ፊትለፊታችን የተቀመጠውን እና የሚያበራውን ወርቅ እንደፍነዋለን፤እንቀብረዉማለን:: ቀጥይበት ጻፊ እንዳይደክምሽ ጻፊ ወርቅ ሥለሚረግጡ ሰዎች፤ የሚያሥተምር ነገር………አይናችንን የሚገልጥልን ጻፊ.

  • ቲጂ commented on August 26, 2018 Reply

    እንደዚህ አይነት ፅሁፍ አንብቤ አላቅም ምርጥ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...