Tidarfelagi.com

ዋግህምራ እና ትግራይ – የረጅም ጉዞ አጭር ማስታወሻ

ሰሞኑን ለስራ ወደ ሰቆጣ ተጉዤ ነበር።
‹‹ካልተቀጠቀጠ አይበላም ቋንጣ፣
የዋግሹሞች ሃገር እንዴት ነው ሰቆጣ›› ተብሎ የተዘፈነላት ሰቆጣ ትንሽ ግን ደማቅ ከተማ ነች። ሃሙስ እለት ገብቼ ስውልባት ለቅዳሜ የድጋፍ ሰልፍ ጠብ- እርግፍ ትል ነበር። ሰንደቅ አላማ ታከፋፍል፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ምስሎች ያሉባቸውን ካናቴራዎች ትሸቅል፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ የያዘ የጨርቅ አምባር ገበያ ታጧጡፍ ነበር።

ወጣቶቿ ሰልፉ አልደርስ ብሏቸው ከሃሙስ ምሽት ጀምረው ሰንደቁን ለብሰው አንዴ በእግራቸው፣ አንዴ በብስክሌት ወይ ደግሞ በባጃጅ ወዲህ ወዲህ ይሉ ነበር። አፍ የሚያስከፍት ቁንጅናቸውን አስቀድመው ከየቤታቸው የሚወጡት ሴቶችም ሃሙስ ቅዳሜ የሆነ ይመስል የባንዲራ ገመዱን ዞማ ጠጉራቸው ላይ ሸብ አድርገው ሽር ብትን ይሉ ነበር።

ሃሙስ ተሲያት ላይ ለስራ ወደምሄድባት ቀዳሚት አስቸጋሪውን ጉዞ ጀመርኩ። መንገድ አልነበረም። በመንገዳችሁ ላይ ሳይሰተሩ እንደ ቆሎ የተበተኑ የኮብልስቶን ድንጋዮችን አስቡ። ከዚያ ተራራ አድርጉት። ከዚያ ቁልቁለት አድርጉት። ከዚያ ሃሩር በረሃ አድርጉት። ከድንጋይ በቀር ምንም የማይታይበት ፈታኝ- እጅግ ፈታኝ- ማለቂያ የሌለው የሚመስል መንገድ አድርጉት። ከሰቆጣ ወደ ቀዳሚት የነበረኝ ጉዞ ይሄ ነበር። በበነጋው ደግሞ በሰልፍ ዝግጅት የምትናጠውን ሰቆጣ ትቼ በኮረኮንች መንገድ 68 ኪሎሜትር ትርቃለች ወደተባለችው የገጠር ከተማ ፅፅቃ አመራሁ።

የቀዳሚት መንገድን መሳይ መንገድ ይዤ ስጓዝ የማየው ይሄን ነበር።

እቴ እስኪብርቶ…እቴ ሃይላንድ ብለው የሚለማመጡ፣ መኪና ተከትለው የሚበርሩ ምስኪን የገጠር ልጆች…
የአሜሪካውን ግራንድ ካኒዮን ባያስንቅ የሚገዳደር ፍፁም ውብ የበረሃ መልከአ ምድር…
የሚያጋይ ሙቀት…
ከሁለት እና ሶስት መኪና ሌላ ዝር የማይልበት ተሂዶ የማያልቅ የሚመስል አቡዋራማ መንገድ
‹‹ደሃነም›› እያሉ በአገውኛ በፈገግታ ሰላምታ የሚያቀርቡ ከመልአክት የተዳቀሉ የሚመስሉ ውብ ሴቶች…
አህያና በሬ አጣምረው በራሳቸው አባባል ‹‹ከማያኮራ የእርሻ መሬታቸው ጋር›› ልረስህ አትረሰኝ ትግል የገጠሙ ታታሪ ገበሬዎች…
እልፍ የድንጋይ ቤቶች…
አይኔን ዛፍ እራበው።

አይደረስ የለ የጓጓንላት ፅፅቃ ደረስን። አንጀት የምትበላ ትንሽ የገጠር ከተማ ናት። የስራ ጉዳያችንን ስንጨርስ ሻይ- ቡና ለማለት አንዷ ዛኒጋባ ቡና ጠጡ ቤት አረፍ አልን።
የሸራ ጣሪያ፣ አንድ ዛፍ እና የዘመመ ቤት ናት።

ሞንደል ሞንደል የምትል ልጃገረድ ልታስተናግደን መጣች። ቡና አዝዘን ከሰቆጣ ባመጣነው አምባሻ ስንምግ ግድግዳው ላይ ከማልታ መጠጥ ማስታወቂያ ጋር በብቸኝነት ከተለጠፈው ምስል ጋር ተጋጨን።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ። ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ መስቀል አደባባይ እጅ ሲነሳ የሚያሳይ ምስል ከተመረጡ ጥቅሶቹ ጋር ተለጥፏል።

‹‹አመራርነት አገልጋይነት እንጂ ገዢነት አይደለም››
‹‹ሹመት ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም››

‹‹በአንድ ጠማማ ዛፍ ደኑ አይውደም››
‹‹አይጥ በበላ ዳዋ አይመታ››

 

እኛ እዚህ ለመድረስ ስንንገላታ ለካስ ፍቅር 801 ኪሎሜትሩን ላፍ አድርጎ ቀድሞን ኖሯል!

..ቅዳሜ በጠዋት የመጨረሻዋን ከተማችን ላይ ስራችንን ለመስራት አቤሪጌሌ ገባን። አቤሪጌሌ የአማራ እና የትግራይ ክልል ድንበር ናት። ድንበሩ በጥቂት ወታደሮች በላላ ሁኔታ ተለይቷል። የጨርቅ ገመድ ነው የለየው።

የደረስንበት ሰአት ለስራ ገና ስለነበር ለቁርስ አንዱ ቤት ዘው ብለን ገባን። በኋላ ላይ ስሟ ትእዛዝ እንደሆነ የነገረችኝ ለግላጋ ልጅ የሚጣፍጥ እንቁላል ፍርፍር በጥቢኛ መሰል አምባሻ አቀረበችልን። ጥርግ አድርገን በልተን ለቡና ስንዘጋጅ ልገልጸው የማልችለው ግሩም የእጣን ሽታ አወደኝ።

እጣን ነፍሴ ነው።

‹‹በናትሽ ይሄ እጣን የዚህ አገር ነው?›› አልኳት ትእዛዝን።

‹አዎን..ከወደድሽው ሮጥ ብዬ ገዝቼ ላምጣልሽ…የአምስት ብር ይሄን ያህላል›› አለችና በመለስተኛ እጅ ሁለት ጭብጥ የሚሆን መጠን ስታሳየኝ ሰፍ ብዬ..

‹‹ካላስቸገርኩሽ…ባክሽ ግዢልኝ…›› አልኳት።

ሳትቆይ ተመለሰች።
ሮጥ ብላ ሄዳ- ድንበር አቋርጣ- ትግራይ ክልል ሄዳ- ሳትቆይ ተመለሰች።

በደግነቷ ልቤ ተነክቶ ብር ልሰጣት ብሞክር የተከፋች መሰለኝ። እንደምንም ይቀመጥልኝ ምናምን ብዬ ጥያት ‹‹ጠላዋን ሳትጠጡ እንዳትሄድ›› ወደተባልነው ወደ ኪሮስ ቤት ሄድን።

የኪሮስ ጠላ ቤት ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ሳይሞላ ጢም ብሎ ሞልቷል። ግማሹን በትግሪኛ፣ ግማሹን በአገውኛ፣ ከፊሉን ደግሞ በአማርኛ የሚያወሩ ወጣቶች ጠላቸውን በትልልቅ ሽክና ይለጉታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተጣልኩ መሰለኝ።

ኪሮስ መጣች።

ጠላ ጠየቅን።
የአዲሳባ ሰዎች መሆናችንን ስታውቅና ጥያቄ ስደረድርባት ሕይወቷን አንድ ሽክና ሳላጋምስ ትግርኛም፣ አማርኛም እየደማመረች ነገረችኝ። አራት ልጆች አሏት። አለሌ ነው ካለችው ባሏ ከተፋታች 12 አመት ሲሆናት ደፋ ቀና ብላ የምታድር ደሃ ግን ጎበዝ ሴት ናት።
ጠላዬን የምችለውን ያህል ጠጥቼ ልሄድ ስል ሽክናውን በጣም ስለወደድኩትና ብርቅ ስለሰራብኝ አግባብተው እንድትሸጥልኝ እንድታደርግ ጓደኞችዋን ለመንኩ። 

አዘነችብኝ።

ሽክናውን ስለፈለግኩ ሳይሆን ልግዛው ስላልኩ።

እንዴት ይሄን ሁሉ አውርተን ልግዛው ትላለች ብላ የእውነት ተከፋች። አግባብቼ ሽክናውን ስቀበላት ‹‹የኪሮስ ማስታወሻ ይሆናል…›› ብላ ሰጠችኝና ተሰነባብተን ወጣን።

ስራችን አብቅቶ ያቺን የጨርቅ ገመድ ድንበር ስሻገር በሁለቱም በኩል አገውኛም ትግርኛም አቀላጥፈው የሚናገሩ ጎረቤታሞቹ አንድ ህዝብ መሆናቸውን ሳስብ እኛ በየፌስቡኩ የምንጠዛጠዘውን ነገር አይተው ያዝኑብን መሰለኝ።
ድንበር ነው የተባለውን ባቋርጥም የማያቸው ሰዎች አንድ ናቸው። መልካቸውን፣ ኑሯቸውን እና ቋንቋቸውን የሚጋሩ አንድ ህዝብ ናቸው።

የመቀሌ ጉዞዬን ስጀመር የማስበው ስለዚህ ነበር፤ ሰሜን ሆነ ደቡብ፣ ምእራብ ሆነ ምስራቅ ገጠሪቱ ኢትዮጰያን ባየሁ ቁጥር የማየው ልብ የሚሰብር ድህነት እና ልብ የሚያሞቅ ደግነት እንጂ የተለያየ ህዝብ አይደለም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • daab23f@yahoo.com'
    dani commented on August 3, 2018 Reply

    egzihar ystsh hiwi enem besra wedeza heje neber yayehutm kanchi ejg bemibelt huneta neber bihonm ene yemanbeb enji yemetsaf chlota yelegnm tshufochsh betam new yemwedachew tnsh eytawochsh lak bilu beterefe gn betam new yemakebrsh

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...