Tidarfelagi.com

ከእንቅልፍ መልስ…

[ዳንሱን ከዳንሰኛው መነጠል ይቻላልን?]
___
ስለ ማንነት ሲነሳ በመስታወት ውስጥ ‘ፊቱን’ እያየ የሚመሰጥ ሰው ነው በዓይነ ሕሊናዬ የሚታየኝ… የናርሲስ ቢጤ … ናርሲስ በግሪክ ሚቲዮሎጂ ገጾች በውሃ ውስጥ የሚያየውን ምስል ለማምለክ ጥቂት የቀረው ሰው ሆኖ ተስሏል… በማንነት ጉዳይ ሁላችንም ናርሲስት ነን… ከአማናዊው ‘እኛነት’ ይልቅ ጽላሎታዊው ነጸብራቅ ይመስጠናል…
___
መስታወት ውስጥ የምታየው ገጽታ የራስ ምስል [ነጸብራቅ] እንጂ እውነት አይደለም… ነጸብራቅ [Projection] በሰበበ ሁኔታ ላይ የሚመሰረት አቋም ነው ያለው… ያም ማለት መንስኤው እንደሚሆነው ብቻ ነው የሚሆነው… የተነጠለ [Independent] አነዋወር የለውም… Effect ነው እንጂ Cause አይደለም… ቁሳዊ ኑረት ከሌለ ገፃዊ ነጸብራቅ የለም ማለት ነው…
___
ማንነት ግን እንዲህ አይደለም… መንጠልጠልያ የለውም… ራሱን የሚገልጽበት መንገድ እንጂ ራሱን የሚያኖርበት ነገር አይፈልግም… ማን መሆንህ የነገሮች ሁሉ መቆሚያ መሠረት ነው… ማንነትህን ማወቅህ ውስጥ ደግሞ የየትኛውም ጥያቄ መልስ አለ… ማን መሆንህ ካልገባህ ግን በጥላህ ውስጥ ትጠፋለህ… በድንግዝግዝ ትቆያለህ…
___
“Know that one thing by knowing which everything else is known” ~ Vedanta
___
‘የማንነት’ ትርጉም በሙያ መስክ ፈለግ – በማሕበረሰባዊ ስምምነት ጠገግ – በቤተ ሐይማኖት ሕግና በፖለቲካ አስተሳሰብ ጥግ ውስጥ የየራሱን መልክና ቅርጽ እየያዘ ስለሚተነተን ይሆነኝ ብለው የልዩነት ዘፈናቸውን ለሚያደምቁበት ወገኖች አዝማች መሆኑ አልቀረም…
___
ከ Race (ethnicity)፣ Religion፣ Gender (sexual orientation)፣ Ability፣ Age፣ Education እና Socio-Economic status የሚዘል ‘ማንነት’ ማየት ካልጀመርክ አንድነት አይገባህም… እውነተኛውን ‘እኔነት’ ከተነገረህ ‘ማንነት’ መለየት ካልጀመርክ ከራስ ባዳነት አትፋታም…
___
በማንነት ፍለጋ ውስጥ ‘ነኝ’ የሚሉትን እየነቀሱ ነኝ የማይሉትን እያሳነሱ መጓዝ ከአማናዊው እኔ የሚያደርስ ስልት እንደሆነ ይታመናል… እንቀጥል…
___
፩ – አካል እንደ ማንነት
~
ለምሳሌ ‘የኔ እጅ’ ትላለህ እንጂ ‘እጄ እኔን ነው’ አትልም… ‘ዓይኑ የእኔ ነው’ ትላለህ እንጂ ‘እኔ ዓይኔን ነኝ’ አትልም… እግርህን፣ ልብህን፣ ጸጉርህን፣ የሰውነት ክፍልህን እያንዳንዱን እየቆረጥክ ብትቀንሰው ‘ያንተ የሆነው’ ተቀነሰ እንጂ ‘አንተ ራስህ’ ግን አልጠፋህም… ታዲያ ‘የኔ’ የሚለው ‘እኔህ’ የት ነው ያለው?
___
ነገሩን መረር እናድርገው… ልብህን ብታወጣት ‘እሞታለሁ – ከሞትኩ የለሁም’ ትል ይሆናል… አርቴፊሻል ልብ ቢገጠምልህ ግን ‘ሞት’ ይሉትን ታፔላ መዝለልህ አይቀርም… እስኪ አንገትህን እንቁረጠው…. ኦው… ይሄማ ከባድ ነው… እስትንፋስህ ትሰናበታለች… ታዲያ ‘እኔህ’ ያለው ጭንቅላትህ ውስጥ ይሆን እንዴ?… ግን የቱ ጋ?…
___
ነገሩን በደንብ ካሰብከው እኔ ባዩ ማንነት ‘ተጨባጭ’ አይደለም… ከአካል መዋቅርህ ጋር ስታያይዘው ብትቆይም በመጨረሻ የሚገባህ ‘የእኔ’ የምትለው አካል እንጂ እኔህን የሆነ አካል እንደሌለ ነው… እኔታ ከአካላዊ ኑረት ሳይነጠል በሕላዌው ግን ሳይንጠለጠል የሚኖር ነው…
___
የአካል ጠጣር መምሰል ‘በማየት ማመን ነው’ ሲያጸናን የእይታ ውስንነት ደግሞ ከሚታየው ጀርባ ካለው እውነት አፋትቶናል… እንደ እውነቱ ከሆነ አካላችን እንደምናስበው Solid አይደለም… በአንድ ፊዚስት ዓይን ስንታይ በተንተን ብለው ከሚታዩ Electrical discharges ውጭ ያለው ሰፊ ቦታ ባዶ /Void/ ነው…
___
ሰውነታችን የተሰራው ከአተም ነው… አተም ደግሞ ለአዕምሮ በማይመጠን ፍጥነት እባዶው ላይ በሚሾሩ ፓርቲክሎች [leptons, quarks, እና mesons] የተገነባ ነው… እኒህ ፓርቲክሎች ጠጣር አይደሉም… ይልቁንም 99.99% ይዞታቸው ባዶ ነው… ችግሩ የስሜት ሕዋሶቻችን ይዋሻሉ… ‘የሌለ’ እንዳለ እንድናምን ያደርጉናል… በዚህ ምክንያት እንኳን ‘ሞተህ’ እያለህም ‘የለም’ በሚባል ሥጋ ላይ ማንነትህን ገንብተሃል ማለት ነው…
___
እንዲህ ዓይነቱ ማቀናነስ ወደ ስምህ፣ ስራህ፣ ዝናህ፣ ክህሎትህ… ወዘተ ሲመጣ ተመሳሳይ ውጤት ነው ያለው… አንተ ይህን ሁሉ አይደለህም… ያለነዚህ ሁሉ ‘እኔ’ አለና… የድርጊት ተመልካች – የኑረት ታዛቢ ሆኖ… ስለዚህ አካላዊ መገለጥ ውስጥ የሚታዩት የቆዳ ቀለም፣ ጾታ፣ አቅምና ዕድሜ ማንነት አይደሉም ማለት ነው…
___
ማወራረጃ…
~
“Reality is merely an illusion, albeit a very persistent one.” ~ Albert Einstein
___
፪ – ሐይማኖት እንደ ማንነት
___
‘ክርስቲያን ነኝ’ ከሚለው ‘አስተሳሰብህ’ ወይም ‘ትውስታህ’ ውጭ ክርስቲያን የሆነው ምንህ ነው?… በአንዳች ተዓምር አይሁዳዊነትህን ብትዘነጋው ‘አይሁዳዊ ነኝ’ የምትለው እንዴት ነው?… እስልምናህን ‘ትተህ’ ፕሮቴስታንት ‘ብትሆን’ ምንህ ነው ፕሮቴስታንት የሚሆነው?… ምንህም… Its all about thought!!
___
ሐይማኖት ‘ልክና ስህተት’ የሚሰፈርበት ቁና ሆኗል… ቀድሞ አብርሆት በጎበኛቸው ሰዎች የደረሰ አንድ ትምህርት ነበር… ትምህርቱ ሁሉን ያንጽ ሁሉን ያነቃ ዘንድ ቢነገርም የሆኑ ወገኖች ‘የእኛ’ ብለው ስለለዩት ብቻ ‘ሌሎች’ ለትምህርቱ እውነት ባዕዳን ሆነዋል… እነዚያም ‘የእኛ ብቻ’ የሚሉትን ይቆርሱና ከኑረት አሃዱ እስከ ሰማይ መንገዱ ድረስ ትንታኔና ዝርዝር አበጅተው ‘እኛ ነን ልክ’ ‘እናንተ ተሳስታችኋል’ ውዝግብ ይገነባሉ… መምህራኑ ዛሬ ‘ተመልሰው ቢመጡ’ በስማቸው እልፍ አጥር ተበጅቶ ምድሪቱ የቁርቋሶ ሜዳ መሆኗን ቢያዩ የሚገርማቸው ይመስለኛል… በቃል ልዩነት ካልሆነ በቀር “በእናንተ ሊደረግ የማትፈልጉትን በሌላው ላይ አታድርጉ” ከሚል መልዕክት ውጭ አልተውምና…
___
ይህን ዘላለማዊ እውነት የኑረትህ አካል ለማድረግ ግንብ ማበጀት አይጠበቅብህም… ለሺህ ዓመታት በዘለቀ ‘የልክ ነህ አይደለህም’ አዙሪት ውስጥ መጦዝ አይጠበቅብህም… የሚመችህን ተቀብለህ የማይመስልህን መተው እየቻልክ ከሂንዱ አጥርህ ወደ ቡዲስቱ በር ጦር መስበቅ አይጠበቅብህም… አንዱን ኢየሱስ ከሺህ ምንተሺህ ጎራ ዶለህ አንድነትን ማምከን አይጠበቅብህም… ‘ማንነቴ – ምልክቴ – ሕልውናዬ’ እያልክ ሌላኛውን ማጥቃት አይጠበቅብህም… ቁምነገሩ ምን መሰለህ… ያንተ ሐይማኖት እንጂ ‘አንተን’ የሆነ ሐይማኖት የለም… መንፈስ ሐይማኖት የለውምና…
___
ማወራረጃ…
~
“You are not a human being in search of a spiritual experience. You are a spiritual being immersed in a human experience.” ~ Pierre Teilhard de Chardin [French philosopher] ___
፫ – ብሔር እንደ ማንነት
___
የሰውን ልጅ እጅግ ከሚያሳንሱ ነገሮች ዋነኛው የብሔር ‘ማንነት’ ይመስለኛል… ብሔርተኝነት ከሁዳድ ጋርዮሽ የመዳፍ ቁርስራሽ የመምረጥ ሂደት ነው… እስካሁን ከምናውቀውም በላይ ሌሎች ዩኒቨርሶች [Multi verse] እንዳሉ የሚያትተውን የ Parallel universe ቲዎሪ ሳነብ በብሔር መንደርተኝነት ሰበብ ልክና ገደብ ከሌለው ሕዋ አንፃር የድቃቂ አቧራን ያህል ዓይን የማትቆረቁረውን ምድርን ወደ ሌሎች ብናኞች የመከፋፈል ክፋታችን ጎልቶ ይሰማኛል…
___
በእኔ እምነት አማርኛን የሚችል እንጂ ‘አማራ ማንነት’ ያለው ሰው የለም… ጉራጊኛ የሚችል እንጂ ‘ጉራጌ’ የሆነ ሰው የለም… ሌላውም ሁሉ እንዲሁ ነው…
___
ኦሮሞ – ትግሬ ወይም ወላይታ የሆነው ምንህ ነው?… እጅህ.. እግርህ… ደምህ… ዲኤንኤህ… የብሔር ማንነትህን የያዝከው በምንህ ነው?… በሃሳብ [thought] ወይም ትውስታህ [memory] ውስጥ ካልሆነ በቀር… ኢትዮጵያዊነት እሳቤ ነው… አሜሪካዊነት thought ነው… ብሔርተኝነትም እንዲሁ… ‘እንዲህ ነኝ’ ስላልክ ‘እንዲያ’ አትሆንም… እንዲያነትህ ከአንተ እሳቤና ትውስታ ውጭ ‘ሕይወት’ የለውም… እስኪ አስበው… thought, memory እና perception የሚባሉ ነገሮችህ በአንዳች ተዓምር ቢነጠቁ ራስህን የምትገልጸው እንዴት ነው?… እንደምንም!!… ጥልቅ ዝምታ ብቻ ነው ሚተርፍህ… Silence!!
___
እዚህ ተወልደህ ቻይና ውስጥ ብታድግ ቋንቋህ ማንደሪን ይሆን ነበር… ስለሆነም ቋንቋ የተገኘህበት ቦታ ማሳያ አልያም ተጋልጦ [exposure] የቸረህ ሃብት እንጂ ማንነት ሊሆን አይችልም… ቋንቋ እውቀት ነው – አለቀ!!… አስር ቋንቋ ብትችል አስር ‘ማንነት’ ሊኖርህ ነው?… ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡት የባሕል እሳቤዎችና የአኗኗር ዘይቤም ለተገኘህበት ቦታ Social conditioning የሚገዙ ናቸው… አንተ ግን እልቅናህን በውዳቂ ስምምነት ውስጥ ማጎርህ ሳያንስ ‘ነኝ’ ላልከው አድልተህ ‘ሌላውን’ ጠላት አድርገህ ትፈርጃለህ…
___
ማንነት መገኛህን ተከትሎ አይለዋወጥም… አስተሳሰብህን ተከትሎ አያንስም… ግምትህን ተመስርቶ አይመዘንም… እጅግ ሰፊ ነው… እጅግ ጥልቅ… እኔና አንተ ከምድሪቱ እንገዝፋለን… በአጭር ቁመት – በጠባብ ደረት ከተመተረው ፈራሽ ሥጋ በላይ ነን… ከጊዜና ቦታ [Space and time] ስፍርም ውጭ ነን… ከማንነትህ ርቀት ጋር ሲተያይ ሰውነትም አይመትርህ…
___
ማወራረጃ…
~
“Once you label me you negate me.” ~ Soren Kierkegaard
___
እነሆ ውብ መስመር…
___
“We are all visitors to this time, this place. We are just passing through. Our purpose here is to observe, to learn, to grow, to LOVE…and then we return home.” Aboriginal Proverb
___
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!
መልካም አሁን

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...