Tidarfelagi.com

‹‹ወንጀልና ቅጣት›› (ክፍል ሁለት)

…ኦ…ሄርሜላ!
ለድርጅቱ በገንዘብ ያዥነት የተቀጠረች ሳይሆን ለኔ በፈተናነት የመጣች ትመስል ነበር። የሆነች እንከን አልባ ነገር። ሹ…ል እና ትልልቅ ጡቶች። ሙትት ያለ አንጀት። በቀጭን ወገቧ እህህህ…እያለች በመከራ የምትጎትተው ትልቅ ቂጥ። ስስ ግን ሳሙኝ፣ ግመጡኝ የሚል ከንፈር።

ሄርሜላ….

ፈተናዬን ሲያበዙት ፊልድ በሄድኩ ቁጥር ስልጠናው ላይ አበል ትክፈል ብለው አብረው ይልኩናል። ሃዋሳ ላይ ለትንሽ አመለጥኳት….መቀሌ ላይ ለጥቂት ሳትኳት፣ አርባምንጭ በመከራ አለፍኳት …ደሴ ግን…ደሴ ላይ ግን ብርዱና ውበቷ አሲረውብኝ ወደቅኩላት። ቀመስኳት። አጣጣምኳት። የተመኘሁትን ጡት እንደ መንፈቅ ልጅ መጠመጥኩ። የጓጓሁለትን ወገብ አቀፍኩ። የቋመጥኩለትን መቀመጫ ጨብጥኩ። ያለምኩትን ከንፈር ጎረስኩ።

ሲነጋ በአንሶላ ተጠቅልላ አይን አይኔን ስታየኝ ነቃሁ። ከባይተዋር ሰው ጋር ባይተዋር አልጋ ላይ ተኝቴ ሲነጋብኝ ፍንጣሪ የጥፋተኝነት ስሜት ስላልተሰማኝ ጥፋተኝነት ተሰማኝ። ትራሴን ተንተርሼ እንደተኛሁ ፣ እንዴት አደርሽ እንኳን ሳልላት-
– ስሚ ሄርሜላ…ትላንት…ስህተት ነው የሰራነው….እኔ እጮኛ አለኝ…አልኳት
– አራቴ ስህተት አለ? ሃሃ….አለችና ያን ከንፈሯን ይዛ ወደከንፈሬ ስትጠጋ ሸሸት ብዬ..
– የምሬን ነው…ስህተት ነው….እጮኛዬን እወዳታለሁ…አልኩ
በፍፁም ግዴለሽነት ከአልጋ ውስጥ ውስጥ መለመላዋን ወጥታ ፈት ለፊቴ ቆመች። ከእኔ በፊት እዚህ ቦታ ሺህ ጊዜ የቆመች፣ ሺህ ጊዜ የሌላን ሰው ገላ አቅፋ ያደረች ልምድ ያላት አሳሳች ትመስላለች።
– አንድ ነገር አንዴ ከሆነ ስህተት ከተደጋገመ ውሳኔ ነው የሚባለው….ለማንኛውም ይመችህ…ሰአት ሄዷል …ልታጠብ…ብላ ታላቅ ቂጧን እያገላበጠች ወደ መታጠቢያው ክፍል ሄደች…

ምንድነው ያለችው?

አዲሳባ ስመለስና ቤዛን ሳገኛት ፀፀት ይሰማኛል፣ የሰራሁት ሃጥያት ያሰቃየኛል ብዬ ጠብቄ ነበር። ያልተለወጠው ግትር ባህሪዋ ይሆን የኔ አይኑን በጨው ያጠበ ባለጌ ሰው መሆን ሽውም አላለኝ። የሄርሜላን ሴትነት ያገኘው ወንድነቴ ምሱን አገኘ መሰለኝ በትራስ ታጥሮ የሚተኛው የቤዛ ገላ አላጓጓው አለ። ማስፈራሪያና ቅጣቷ አልሰማው አለ።

ሄርሜላን በማስታገሻነት በወሰድኩ አንድ ሳምንት ካለፈ ይመስለኛል ቤዛ ባንዱ ምሽት እንደለመደችው ልታሰቃየኝ ስትሞክር ቀድሜያት ግንባሯን ሳምኩና ጀርባዬን ሰጥቼያት ተኛሁ። ደቂቃም ሳይቆይ በቀጫጭን ጣቶቿ ጀርባዬን ትዳብስ…እጆቿን ወደ ጉያዬ ትሰድ ጀመር።

ዝም አልኳት።
በግድ ወደ እሷ ገልብጣኝ-
– ሚኪዬ…አለችኝ በመኝታ ቤት ድምፅዋ…
– አቤት…አልኩ ቡዝ ያሉ ውብ አይኖቿን እያየሁ። ወደ ግራ ያዘነበለ አንገቷን፣ ጫፋቸው የከረረ ጡቶችዋን በስስ ካናቴራዋ ውስጥ እየታዘብኩ።
– አልናፈቅኩህም?…
– ናፍቀሽኛል….
– ምነው መጠየቅ እንኳን ተውክ ታዲያ…
– ጠይቄ ጠይቄ ሰለቸኛ!

ዘላ ተከመረችብኝ።

ቅጣቴ ባልጠበቅኩት ሁኔታ ተቋጭቶ የኔ ወደሆነው ቦታ እንድዘልቅ ተፈቀደልኝ።

ከዚያ ምሽት በኋላ እኔና ቤዛ የበፊቶቹ ሚኪና ቤዛ ሆንን። የአግባኝ ጥያቄዋ ከጭቅጭቅነት ወደ ልመና ዝቅ ብሎ አንጀት በሚበላ ሁኔታ የምታቀርበው ተማፅኖ ብቻ ሆነ። ከንግግር ይልቅ በሌላ መልኩ የምትገፋብኝ ረቂቅ አጀንዳ ሆነ። ሶፋ እንደመቀየር፣ የኩሽና ኮተት እንደማሟላት፣ ምጣድ እንደመግዛት፣ ሰፋ ያለ ቤት እንከራይ እንደማለት አይነት ረቂቅ አጀንዳ።

ግፊቷን ችዬ መደበኛ ሕይወት ወደመኖሬ ስመለስ አድብቶ የቆየው የአግባኝ ጥያቄዋ ተመልሶ መጣ። እጅ እጅ አለኝ።

– አንቺ ቆይ ለምን አትረጋጊም….እኔ ዝግጁ ሳልሆን ባገባሽ ጥሩ የሚሆን ይመስልሻል? አልኩ በአንዱ ቀን የጋለ ጭቅጭቅ ስንጀምር
– ምንድነው ምትጠብቀው? ቤትህ ተሟልቷል። ታውቀኛለሁ። አውቅሃለሁ። እንዋደዳለን…ምንድነው ምትጠብቀው…ከዚህ ወዲህ አዲስ ፀባይ አይኖረኝም…ለምን አታገባኝም…እጆቿን እያወናጨፈች….
– እንተዋወቃለን? እርግጠኛ ነሽ?
– ምን ማለት ነው ይሄ ደግሞ?
– ምንም ማለት አይደለም ግን ምን ያጣድፈናል?
– ምን ያጣድፈናል? ሶስት አመት በላይ አብረን ቆየን…ምን ይጎትተናል?
– ገና ነው..
– ገና አይደለም…ወይ አሁን ታገባኛለህ…ወይ እንለያያለን…በቃ…
– በቃ?!
– አዎ በቃ….
– ይሄው ነው ቤዛ?
– ይሄው ነው…እስክትወስን ሴክስ የሚባል ነገር የለም፡ ውሳኔው ያንተ ነው….
የመኝታ ቤት በሩን ያለርህራሄ ድርግም አድርጋ ዘግታው እዛው ዋለች።
እስክትወስን ሴክስ የሚባል ነገር የለም። እስክትወስን ሴክስ የሚባል ነገር የለም። እስክትወስን ሴክስ የሚባል ነገር የለም።
ሱቅ ሄጄ ስድሰት ቢራ ይዤ መጣሁና አንዱን ከፍቼ መጠጣት ጀመርኩ።

የመጨረሻ ጠርሙሴን ሳጋምስ ወደ ሳሎን ብቅ አለች።

አጠገቤ ቁጭ አለች። አንዴ እኔን አንዴ ባዶ የቢራ ጠርሙሶቹን አየችና

– ሚኪ….አለችኝ
– አቤት….
– አትወደኝም?….
– እወድሻለሁ…ግን ይሄን ማስፈራራት ማቆም አለብሽ…ትዳር አንደዚህ አይቆይም….
– የምን ማስፈራራት?
– ሴክስ የለም ምናምን….ብቸኛው የቅጣት መሳሪያሽ እሱ ይመስላል…ጥሩ አይደለም…..አልኩ ጠርሙሱን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጬ እያየኋት…
– ጥሩ አይደለም ማለት…
– ማለት…የራበው ልጅ ምግብ ሰርቆም ቢሆን ይበላል…
ብድግ አለች።
– ምን አልክ አንተ!? ጮኸችብኝ።
– ምን አልኩ? ያልኩትን ነገር ለማሰብ ሞከርኩ። ምንድነው ያልኩት…
– የራበው ልጅ ምግብ ፍለጋ ይሰርቃል ማለት ምንድነው?

ወየው! ምንድነው ያልኩት? ምንድነው ያልኩት?
– ምንም ማለት አይደለም…አባባል ነው…
– አባባልማ አይደለም…በደንብ አስበህበት ነው የተናገርከው…

ወየው!
– ንገረኛ!
– ምን ልንገርሽ?
– ሰርቀሃል?
– እ?
– ሰርቀሃል ወይ?

ስድስቱ ቢራ ይሆን ግዴለሽነቴ ወይ ሁለቱም አዎ አልኳት። አልገርምም? አንዴ አምልጦኛል እና አዎ ሰርቄያለሁ አልኳት። ከግድግዳ መጋጨት ሲቀራት ሁሉን ነገር ሆነች። አለቀሰች። ጮኸች። በጥፊ ልትለኝ ሞከረች። ደጅ ወጣች። ተመልሳ ገባች። አለቀሰች። ጮኸች። ፀጉሯን ይዛ አቀርቅራ ብዙ የማይሰማኝ ነገር አለች።

አሳዘነችኝ። በጣም አሳዘነችኝ። ግን ደግሞ አስርባ ሄርሜላን እንድበላ ያደረገችኝ እሷ ናት በሚል ወልጋዳ ይሁን ትክክለኛ ሰበብ ፀፀት ሳይሰማኝ ቀረ። ገፍትራ ሄርሜላ ጉድጓድ የከተተችኝ እሷ ናት….ምናምን እያልኩ በመናገሬ ሳልፀፀት ዝም ብዬ የምትሆነውን አየሁ። ምናልባት የማላውቀው የልቤ ክፍል ለትዳር ዝግጁ ባለመሆኔ አላገባህም ብላ እንድትተወኝ…ሙሉ ነጻነቴን እንድታቀዳጀኝ ፈልጎ ይሆናል…ምናልባት….

ወንጀል እና ቅጣት (ክፍል ሶስት)

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • weluteklit2017@gmail.com'
    ኢዞና ናዛኢ commented on February 2, 2019 Reply

    አሪፍ ነው:ቀጥዪበት..

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...