Tidarfelagi.com

ከባልሽ ሐብታሙን ሽማግሌ ከመረጥሽ በኋላ (ክፍል ሁለት)

ያለ ተጨማሪ ጥቅማጥቅም ለተከታታይ ቀናት በግብዣ ያጣድፍሻል። በስጦታ ያንበሸብሽሻል።
ምንም ነገር ውድ ነው ከማይል ወንድ ጋር መሆን ምንኛ ያስደስታል? ያየሽውን ሁሉ በሁለትና በሶስት አባዝቶ፣ ያማረሽን ሁሉ በጅምላ ገዝቶ የሚሰጥ ወዳጅ እንዴት ያረካል? ብለሽ ታስቢያለሽ።
የቁርስ-ብረንች-ምሳ- እራት ግብዣዎቹ ያልለመድሻቸው አይነት ናቸው።
ሬስቶራንቶቹን ከዚህ በፊት በአይንም አታውቂያቸውም። ምግቦቹን አለመድሻቸውም። ስፓጌቲ በክሪም ሶስ የምስር ወጥን ያህል ባያስደስትሽም አቶ ይሄይስ ግን ሳትደርሺ ቀድሞ ያዝልሻል።
ትበይዋለሽ።

ኪውከምበር ሱፕ እና ኤግ ፕላንት ሳላድ አንጀትሽ ባይደርሱም ፍርፍር ያቆመ ሆድሽን ትሞይባቸዋለሽ።
የሚጋብዝሽ መጠጥ ስሙ ለጆሮሽ ባዳ ጣእሙ ደግሞ ለምላስሸ እንግዳ ነው።
ግን ስትጠጪው ሁሌም በሃሴት እንደተንሳፈፍሽ ነው።
ከአታካች እና ንትርክ የበዛበት የእጥረት እና የአለቀብኝ ሕይወትሽ ከመቅስፈት ተመንጥቀሽ ወጥተሻል። ከቁጠባ ተላቀሽ ወደ መትረፍረፍ አለም በቀናት ተቀላቅለሻል። ከታክሲ ሰልፍ ሕይወት ድንገት ተለያይተሸ በውድ መኪና፣ በሹፌር መንሸራሸርን ለምደሻል።

የካፒታል ሆቴል ስፓ ሰራተኞች ሳትደርሺ መምጣትሽን ያውቃሉ።
የኤክስክሉሲቭ ቡቲክ ጢባራም ሰራተኞች የጫማና ልብስ ልኬትሽን አበጥረው ያውቃሉ።
የፀጉርና የሜክአፕ ቅራቅንቦዎችሽ ማስቀመጪያ እስክታጪ በዝተውልሻል፡
ወዝና ደምግባትሽ ጢቅ ብሎ የሃያ አንድ አመት ጉብል መስለሻል፡
ለካ ገንዘብ ካገኘች ሁሏም ሴት ውብ፣ ሁሏም ሴት ወጣት ናት ብለሽ ታስቢያለሽ።
አቶ ይሄይስ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሰጠሸ። ክላስ ነው። ከፍ ነው ያደረገሽ። ከፍ።
ሜርሴዲስ መኪናው ውስጥ ሲያስገባሽና ቂጥሽ ምቾቱ ቂቤ ላይ የተቀመጥሽ የሚመስለው ወንበር ላይ ሲቀመጥ ክላስሽ ከፍ ማለቱ ይገባሻል።

ተሄዶ የማይጨረስ ሚስቱና ልጆቹ የማያውቁት – ሰፊ- ግን ሕይወት አልባ ቤቱ ገብተሸ ትልልቅ ሶፋዎቹ ውስጥ ስትቀመጪ ሳይሆን ስትሰምጪ ውድ ወይን ቀድቶ ያመጣልሻል።
ሽማግሌ ስለሆነ ሴት ሲይዝ በስርአት ነው። እንደ ወይዘሮ በክብር ይይዝሻል። ይንከባከብሻል። የድሮ ሮማንስ ደስ ይላል ብለሽ ታስቢያለሽ። የሚያቀብጥ ወንድ ደስ ያሰኛል ብለሽ ታስቢያለሽ።
ወይን ቀድቶ ሲያመጣልሽ…
የቤት ልጆች ስለማይጠጡ ትሽኮረመሚና ‹‹አረ እኔ ዝም ብዬ እኮ አልጠጣም…ለሆነ ኦኬዥን ካልሆነ›› ብለሽ ትግደረደሪያለሽ።

ሳቅ ብሎ ምንም ሳይል በወይን የተሞላውን ብርጭቆ ይገፋልሻል። ሳያስገድድሽ፣ ያለ ቃላት ጠጪ ይልሻል።
ትቀበያለሽ። ትጠጪያለሽ።
ይሄ ወይን እንደ ጉደር አንጀትሽን አያቃጥለውም። እንጆሬ እንጆሬ ይላል፣ ጉሮሮሽን እያሞቀ ሲወርድ ፍፁም መዝናናት ፍፁም መመቸት ይሰማሻል። ሁለመናሽ ይከፋፈታል።
ትንሽ ቆይቶ ይመጣና ሶፋው እጀታ ላይ ተቀምጦ ጣቶቹን በጠጉርሽ መሃል ሲያመላልስ በማፈር ታይዋለሽ። ተው አትይውም ግን ደግሞ ሌላ ቦታ እንዲነካሽም አታበረታቺውም።
የእሱ አይነት ወንድ ፣ የመረጣት ሴትን ቤቱ አምጥቶ ፣ እጆቹን በፈለገው ፍጥነት የትም የሰውነቷ ክፍል መውሰድ እንደሚችል ስለሚረዳ ማበረታታት ወይ መከልከልን አይፈልግም። ዝም ብሎ ማየት ነው። ዝም።
ከአቶ ይሄይስ ጋር አንሶላ የተጋራሽበት የመጀመሪያው እለት ከባልሽም ከድሮ ቦይፍሬንዶችሽም የተለየ ቀን እንደነበር ታውቂያለሽ።

በእቃ ብቻ የተሞላ ትልቅ ቤቱ ሳይሆን ቅንጡ ሆቴል ይወስድሻል።
በጣልያንኛ ሙዚቃ የታጀበ በደንብ ያልበሰለ የጥጃ ስጋ ስቴክ ምሳ ይጋብዝሻል።
የጥጃ ስጋ ከበሬ ስጋ ለጤና እንደሚሻል ያወራሻል።
ሚዲየም ሬር ከበሰለ ስጋ እንደሚመረጥ ይነግርሻል።
ደም ደም እያለሽ ስቴኩን ትበያለሽ።
‹‹ ግን በቀን?› እያልሽ ወይንሽን ትጠጪያለሽ።
አሁንም አሁንም የሚፈልገውንም የማይፈልገውንም ሳይጠይቅ በሚያመጡለት አርጋጅ አሸርጋጅ አስተናጋጆች ትወረራላችሁ። ምሳው ማብቂያ ላይ ኬክ መብላት ለቅርፅሽ እንደማይበጅ ይነግርሽና ፍሩት ሳላድ ያዝልሻል። በስምምነት ሙልጭ አድርገሽ ትበያለሽ።
ልትሄዱ ስትዘጋጁ እሱን ብቻ የሚያስተናግድ የሚመስለው የሆቴሉን ማናጀር ሲጠቅሰው ታያለሽ። ‹
‹ክፍላችን ዝግጁ ነው?›› እያለ እንደሆነ ይገባሻል። በተቀመጥሽበት ትነቃነቂና ቀኑ ምን ሊመስል እንደሚችል ታስቢያለሽ።
ዝግጁ ነሽ።
ክፍሉ ሽቶ ሽቶ ይላል።

አልጋው ላይ የተበተኑት የፅጌረዳ ቅጠሎች ስታዩ ምን አይነት አሰጣጥ ሊወድ እንደሚችል ማሰብ ትጀምሪያለሽ። አይናፋር ወይስ ነብር? ስግብግብ ወይስ ግድርድር?
እሱ እንዲመራሽ ለማድረግ ትወሰኚያለሽ።
ቢያንስ ሰላሳ አመት እንደሚበልጥሽ ታስቢና ‹‹አስተማሪ›› መሆን ሊፈልግ እንደሚችል ትገምቺያለሽ። የምትለብሽውን ልብስ ከመረጠልሽ፣ የምትመገቢውን ቀድሞ ካዘዘልሽ እንደዚያ ነው የሚሆነው።
የሚያስተምራት ትንሽዬ ልጅ ነው የሚፈልገው ብለሽ ትገምቻለሽ።
ከዚያ ደግሞ በሁለቱ መሃል ለመጫወት ታስቢያለሽ። አለ አይደል…መስገብገብ ያዋርድሻል። መቀዛቀዝ ደግሞ ቅር ያሰኘዋል።
ተጣጥቤ ልምጣ ትይና የቤትሽን ሳሎን ሁለት የሚያህለው ቅንጡ መታጠቢያ ቤት ትገቢያለሽ።
በመስታወት የተሞላ ክፍል ነው። አይኖችሽ ግን ራስሽን ከማየት ይሸሻሉ። በማታውቂው ምክንያት ራስሽን ማየት ይጠላሉ።
የምታደርጊውን አድርገሽ ስትወጪ አልጋ ውስጥ ገብቶ ታገኚዋለሽ። እርቃኑን መሆኑን ታውቂያለሽ። እድሜ ያላላማቸው የእጆቹ ጡንቻዎች ብቻ ይታዩሻል። ከነ ልብስሽ ሄደሽ አልጋው ውስጥ ትገቢያለሽ።
የሚፈልገውን ሁሉ ትሆኚለታለሽ። ቃል ሳያወጣ በመራሽ ሁሉ ትሄጂለታለሽ።
ደስ ይለዋል።
በጣም-በጣም ደስ ይለዋል።
ከአልጋ ወጥቶ እርቃኑን ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሲሄድ ግን ባታይው ደስ የሚልሽን ነገር ታይና ቅሬታ ይሰማሻል። ሲራመድ እንደ ጨርቅ የሚውለበለበው የረገበ የሽማግሌ ቂጡ ያስጠላሻል። ለስላሳው አንሶላ፣ ምቹው አልጋ ግን ያፅናናሻል።
ሲመለስ አልጋው ውስጥ ገብቶ ያቅፍሽና ወሬ ይጀመራል።
ከዚያ ስራሽን እንድታቆሚ ይነግርሻል።
ከበቂ በላይ ተቆራጭ እንደሚያደርግልሽ፣ ቀብራራ ቤት እንደሚያስቀምጥሽ ያበስርሻል። ባልሽን እንድትተዩ ያዝሻል።
ከወራት በኋላ በችግር የተነቃነቀው የኪራይ ጎጆሽ ‹‹ድሮም አይመጥንሽም ነበር›. ብለው በሚያጨበጭቡልሽ ወላጆችሽ ፣ ‹‹በሌለ አቅማችን አስተምረን መልሰን እንርዳ እንዴ›› ብለው ገንዘብ ቸገረኝ ስጡኝ ስትዬ ይማረሩብሽ በነበሩ ቤተሰቦችሽ ፈጣን እርዳታ ፈርሷል። በአዲሱ ሕይወትሽ በሚቀኑብሽ ጓደኞችሽ ይሁንታ ድምጥማጡ ጠፍቷል።
አቶ ይሄይስ ቃሉን ጠብቋል።

አጥፍተሸ ልትጨርሺው የሚቸግርሽ ተቆራጭሽን ከጭማሪ ጋር ሳያሳልስ መስጠት ቀጥሏል።
ያሻሽን ሁሉ ይገዛልሻል። ኢንቨስት ያደረግኩበት የወዳጄ ካምፓኒ ነው ባለው ገና ቀለም ተቀብቶ ያልደረቀ ውብ አፓርትማ ውስጥ ትልቁን መርጦ- እቃ አሟልቶ አሰቀምጦሻል። መንጃ ፈቃድ ቶሎ እንድታወጪ አሳስቦሻል።
ስራሽን ብቻ ሳይሆን የማታ ማታ የማስትሬት ፕሮግራም ትምህርትሽን አቋርጠሻል።
ቀኖችሽን በስፓ ቀጠሮ፣ በመኪና ልምምድ፣ በሾፒንግ ዙረትና ኔትፍሊክስ በማየት መሙላት ከጀመርሽ ሰነባብተሻል።
እና….ሕይወት በእንዲህ ሁኔታ አምራና ተውባ በመቀጠል ላይ ሳለች….
የይሄይስ ሚስት እንደተፈራው ትሞታለች።
(ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...