Tidarfelagi.com

ከአዳም ረታ ቃለ መጠይቅ

በድርሰቶችህ ውስጥ መልክዓ ምድራዊ ገለጻን የገጸባሕሪያት ልቦናዊ መልክ ማሳያ አድርገህ ስትጠቀም ይስተዋላል። የዚህ ምክኒያቱ የገለጻ ፍቅር ነው ወይንስ ከዚህ በፊት ያጠናኸው የጂኦግራፊ ትምህርት ተጽእኖ ነው?

ጂኦግራፊ መልክዓ ምድር ብቻ አይደለም። መዓት አይነት ጂኦግራፊ አለ፤ ስለዚህ እሱ አይመስለኝም።
ጂኦግራፊ ስትማር ስለ መልክዓ ምድር ውበት አትማርም። Aesthetics የለውም፤ ሳይንስ ነው። ትመዝናለህ፣ የአለትን ይዘት፣ የተራራን ከፍታ በጫማ (feet) ትለካለህ።
ድርሰቴ ውስጥ የተራራን ከፍታ በሜትር የጻፍኩበት ቦታ የለም። 🙂
ምናልባት ያደግኩበት አካባቢ ይሆናል። የከተማዋ መጨረሻ ነበር። መልክዓ ምድሩ በጣም የሚያምር ነበር። አሁን ቤት ተሰርቶበት መንገድ ወጥቶበት ጠፍቷል። እና ከዚያ መልክዓ ምድር ተምሬያለሁ። ስለዚህ የማደርገው ነገር፤ ያንን ያደግኩበትን መረጃ መጥራትና መረጃዎቹን ወደየድርሰቶቼ መበታተን ነው። ይሄ ከጂኦግራፊ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።››

ከነባሩ የስነ ጽሁፍ ልማድ የማፈንገጥ ነገር አንተ ላይ ይታያል። ይሄ ምክኒያታዊ ነው?

ከስራው ነው የምትነሳው። ከሕጎች አይደለም። ስራው ነው ሕጎችን የሚጠይቀው። ስርዓተ ደንቦቹ ልክ እንደሆኑና እንዳልሆኑ የሚፈትሸው። መጨነቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
እኔ ማሕሌትን ስጽፍ ስለ ሕግ አላውቅም። ፕሎት፣ ጭብጥ የእንግሊዘኞቹን (ሕጎች) ሁሉ አላውቃቸውም። የሰራሁት በስሜት ነው። ታሪከ እንዲህ መሆን አለበት በሚል ነው የተነሳሁት። እዚያ ውስጥ ሕግ ይዞ ላጥና ለሚል ሕግ ይዤ የተከተልኩባቸው ቦታዎች አሉ። እነዚያን ግን text book ወስጄ አላነበብኳቸውም። ከዚህ ስሜት በመነሳት ሌላም ትልቅ ስራ ሕግ ሳትከተል በመስራት ሕጉ የሚጠይቃቸውን አንዳንድ ነገሮች ልታሟላ ትችላለህ። ሕጉን የሚጻረሩ ነገሮችም ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ዋናው ነገር ድርሰቱ ሙሉ ነው ወይ? የሚያነበውን ሰው ያዝነናዋል ወይ? የሆነ ነገር ከዚያ ያገኛል ወይ? ያ ነው መፈተሻው።

ባንተ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረብህ ደራሲ ማነው? ከተጽዕኖ ውጪስ መሆን ይቻላል?

አዎ። ከተጽዕኖ ውጪ መሆን የሚቻል ይመስለኛል። ማን ተጽዕኖ አሳደረብኝ ብዬ ልነግርህ አልችልም። ቃላት ታውቃለህ። ቃላትን ከመዝገበ ቃላት ታገኛለህ። መዝገበ ቃላት ተጽዕኖ አደረገብኝ ማለት ግን አትችልም።
ሕይወት ውስጥ ስትኖር የምታያቸው ነገሮች አሉ። እና የራስህ ዓይን አለ፣ የራስህ ስሜት አለ፣ የራስህ ስድስት ሕዋሳት አሉ (ማሰብን ጨምሮ)። በነዚህ ሴራ (ሴራ ልበለው ወይንም ትብብር) ራስህን ከተጽዕኖ ልታወጣ ካልቻልክ ግለሰብ ላትሆን ትችላለህ። በርግጥ ንጹህ የሆነ ግለሰበ የለም። ግን በሆነ መልክ ልምድ የሚያሳይህ ነገር አለ። እናም ከዚያ ከልምድህ ነው የምትነሳው።
በርግጥ እዚህ ስትደርስ እያነበብክ ነው የመጣኸው። እያነበብክ ስትመጣ ከብዙ ደራሲያን ጋር እየታከክ ነው የምትሄደው። ሳታውቀው ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ የሚችል ሰው ሊኖር ይችላል። ተጽዕኖ ማን ሊያሳድርብኝ እነደሚችል ላውቅ እችላለሁ። አንድ ድርሰት አንብቤ ገና ከመጀመርያው የምወደውን አይነት ነገር ይጽፋል፣ ተጽዕኖ ያደርግብኛል ወይንም አያደርግብኝም ብዬ መወሰን እችላለሁ። ይሄ ነገር ራሴን የማግለል ዕድል ይሰጠኛል። ራሴን ማግለል ስልህ፤ በራሴ ዓይን ለማየት የመሞከር፣ በራሴ ልምድ ነገሮችን ለመተርጎም የመሞከር ማለት ነው። ስለዚህ ተጽዕ ያደረገብኝ ደራሲ የለም ማለት ነው የምችለው። ምክኒያቱም ራሴን በጥቼ ነው የምጽፈው። በጣም ራሴ ውስጥ ሆኜ ነው የምጽፈው።

(ስለዚህ አንተ ሳታውቀው ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ የሚችለው ደራሲ በሀያሲያን ዓይን ሊታይ ይችላል ማለት ነው?)

አንድ ሀያሲ ከተጽዕኖ ልትላቀቅ አትችልም የማለት መብት አለው። ድርሰቶቼን ተንትኖ፣ ነገሮችን አገነኛኝቶ ይሄ ሰው የዚህ ተጽዕኖ አለበት ማለት ይችላል። መተቸትም ይችላል። ተጽዕኖ አለብህ ሲል ግን ለምን ተጽዕኖ አሳደረበት.፣ እንዴት ነው ተጽዕኖ ያሳደረበት፣ የቱ ጋ ነው ተጽዕኖ ያሳደረበት…. እነዛን ሁሉ መተንተን አለበት።

ጎበዝ ደራሲ ትፈራለህ? 🙂

🙂 መፍራት ሳይሆን፤ አነበዋለሁ፣ እደሰትበታለሁ፣ ከዛ በኋላ ወደራሴ ዓለም ነው የምሄደው። ያገርህን ሁኔታ ለመግለጽ ከራስህ ልምድ በላይ ማን አለ?

ጥቃቅን ነገሮች ላይ ትኩረት ልታደርግ የቻልክበት ዐቢይ ምክኒያት ምንድን ነው?

ወደ አካባቢሀ የመምጣት ነገር መሰለኝ። ድርሰቶች ብዙ ጊዜ ከትልቅ ሀሳብ (Grand Ideas) ይነሳሉ። ስለ ፍቅር ስትጽፍ ፍቅርን አክብደህ የማምጣት፣ ስለ ጥላቻ ስትጽፍ ጥላቻን አክብደህ የማምጣት፣ እነዚህ ነገሮች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኛል። ልጅ እያለሁ የማነባቸው ጽሁፎች በሙሉ በዚህ አድርቀውኛል።
እናም ወደ ዕውነት መምጣት አለብህ። ዕውነት ደግሞ እነዛ (ጥቃቅን) ነገሮች ናቸው። ወደ ሕይወት ስትመጣ እነዛ ነገሮች ናቸው። ገበያ ውስጥ ስትገባ ያሉት እነዛ ነገሮች ናቸው። ትምሕርት ቤት ስትገባ ከሰው ውጪ ያሉት እስኪርቢቶ፣ ወረቀት… እነዚህ ትንንሽ ነገሮች ናቸው።
ሰለጠነ የምንለው ዓለም ወይንም ባሕላዊ መልክዓ ምድርህ ውስጥ እነዚህ ጥቃቅን ነገሮች ትልቅ ቦታ አላቸው።
እርሳስን ልትንቃት ትችላለህ። ሁለት ልጆች ግን ሊጣሉባት ይችላሉ። ሊደባደቡባት ሊደማሙባት ይችላሉ።
ለምሳሌ ኩሳንኩስ ውስጥ በጣም ትንንሽ ነገሮች ናቸው ያሉት።
ሻሽ አለ። አንድ ሰው ገበያ ሄዶ ሻሽ ገዛ ብለህ ልትናገር ትችላለህ። ወይንም እትዬ እንትና እና እትዬ እንትና ሻሻቸውን ሳያውቁት ተለዋውጠው ሻሼን ወሰድሽብኝ ተባባሉ ምናምን ብለህ የዚህ አይነት ሴራ ልትፈጥር ትችላለህ። ሻሽን ለብቻው ወስደህ (ድርሰት) ስትሰራ ግን ሲግኒፊካንስ መሰጠት ለሚገባቸው ግን ለሳትናቸው ነገሮች ሲግኒፊካንስ መስጠት ነው።
ጡትን ውሰድ፤ ወተት…… እዛ ውስጥ የሰው ልጅ አንድ መሰረታዊ እውነታን የሳተበት ነገር እንዳለ ለማሳየት የተሰራ ነው።
ወደራስ የመምጣት፤ ወደ ተጨባጩ ዓለም፣ ስትታከከው ወደምትውለው ነገር መምጣት ነው። ወደ አዕምሮ ውስጥ የመሄድ አይደለም። ድርሰት ውስጥ ቅንነት ምንድን ነው ብለህ አትፈላሰፍም። በኦብጀክትስ፣ በቲንግስ ታሳየዋለህ። እነዛ ውስጥ ደግሞ ባሕል ተገንብቷል።
ነገሮች ከራሳቸው ውጪ ሌላ ሰፊ ሲግኒፊካንስ እንደያዙም ስለምረዳ ነው።
አለንጋ መደብደቢያ ሊሆን ይችላል። እዛ ውስጥ ግን ለብዙ መቶ አመታት የተዋቀረ ባሕል አለ። ስለዚህ ለነዚህ ነገሮች ቦታ በመስጠት መልዕክቱ ጠንከር ባለ ሁኔታ ይተላለፋል።

አዳም ረታ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ የተወሰደ
2004 ዓ.ም

 

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

3 Comments

 • J09157925@GMAIL.COM'
  Yohannese Girma commented on October 27, 2016 Reply

  በጣም ይምራል በጣም አስተማሪ ታሪክ ያለክ ሰው ነክ ግን ሙሉ ግለ ታሪክህን ማግኘት አልቻልኩም በጣም አጫጭር ናቸው ምናልባት ሌላ ቦታ የተጻፈልክ ካለ እባክህ ብትነግረኝ አመሰግናለው

 • haliya.temam@yahoo.com'
  haliya commented on March 3, 2017 Reply

  Number one!!

 • ka2221 commented on September 28, 2018 Reply

  always…impressed with u….not just the writings…..
  i sometimes feel some of is your own history.

  I have read your books…..but i loved “yiwosdal menged……..”

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...