Tidarfelagi.com

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ

የጦር አርበኛ፣ ፀሐፊ- ተውኔት፣ ደራሲ፣ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ እና ዲፕሎማት- ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ

በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም ተወለዱ።አባታቸው ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘደንት፤ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያከወጡ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዘደንት ፤በዳግማዊ ምኒልክ ሹመትም የመጀመሪያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪየነበሩት ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲሆኑ ታናሽ እህታቸው ደግሞ የውብዳር ገብሩ (እማሆይ ጽጌ ማርያም) ናቸው።
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት እቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህረት ከፊደል መቁጠርእስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባትእስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።

ወይዘሮ ስንዱ ወደፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በ1921 ዓ.ም (ፊታውራሪ አመዴ 1919ዓ.ም ይላሉ) ወደ ስዊስ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮውስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውንየጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተውትምህርታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም በስዊስ እናበፈረንሳይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይለአምስት ዓመታት እዛው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም በአዲስ አበባ በቅዱስጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሳይኛ ቋንቋን፣ ሀይጅን፣ ቁጥርንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን ማስተማር ጀመሩ።

ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ወይዘሮ ስንዱ ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችንለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። በዚህ ወቅት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂትአምልጠው ጎሬ ላይ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀልለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ አማክረው በተሰጣቸው አምስትመቶ ብር አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግንእርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በጣልያን ሠራዊት እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ አመጧቸውና የቁምእስረኛ ሆኑ።

የካቲት 12 ቀን 1929ዓ.ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበርወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ።በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምንጭምር) ሆነው በመርከብ “አዚናራ” ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤትተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ። ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥም፣ በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።

ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማየሚገኘው የወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የእቴጌ መነን ትምህርትቤት ምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴትርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል። ከ1948 ዓ.ምእስከ 1952ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነውም አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባልበነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶችእኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና “የወንድ ዓለም” በገነነበትየታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ በመሆን አገልግለዋል። ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላበረከቷቸውአስተዋጽዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲየክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።

የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግናና ፀረ-ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ(የክቡርት ዶክተር) ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ምበተወለዱ በ93 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፎ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል።

One Comment

  • አንዱአለም አበራ commented on November 11, 2016 Reply

    የእውነት አድናቂያችሁ ነኝ
    ይህ ትውልድ የታሪክ ጀግኖችን ቢዘክራቸው
    አባቱን አያቱን ማንነቱን
    ማወቅ ኩራት ነው

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...