Tidarfelagi.com

ከመኖሪያ ቤቱ ስር…(ክፍል፦30)

ጋደም እንዳለሁ ሸለብ አረገይ ወድያው ተሁለት አንዳቸው ለሽንት ቲወጡ ሰማሁ ብድግ አልሁና የክፍሌን በር በመጠኑ ከፍቼ ትመለከት የሽንት ቤቱ መብራት በርቷል።ትጠባባቅ ሻንቆ በውስጥ ሙታንታ ተሽንት ቤት ወጣ። እንዳየሁት በሁለት እግሩ የሚሄድ ትልቅ በሬ እንዢ ሰውም አልመስልሽ አለይ።

ወደ እትዬ መኝታ ክፍል ቲገባ ጆሮየን ቀስሬ ባደምጥም በሩን ቲዘጋም ቲቆልፍም አልተሰማይም።ግዜ ታላጠፋ እሻንጣዬ ውስጥ የደበቅሁትን ሽጉጥ እና ሴንጢ አወጣሁና እወገቤ ላይ መቀነት አጥብቄ በማሰር ሴንጢውን እጎኔ ላይ ሽጥሁና ሽጉጡን በሁለት እጄ አጥብቄ በመያዝ ተክፍሌ ወጣሁ።

ወደ እትዬ ክፍል ተመሄዴ በፊት ወደ ሳሎኑ መሀል ተጠጋሁና ወደ እትዬ ምኝታ ቤት ፊት ለፊት ትመለከት ሻንቆ በጀርባው ተዘርግቶ ያንኮራፋል። በዛ ግዙፍ ሰውነቱ ደብቋቸው ይሁን እላያቸው ላይ የሰፈረባቸው ግዜ እፍራሹ ውስጥ ሰጥመው እትዬ ግን አልታዩኝም።

እሄን ሰውዬ አጠገቡ ሄጄ ሽጉጡን ውሃ እንደያዘ ብርጭቆ አፉ ላይ ደቅኜ ታልጋትኩት በቀር ሽጉጥ እንኳን ልተኩስ በጄ ይዤ የማላውቅ ልዥ ታልጠጋ ብተኩስ ስቼው ጉድ እሆናለሁ አልሁና በቀስታ እስተበሩ ተጠጋሁ። እስታሁን ግን እትዬ አልታዩኝም ሴትዮዋን ሻንቆ ዋጣቸው እንዴ? እያልሁ በቀስታ ተጠጋሁ። አጠገቡ እንደደረስሁ እንደጨርቅ እስሩ ተጠቅልለው ተኝተዋል።ሽጉጡን እግንባሩ ላይ አረግሁና” የፈሪ ዱላ ” እንዲሉ የፍርሃቴን ቃታውን ደጋግሜ ትለሳብሁት አናቱ ፈርሶ አልጋው በደም ታጠበ። ሻንቆን በመግደሌ ተተፈጠረብኝ ድንጋጤ ታልወጣ እንደፈዘዝሁ እትዬ ተመቅፅበት ተተኙበት ተፈናጥረው ተነሱና “ተይ ሰንዬ ፣ ተይ የኔ ልዥ “እያሉ እንደ ፌንጣ ታንድ ጥግ ወደ አንዱ ጥግ ቲዘሉ ተድንጋጤዬ ተመልሼ ከንፈሬን ነክሼ እየተንቀጠቀጥሁ ሽጉጡን አልጋው ላይ እየዘለሉ ተቦታ ቦታ ወደ ሚሯሯጡት እትዬ ቀና ተማረጌ እንደበረኛ ተወርውረው አናቴ ላይ ተከመሩብይ። ተያይዘን ወደ በሩ ግድም እንደወደቅን የያዝሁት ሽጉጥ ተፈናጥሮ እሳሎኑ መሃል ታለው ሶፋ ስር ገባ። በፍጥነት ተላዬ ላይ ተነስተው ወደ ሽጉጡ ሊበሩ ቲሉ ተንፏቅቄ ሁለት እግራቸውን በሁለት እጄ አፈፍ አረኩ እና ተመሬት ቀላቀልኋቸው። ፈጥኜ እሆዳቸው ላይ ቂብ አልሁና ጠጉራቸውን ይዤ ሽቅብ እየጎተትሁ ደጋግሜ ተመሬት አላተምኋቸው። ተዛ ሴንጥዬን ተመቀነቴ ላይ መዝዤ አንገታቸው ላይ ልሽጠው ተማሰቤ እግራቸውን እፊቴ ላይ እንዴት ሆነው እንዳመጡት እንዣ አፍንጫዬን ብለው ወደ ዥርባዬ ዘረሩኝ። ተወደቅሁበት ታልነሳ ተምኔው ሽጉጡን ተሶፋው ስር እንዳነሱት ታይታወቀይ  “አንቺ ከሀዲ ! ፣ አንቺ ነብሰ ገዳይ !”እያሉ ቁልቁል ቲያነጣጥሩብኝ ልጅቱ ፈታው ነው መሰል ቴት መጣ ሳይባል በልሁ ተጀርባቸው መጥቶ አንገታቸውን ቆርጦ ጣለው። የደማቸው ፍንጥርጣሪ ፍቴን አለበሰይ። በልሁ ቁልቁል አየኝና እትዬን በመግደሉ ደስታው አሰከረው መሰል ሳሎኑ ውስጥ እየተሽከረከረ ፉከራውን ዠመረዋ….

ዘራፍ አካኪ ዘራፍ  ዘራፍ አካኪ ዘራፍ!

እኔ በልሁ የቆፍጣናው ልጅ

የጀግኖቹ ዘር ተሳት የምፋጅ

ለወዳጅ እንዢ ለጠላት አልበጅ!

ዘራፍ አካኪ ዘራፍ ዘራፍ አካኪ ዘራፍ

ግምባርክን ቲሊኝ ደረት የምሰጥ

ደረትክን ቲሉኝ ግንባር የምሰጥ

ክብሬን ቀብሬ የማልቀላውጥ

ከምለማመጥ ሞቴን የምመርጥ

ላመነበት ማች የወንዶቹ ፈርጥ!

ግቢልኝ ሰንዬ ብሎ ወኔዬን ቲቀሰቅሰው አልስችል እለኝና ገባሁለታ!

በለው በለው እና አሳጣው መድረሻ!

በለው በለው እና አሳጣው መድረሻ!

የሰውልክ አያውቅም ባለጌና ውሻ !  ዥግና ….ቀጠለ በልሁ!

ዘራፍ አካኪ ዘራፍ ዘራፍ አካኪ ዘራፍ

እኔ በልሁ የወርቆቹ ወርቅ

ሰውን አክባሪ ህጣን የማልንቅ

ለሀገሬ ማች የማብረቀርቅ

ፈርቼም ማላውቅ፥ ሸሽቼም ማላውቅ!

በፈሪ ድላ ተመሬት ልወድቅ አረ በሳቅ…

ዘራፍ አካኪ ዘራፍ….ዘራፍ አካኪ ዘራፍ….

ልጫንህ ታሉኝ የምተናነቅ

ደፍረው ተነኩኝ ሱሪ የማስወልቅ!

ልኩን የማሳይ ልኩን ለማያውቅ!

ዘራፍ አካኪ ዘራፍ….

በይህ መሀል ሞቷል ያልሁት ሻንቆ ተፈረሰ አናቱ ላይ የሚዥቅዥቀውን ደም ተፊቱ ላይ እየጠረገ ሽጉጡን ደግኖ ተበልሁ ዥርባ ቲመጣ በድንጋጤ በልሁ ተጀርባህ ብዬ በመጮህ ትነሳ መላ አካላቴ በላብ ተዘፍቃል በእውን የሆነ ያህል ሰውነቴ እየተንዘፈዘፈ ዙርያየን ትቃኝ እክፍሌ ውስጥ ብቻየን ነኝ ምነው ፈጣሪዬ….

ይቀጥላል

One Comment

  • Anonymous commented on April 19, 2020 Reply

    ያምራል P 31 ይቀጥል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...