Tidarfelagi.com

ካልፎሂያጁ ማስታወሻ

‘ እቴ ሸንኮሬ’ የተባለ ያበሻ ሬስቶራንት ውስጥ ተቀምጨ ያዘዝኩትን በያይነቱ እጠብቃለሁ፤
ከፊትለፊቴ ባለው ግድግዳ ላይ የነገስታት ምስሎች ተደርድረው ይታያሉ፤ አጼ ቴዎድሮስ፥ ሀጸይ ዮሀንስ ፥ አጼ ምኒልክ ፥ ልጅ ኢያሱ፤ አጼይት ዘውዲቱና አጼ ሐይለስላሴ ይታዩኛል፤ ሰአሊው አጼ ተክለጊዮርጊስን ዘሏቸዋል።

ያዘዝኩት ምግብ መጣልኝ ፤ በያይነቱ ብለው ያቀረቡልኝን አየሁትና ለረጅም ደቂቃ ተከዝኩ። ብጫ ክክ- ቀላ ያለ ክክ-ቀለም አልባ ክክ፤ ክክ በየፈርጁ ነው ያመጡልኝ፤ አንዱን ፍንካች ክክ ብድግ አድርጌ በመዳፌ መዘንኩት ፤ ቀዳዳ ቢበጀለት የካፖርት ቁልፍ ይሆናል ፤ ክኩ እንዲህ ከጠበደለ አተሩ ምን ሊያክል ነው? ከቶ በምን ከኩት? በቡልዶዘር መሆን አለበት ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጥፋት ላይ የሚገኘው ቀይስር በስፋትና በጥራት ተሰርቶ፤ የጽጌረዳ ጉንጉን መስሎ ክኩን ከቦታል፤ ባንጻሩ፤ የምወደው ስንግ ቃርያ እንደ አጼ ተክለጊዮርጊስን ስእል ተዘሏል፤
“ አገር ቤት ያለህ ይመስለኝ ነበር “ አለኝ አጠገቤ ተቀምጦ የሸክላ ጥብስ የሚንድ ሰውየ።
“ የክብር ዲያስፖራ ማእረግ ሰጥተውኝ ልቀበል መጥቼ ነው እንጂ ኑሮየ አገር ቤት ነው ” ስል መለስኩለት።
“ አደራ እዚህ የተረገመ አገር ውስጥ እንዳትቀር ! “
“ ይሄን ያክል አስመርሮሃል? “ ስል ጠየኩት።
“ አታምነኝም፤ ከዚህ አገር ልጠፋ ሁለት ጊዜ ሞክሬ, ሁለት ጊዜ ከድንበር መለሱኝ”
“ አሜሪካኖች ስስታም ናቸው “ ቀጠለ ሰውየው “ በምድራቸው ውስጥ ያለው ነዳጅ ዘይት ከቀይ ባህር ይበልጣል፤ ግን ነክተውት አያውቁም፤ ለመጭው ትውልድ ይቆጥቡታል፤ ግን መጭው ትውልድ የሚሉት መቼም የሚመጣ አይመስልም፤ ነጭ ዜጎቻቸው ልጅ መውለድ እያቆሙ ነው ፤ እንደምታየው አበሻ አንድ ሁለት ይወልድና ሃላፊነት ሲከብደው ያቆማል ፤ በተቃራኒው የስፓኒሽ ስደተኞች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ይዋለዳሉ ፤ አውቶብስ ፌርማታ ላይ አንዲት ስፓኒሽ ሴትዮ ካጠገብህ ከቆመች ልብ ብለህ እያት ፤ ድርስ ርጉዝ ናት፤ እግሯ ስር በጋሪ የሚገፋ ህጻን ይኖራል። ከጎኗ ሌላ ጩጩ ሽኮኮ የተሸከመ ፤ባል ቆሟል ፤ አንድ ስፓኒሽ ስደተኛ ፤ ግለሰብ ሆኖ መጥቶ ከጥቂት አመታት በሁዋላ ህብረተሰብ ይሆናል፤ መጭው ዘመን የስፓኒሽ ነው ፤ “ርስትህን ባእድ ይውረሰው “ የሚለው የቅዱስ መጽሀፍ ርግማን ለአስቆርቱ ይሁዳ ቢነገርም ባሜሪካ ላይ እንደሚደርስ ጥርጥር የለኝም “
“ ይሄን ያህል አሜሪካ ካስጠላችህ ለምን ከታሊባን ጎን ቆመህ አትዋጋም?” አልኩት ።
“ አሜሪካ መንግስት ለስራ ፈት የሚሰጠውን ድጎማ እቀበላለሁ፤ ከዛ ደግሞ በድብቅ በካሽ እሰራለሁ፤ ሲሰተሙን እንዳቅሜ እየሸወድኩ ታክስ አልከፍልም፤ አላማየ አሜሪካን በኢኮኖሚ ማሽመድመድ ነው ፤ ይሄ ትግል ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል?” አለና በሸክላ ድስቱ ውስጥ የቀረውን ጥብስ ሙትና ቁስለኛ ማድረግ ቀጠለ።

ከሰውየው ከተለያየሁ በሁዋላ ወደ ሽንት ቤት ጎራ አልሁ።
የሽንት ቤቱ ግድግዳ ላይ ” Game over TPLF “ የሚል ጽሁፍ በስኪብርቶ ተሞንጭሮ አየሁ ፤
ከጎኑ ሌላ ያልታወቀ ደራሲ “ Tdf ገና ይበዳሀል ! “ የሚል ቃል አስፍሯል፤ እምደንቅ ነው! ኢትዮጵያውያን ብንከፋፈልም ብንጋደልም፤ አንድ ሽንት ቤት መጋራት አላቆምንም።

ከሽንት ቤቱ ወጥቼ የሱርየን ማንገቻ ሳጠባብቅ አንዱ እጁን እየታጠበ በቆረጣ ያየኛል ፤ ብዙም ሳይቆይ፥ ነቀፋ ይሁን ሙገሳ በቅጡ መለየት ያልቻልኩት ነገር ተናገረ ፤
“በጣም ስለማደንቅህ ሽንት ቤት ገብተህ የምትጽዳዳ አይመስለኝም ነበር “ ሲለኝ ሰማሁ፤
“ልጸዳዳ ሳይሆን ላጸዳ ገብቼ ነው ዠለስ “

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

4 Comments

 • temushashe15@gmail.com'
  temsgengabre commented on August 15, 2021 Reply

  Wow yemiewdad book

  • temushashe15@gmail.com'
   temsgengabre commented on August 15, 2021 Reply

   ታጋቹማስታወሻ ምርጥ መፀሀፍ ነው

 • temushashe15@gmail.com'
  temsgengabre commented on August 15, 2021 Reply

  Diredewa

 • heilysix@gmail.com'
  Heilysix commented on August 19, 2021 Reply

  Yes
  [Link deleted]

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...