Tidarfelagi.com

ካልፎ ሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ

(ትራጄዲ ትረካ)

ሰሞኑን የወንድሙ ጂራን ዘፈን የምገርበው ያለ ምክንያት አይደለም።
ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ካልሲየን ፍለጋ በየጥጉ እሰማራለሁ። የቀኝ ካልሲየ ምስኪን ናት። እንደ ገራም የድመት ግልገል ከመመገቢያው ጠረጴዛ እግር ስር ኩርትም ብላ ትገኛለች። የግራ ካልሲየን ግን እፀ -መሰውር የረገጥሁባት ይመስል ደብዛዋ ይጠፋል። አልጋው ስር- ሶፋው ስር -ምንጣፉ ስር ፈልጌ ተስፋ ልቆርጥ ትንሽ ሲቀረኝ ወንድሙ ጅራ” አለች አለች አንድ ቦታ” እያለ ያበረታታኛል።

የዚያን ቀን በጠዋት ተነስቸ ወደ ጨዋ ሚኒ ማርኬት መራመድ ጀመርኩ። ምንገዱ ዳር የሆነ ሰውየ እያፍዋጨ ሽንቱን የጥድ ችግኝ ስር ይሸናል። የጥዱ ችግኝ ደርቆ አንዲት ቅጠል ብቻ ቀርቶታል። ሳይደበድብ ብዙ ጊዜ በመቆየቱ የተነሳ ቅጠል ማቆጥቆጥ የጀመረ የፖሊስ ቆመጥ ነው ሚመስል። (ወይ አገላለፄ😉)

በሸናተኛው ሰውየ ፊት ላይ የሚታየውን ጥኑ በራስ መተማመንና ኩራት ስመለከት ሰውየው እየሸና መሆኑን ማመን ሁሉ ከበደኝ ። በቃ ለችግኙ ማዳበርያ በፈሳሽ መልክ የሚያበረክት ነው የሚመስለው!! ደሞ የረባ እቃ እንዳለው ሰው በጣቱ እንኩዋ አልከለለውም። እቃይቱ በጣም ጢኖ ከመሆኑዋ የተነሳ አማራጭ እምብርት ትመስላለች።

ግልምጥምጥ አረኩት። በስራው ተሸማቆ እኔንም የኢትዮጵያ ህዝብንም ይቅርታ ይጠይቃል ብየ ሳስብ-

“ጀለሴ! ልትሸኚ ፈልገሽ ከሆነ ወረፋ ጠብቂ” አይለኝም?!
ሰውየው በዚህ መጠን ማፈር የተሳነው መሆኑ ስረዳ ሳላደንቀው ማለፍ ከበደኝ።

ስለማድነቅ ሲነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ።

በቀደምለት በረከቦት ጎዳና እየተወዘወዝሁ “ላቀች አስፋው የቀብር አስፈፃሚ” ፊትለፊት ስደርስ አምስት ጎረምሳ የሃይስኩል ተማሪዎች “አድናቂህ ነን ፈርምልን” እያሉ ተጠመጠሙብኝ። በደስታ ላለቅስ ምንም አልቀረኝ ። ባለፈው አንዱ ሲያትል የሚኖር አድናቂየ “እንኩዋን እጠቀመዋለሁ በመስታውት ሳጥን ውስጥ እጎበኘዋለሁ”” ብየ አልሜው የማላቀውን “አይፎን -ሰቨን ” ላከልኝ።

አሁን ደግሞ እኒህ ወጣቶች ፊርማየን ለመውሰድ ሲጋፉ ማየት ምንኛ ልብ ይነካል? የደስታ እንባየን በይበሉባየ እያበስኩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ፈረምኩ። ለልጆች ፊርማየን አርከፍክፌ ትንሽ አለፍ እንዳልኩ የሱሪየ የግራ ኪስ ሲቀልለኝ ተሰማኝ ። ወገን ተበላሁ! ሞባይሌ! አይፎኔ! ሄዱዋል! ለካ ፊርማ ጠያቂ ጎረምሶች ሲያደንቁልኝ የኖሩት በዚህ ሰፈር አይፎን ሰባት ደፍሬ መጠቀሜን ኑሩዋል።

ፖሊስ ጣቢያ ሂጄ በንባና በቁጣ የታጀበ አቤቱታ ሳቀርብ ሳጅን አበበ ምን ቢለኝ መጥፎ ነው?!” አንተ አይፎን ሰቭንን የመሰለ ንብረት እንዴት በኪስህ ትይዛለህ?”

” ታድያ እንደቡዳ መዳኒት ባንገቴ ዙርያ እንዳንጠለጥለው ፈለግህ?”

ከዚያን ቀን ጀምሮ ሰው መንገድ ላይ “አድናቂህ ነኝ” ሲለኝ ዘለህ እነቀው እነቀው የሚለኝ።

ጨዋ ሚኒማርኬት ደርሼ: አንድ ኪሎ ብርቱካን ሸምቸ ልወጣ ስል ማሾ በወሬ ጠመደችኝ።

“ስማ! ምኡዝን አታጣብሰኝም?”

“ምኡዝ ይቅርብሽ ባለትዳር ነው። ከፈለግሽ ካሳን ላስተዋውቅሽ! ”

“እኔ ባለትዳር ነው ምርጫየ”

“እኮ ለምን?” የሚል ትርጉም ያዘለ ፊት አሳየሁዋት።

“ባለትዳር ወንድ የተጨማደደ ሸሚዝ አይለብስም። ካልሲው አይሸትም። አልጋ ላይም ጥሩ ልምድ አለው። ሲበቃኝ ዞር በል ብለው ዞር ይላል እንጂ መሄጃ እንደሌለው አይገግምም። ከሁሉ በላይ ግን ምስጢር ይጠብቃል። የራሱን ጉድ ለመደበቅ ሲል ከኔጋ ያደረገውን አይዘረግፍም። ”

“ይገርማል!”

“ታዲያ ለምን አታስተዋውቀኝም?! ለነገሩ ተወው! የፈጠርከው ገፀባህርይ ይሆናል! ወይም የራስህ alter ego ሊሆን ይችላል። ካሳ ያልከው ግን ማን ነው?”

” ካሳ ካሳኖቫ ወንደላጤ ወዳጄ ነው! የባነነ ነው! ጥሩ ልብ አለው። ፍቅር ሲሰራም እንደ ጉንዳን ነው” አልኩ።

“ጉንዳን እንዴት ነው ፍቅር የሚሰራው?” አለች እየሳቀች

“ጉንዳን አንዴ ፍቅረኛው ገላ ላይ ፊጥ ካለ አንገቱን ካልቀነጠሽው በቀር አይላቀቅም”

ተሰባብቻት ስወጣ።

“ለብርቱ ጉዳይ ነገ ላገኝህ እፈልጋለሁ!”

“ሰሞኑን ጊዜ የለኝም”

“ጉንዳን ሲሳረር ለማየት ጊዜ አለህ! ለኔ ጊዜ የለህም”

2

የገዛሁትን ብርቱካን ይዠ የት እንደምሄድ ልናዘዝ። ወዳጄ ካሳ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ለመጠየቅ ወደ ኮርያ ሆስፒታል ልሄድ ነው። ካሳ ወደ ” እንደሻው” አልቤርጎ የተለያዩ ቆነጃጅትን ይዞ ሲመጣ ያልቤርጎው ዘበኛው በክፉ አይን ሲመለከተው ቆይቱዋል። እዚህ አገር የባንክ ቤት ዘበኛን እና የአልቤርጎ ዘበኛን ያክል ለቅናት የሚያጋልጥ ስራ የለም። የበይ ተመልካችና የበጅ ተመልካች ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው።

አንድ ቀን ካሳ እንደልማዱ አንዲቱን ይዞ ሲመጣ ዘበኛው ዝምታውን ሰበረ።

“ልጄ! ደና ውለሻል ! ይሄኔ አንቺ ፍቅረኛየ ነው ብለሽ ታስቢ ይሆናል። እንዲያውም በተክሊል አገባሻለሁ ብሎ ዋሽቶልሽ ይሆናል። እሱ ግን የለየለት አለሌ ነው!! በየቀኑ አዳዲስ ሴት እንደሚያፈራርቅ የምናውቀው እኔና መዳንያለም ነን”

ዘበኛው ይህንን ጥቆማ ከሰጠ በሁዋላ በእርካታ ተነፈሰ። ልጂቱዋ ካሳን ዘልላ ታንቀዋለች ብሎ ጠብቆ ስለነበር ለገላጋይነት ተዘጋጀ።

ልጂቱዋ ግን ካሳ ትከሻ ላይ ራሱዋን አንተርሳ” አውቃለሁ ሼባው ! በማያገባህ አትግባ” አለች ።

ዘበኛው ክው አለ። ግን በቀላሉ እጅ አልሰጠም።

” የዛሬ ልጆች አግድም አደጎች መሆናችሁ ግልጥ ነው። ቢሆንም ከወግ ባህላችን ውጭ የሆነ ድርጊት ሲፈፀም ሳይ መታገስ አቅቶኝ ነው። እኔም አንቺን የምታክል ቀንበጥ ልጅ አለችኝ። በየደረሳችሁበት እየገለባችሁ እሄን መከረኛ ህዝብ ለበሽታና ላልተፈለገ ርግዝና ስትዳርጉት ዝም ብየ አልመለከትም”

ካሳ ሳቁን ማፈን አልቻለም። ወገቡን ይዞ እንባው እስኪፈስ መንከትከት ጀመረ።
አንድ ሰው የግል ቅናቱን በዚህ ደረጃ ህዝባዊ ገፅታ ማላበስ ይችላል ብሎ አስቦ አያውቅም።

ካሳ ሲስቅ ዘበኛው ንዴቱን መቆጣጠር አልቻለም። ብድግ አለና በክላሹ ሰደፍ የካሳን አናት ነረተው። ምቱ “አንዝር ምት ” ይባላል።

ታሪኩን ከመቀጠሌ በፊት “አንዝር ምት ” ምን ማለት እንደሆነ ላብራራ። ለማብራሪያው ድጋፍ የሚሆነው የባህርዳር ወዳጄ የነገረኝ ገጠመኝ ነው።

ሰውየው ከባልንጀሮቹ ጋር ጠላ እየጠጣ ነው። ድንገት “አያ አጥናፉ”የሚል ድምፅ ሰማና ማን ነው የሚጠራኝ ብሎ ወደ በረንዳ ብቅ አለ። ይህን ጊዜ ጨለማ ለብሶ ሲጠብቀው የቆየው የሚስቱ ውሽማ በቆላ ከዘራ ቅንድቡ ላይ ይጠነብሰዋል። ሰውየው ምንም ጥቃቅን ጠላት ቢኖረውም እንዲህ “አይነት ምት ጨክኖ የሚመታኝ ሰው ይኖራል “ብሎ አላሰበም። ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ ነዘረው። በቃ ከበረንዳው ፊትለፊት የቆመው የኤሌትሪክ እንጨት ላዩ ላይ የወደቀበት ነው የመሰለው። ነፍሱ መለስ ስትልለት ወደ ጠላ ቤቱ እየሮጠ ገብቶ ምን አለ?

“ጎበዝ ባልቦላውን አጥፉት ልናልቅ ነው”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

2 Comments

  • abeleyob27@gmail.com'
    aschenaki commented on May 28, 2017 Reply

    ene bezu anbabi aydelehum gen bagegnehut agatami yemetetsefachewun negeroch anebalehu betam new yemewedachew yehone eyaznanu kum neger yemiyaschebetu nachew

  • abbeto commented on June 9, 2017 Reply

    ha ha ha er bewketu hoden atasekew

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...