Tidarfelagi.com

ወንጀል እና ቅጣት (ክፍል ሶስት)

አሳዘነችኝ። በጣም አሳዘነችኝ። ግን ደግሞ አስርባ ሄርሜላን እንድበላ ያደረገችኝ እሷ ናት በሚል ወልጋዳ ይሁን ትክክለኛ ሰበብ ፀፀት ሳይሰማኝ ቀረ። ገፍትራ ሄርሜላ ጉድጓድ የከተተችኝ እሷ ናት….ምናምን እያልኩ በመናገሬ ሳልፀፀት ዝም ብዬ የምትሆነውን አየሁ። ምናልባት የማላውቀው የልቤ ክፍል ለትዳር ዝግጁ ባለመሆኔ አላገባህም ብላ እንድትተወኝ…ሙሉ ነጻነቴን እንድታቀዳጀኝ ፈልጎ ይሆናል…ምናልባት….

ሃጥያቴን በብቅል ግፊት ከተናዘዝኩ በኋላ መቼም ሰው አታደርገኝም…የኔ እና የእሷ ነገር አለቀ ደቀቀ ብዬ…ሂሳቤን አገኛለሁ ብዬ ስጠብቅ ሲሻት ተደብራ ከመጋገር፣ ሲሻት ከሰላምታ ያላለፈ ነገር ባለመናገር ከመቅጣት በቀር ትታኝ አልሄደችም።
እንደ ድሮው ቤቴ ትመጣለች፣ ስደውል ታነሳለች፣ እንገናኝ ስላት ታገኘኛለች። አብራኝ መተኛት ሲቀራት አብራኝ ትሆናለች። ሰብሬያት እንዳልሰበርኳት፣ አኩርፋኝ እንዳላኮረፈችኝ ትሆናለች። ዝም ስትለኝ ሰአቱ ቀን ይሆንብኛል። ቀኑ ሳምንት….ቅጣቴ ይሄ ነው? የሃጥያቴ ክፍያ በዝምታ መንገብገብ ነው?

ሶስት ቀን በሶስት አመታት ፍጥነት እየተጎተተ ካለፈ በኋላ ቁርጤን ልወቅ ብዬ ወሰንኩ። ቃተኛ ቁጭ ብለን ጥብስ ፍርፍራችንን በተለመደው ዝምታ ስንበላ
– ቤዚ…አልኳት
– እ….
መስረቄን ካወቀች ወዲህ ወዬዎቿ…በ እ…ተተክተዋል። ምንድነው እ ብሎ ነገር? ላናግርህ አልፈልግም ስለዚህ ከአንዲት ፊደል በቀር አይገባህም ነው?
– ይቅር ብለሽኛል? አልኳት ጥብስ ፍርፍሩን መብላትም ማየትም አቁሜ እያየኋት
– እ?
ኡፋ! …..የምን እ ነው?
– ይቅርታ አድርገሽልኛል ወይ….
– እዚህ ሰው ፊት ስለሱ ማውራት አልፈልግም…ቤት ስንሄድ እናወራለን….አለችኝ …ለአስተናጋጁ ሲሆን ከብርሃን የተሰራ የሚመስል ቀይ ዳማ ፊቷ ለኔ ሲሆን ባንዴ የሚዳምንላት እንዴት ነው?
ዝም ብያት እስክንጨርስ ጠበቅኩ።
ቤት ገባን። መልሼ ጠየቅኳት።

– አላውቅም…እያሰብኩበት ነው….አለችኝና ወደ መኝታ ቤት ሄደች።
ጓደኖቼን አማከርኩ። ይቅር ባትልህ አብራህ አትቆይም..ያደረግከው ነገር እኮ ከባድ ነው ትንሽ ታገስ…እሷ ሆና ነው እንጂ ሌላ ሴት ብትሆን ይሄኔ ቆርጣልህ ነበር…ምናምን ሲሉኝ የዝምታ ቅጣቴን በፀጋ ለመቀበል ወስኜ ቆየሁ።

ትንሽ ጊዜ ካለፈ በኋላ በአንዱ ቀነ ከመሬት ተነስታ ላንጋኖ እንሂድ ምናምን ብላ ወጠረችኝ።
– ለምን አልኳት
– እኔ ስለፈለግኩ አለችኝ። ፊቷን ሳየው ግን ‹‹ከሌላ ሴት ጋር ስለተኛህ እና የፈለግኩትን ነገር ማድረግ ስላለብህ›› ተብሎ የተፃፈ መሰለኝ። እጄ ላይ ብዙ ብር አልነበረምና
– ደሞዝ ስቀበል…ከአስር ቀን በኋላ ብንሄድስ? አልኳት በሚለማመጥ ድምፅ…
– እኔ አሁን ነው መሄድ የፈለግኩት…ካልፈለግህ አልፈልግም በል….ብስጭትጭት አደረጋት።
ከሌላ ሴት ጋር ስለተኛሁ ፣ ከጓደኛዬ ብር ተበደርኩና ሄድን።
ላንጋኖ ስንደርስ አይቼ የማላውቀውን ክር ሊሆን ትንሽ የቀረው ጡትና ቂጥ በአግባቡ የማይይዘ ‹‹የዋና ልብስ›› ለብሳ ልክ ብቻዋን እንደመጣች…ልክ ወንድ ልታጠመድ ታጥባ ተቀሽራ እንደወጣች ሴት ቢቹ ላይ ስትንቧችበት ዝም ብዬ አየኋት።

ከሌላ ሴት ጋር ስለተኛሁ ብጉራቸውን እያፈረጡ ተጠግተዋት ሰልክ ቁጥር እየጠየቋት እንደሆነ የሚያስታውቁ ወንዶች ሲያንዣብቡባት፣ ሲያወሯት፣ በሚጢጢ ጨርቅ የተሸፈነ ምንተእፍረትዋን በአይናቸው ሲያወልቁ እያየሁ ዝም አልኳት።

ከሌላ ሴት ጋር ስለተኛሁ ማታ ክፍላችን ገብተን ለማንም ኤግዚቢሽን ያቀረበችውን ገላዋን ለመንካት እንኳን ሰትከለክለኝ…እንደ እሾህ ስትሸሸኝ….አትንካኝ ሬዲ አይደለሁም ብላ ፍቅርን ስትነፍገኝ ዝም አልኳት።

አዲሳባ ተመልሰን የማልወደው ጫጫታም ካፌ እየወሰደች ለሰአታት አርፍዳ ስትጎልተኝ፣ አምስት ደቂቃ ዘግይቼ ቤት ከገባሁ አንበሳ ሆና ስትቆጣኝ፣ ከጓደኞቼ እንድቆራረጥ አትሄድም ብላ ስታስቀረኝ፣ የዘመዶቿን ሰርግ ይዛኝ ሄዳ ብቻዬን ትታኝ ስትረሳኝ፣ ሃጥያቴን ነግራቸው የናቁኝ ሴት ጓደኞቿን በሙሉ አምጥታ (አራት ናቸው) የሁለት መቶ ሃምሳ ብር ክትፎ ስታስጋብዘኝ…ከሌላ ሴት ተኝታቸለሁ እና ቅጣቴን ልቀበል…ሂሳቤን ላግኝ ብዬ ዝም አልኳት።

ይባስ ብላ አንዷ ቀለብላባ ጓደኛዋ በንቀትም በሴሰኝነትም ተነድታ ስልክም እየደወለች፣ ቤቴም ‹‹ቤዛ የለችም›› ብላ የሌለችበተትን ሰአት መርጥ እየመጣች እንድተኛት ስትጋብዘኝ…ከአንዷ ጋር ከማገጥክ ከእኛስ ጋር ብትማግጥ በሚል ሁኔታ ስትቀበጠበጥብኝ ጥፋቱ የኔ ነው ብዬ ዝም አልኳት።

ከሳምንታት በኋላ ግን እጅ እጅ እያለኝ መጣ። እኔን አስቀንታ ለመመለስ የምትለፋው፣ ላገኘችው ሰው ሁሉ ሃጥያቴን ነግራ ስሜን የምታጠፋው፣ በውሃ አረረ ፊቴን ፊት የምትነሳው፣ በሁሉም ነገር ስሜቴን የምታሸማቅቀው ነገር ከፍቅሯ እየበለጠ ነገሩ እጅ እጅ እያለኝ መጣ።
ጭራሽ አሁን ደግሞ ሃገር ውስጥ ስለሰራሁት ስህተት አልሰሙም ብዬ የተማመንኩባቸው እንደዛ የሚወዱኝ…እንደልጅ የሚንከባከቡኝ ቤተሰቦቿ ጋር ሄዳ ማውራቷ፣ ልታዋርደኝ መጨከኗ…በእኔና በእሷ ጉዳይ ማስገባቷ ልቤን አደነደነው። ልጠይቃት ይገባል። ይቅር ብለሽኛል ወይስ ቅጣቴ የእድሜ ልክ ነው? አፉ ብለሽኛል ወይስ አንቺ ካለሽበት ሕይወቴ እንዲህ ሊሆን ነው? ብዬ ልጠይቃት ይገባል።
እትዬ ሌንሴና እህቶቿ እንዲያ ባገባጠሩኝ እለት ማታ ቤት ቁጭ ብለን ወይን ስንጠጣ (ላወራት ስጀምር ነው አንዱን ጠርሙስ ጨርሳ ወደ ሁለተኛው መግባቷን ያየሁት)
– ቤዚ …አልኳት
– እ…
(እ…ን አሁንማ ለምጄዋለሁ)
– መቼ ነው እንደ ድሮው የምትሆኚልኝ? ቅጣቴ አልበዛም? አልኳት
– ያደረግከውን ነገር ረሳኸው…? ከሌላ ሴት ጋር እኮ ነው ሴክስ ያደረግከው…ሴ….ክ….ስ….
ወይኑም ነገሩም እንዳሰከራት ገባኝ።
-አውቃለሁ…አጠፋሁ…አይበቃኝም ቅጣቱ…እንዴት እንደዚህ እንቀጥላለን….ብንቀጥልስ…እስከመቼ ድሮ ለሰራሁት ጥፋት እድሜዬን ሙሉ እከፍላለሁ…
– ወር የማይሞላ ጊዜ ነው እድሜዬን ሙሉ የምትለው..
– አይደለም…
– ታዲያ…
– ማለቴ…ብንጋባ እንኳን አንድ ነገር ባጠፋሁ ቁጥር አንተ እኮ…እያልሽኝ እስከመቼ እንኖራለን…
– ሃሃ…..አሁን ነው መጋባት ያማረህ….? ደ…ፋ…ር….

ወሬያችን እንኳን እንዳሁኑ በአልኮል ፈረስ ተሳፍራ በደህናውም ጊዜ ትርጉም ያለው ነገር ሊወጣው እንደማይችል ተረዳሁና ዝም አልኳት።
– ምን ይ…ዘ…ጋ…ሃ…ል? አለች ፊደል እንደሚቆጥር ሰው ቃላቶቹን እየጎተተች…
– ጥቅም የለውም ብዬ ነው…
– ም…ኑ..
– እንዲህ ሆነሸ ማውራቱ….
– እና..ውራ…ማውራት አይደል የፈለግከው…እናውራ…
– ግዴለም ነገ ይደርሰል…
– አይ…ሆ…ን…ም አሁን እናውራ…
– ቤዚ…ይቅር
– አይ…ቀርም…እናውራ…እናወ…..ራ….
እንደለቅሶ ይሰራት ጀመር። ቤዚዬ….
– እሺ አልኳት እንዳታለቅስ…
– እሺ…ልጅቷ…እንዴት ነበረች…ጎበዝ ናት…..?
– ማ? አልኩኝ ደንገጥ ብዬ..
– እናውራ አላልክም…እናውራ….ያቺ አብረሃት የተኛሃት ልጅ…ጎበዝ ናት….ማለት…ከኔ ትበልጣለች?

ዝም አልኳት።
– ንገረኛ! እንዴት ነበረች…ትበልጠኛለች…..? ለቅሶ ጀመረች።
አቀፍኳት።

– ንገረኝ…..በለጠችኝ…ደስ አለችህ…ጎበዝ….
– ተይ ተይ በቃ…ቤዚዬ…ይቅርታ…በቃ…ይቅርታ አታልቅሺ አልኩና አጥብቄ አቅፌ ፀጉሯ ላይ…አይኖችዋን አፈራርቄ ሳምኳቸው።
– አትሳመኝ….ብላ ተፈናጥራ ተነሳች።
– እ?
– አትሳመኝ….እሷን በሳምክበት አፍ አትሳመኝ….ሚ..ኪ….ከሁሉ ሚያሳዝነኝ ምን እንደሆን ታውቃለህ…..አለችኝ ተመልሳ እየተቀመጠች።
ዝም አልኩ።
ቀጠለች-
– እወድሃለሁ…ማለቴ…ካላንተ ወንድ አልፈልግም…ጓደኞቼም ቤተሰቦቼም ቢመክሩኝም ባንተ መጨከን አቃተኝ…ሳምሪ ወንድ ልጅ አንዴ ከተልከሰከሰ ሁሌም ይልከሰከሳል…ይቅር ካልሽው እንደ ፈቃድ ነው ሚወስደው…ይቅርብሽ ብላኝ ነበር…ይሄን ታውቃለህ? እህቶቼ ለአይን ጠልተውሃል…እማዬማ ቤቴ አይምጣ ብላለች…እኔ ግን እወድሃለሁ…ልቤን ቢያመኝም…እወድሃለሁ…
– እነሱን ተያቸወ…አንቺ ከወደድሽኝ የኔ ጉዳይ ካንቺ ነው….አልኩ ፈጠን ብዬ…
– አይደለማ…..እወድሃለሁ ግን ውስጤ ቆስሏል…ባልድንስ…ከንፈርህን ባየሁት ቁጥር እንዴት እንደሳምካት ነው የማስበው….ከእሷ ጋር የተኛኸውን..አተ..አተ…አተኛ..ኘት..ኘት እያሰብኩ እንዴት አብሬህ እተኛለሁ….ደሞ….ደሞ እንዴት ብዬ ወደፊት አምንሃለሁ…

ተስፋ በመቁረጥ ዝም አልኩ። የማያቋርጠው ቅጣቴ ምንጭ አሁን ተገለፀልኝ። ፍቅሯን ባላጣም የእምነት ድልድዩን እንዳይጠገን አድርጌ ሰብሬዋለሁ። ከእንግዲህ እንደማዘር ቴሬሳ መልካም ሰው ብሆን ባጠፋሁት ጥፋት እንጂ በንጽህናዬ አልመዘንም። እንደ ጋንዲ ሩህሩህ ብሆን…ስረገጥ እኖራለሁ እንጂ አልከበርም። ግራ ጉንጬን ስሰጥ ቀኝ ጉንጬን በቡጢ ስደበደብ እኖራለሁ እንጂ ይቅር አልባልም።

ቤዛ ስኳሯ ተባብሶ ቃላቶቿ በማይገባኝ ደረጃ ሲጠባበቁ፣ ሰውነቷ ሲዝል ስብስብ አድርጌ አነሳኋትና አስተኛኋት።

ለብዙ ደቂቀዎች አጠገቧ ተቀምጬ ቆየሁና ጥልቅ እንቅልፍ ሲወስዳት ግንባሯን ሳምኩት።

ተገላበጠችና….፣ – ወንድ ልጅ አንዴ…አንዴ ከተልከሰከሰ ሁሌ ልክስክስ ነው…ብላ አጉረመረመች።

መለያየት አለብን።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

2 Comments

  • abdishasweet@gmail.com'
    ኣብዲ commented on September 17, 2018 Reply

    እግዚሔር ይስጥልን…ጥፍጥ ያለ ስራ ነው!!

  • danielshawul7@gmail.com'
    D commented on November 27, 2018 Reply

    konjo tarik …..

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...