Tidarfelagi.com

‹‹ወንጀልና ቅጣት›› (ክፍል አንድ)

እትዬ ሌንሴ ፊት ነሱኝ።

ለወትሮው ከፊልድ ምናምን ስመለስ እንኳን ኬሻ ሙሉ ከሰል፣ ሶስት አራት ኪሎ ቲማቲም ወይ ሽንኩርት ወይ ደግሞ ጎመን ምናምን ይዤ መጥቼ የመኪናዬን ጲጵ ሲሰሙ ጠብ እርግፍ ብለው ያስተናግዱኝ ነበር። ቤት ያፈራውን ጭኮ፣ ቅንጬ ወይም ፍርፍር በፍጥነት አቅርበው በግድ ያስበሉኝ ነበር።
ዛሬ ግን በተወደደ ከሰል ከየትና የት ካለ ኩሊ ራሴ አውርጄ (እጄ ከሰል በከሰል ሆኗል) ሳሎናቸው ስገባ እዛ…ሁልጊዜ የሚቀመጡበት አሮጌ ፎቴ ላይ የሚወደውን ሰው መርዶ የሰማ ሰው መስለው ተጎልተዋል።

ሃሳብ ገብቷቸው አልሰሙኝ ይሆን?

ሁሌም ወፍራም ላስቲክ የሚለብሰውን ምንጣፋቸውን በጭቃ ጫማዬ እንዳላቆሽሽ እየተሳቀቅኩ፣ ከሰል በከሰል የሆነ እጄን እነዳንከረፈፍኩ አጠገባቸው ደርሼ ሰላም ልላቸው ብጠጋቸው እያዩኝ እንደማያዩ መስለው ፊት ነሱኝ።

ምን አጥፍቼ ነው?
– እንዴት ሰነበቱ እትዬ ሌንሴ ከማለቴ
– አረ ምንጣፌን! ምንጣፌን አታቆሽሽብኝ እንጂ…ለራሴ ሰራተኛም የለኝ… አሉኝና ደልዳላ ሰውነታቸውን እያሞናደሉ ወደ ጓዳ ገቡ።

አረ ፊት መንሳት!

መጥፎ ሰው አይደለሁም። ያው እንደሁሉም ሰው ስህተትና ጥቂት ደደብነት ባያጣኝም መጥፎ ሰው አይደለሁም። አንድ መጥፎ ነገር ያደረገ ሰው መጥፎ ሰው ነው? አይመስለኝም።

የፍቅረኛዬ እናት እትዬ ሌንሴ ለምን እንደተናደዱብኝ የጠረጠርኩት ባዶው ሳሎን ውስጥ ጥለውኝ ጓዳ በገቡ በደቂቃዎች ውስጥ ነው። ቤዛ የሰራሁትን ስህተት ነግራቸው ነው።
ወሬኛ።

እጆቼን እንዳንከረፈፍኩ መታጠቢያ ውሃ ፍለጋ ደጅ ወጣሁ።
የቤዛ ታላቅ እህት ምህረት ፊቷን ካመጣሁት ከሰል አጥቁራ ጠበቀችኝ።
– አረ ውሃ ፈልገሽ አስታጥቢኝ በናትሽ አልኳት ሰላምታ ለመስጠም ሳልሞክር። በአይኖቿ ሰማይ ድረስ አጉናኝ መሬት ስታፈርጠኝ ይታወቀኛል። (እሷም ሰምታለች ማለት ነው። )
– ውሃ የለችም…ቤትህ ታጠብ…ብላኝ በረንዳ ላይ ያስቀመጥኩትን ኬሻ ሙሉ ከሰል ልክ እንደሰው ገላምጣው ጥላኝ ወደ ቤት ገባች።

ይህችን ይወዳል ሚካኤል!

በሁለቱም ሁኔታ እየተበሳጨሁ ያመጣሁትን ከሰል ብድግ አድርገህ ለራስህ እናት ውሰድ ውሰድ እያለኝ ወደ መኪናዬ ስሄድ የቤዛ ትንሽ እህት እምነት ገጠመችኝ። እኔንና እጆቼን አመሳቅላ አይታ…
– ምነው ውሃ የለም እንዴ በቤቱ? አለችኝ (ይህችኛዋ ገና አልሰማችም ማለት ነው)
– ማዘርም ምህረትም ፊት ነሱኝ…ማን ያስታጥበኝ…አልኳት አይን አይኗን እያየሁ
– አውነታቸውን ነው ለነገሩ…እንዳንተ አይነቱ ቆሻሻ እንኳን በጆግ ውሃ በአባይም ቢታጠብ አይነፃ! አለችና መልስ እንኳን ሳትጠብቅ እየተመናቀረች ጥላኝ ሄደች። (ሰምታለች)

አሁን ነገሩ ፍንትው አለልኝ። የወሬ ሰንሰለቱ ተገለጠልኝ። ቤዛ እና ቤተሰቧ እንደማይለያይ መንጋ ናቸው። የሚያስቡት አንድ ላይ። የሚስቁት አንድ ላይ። የሚያኮርፉት አንድ ላይ። የሚወዱት አንድ ላይ። የሚጠሉት አንድ ላይ። ወሬ አይደባበቁ…ምስጢር አያውቁ…ብሽቆች።

መኪናዬ ውስጥ ገብቼ በአንዱ ቁራጭ ፎጣ የእጆቼን ከሰል ለማስለቀቅ ስሞክር ንዴቴ ጨመረ።

ለምን ነገረቻቸው?
ይቅር ብዬሃለሁ ምናምን ብላኝ ለምን ስለስህተቴ ለቤተሰቧ ነገረች? ስለግል ጉዳያችን ለቤተሰብ ቱስ ማለቱ…እኔን ከማስገመት በቀር ምንድነው ትርጉሙ? ቤት ቤት ከወንጀሌ የማይመጣጠን የምትቀጣኝ ቅጣት አንሶ ይወዱኝ በነበሩ ቤተሰቦቿ ዘንድ ቀልዬ እንድታይ ለማድረግ?

…ነገሩ ቆይቷል። ማለቴ አንድ አምስት ወር አልፎታል። አብረን መኖረ ሲቀረን ሳንጋባ የተጋባን ጥንዶች ሆነን ነበር። ቤተሰብ ያውቀኛል። ቤተሰብ ያውቃታል። ከሳምንቱ አብዛኛውን ቀን አብረን ውለን እናድራለን። ጉሮ ወሸባዬ እና አሸወይና እና የማዘጋጃ ቤት ፊርማ ሲቀር ተጋብተናል ሊባል ይችል ነበር። በዛው ሰሞን ከየት መጣ ሳልለው ቤዛ አድርጋ የማታውቀውን የ‹‹እንጋባ›› ንዝንዛዋን መጀመሪያ ለዘብ፣ በኋላ ክርር አድርጋ ጀመረች።

አይኗ ከቬሎ ሱቆች፣ ሃሳቧ ከሰርግ አልላቀቅ አለ። እኔ ደግሞ ላገባ (ት) አልፈለግኩም። ስለማልወዳት አይደለም። እወዳታለሁ። ላገባት የማልፈልገው እንደወደድኳት መቆየት ስለምፈልግ ነው።

ከአምስቱ የቅርብ ጓደኞቼ ሶስቱን ሚዜ ሆኜ ድሬያለሁ። ከተጋቡ ወዲህ በደስታቸው ፈንታ የጨመረው ቦርጭና ንጭንጫቸው ብቻ ነው። ጋኔን አይደለም ያገቡት። ያፈቀሯቸውን ሴቶች ነው ያገቡት። ግን አንድም ቀን ስለትዳር ወይ ስለሚስት በጎ ነገር ሲወጣቸው አላየሁም። አልሰማሁም።

ቅልጥ ያለ ፑል እየተጫወትን ተደውሎ ይጠራሉ።
…ዳይፐር እንዳትረሳ…ምጣዱ እንደገና ተበላሽቷል። …የውሃ ዛሬ መክፈል አለብህ….ባቢ ትኩሳት አለው…የእማማ ማህበር እኮ ዛሬ ነው…

ቶሎ ና።
ቶሎ ድረስ።
አሁኑኑ እንድትመጣ።
እንዳታረፍድ።
እንዳታመሽ። …

እንዲህ ያሉ ትእዛዞች በሚበዙበት የጭቆና አገዛዝ ወድቀዋል። እኔ ደግሞ ነፃነቴን አጥብቄ የምወድ ሰው ነኝ። ድንበር፣ መስመር፣ ሰአት እላፊ አልወድም። ትእዛዝ ይጎረብጠኛል። መሆን አለበት ያመኛል። እንዲህ አድርግ ይረብሸኛል።

ቤዛንም ነፃነቴንም እወዳለሁና የትዳርን እግረ-ሙቅ ‹ትንሽ እንቆይ›› ምናምን ብዬ በጨዋኛ እምቢ አልኳት።
አቤት አለዋወጥ! ተለዋወጠችብኝ። ለሕይወቷ የሰጋች እስስት እንዲደዚሀ አትለዋወጥም። ይባስ ብላ…

– እማዬ ወንድ ልጅ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ከትዳር በፊት ካገኘ አያገባሽም ብላኛለች ብላ ለሁለት ወር ተኩል የምወደውን፣ የምኖርለትን ገላዋን ከለከለችኝ።

አበድኩ። ማለቴ በጣም አበድኩ። የገዛ ገርልፍሬንዴ ጭኖች መሃ ለመግባት የትዳር የምስክር ወረቀት ስጠየቅ ጊዜ በጣም ተናደድኩ።

ደግሞ እኮ ልታሰቃየኝ አብራኝ ታድራለች። ልክ ዛሬ ራራችልኝ..ፈቀደችልኝ፣ ቅጣቴ ሊያበቃ ነው ምናምን ብዬ ሁለመናዬ እንደ ጅብራ ሲገተር እንደ ታናሸ ወንድም ግንባሬን ስማኝ ራሷን በመአት ትራሶች አጥራ ትተኛለች።

ከይሲ አይደለች?

ብላት- ብሰራት ሁለት ወር ተኩል ሙሉ ራሷን ነፈገችኝ። አስቡት፤ ወንድ ነኝ። ወጣት ነኝ። ከቆንጆ ሴት አጠገብ የተኛሁ ወጣት ወንድ ነኝ። የፍትወት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ትዝታ አለኝ።

ከይሲ ናት።

ቢሆንም አይኔ ሌላ አላማተረም። ልቤ ለሌላ አልነሆለለም። ቅጣቱ እንዲቀልልኝ፣ በምህረቷ እንድትጎበኘኝ ብሞት አድርጌ የማላውቀውን በፊልም እንደማያቸው ወንዶች አበባ ምናምን እየገዛሁ እሰጣት ጀመር። መብራት ሳይጠፋ ሻማ ምናምን ለኩሼ፣ ወይን ቀድቼ ላሳዝናት ሞከርኩ። እሷ ግን ፍንክች አላለችም።

ገላዋን እያዛጋሁ ሳምንታት አለፉ።

አንጎሌና ገላዬ ሌላ ማሰብ በማይችልበት በዚህ ከፍተኛ የወሲብ ድርቅ ጊዜ ነው የቢሯችን ኤች አር አፈር ይብላና ሄርሜላን የቀጠረው።

ኦ…ሄርሜላ!
ለድርጅቱ በገንዘብ ያዥነት የተቀጠረች ሳይሆን ለኔ በፈተናነት የመጣች ትመስል ነበር። የሆነች እንከን አልባ ነገር። ሹ…ል እና ትልልቅ ጡቶች። ሙትት ያለ አንጀት። በቀጭን ወገቧ እህህህ…እያለች በመከራ የምትጎትተው ትልቅ ቂጥ። ስስ ግን ሳሙኝ፣ ግመጡኝ የሚል ከንፈር። …..

ሄርሜላ….

ወንጀልና ቅጣት (ክፍል ሁለት)

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...