Tidarfelagi.com

ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ

(የሚያስተክዝ ወግ)

ከየረር በር እስከ ቦሌ የሚሄድ ምኒባስ የመሳፈር እድል ያልገጠመው ሰው ስለ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ልተንትን ቢል ማን ይሰማዋል?

እና ትናንት የተሳፈርኩበት ምኒባስ ካፍ እስከ ሰደፍ ሞልቶ ነበር፤ የምኒባሱ ነባር ወንበር የተሳፋሪውን ብዛት ባገናዘበ መልኩ ሽግሽግ ተደርግጎበታል፤
ወደ ሁዋለኛው ወንበር በሚወስደው ቀጭን መተላለፊያ ላይ የሚብረከረክ እግር ያለው አግዳሚ ወንበር ተዘርግቱዋል፤ወያላው ካግዳሚው ወንበርና በበሩ መካከል የተረፈችውን ክፍተት እንኩዋን ለግራችን መዘርጊያ ብሎ አልማራትም፤ ላንድ ሰው መቀመጫ የምትሆን ሙዳየ ምፅዋት የምትመስል ሳጥን አኑሮባታል።

እኔ በበኩሌ ታክሲ ውስጥ የሰው ኪስ ያወለቀ በስርቆት ሊከሰስ አይገባውም ባይ ነኝ፤ ምክንያቱም ፤ እጅህን ከደረትህ ላይ ባነሳህ ቁጥር ሌላ ሰው ኪስ ውስጥ የመግባት እድልህ ሰፊ ነው፤

ባገራችን የወሲብ ትንኮሳ ዋናው መነሻ የስነምግባር እጥረት ሳይሆን የትራንስፖርት እጥረት መሆኑ የገባኝ የዚያን ቀን ነው፤ አልፎ አልፎ በሴት ተሳፋሪዎችና በወንድ ተሳፋሪዎች ማህል ፤የግብረስጋ እንኩዋ ባይሆን የግብረ ወንበር ግንኝነት ያጋጥማል፤ ሳትፈልግ፤ከፊትለፊትህ ካለው ወንበር ሞልቶ የፈሰሰ የሴት ልጅ ገላ ጉልበትህ ላይ Assቀምጠህ ረጅም ምንገድ ልትጉዋዝ ትችላለህ፤

የታክሲው መደበኛ ወንበሮች እንደ ማሽላ ቂጣ ተበጣጥሰዋል ፤ወንበር አገኘሁ ብለህ፤ ተንደርድረህ፤ ባንደኛው የወንበር ቅሪት ላይ ፊጥ ብትልበት አፈንግጦ የወጣ ሚስማር፤ ቂጥህ ላይ ማንም የማያደንቀው ዲምፕል ሊበጅልህ ይችላል፤ እኔ የተቀመጥሁበት የሁዋለኛው ወንበርማ የትየ አዛለችን ታጣፊ አልጋ አስታወሰኝ፤

የዛሬ ምናምን አመት እኔና ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ፤አስኒ ጋለሪ ግርጌ ፤በዘጠና ብር ቤት ተከራይተን ነበር፤አይ ጊዜ! ዛሬ በዘጠና ብር ቤት ይቅርና የእዝን ኩባያ መከራየት አትችልም፤ በርግጥ ቤቱ መለስተኛ ኮንቴይነር የሚያክል ሆኖ ባለ አንድ ክፍል ነው፤ እኔና ፍቅር “ሳሎኑን አንተ ውሰደው ምኝታ ቤቱን እኔ ልውሰደው ብለን” የምንከፋፈልበት እድል ስላልነበረን ግድግዳ ተከፋፈልን፤ እኔ በምስራቅ በኩል ባለው ግድግዳ ወስጄ የምርቃቴ ቀን የለበስኩትን ሱፍ ሰቀልሁበት፤

ፍቅር ይልቃል ድርሻውን የምራቡን ግድግዳ ወስዶ ”

“የወፍ ስጋ በላሁ ቢጥመኝ መረቁ..” ብሎ የሚጀምር ፤በዳንቴል የተጣፈ የግጥም ጥቅስ ሰቀለ፤(ጥቅሱን ካገር ቤት ይዞት ነው የመጣ)

ቤቲቱን ያከራየን ደላላ “ቤቱ ፈርኒሽድ ነው ” ሲል ምን ለማለት እንደፈልፍገ የገባኝ ቆይቶ ነው፤በቤቱ የምስራቅ ማእዘን ላይ ፤ እግር ያለው ያሸዋ ማጣርያ ወንፊት የሚመስል የረገበ አሮጌ የሽቦ አልጋ ተተክሉዋል፤ ያልጋው እግር በወለሉ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተቀብሮ ከመኖሩ የተነሳ ቅጠል ማቆጥቆጥ ሁሉ ጅምሩዋል፤ እዛ ላይ መተኛት ማለት በቃ ራስን ወፌ ይላ እንደመስቀል ነው ፤ እንዲያውም ፍቅር ይልቃል “ ተኝተህ ሳይህ፤ መቀስ ምት እየመታ ባየር ላይ ባስማት ተንሳፎ የቀረ ተጫዋች ትመስላለህ” ይለኝ ነበር፤አልጋው ላይ አንድ ሳምንት እንደተኛሁበት ቅዠት ይጫወትብኝ ጀመር፤

ሲብስብኝ አንድ ቀን አከራያችንን እትየ አዛለችን ጠርቼ ፤

“እትየ አዙ ! ይቅርታ አርጉልኝና ይሄ አልጋ…”ብየ ሳልጨርስ

“ አልጋ አልከው? አላወቅኸውም እንጂ ቅርስ ላይ ነው ተኝተህ የምታድር ! አያቴም አባቴም ለረጂም ጊዜ ታመው የሞቱት እዚህ አልጋ ላይ ነው”፤አሉኝ

በማግስቱ እኔና ደባሌ ቤቱን ጥለን ጠፋን፤

ወደ ምኒባሱ እንመለስ፤ አንድ ሰው ምኒባስ ውስጥ ካልገባ በቀር የውሃ እጥረት የሚያስከትለውን ያካባቢ ውድመት እንዴት ሊረዳ ይችላል፤

አጠገቤ፤ ሚጢጢ ራስና የትየለለሌ ትከሻ ያለው፤ የተገለበጠ ሚዶ የመሰለ ጎረምሳ ቁጭ ብሎ ነበር፤አጠገቡ ቁጭ ብሎ በከስክስ ጫማው ህዳርን የሚያጥነውን ተሳፋሪ ምን አለው መስላችሁ?

“ጀለሴ! ጫማህን ለፈደራል ፖሊስ ለምን አታከራየውም? ጠረኑኮ ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ ይበትናል”


ቦሌ ድልድይ ጋ ስንደርስ፤ እጄን ወደ ሱሪየ የግራ ኪስ ሰድድሁ! የተልባ ማሻው ሚካየል ድረስልኝ! ሁለት መቶ ብር አጭቆ የያዘ ቦርሳየ በነበረበት የለም፤ መጀመርያ ደነገጥሁ፤ አጥብቄም አዘንሁ፤ ወድያው ግን ተፅናናሁ፤ በዚህ ግፍያ ማሃል፤ ግራ ኩላሊቴ በነበረበት ቦታ መገኜቱም ተመስጌን ነው፡

የደረሰብኝን ለወያላውና ተናግሬ የምከፍለው ሁለት ብር እንደሌለኝ ለማስረዳት ሞከርኩ፤ፍንክች አላሉም፡ ከግራ ቀኝ ጠምደው ያዋክቡኝ ጀመር፤ ቢጨንቀኝ ሹፌሩን “የስልክ ቁጥርህን ስጠኝና የሁለት ብር ካርድ ትራንስፈር ላድርግልህ”አልሁት፤

በጭቅጭቃችን ማሃል ሹፌሩ አተኩሮ ፊቴን ሾፈውና፤

“አንተ ገጣሚው ሰውየ ነህ አይደል?”
አለኝ፤

እየተሽኮረመምሁ መሆኔን ገለጥሁ፤’ አንተ ደህና! ከፈለግህ ለዛሬ መዋያ የሚሆን አንድ ሁለት መቶ ብር አበድርሃለሁ” ይለኛል ብየ ስጠብቅ፤

‘ ያን ሁሉ መፃፍ እየቸበቸብህ እንዴት ሁለት ብር መክፈል ያቅትሃል?”ብሎ ጮኸብኝ

“እንደ ነገርሁህ ቦርሳየን ዘርፈውኝ ነው”

“በቃ ለጥቅስ የሚሆን ሁለት መስመር ግጥም ገጥምሀ ስጠንና ሂድ”አለኝ ወያላው፤

ትንሽ አሰብሁና የዛሬ ምናምን አመት ፍቅር ይልቃል ግድግዳ ላይ ያየሁዋትን ጥቅስ በወረቄት ገልብጨ አቀበልሁት፤

የወፍ ስጋ በላሁ ቢጥመኝ መረቁ
መታማት አይቀርም ምን ቢጠነቀቁ፤

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

2 Comments

 • ልሳን commented on December 14, 2017 Reply

  አንተና ፍቅር ይልቃል በ ዘጠና ብር በተከራያችሁበት ግዜ እኔ በ መቶ ሃምሳ ብር ሙሉ ግቢ ተከራይቼ ነበር

  የወፍ ስጋ በላሁ ቢጥመኝ መረቁ
  መታማት አይቀርም ምን ቢጠነቀቁ ደስ ይላል ደስ ይላል ፡፡

 • kenedinigus@gmail.com'
  Kenedy commented on June 18, 2020 Reply

  እኔ ልሙትልህ ሸጋ ጥፌት ጥፈሀል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...