Tidarfelagi.com

ውጉዝ ከ መ ቄስ በላይ

በድሮ ዘመን አንድ አርዮስ የሚባል የነገረ ክርስትና ሊቅ ነበረ። እነሱ “አርኪሜዴት“ የሚሏቸው ስብስብ ደረጃ የደረሰ ሁላ ነበር። እናም በዛን ዘመን ጋሽ አርዮስ ተመራመርኩ፡ አወኩ አለና(በሴይጣን አነሳሽነትም ይመስለኛል) ቤተክርስትያንን ለሁለት የሚከፍል የኑፋቄ ትምህርት ይዞ ተነሳ። በዚህ ዘመን ደግሞ ቄስ በላይ የሚባል በነገረ ክርስትና የትምህርተ ደረጃው የክብር መጠሪያ ብቻ ከሆነው የሊቀአእላፍነት ደረጃ ያላለፈ ተራ ግለሰብ በገባው ሳይሆን ባልገባው መጠን የቤተከርስትያንን ስርአተ አስተዳደር እቀይራለሁ ብሎ ተነስቷል አሉ። ሊቀአእላፍ ቄስ በላይ (ከጀርባው ያለውን ሃይል ስም እናንተ ሙሉበት) ቤተክርስትያናችንን ለሁለት ለመክፈል እላይ ታች ይል ይዟል። አርዮስ የክርስቶስን አምላክነት የአብ የወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ፍጹም ክዶ ሲነሳ በዛን ጊዜ የነበሩ አባቶች ቀንዱን ብው አብረርውታል። ክርስትያኖችም ከዛን ዘመን ጀምሮ አስከፊ ሃሳብ ስንሰማ በልማድ “ውጉዝ ከ መ አርዮስ“ እንላለን።

አሁን ደግሞ በጠባብ ዘረኝት አእምሮው የታወከው የኦሮሚያ ክልል የእምባ ጠባቂ ተቋም ሃላፊ ቄስ በላይ እራሱንና ጥቂት መሰሎቹን ሰብስቦ ከጥንት ጀምሮ የራሷንም ሆነ የሀገረ ኢትዮጲያን አንድነት አስጠብቃ እዚህ የደረሰችውን ቅድስት ቤተክርስትያን ፍጹም ክርስትያናዊ ባልሆነ የጠነባ የዘረኝት አስተምህሮ ለመከፋፈል ቆርጦ ተነስቷል። ይህን ድብቅ አላማውን የሚያስፈጽምበት መሸፈኛው ደግሞ ቤተክህነት ለልጆቿ በሚገባቸው ቋንቋ ተደራሽ አልሆነችም ፡ የዘር መድልኦ(የሰሜነኞች ጫና) አለ ወዘተ ወዘተ የሚሉ ወቅታዊ ከሆነው የተቀጣጠለ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር የሚሄዱ ለስሜት ቅርብ የሆኑ ሃሳቦችን በማነሳሳት ነው። “ውጉዝ ከ መ ቄስ በላይ“ የሚባልበት ዘመን ቅርብ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። አርዮስም እስቲ ትንሽ ይረፍበት።

በነገራችን ላይ የኦሮሚያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽነር የሆኑትና ከዚህ ቀደም ከሌሎች መሰሎቻቸው ጋር በመሆን ,በተጭበረበረ ምርጫ ኢሃዴግን ወክለው ፓርላማ የነበሩት አቶ በላይ መኮንን ይህንን ድርጊት ለመፈጸም ለምን ተነሳሱ የሚለውን መጠየቅ ያሻል። ከግምቶቼ በጥቂቱ

1ኛ .በቅንነት ለኦሮሚያ ህዝብ ተቆርቁረው ….ህዝቡ የቤተክርስትያኗን መንፈሳዊ አገልግሎት በበቂ ሁኔታና እና በሚፈልገው መልኩ እያገኘ ባለመሆኑ የኦሮሚያ ጠቅላይ ቤተክህነት በማቋቋም ችግሮቹን ለመፍታት አልመው

2ኛ.ቤተክርስትያኗን ለማዳከም የሚፈልግ ሌላ አካል ገንዘብ ከፍሏቸው

3ኛ.በብጥብጥ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልግ አካል ይህንን አይነኬ የሆነ ኢሹ በመነካካት በህዝቡ ዘንድ ወዥንብር እና ሁከት ለማንሳት የሰውየውን ደካማ ጎን መጠቀሚያ አድርጎት

4ኛ.ሰውየው ሃይማኖታቸውን ቀይረው በአዲሱ ሃይማኖታቸው የተሰጣቸውን ድብቅ አላማ እያስፈጸሙ

5ኛ. የራሳቸው የቄስ በላይ የግል የስልጣን ጥም እና ኢጎ

6ኛ. የአእምሮ መታወክ(ሰይጣንም እየጋለባቸው ሊሆን ይችላል)

በዛም አለ በዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ከ 6ቱ አያልፍም ባይ ነኝ።
በእርግጥ ቤተክህነት ግን ለኦሮሞ ህዝብ አልደከመችምን?! ይህቺ ቤተክርስያን ቅዳሴን በኦሮምኛ አስተርጉማ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በኦሮምኛ ቋንቋ እየተቀደሰ አይደለምን?!

በእርግጥ ጠባባቹ እንደሚሉት የኢትዮጲያ ቅድስት ቤተክርስትያን ለኦሮሞ አባቶች ቦታ የላትምን?! ግለሰብን በብሄረሰቡ መደብ እየመደቡ ለመመዘን ብጸየፍም እነዚህ ጠባብ ብሄርተኞች በሄዱበት መንገድ በግድ ልሂድ ብል እንኳን ኦሮሚያ ውስጥ ከሚገኙ 18 ጳጳሳት 16ቱ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች መሆናቸውን እያወኩ ቤተክህነት በሰሜነኞች ጫና ወድቃለች ብዬ ለመናገር እንደነ ቄስ በላይ ከእውነት እና ከአመክንዮ ጋር መቆራረጥ ግድ ይለኛል።

እኔ በተወለድኩበት ባሌ ክፍለ ሀገር እንኳን ጳጳሱ አቡነ ዮሴፍ፡ ያደኩበትና የተማርኩበት አርሲ(አሁን ለሁለት ተከፍሎ) ጳጳሳት አቡነ ያሬድና አቡነ ሄኖክም የኦሮሞ ብሄረሰብ ልጆች ናቸው። እራሳቸው ቄስ በላይስ ይህቺ ዛሬ ሊያፈርሷት ቆርጠው የተነሱባት ቤተክርስትያን ባለውለታቸው አልነበረችምን?! አንድ ቄስ(ጳጳስ ያልሆነ የቤተክርስትያኗ አባል) ሊደርስ የሚችለበትን ከፍተኘ ማእረግ ለእኝሁ የበሉበትን ወጭት ሰባሪ ቄስ አልሰጠቻቸውም ነበርን?! የጠቅላይ ቤተክህነቱ ምክትል ስራአስኪያጅ ፡ እና የአዲስአበባ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ አድርጋ የሾማቻቸውስ ይህቺ ዛሬ የተነሱባት ቤተከርስትያን አልነበረችምን?! ዛሬ ቄስ በላይ የመጡበትን መንገድ ዞር ብለው ሲያዩት የነበሩበት ቦታ ይገባቸው እንደነበረስ ያምኑበት ይሆን?! ቆይ የትኛው የቤተከርስትያን አስተምህሮት ነው ከበላዮቻቸው እና ሌሎች ወንድም አገልጋዮች ውጪ የፖለቲካ ሚዲያዎችን ጠርተው በማን አለብኘነት እና በእብሪት መግለጫ እንዲሰጡ የሚፈቅድላቸው?!

በብዙ ነገሮች ላይ ዝምታን እንመርጥ ይሆናል…በቤተክርስትያናችን እና በሀገር አንድነታችን ላይ ግን የምንደራደርበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም!
በዚህ ሰውና በስብስቡ ዙሪያ ያለኝን ምልከታ በቀጣይም ይዤ እቀርባለሁ….
እስከዛው ደህና ሁኑ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...