Tidarfelagi.com

ከባልሽ ሐብታሙን ሽማግሌ ከመረጥሽ በኋላ (ክፍል ሶስት)

አጭር ገመድ

ማነኝ ብለሽ ትሄጃለሽ? ስለዚህ የሚስቱን ለቅሶ አትሄጅም ። ቀብሯ ላይ አትገኚም። አቶ ይሄይስ የጠበቀው ቢሆንም ከባድ ሃዘን ላይ ስለሆነ ከሳምንት በላይ አይደውልልሽም።

የገባልሽን ቃል ሳያጓድል – ግን ደግሞ ምንም ሳይጨምር መንፈቅ ያልፋል።
የመንጃ ፈቃድ አውጥተሸ ኒሳን ጁክ መያዝ ጀምረሻል። መኪናው ግን በስምሽ አይደለም።
ተቆጥሮ ከሚሰጥሽ ዳጎስ ያለ የወር ተቆራጭሽ እና ስጦታዎችሽ ውጪ ባንክ በስምሽ የተቀመጠ ገንዘብ፣ መሬት ላይ በስምሽ የተገዛ ንብረት የለም።

አቶ ይሄይስ ሁሉን ሰጥቶሻል። በሌላ በኩል ደግሞ የሰጠሸን ሁሉ በራሱ ስም በማድረግ ሁሉን ነስቶሻል።
ከራስሽ ጋር ስታወሪ ይሄ ነገር እኮ የሚያበሽቅ ነገር አለው ትያለሽ።
ተምረሽ የለ? ዛሬ ቢደላሽም ነገ አንዳች ነገር ቢፈጥር ያለሽ ሁሉ ከመቅፅበት ሊወሰድ እንደሚችል፣ እርቃንሽን ልትቀሪ እንደምትችይ ስታስቢ አልፎ አልፎ ይቆረቁርሻል።

የኑሮሽ ግዚያዊነት ያሳስብሻል። የእያንዳንዷ ንብረትሽን የሌላ ሰውነት ያስጨንቅሻል።
አንዳንዴ አፓርትማሽ ውስጥ ወዲህ ወዲያ እያልሽ፣ ስለምትቀመጪበት ሶፋ፣ ስለምታዬው ቴሌቪዥን፣ ስለምትተኚበት አልጋ፣ ስለተሟላው ዘመናዊ ኩሽናሽ ስታስቢ፤ ከአቶ ይሄይስ ብትለያዩ አንዲት ብረት ድስትም ላይ፣ አንዲት ጭልፋም ላይ የኔ ናት ብለሽ ማዘዝ እንደማትችይ ሲሰማሽ ትረበሻለሽ። በድንገት የለመድሽው ምቾት በዚያው ፍጥነት ሊነጠቅ እንደሚችል ስትገነዘቢ ትባቢያለሽ።

ከአዲሱ ሲሳይሽ የሚቀራመቱት ጓደኞችሽ ከዚህ በፊት በወሬ ወሬ የሰሙትን ታሪክ እያነሱ ‹‹ነገ ስትጣሉ አሽቀንጥሮ እንዳይጥልሽ አግባኝ በይው›› ብለው ይመክሩሻል። ‹‹ሚስቱ ሞታ የለ…ነጻ ሰው አይደል? አግባኝ በይው›› እያሉ ይወተውቱሻል።

ያኔ ይህንን ኑሮ ቋሚ የማድረግ ብቸኛ ዋስትናሽ ጋብቻ መሆኑን ትረጂያለሽ።
ግን ደግሞ በዚህ ግንኙነት ውስጥ እንዲህ ያለ ጥያቄ- ያውም በዚህ ሰአት- ያውም ከእንደ ይሄይስ አይነቱ ‹‹ልምራሽ ባይ›› ወንድ ጋር ማንሳቱ ያለሽንም የሚያሳጣሽ፣ አውላላ ሜዳ ላይ የሚጥልሽ ይመስልሽና ትሰጊያለሽ።
ደስተኛ እና ምቹ ሕይወትሽ በእንዲህ ያለው ሰቀቀን መረበሽ ይጀምራል።
በጓደኞችሽ ‹‹ዝም ብለሽ ከፈዘዝሽለት በሌላ ይተካሽና ጉድ ይሰራሻል›› ምክር ሆድሽ መተራመስ ይቀጥላል። በየቀኑ መስታወት ፊት ስትቆሚ በወር በወር ያረጀሽ ይመስልሻል፡:፡
እርግጠኝነት ማጣትሽ፣ ምቾትሽ ዘላቂ መሆኑን አለማረጋገጥሽ ይከነክንሻል። አልፎ አልፎም- ደካማ ስትሆኚለት- ያ- ትሸሺው የነበረ የእጦት ግን የእርግጠኝነት ሕይወትሽን በስሱ ያስናፍቅሻል።
አለ አይደል…
ቁምሳጥኔ ትንሽ ነበረች- ግን የኔ ነበረች
አልጋዬ የማትረባ ነበረች- ግን የኔ ነበረች አይነት ሃሳብ ሽው- ውል ይልሻል።
‹‹ሁሉም አለኝ ግን ምንም የለኝም›› የማለት ሃሳብ ወጥሮ ይይዝሻል።

ብዙ ሳይቆይ ደፈር ትይና ‹‹ለምን አንጋባም?›› ብለሽ ትጠይቂዋለሽ። በዚያ ማስመሰል በማይችል ሁኔታው አይቶሽ ‹‹የምርሽን ነው?›› ይልሻል።
ፈራ ተባ እያልሽ ‹‹እህ…በዚህ ይቀለዳል እንዴ..?›› ትያለሽ።
ጊዜ ይለፍ እንጂ ያንቺና የአቶ ይሄይስ ግንኑነት ልክ ያኔ የተገናኛችሁ ቀን- ልክ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ አንሶላ የተጋፈፈፋችሁ እለት የነበረው አይነት ነው። አንቺ ፈሪ፣ እሱ ደፋር፣ አንቺ ተመሪ እሱ መሪ። የግንኙነታችሁ ሾፋሪ እሱ ነው።
ባሻው መንገድ ባሻው ፍጥነት ይነዳችኋል፥፥ ያንቺ ስራ ቀበቶሽን አድርገሽ የተሳፋሪ ወንበር ላይ መቀመጥ ነው ።
በማያወላውል ሁኔታ መልስ ይሰጥሻል።
‹‹ሚስቴ ከሞተች አመት እንኳን አልሞላት! ደግሞ ስንቴ ነው ዳግመኛ ጋብቻ እንደማልፈልግ የነገርኩሽ?…››
ወሽመጥ ይቆርጣል አይደል? ቅስምሽ መሰበር ነበረበት። ግን አይሰበርም።
በእርግጥ ንግግሩ ሲተረጎም ቦታሽን አታምታቺ ማለቱ መሆኑ ይገባሻል።
ግን አቶ ይሄይስ ልክ ነው። ሲጋገኝሽ በወሰነልሽ ሕይወት የተስማማሽው አንቺ አይደለሽም?
‹ስራ ትቻለሁ…ትምህርት አቋርጫለሁ…ምንም ንብረት በስሜ የለም…ነገ…ማለቴ ብንጣላ…ወይ ሌላ ሴት ጋር ብትሄድ ምን እሆናለሁ?›› ብለሽ መጠየቅ ነበረብሽ።
ግን አትጠይቂውም።
አቶ አይሄይስ ካንቺ ያማሩ፣ ካንቺ በእድሜ ያነሱ፣ ካንቺ ያነሰ ጥቅምን የሚቀበሉ ሌላ ብዙ ቆነጃጅት እንደሌሉት እርግጠኛ አይደለሽም።

አንዳንዴ የሴት ዲኦር ዲኦር እየሸተተ ይመጣል። አልፎ አልፎ በረንዳሽ ላይ ዝቅ ባለ ድምፅ ሴት ያባብላል።
ምናልባት ብዙ ለጊዜው የሚሰጡ አፓርትማዎች ይኖሩታል።
ምናልባት ብዙ ለሚፈልጋት የሚሰጣቸው በስሙ ያሉ መኪኖች ይኖሩታል። ….
ስለዚህ አትጠይቂውም።
ማርገዝን አስበሽ ነበር። ያቺ የማታረጅ ወንድን የማጥመጃ ዘዴን እንዴት ላታስቢያት ትችያለሽ? ግን ያላቀደውን የማይከውን፣ ያላሰበውን የማይፈፅም፣ የማይቆጣጠረውን የማይፈልግ ሰው ሰለሆነ እሳት መጫር መስሎሽ ትተሽዋል። በንዴት ቱግ፣ እፍ ብሎ እንደሚጠፋ እንደሚል ታውቂዋለሽ።
በዚያ ላይ ያንን ሕይወት- አግብቶ የመውለድን- ወልዶ የማሳደግን- አሳድጎ የመዳርን ሕይወትን ያለፈን ሰው ‹‹እንካ በአያትነት ዘመንህ አባት ሁን›› ብትይው ከንዴት ውጪ ምን ሊሰማው ይችላል?
የህልም ሕይወቱን የሚያጠለሽ ነገር ሆኖ ነው የሚሰማው። ያንቺም የምቾት አለም በቋጠርሽው ልጅ እንደሚደረመስ ታስቢያለሽ። ትተይዋለሽ።

ከቅምጥነት ወደ ሚስትነት እንደማታድጊ፣ መስዋአትነት ለከፈልሽለት የምቾት ህይወትሽ ቋሚ ሰርተፍኬት እንደማታገኚ ሲገባሽ በፊት እንደ ዋዛ የምታልፊያቸው ነገሮች ያበሳጩሻል።
ታዛዥ ባህሪሽ ሲበላሽ፣
‹‹እሺ›› ባይነትሽ ሲበርድ
አቶ ይሄይስ እግር ይቀንሳል።
የ‹‹ነገስ›› ጥያቄሽ ሲደጋገም፣
የ‹‹ምን እሆናለሁ›› ንዝንዝሽ ሳታውቂው ካፍሽ መውጣት ሲያበዛ አቶ ይሄይስ ተቆራጩ ላይ መዘናጋት፣ ስጦታው ላይ ጋብ ማለት ይጀምራል።
ይሄኔ ትደናገጫለሽ።
ይሄኔ ትበረግጊያለሽ።
የሚሰራውን የሚያውቅ ሰው ነውና መበርገግሽን ሲመለከት ተመልሶ ይመጣል። ነገር ሁሉ እንደነበረው ይሆናል። ተቆራጩ ይመለሳል፣ ስጦታው መጉረፉን ይቀጥላል።
በአጭር ገመድ እንደታሰርሽ ይገባሻል። ራቅ ብዬ ልሂድ ስትዩ የምትታነቂ መሆንሽ ይገለፅልሻል።
ያኔ ሰው የሚቀናበት ኑሮሽ በታዛዥነት እንደተመሰረተ ይታወስሽና ወደ ቀደመችው አይናፋርና ግድርድር፣ ጥያቄ የማትጠይቅና ያገኘችውን ተቀበላ ለዛሬ ብቻ የምትኖር ምስኪን ሴት ትሆኛለሽ።
ያኔ ትምህርቴን ባላቆምኩ- ስራዬን ባልተውኩ- እንደምንም ብዬ በራሴ በቆምኩ እያለች ውስጥሽ የምትንፈራፈረውን ሴት ታፍኚና ‹‹የዘልአለም ቅምጥ›› ለመሆን ትወስኚያለሽ።
መልሰሽ ደግሞ ሰላሳ ሲያልፈኝ ቢተወኝሽ በሚል ክፉ ሃሳብ ትረበሺያለሽ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...