Tidarfelagi.com

“ከገዳይ ጋር ፍቅር”

አይጥ የድመቱ ነገር ግራ ገብቷታል። በተደጋጋሚ ፍቅሯን ልታሳየው ብትሞክርም ሊገባው አልቻለም። ከጉድጓዷ ስትወጣ አምራ እና ተኳኩላ ትወጣች። ድመቱ እንደ ሁል ጊዜ ከጉድጓዷ ፊት ለፊት ሆኖ ታገኘዋለች። አማላይ እንቅስቃሴ ልታሳየው ትሞክራለች። በፍቅር ዓይን ታየዋለች። እሱ ፍንክች የለም። እንዲህ መውደዷን ልታሳየው እየሞከረችም፣ ሮጦ ይመጣባታል- ሊበላት! እሷ በልቧ ስትፈልገው እሱ ለሆዱ ነው የሚፈልጋት። ቱርርር ብላ ወደ ጉድጓዷ ትገባለች። ፍጥነቱን ስለምታውቅ ከጉድጓዷ ብዙ አትርቅም። ውስጥ ገብታ ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች። ምን ዓይነት እድል ከድመት ፍቅር እንደጣላት ታማርራለች። ብቸነቷ አንጀቷ ድረስ ዘልቆ ይሰማታል። በዚሁ ድመት ተበልተው ያለቁት ዘመዶቿ ይታወሳቷል።አቤት ዘመዷቿ ይሄንን ቢያውቁ እንዴት ያዝኑባት!! ምን ቀን ነው የወደድኩት እያለች እድሏን ትረግማለች። ቢሆንም፣ ፍቅር ከሁሉ በላይ ነው እያለች ትፅናናለች።

ከመች ጀምራ እንደሆነ አትወቅ እንጂ፣ድመቱን በጣም ወዳዋለች። በተለይ ወንዳወንድነቱ፣ የማይፈታ ፊቱ፣ ቅልጥፍና እና ፍጥነቱን…. ምን ያደርጋል እሱ ግን ሊረዳላት አልቻለም።
***********
ድመትም በበኩሉ የአይጧ ሁኔታ ግራ አጋብቶታል። የሌሎች ዓይጦችን ባህሪ ሊያገኝባት አልቻለም። ሞንዳላ ሰውነቷ ሆዱን በአምሮት ያላውሰዋል። ነገረ ስራዋ ግን የአዳኝ እና የታዳኝ አልሆንበት ብሏል። ወዳጅነት የፈለገች መስሎታል።ምን አልባት ለዓላማ ሁሌ መሮጥ አያስፈልግ ይሆናል። አቋራጭ መንገዶች አይጠፉም። ባናግራትስ ሲል አሰበ። ወሰነ፣ አዎ አናግራታለሁ!!

…. አይጥ እንደተለመደው ተኳኩላ ወጣች። ዛሬ ደግሞ በጣም አምሮባታል ሲል አሰበ ድመት። እንዳሰበውም አስተያየቷ የፍቅር ነው። እንደ ሌላው ጊዜ ሊይዛት አልበረረም። ትክ ብሎ አያት። ደንገጥ ያለች መሰለው። መናገር እንዳለበት አመነ፤

“እኔ የምልሽ አይጥ…”
አይጥ በድንጋጤ ልቧ ቀጥ ልትል!! ተደነጋገረች። “ ምን አልከኝ ድመት?…. አይጥኛ ትችላለህ እንዴ?!”
ድመት ፈገግ ብሎ፣ “ አዎ! በፊት አባቴ ይጠቅምሃል ብሎ አስተምሮኝ ነበር። ይሄው ከአንቺ ጋር ለማውራት ጠቀመኝ አይደል?”
በውጧ አምላኳን አመሰገነች። “ እሱስ አዎ! እኔም ትንሽ ድመትኛ እሞክራለሁ። ምን ልትለኝ ነበር ግን?” ጎጉታለች።
“ ሁሌ ለምን እንደዛ እንደምታይኝ ግራ ይገባኛል። ምን አልባት የኔ አይነት ተመሳሳይ ስሜት ይኖርሽ ይሆን ወይ ብዬ ነው”
ምንድነው ያንተ ስሜት?…” የልብ ምቷ ከጥያቄዋ በልጦ እንዳይሰማባት ሰጋች። ድመት ለአፍታ ዝም አለ። እንደማመንታት እያለ፤
“ በጣም እወድሻለሁ!” አለ። አይጥ የሰማችው ዱብ እዳ ሆነባት። በደስታ ዘለለች። ፂፅ ፂፅ ፂፅ…. እያለች ፉጨታን አስነካችው። ደስታዋን ስጥጨርስ አንድ የከነከናትን ጥያቄ ጠየቀችው፤
“ታዲያ ከወደድከኝ ለምን ነበር የምታሳድደኝ”
“ ዋናው ምክንያት የኔ አይነት ስሜት ይኖርሻል ብዬ አለማመኔ ነው።ይሄን ስሜት ለማጥፋት አንቺን ማጥፋት አለብኝ ብዬ አመንኩ። ለዛ ነበር ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ የማድንሽ። በዛ ለይ ደግሞ ዘመዶችሽን ሁሉ ጨርሼ እንዴት ትወጅኛለሽ ብዬ ላስብ?”
“እሱን እንርሳው። ምንም ነገር በፍቅር ፊት ትንሽ ነው። ይልቅ…..ታገባኛለህ?”
“ካገባሽኝ እማ በምን እድሌ!”… አይጥ ከደስታዋ ብዛት ሮጣ ተጠመጠመችበት። አቅፎ ሳማት።
“ አሁኑኑ እንድንጋባ ነው የምፈልገው… ግን ዘመዶቻችን ማወቅ አለባቸው። እኔ የሩቅ ዘመዶቼን ካሉበት ሄጄ እጠራቸዋለሁ። አንተም ሌሎች ድመቶችን ጥራ! ፍቅራችንን ሁሉም ይወቁት…”
ድመት እንደ ቆዘመ፤ “በጣም ይቅርታ የኔ፣ ማንም ባያውቀው ደስ ይለኛል። ድመቶች ይህንን እንዳወቁ ወዲያ ከድመቶች ማህበር ያገሉኛል። ለፍቅርሽ ስል መገለሌ ምንም አልነበረም። ግን አንቺን የገባሽበት ገብተው ያጠፉብኛል። ያ እንዲሆን ደግሞ አልፈልግም። ጋብቻችንን ግን አሁኑኑ ብንፈፅም ደስ ይለኛል።”
አይጥ ተስማማች። ማንም ወደማያያቸው ጭር ያለቦታ ሄዱ። አይጥ ተንጠራርታ ከሳመችው በኋላ፤
“ይሄ እንግዲህ የሚስትነቴ ማህተም ነው። በቀሪ ዘመኔ መልካም ሚስት ልሆንህ ቃል እገባለሁ። አሁን ደግሞ፣ እቅፍ አድርገኝ ወሲብ እንድናደርግ እፈልጋለሁ” ብላ ለወሲብ የሚጋብዝ ልፊያ ጀመረች። ድመት ልፊያውን ወደደው። ሰዓቱ አሁን ነው ሲል አሰበ። በልፊያው መሃል በጥፍሩ ቆንጠጥ አድርጎ ያዛት። “ኸረ አሳመምከኝ” አለች አይጥ። አይጥ አያያዙን ጠበቅ አድርጎ፤

“ ትወጂኝ ነበር አይደል? ያው ለአጭር ጊዜም ቢሆን እሱን እንድታገኚ አደረኩ። ልታገቢኝ ትፈልጊ ነበር እንድታገቢኝ ፈቀድኩ። እስካሁን ግን የኔን ፍላጎት አላሟሽልኝም። …ከዘመዶችሽ ተለይተሽ አስቸገርሽኝ። ምንም ያህል ብለፋ ልይዝሽ አልቻልኩም። ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ፣ እልህ ያዘኝ። የፍቅር አተያይሽ መንገዴን መቀየር እንዳለብኝ ነገረኝ። መንገዴን ቀየርኩ። እናም ይሄው እጄ ገባሽ!” ከት ብሎ ሳቀ። አይጥ በላብ ተዋጠች።እየተርበተበተች፣
“ ያ ሁላ መውደድህ የውሸት ነበር? ይህን ሁሉ ያደረከው ልትበላኝ ነው??…”
“ አይ አቅፌሽ ልዞር ነው…. እስቲ እንደሁ ጭድ እሳት ላይ ዘሎ ይወጣል? በይ ደህና ሁኚ…” አንገቷን ሲጥ አድርጎ ያዛት። አይጥ በጣር እየተፈራገጠች በድመትኛ ለመነችው…
“ እባክህ… ቢያንስ ትንሽ ደስታዬን…..” አልሰማትም። ሰለቀጣት። አጣጥሟት እንደጨረሰ ወደ ቤቱ መንገድ ጀመረ። በመንገዱ ላይ ግን የመጨረሻ የልመና ድምፅዋ እየተመላለሰ አስቸገረው። በድመትኛ እንደተማፀነችው ትዝ አለው። ከበላት በኋላ የጠበቀን ያህል እርካታ አለማግኘቱ ተሰማው። ለከነረቱ ቅፅበታዊ ስሜት የምትወደውን አይጥ እንደገደለ ተሰማው። ፍቅርን ይዞት ያውቀዋል። እንዴት እንደጨከነ ሊገባው አልቻለም። ጀብዱ በመሰለው ድርጊቱ ውስጥ እርካታ አጣ። ፀፀት ያኝከው ጀመር።ሆዱ ተረባበሸ። ወደ ላይ ይታገለው ጀመር። አስመለሰው። አይጧ ብዙ ቦታ እንደተቆራረጠች ከሆዱ ወጣች። በልቷት እንኳ ሆዱ ለማትረጋው፣ እንዲህ በማድረጉ ክፉኛ አዘነ።የዋህነቷ ተሰማው። ሲምኑት የሚከዳ ከሃዲነቱ ዘልቆ ተሰማው። የእንባ ዘለላዎች ከዐይኑ ተንከባለው ወረዱ። በትምክህት ቀና ብሎ የነበረው አንገቱ ደፍቶ ወደ ቤቱ ማዝገም ጀመረ። በውስጡ ለራሱ እንዲህ አለ፤
“በዓለም ላይ በፍቅር የቀረበን አቅመ ደካማ ገድሎ እንደ መፎከር ትልቅ ወንጀል የለም!!”

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

2 Comments

 • ዳንኤል አዋጁ commented on February 19, 2016 Reply

  በጣም ደስ የሚል አጭር ታሪክ።
  “አይጥ ሞቶን ስትሻ ስታበዛ ሩጫ
  ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ
  ሲባል የነበረው እስከነ ተረቱ
  ባንች ላይ ደረሰ በክልፍልፊቱ”

 • ዮናስ ታደለ commented on February 5, 2020 Reply

  በጣም አስተማሪ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...