Tidarfelagi.com

ከመኖሪያ ቤቱ ስር…(ክፍል፦14)

ብጋደምም  እንቅልፍ  ተየት ይመጣል ። ፈጣሪዬ እባክህ ክፉውን እርቅለት። እንደው በልሁ ምንም ታይሆን በፊት አንዴ   ባወራሁት እና  ምን  እንደሚለኝ  በሰማሁ። እሄን አርጊ ታለኝ ምንም ይሁን ምን ተማረግ አልመለስም !። ተዳንም ባንድ ላይ! ተሞትንም ባንድ ላይ! እዚህ ቤት ውስጥ  ምን አለው ታለኔ እኔስ ብሆን …የሀሳብ ተካፋዬ ፣ ቲከፋኝ ማልቀሻዬ፣ ትሳሳት መካሪዬ፣ ታላንተ ማን አለኝ። እንዴት ልሁንልህ ?የኔ ድሃ። በምን አቅሜ ተዚህ ጉድ ላውጣህ መላው ጠፋኝ እኮ በልሁ  እህህህህህ!።

እኔ ባዳይቱ እንዲህ የሆንኩኝ አምጣ የወለደችህ እናትህ ብታይህ ምን ይውጣት ይሆን? አይ እትዬ ነብሶት አይማር ቀጣዩ እቅዶ ምን ይሆን?

ሜዳውን ሲያጠቡት ፥  ገዘፈ ተራራው

ማን ይሆን ተረኛው  ፥  ለሞት የሚጠራው።

አለች እምዬ።

ምንም ታላረግልህ  ቀጣይ ተረኛይቱ  እኔው መሆኔ  ነው ምን ይሻለኛል….ሆድ ብሶኝ ትንሰቀሰቅ በዛው  እንቅልፍ እንደ ጣለኝ ያወቅሁት እትዬ በሬን በሀይል አንኲኩተው ቲቀሰቅሱኝ ነበር።

ተረፋዱ ሶስት ሰአት ሆኗል።ወይ ዘሬስ ገደሉኝ እያልሁ ተክፍሌ ትወጣ ስልክ ላይ ተጥደዋል።

“ሁሉን ነገር በቅዳችን መሰረት ስላከናወንከው ደስ ብሎኛል የኔ ባርያ”  አሉና ስልኩን ዘጉት ያንን አረመኔ ሻንቆን ነው መሰል። ተዛ ቀጠል አርገው  ወደ ላይ እያዩ “ፈጣሪ ይመስገን እየተሳካ ነው” አሉ።የትኛውን ፈጣሪያቸውን እንደሚያመሰግኑ ተምታታብኝ።ቁርስ ከበሉ ቡሀላ በደስታ እየተፍነከነኩ ተነስተው ሙሉ ጠርሙስ ውስኪ  አወረዱና በረዶ እንዳመጣላቸው አዘዙኝ።

ምነው እኝህ ሴትዬ እሄን ውስኪ ልፈው ልፈው  ክምብል ባሉልኝና በልሁ ጋር በገባሁ። ሞቅ አላቸው መሰል ሳቅ ሳቅ ይላቸው ጀመር።

ደሞ መልሰው እኔን ገልመጥ ያረጉኛል ዛሬ እኝህ ሴትዬ ነገር ተፈለጉኝ  እፊታቸው ባለው ጠርሙስ አናታቸውን ብዬ ነው እምገላግላቸው እያልሁ ታስብ…

ድንገት “ነይ እዚህ እፊቴ ቁሚ” አሉኝ ቆምኩ። ቀጠሉ “ስሚ አንቺ ማወቅ የለለብሽን የዚህ ቤት ሚስጥሮች ተዛ ተብጣሻም ደሀ በልሁ አልያም በራስሽ መንገድ እንዳወቅሽ ልቤ ጠርጥራል።እሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ  ታውቂያለሽ ? የቤተሰቡ የደህንነት መረብ ውስጥ ገብተሻል ማለት ነው።ባጭሩ ለቤተሰቡ ደህንነት ሲባል እኔ በህይወት እያለሁ መቼም ቢሆን ስራሽን መልቀቅ አትችይም።አይደለም መውጣት የመውጣት ሀሳብ ብታነሺ የመውጫውን መሰላል በሀይል አስረዝምልሽና ወደ ላይኛው ቤት ወደ ገነት ወይ ወደ ሲኦል ዘመዶችሽ በብዛት ያሉበትን መርጬ ያለ ምንም ክፍያ  አደርስሻለሁ ክክክክክክክክክክክ….!”

እንዲህ ነሽ እና ሰናይት አልበዛን እንዴ አሁንስ በዛ  ደሞ የምድሩም አልበቃ አላችሁና የሰማዩንም  መወሰን አማራችሁ። የምድሩን ሂወት ለበጃችሁ ገነት ላልበጃችሁ ሲኦል ትታረጉብን የከረማችሁት ይበቃችኻል።እንዴ እምድርስ ብር ትላላችሁ ተሰው በላይ ሆናችሁ በደሀ ስቃይ ትትደሰቱ ኖራችሁ እትዬ እላይማ ሌጣችንን ነው እምንሄድ ማን ከማን እሚበልጥ መሰሎት ሁሉም እኩል ነው ..ገዥውም አንድ ነው እንደ ምድሩ ሰማንያ ቦታ ገዢ ሰማንያ ቦታ ፈራጅ የለም።እንደምድሩ  የሰው ፈላጭ  ቆራጭ የለም እፍ  ግልግል። እኛስ የምድሩ ይበቃናል ሁለቴ ሲኦል አንገባም ይልቅስ ለራሳችሁ ቀኑ ታይረፍድ ብታስቡበትና ተጋኔን ስራችሁ ብትቆጠቡ ይበጃቹኻል።አልኳቸው በሆዴ። እምናገርበትማ ምን አፍ አለኝ።

ዛሬ አልናገርም ምን እናገራለሁ?

የተናገሩትም እንዳለቁ አውቃለሁ።

አልች እምዋ…

.ይቀጥላል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...