Tidarfelagi.com

ከጊቤ ባሻገር ያለችው ጅማ (ክፍል ሁለት)

እነሆ ከተሚማ ጋር የጂማን ምድር “ሽርርርር” እያልንበት ነው። ሆኖም “ተሚማ” የትናንትናው ሙገሳ አንሶኛል ብላለች። “የነየታችሁት ሐጃ ሞልቶላችሁ በደስታ እንድትፍለቀለቁ ካሻችሁ ሙገሳውን ጨመርመር አድርጉልኝ” ትላለች። ታዲያ እኛም አላንገራገርንም። “ምን ገዶን! አንቺ ሰኚ ሞቲ! ሙገሳ በየዓይነቱ ይኸውልሽ” ብለን በድጋሚ መወድሳችንን ልንደረድርላት ተዘጋጅተናል። እንዲያውም ሙገሳችንን የምንጀምረው እሸትነቷን በማወደስ ነው። ለመወድሳችን የመረጥነውም የሟቹን የዮሴፍ ገመቹን ዜማ ነው። አዝማቹ እንዲህ ይሄዳል።

Naale naale naalen irgixiidhaa
Maddiin furnoo hidhiin buskutiidha.

በአማርኛ ሲተረጎም እንዲህ ይሆናል (አማርኛው አዛማጅ ትርጉም በመሆኑ የኦሮምኛውን ያህል አስደሳች ላይሆን ይችላል)።
ናሌ ናሌ ናሌ እርግጥ ነው።
ጉንጯ ፉርኖ ሲሆን ከንፈሯም ብስኩት ነው።

ፈገግ ያሰኛል አይደል? (ቂቂቂቂቂ….)። አዎን! በኦሮምኛ እንዲህ እያሉ መግጠምም ይቻላል። መወድሱ ከወገብ በታች ያለውን የሰውነት ክፍል አይንካ እንጂ ከወገብ በላይ ያለውን ውበት በሚያውቁት መንገድ ማወደስ ይቻላል። ከወገብ በታች ካለው የሰውነት ክፍልም ተረከዝን ማሞገስ ይቻላል። ከዚያ በላይ ያለውን ክፍል ግን መጥቀስ አይፈቀድም።

ዮሴፍ በግጥሙ ውስጥ “ናሌ ናሌ..” የሚል ሐረግ ደጋግሟል አይደል? ቃሉ እንዲህ ሲደጋገም ትርኪ ምርኪ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ያለቦታው የገባ አይምሰላችሁ። በክፍል አንድ ጽሑፋችን የጠቀስነው “አህለን አህላ” ነው ተቀይሮ እንዲህ የሆነው። ዘፋኙ ዘፈኑን የሚጀምረው በዚህ ሐረግ ነው። ከዚያም እርሱ የዘፈኑን ግጥሞች እያከታተለ ሲጠራ ተቀባዮቹ “ናሌ ናሌ…” እያሉ ጨዋታውን ያደምቁለታል።
*****
አሁን ደግሞ የአማርኛ ተናጋሪዎችን በመወከል ተሚማን እናሞግሳታለን። ለሙገሳችን የመረጥነው ደግሞ የነዋይ ደበበን “ከጊቤ ባሻገር”ን ነው።

ከጊቤ ባሻገር አለች ኧረ አንዲት ሰው…
በፍቅር በናፍቆት ልቤን የምትወዘውዘው ።
አቦል ጀባ ብላኝ ቡናዋን ብቀምሰው፣
እግሬ ወደ ጅማ ሱስ አመላለሰው ።
እንግባ አይመሽም ወይ
ቤትሽ ጅማ ነው ወይ ?

ነዋይ እውነታውን ነው ቁጭ ያደረገው። “ተሚማ” ቄጤማ ጎዝጉዛ፣ ቡናውን አፍልታ ሐድራውን ሞቅ ሞቅ ስታደርገው ፍቅር የምትፈትል ነው የምትመስለው። ከሐድራው የሚፈልቀው ሙሐባ የቡና ሱስ ብቻ ሳይሆን የፍቅር ሱስንም ያስይዛል።

ደግሞ አንድ ነገር ያዙልኝ!! በሌሎች አካባቢዎች እንግዳን በእቅፍ አበባ ነው የሚቀበሉት አይደል?… የጅማዋ ተሚማ ደግሞ ለዚያራ የመጣውን ሰው በቡና ቀንበጥ ነው የምትቀበለው። እንዲህ ያለች ጥበበኛ አርቲስት ናት ተሚማ!
*****
ኧረ ለመሆኑ እኛ በሰፊው ያሞገስናት የጂማዋ “ተሚማ” በርግጥ ፍቅርን ታውቀዋለች?… ምንም አትጠራጠሩ!! ተሚማ ፍቅርን ከማወቅም አልፋ ለፍቅር የምትንበረከክ ልበ-ንጹህ ጉብል ናት። ከልቧ ለምታፈቅረው ሰው ፍቅሯን የምትገልጸው ደግሞ በጣም ኪነታዊ በሆነ መንገድ ነው። እርሱም “ሂዲ ደርቡ” (Hiddii darbuu) ይባላል:: “ሂዲ ደርቡ” የኦሮሞ ሴቶች ለፍቅር መረታታቸውን የሚገልጹበት ወግ ነው። ይህም በአማርኛ “ሎሚ መወርወር” ከምንለው ወግ ጋር ይቀራረባል። ልዩነቱ ግን ተሚማ ፍቅሯን በምትገልጽበት ጊዜ የምትወረውረው “ሎሚ” ሳይሆን “እምቧይ” ነው።

ሁለተኛው ልዩነት ደግሞ “ሂዲ ደርቡ” እንደ “ሎሚ መወርወር” በጥምቀት ብቻ የሚፈጸም አለመሆኑ ነው። ሶስተኛው ልዩነት ተሚማ እምቧዩን ሌሎች ሰዎች እያዩዋት የምትወረውር አለመሆኑ ነው። ሰፉ (Safuu) የሚባለው የኦሮሞ የስነ-ምግባር ደንብ ይህንን እንዳታደርግ ያግዳታል። በመሆኑም ተሚማ የወደደችውን ሰው በእምቧይ የምትመታው ሰው በሌለበት ስፍራ ነው።

በነገራችን ላይ አንዲት ሴት ወንዱን መውደዷን የምትገልጽበት ይህ የ“ሂዲ ደርቡ” ወግ በሀረርጌና በአርሲም ይታወቃል። ነገር ግን በአርሲና በሀረርጌ “ሂዲ ደርቡ” አይባልም። እዚያ ዘንድ “አሴና” ወይንም “አሼና” እየተባለ ነው የሚጠራው፤ በተጨማሪም የሀረርጌና የአርሲ ኮረዶች ፍቅራቸውን የሚገልጹት በብዙ እምቧዮች ነው፤ ወንድዬው ጠዋት ከቤቱ ሊወጣ ሲል ሴቲቷ በአጥር ላይ ተንጠልጥላ ብዙ እምቧዮችን ከፊቱ ትበትንና ወደ ቤቷ ትነጉዳለች፤ ወንድዬውም ጉዳዩን ለወላጆቹ ይነግርና ቤተሰቡ ከተስማማበት ልጅቷን ያገባታል።

በ“ሂዲ ደርቡ” እና “በሎሚ መወርወር” መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት ግን ከላይ ከተገለጹት ውስጥ የለም። ትልቁ ልዩነት ወዲህ ነው ያለው። እንደሚታወቀው “ሎሚ መወርወር” በወንድ የሚፈጸም ወግ ነው። ሴቲቷ ሎሚውን አትወርውርም (ምንም እንኳ ያቺ “ጭራ ቀረሽ” የሚሏት አርቲስት ዘነበች ታደሰ “ሎሚ ብወረውር” እያለች ብትዘፍንም ሴቶች ሎሚ ሲወረውሩ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም)። የጅማዋ ተሚማ የምትከውነው “ሂዲ ደርቡ” ግን በራሷ የሚፈጸም እንጂ በወንድ የሚፈጸምላት አይደለም። ወንድዬው ፍቅሩን የሚገልጸው ነጠላ ገዝቶ በማልበስ ነው እንጂ እምቧይ በመወርወር አይደለም።

ታዲያ ተሚማ የምትወደውን ሰው በእምቧይ የመምታቷን ጀብድ ስትገልጸው ሰምታችኋት ታውቃላችሁ?… ካላወቃችሁ “ፌይሩዝ” የተባለች ወጣት ያዜመችውን በትንሹ ቀንጨብ አድርገን እናሳያችሁ (ከፌይሩዝ የተዋስነው አባባል ለተሚማም ይሆናል)።

Akkasumaan hiddii darbannaanii (ለዚያው ነው እምቧይ መወርወሬ)
Sijaaladhe giddiin naqbnaanii (ግድ ብሎኝ ነው አንተን በማፍቀሬ)

ተሚማ! ጉብሊቷ ወጣት የጅማ!! ስትወደን እንዲህ ነው የምትለን። ለፍቅር መረታቷን እንዲህ ነው የምታስረግጠው። ፍቅሯ ሲብስባት ደግሞ በጣፋጭ አንደበቷ እየዘማመረች ልባችንን ልታፈርሰው ትችላለች። እንዲያውም ታዋቂዋ የጅማ ተወላጅ አርቲስት ሲቲና አባዱላ “ቡርቱካኒ” ብላ ያዜመችው ዝነኛ ዘፈን ተሚማ በፍቅር በምትጨነቅበት ጊዜ የምትቀኘውን እንጉርጉሮ ሊወክል ይችላል። እስቲ ደግሞ የሲቲናን ዘፈን እንዋስና የተሚማን የፍቅር ብሶት እንግለጸው።

Burtukaani mitii hadhaadha miti hadahaadha (ብርቱካን አይደለም ይህስ መራራ ነው)
Kun jaalalaa miti maraachaadha (ፍቅርስ አይደለም ይህስ እብደት ነው)

እጥር ምጥን ቅልብጭ ያለች ግጥም! የፍቅር ፍላጻ ልቧን ወግቶ ህመሙ በሚያስጨንቃት ጊዜ ነው እንዲህ ብላ የምታዜመው ተሚማ! ያቺ ውብ ቄጤማ! የአባጅፋር ልጅ የጅማ!!
*****
ብራቮ! ብራቮ! ተሚማ ሙገሳችንና መወድሳችን ከልብ የፈለቀ መሆኑ ስለገባት በጅማ ምድር ልታንሸራሽረን የገባችውን ቃል በድጋሚ አድሳለች። በመሆኑም ጅማን ልናስሳት ነው። በአሰሳችን ድብርት ቢገጥመን ተሚማ በጣፋጭ አንደበቷ “Hin mukaayinaa” እያለች ድብርቱን ታባርረዋለች (Hin mukaayinaa ብዬ ስጽፍ ከልቤ ሳቅኩኝ….ቂቂቂቂቂቂ… ። ቢሆንም በጣም ደስ እያለኝ ነው የምስቀው። እንደ ሐላዋ በሚጣፍጥ አባባል ድብርትን ማባረር ይሏል ይሄ ነው… Hin mukaayinaa!)።

“Hin mukaayinaa” ምን ዐይነት ትርጉም እንዳለው አውቃችኋልን?…. “እንጨት አትሁኑ” ማለት እኮ ነው። ከሩቅ ሀገር ሊገበኘን የመጣ ሰው እንግድነት እንዳይሰማው ለማድረግ ከፈለግን “አትቦዝን” እንለዋን አይደል?… አዎን! በፈረንጅኛውም “Just feel at home” ማለት ይቻላል። የጅማዋ ተሚማ ግን “Hin mukaayin” ማለትም “እንጨት አትሁን” ነው የምትለው። ተሚማ የምትጠቀምበት Hin mukaayinaa ውስጠ ወይራ ፍቺን ያዘለ ሐረግ ነው። ማዕናውም እንዲህ ሊሆን ይችላል።

እንግድነት የሚሰማው ሰው ዝምታ ያበዛል። ከሰዎች መሃል የወጣ ይመስለዋል። ይህም በመንገድ ላይ ለብቻው ከቆመ ዛፍ ወይንም የኤሌክትሪክ ምሰሶ ጋር ያመሳስለዋል። እርሱን የተጫጫነው ስሜትም በኛ ላይ የድብርት መአት ሊጠራብን ይችላል። እንግዲህ ሰውዬው እንግድነት ተሰምቶት እንደ እንጨት ድርቅ ብሎ ድብርት እንዳይጠራብን ለማድረግ በሚል ነው ተሚማ “Hin mukaayin” የምትለው። ደስ ሲል!!
“Hin mukaayinaa” እንዳለችው ተሚማ እኛም “ሂንሙካይና ጋ ማሎ” እንላችኋለን!!
*****

አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 23/2007
በሀረር ከተማ ተጻፈ።

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...