Tidarfelagi.com

ከሰይፍ ወደ ሰልፊ

አቶ ጮሌ የሚባል ጎልማሳ በምናባችን እንፍጠር። በኒውዝላንድ የሚኖር የፌስቡክ ተንታኝ ነው እንበል። የሙሉጊዜ ስራው ማጋነን ማሙዋረት ነው። የሰበር ዜና አራራ አለበት። ክፉ ዜና ካልሰማ ያዛጋዋል።

በትናንትናው እለት : ዶክተር አብይ ያመፁ ወታደሮችን አወያይቶ በብድግ ብድግ አጫውቶ : ግብር አብልቶ : ሹጉጣቸውን ሳይሆን ሞባይላቸውን ከማህደሩ እንዲመዙ ማድረግ መቻሉ ድንቅ የማረጋጋት ስራ ነው።

አቶ ጮሌ ግን ሁኔታው በዚህ መንገድ መደምደሙ አናዶታል። እሱ የጠበቀው ከቼከውና ከሰለቼው የግል ህይወቱ የሚገላግለው ልብ አንጠልጣይ የፖለቲካ ድራማ ነበር።

ፌስቡክን የሚመራው ያገር ፍቅር ሳይሆን የድራማ ፍቅር መሆኑን ማን ያውቃል? አቶ ጮሌ ከግርግሩ የሚጠብቀው ፌንታዚ ይህንን ሊመስል ይችላል።

———
አብይ እና ደመቀ በቤተመንግስት ሳሎን ውስጥ ታግተው : ወንበራቸው ላይ የፊጥኝ ታስረው አፋቸው ውስጥ የጨርቅ ኳስ ገብቶባቸዋል። ሁለት ታጣቂ አጋቾች የመፈንቅለ መንግስት ማካሄዳቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማርዳት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። ያለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁኔታውን በጭንቀት እየተከታተለ ነው።

ድንገት: ያብይ ጠባቂ እንደ ቻክኖሪስ ከየት መጣ ሳይባል ሳሎኑን በከስክሱ በርግዶ ገባ። በቀኝ እጁ ክላሽ በግራ እጁ የጉምዝ ቀስት ታጥቆ ነበር። በግንባሩ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ በወገቡ ላይ ያባገዳን ባንዲራ ጠምጥሟል። አይ አንበሳው!! አይ ሌንጫኮ!!

ገና እንደገባ: ዘልሎ አንድኛውን አጋች በርግጫ ደረቱ ላይ ሲመታው አጋቹ በቤተመንግስቱ መስኮት ወጥቶ : ጥቂት በረራ ካካሄደ በሁዋላ : ሸራተን ሆቴል በረንዳ ላይ ተፈጠፈጠ። ይህንን መአት የተመለከተው ሌላው አጋች ወጥቶ ፈረጠጠ። ያብይ አህመድ ቻክኖሪስ የሚሮጠውን ሰውየ በንቀት እያየ ሲጃራ አውጥቶ በዝግታ ለኮስ። ቀና ብሎ ባፉ ያለውን ጭስ ሲለቀው የኢትዮጵያን ካርታ አየር ላይ ሰራ። ከዚያ ሲጃራውን አንዴ ከመጠጠው በሁዋላ በቀስቱ ጫፍ ላይ ሰካው። ያብይ አጋች እየሮጠ አራት ኪሎ ደርሱዋል። ያብይ ቦዲጋርድ ቀስቱን ሲተኩስ አጋቹ ሰውየ እንደጡዋፍ ሲነድ አንድ ሆነ።


ጨዋታውን እናቆየውና አብይ ባመፀኛ ወታደሮች ላይ የማያዳግም ቅጣት ባለመውሰዱ የተናደዳችሁ ያቶ ጮሌ ቢጤ ጄብደኞች እስቲ ታሪክን ላስታውሳችሁ።

ቀዳማዊ ሀይለስላሴን ለማውረድ የሞከረው የታህሳስ ግርግር ያለቃ ነዋይን ቤተሰቦችን በስቅላት በመቅጣት ተጠናቀቀ። ይህ የመቀጣጫ ርምጃ ቀጣይ አመፆችን አላደረቃቸውም። ጄኔራል ታደሰ ብሩ በንጉሱ ላይ እጁን እንዳያነሳ አላስቆመውም። ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ የደርግ መኮንኖች ሀይለስላሴ ላይ እንዳያምፁ አልገታቸውም:

ችግረኛውን በመግደል ችግርን ማስወገድ አይቻልም።

አብይና ደመቀ ቀደምቶቻችሁ በሰይፍ ሞክረው ያቃታቸውን በሰልፊ ለመፍታት መሞከራችሁን አድንቂያለሁ። ነገ ደሞ ሌላ ቀን ነው።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...