Tidarfelagi.com

ከመሄድሽ ወዲያ…

ከመሄድሽ ወዲያ…

በምን አይነት እርጉሚት ቀን እንደሁ እንጃ፣ በምን ኀይል አንደበቴ መታዘዝን እንዳገኘ… “ሂጂልኝ!” አልኩሽ፤ “ሂጂሊኝ፣ ከቤቴ ውጪ! ተይኝ!” አልኩሽ፡፡ ትዝ ይለኛል፣ ዐይኖችሽ ውስጥ የነበረው ግርምት እና ድንጋጤ! መልስ እንኳ አልሰጠሸኝም፡፡ ሄድሽ!
ግን……
የዐይን እርግብግቢት ታህል እንኳን ካልቆየች መሄድሽ በኋላ፣ የንጥሻ ያህል እንኳን ካልቆየች መሄድሽ በኋላ… እግርሽ ቤቴን በለቀቀችባት ቅፅበት፣ ጨለማ ቤቴ ላይ ፈሰሰ፡፡ ልቤ ላይ ባዶነት ወደቀ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ባደረኩት ደነገጥኩ፡፡ በሆነው ደነገጥኩ፡፡ ተጣድፌ ልፈልግሽ ወጣሁ፡፡ አልነበርሽም-ሄደሻል!

አወይ ቤቴ ሞኙ፣ ምኑ የዋህ ኖሯል
ምሶሶውን ጥሎ፣ ለመቆም ይጥራል፡፡

ከመሄድሽ በኋላ፣ ደስታዬ የሀዘን መሰረት ሆነ፡፡ ታቹ ላይ፣ላዩ ታች ሆነብኝ፡፡ ሁሉ ነገር ተገለባበጠብኝ፤
እ. . . . . ህ እ እ ህ

ን. . . . . ዲ ን ን ዲ

ዲ. . . . . ን ዲ ዲ ን
ህ. . . . . እ ህ ህ እ

…. ለካ እኔን ሆነሽ ነበር፡፡ የሌለሽ ሲመስለኝ፣ በህይወቴ ውስጥ ዋጋሽ ምንም ሲመስለኝ…. ከአንቺነትሽ አልፈሽ እኔን ሆነሽ ነበር ለካ! መኖርሽን ክጄ፣ ህልውናዬ ላይ ያለሽን ስፍራ ማየት ተስኖኝ ፣ እራሴኑ ነበር ለካ ያበረርኩት! ሂጂ አልኩሽ፡፡ ስትሄጂ… እኔነቴ ፈረሰ፡፡ ባዶ ሆንኩ! ባዶ ቦታዬን ሁሉ እንባ ሞላው… ተመሳቀልኩ!

አንቺ በመሄድሽ፣
እየሳቅኩ አነባሁ፣ እያነባሁ ሳቅኩኝ
ሀዘን ልቤ ገባ፣ ደስታ ቤቴን ናድኩኝ
››››››› ‹‹‹‹‹‹‹
ከመሄድሽ በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ፀሀይ ስትወጣ አየሁ፡፡ ሰው ሆኜ ሰው መሆን ናፈቀኝ፡፡ ቅርቡ ሁሉ አይደርሱት ርቀት ሆነብኝ፡፡ ልቤ ከእሬት መረረ…..

አንቺ በመሄድሽ፣
ሙላቴ ጎደለ፣ ጉድለቴም አየለ
ጣፋጭ ልቤ መሀል እሬት ተጨመረ
ቀኑና ጨለማው በአንድ ተቋጠረ
በሰዎች ጫካ ውስጥ ብቸኝነት ዋጠኝ
ከሰውነት ወጣሁ፣ ሰው መሆን ናፈቀኝ፡፡
›››››› ‹‹‹‹‹‹‹
የት ነሽ? “ሂጂልኝ!” የሚል ሲኦል ቃሌ፣ እስከየትኛው የዓለም ጥግ ገፋሽ? እዚህ ነኝ በይኝ እባክሽ…!
…አቤት ባለሽ እና በመሄድሽ መሀል ያለው ልዩነት! ግዝፈቱ… ርቀቱ…ርቅቀቱ…! በሁለት የተለያየ ዘመን፣ በሁለት የተለያየ የህይወት ህይወትና የህይወት መልኮች ውስጥ እንደመኖር…. አንዳች ትስስር የሌለው!

…እባክሽ የት ነሽ? ለቅሶ የቤቴ ሙዚቃ ሆነ፣ ሀዘን የቤቴ ዋልታ ሆነ- ፀፀት ማገሬ፣ ስቅየት ሀገሬ…… ሆነ! እዚህ ነኝ በይኝ እባክሽ? ይቅር ባትይኝም ይቅርታዬን ልጠይቅ፡፡ በዴሌን እግርሽ ላይ ወድቄ በእንባዬ ልጠብ! አንዴ እይኝና ያላንቺ እንዴት ብስክስክ ወንፊት እንደሆንኩ ታዘቢ፡፡ ያላንቺ እንዲህ የምንኳኳ ባዶ ቆርቆሮ ነበርኩና ለካ?! መኖርሽ ሙላት ሆኖ ያቆመኝ ባዶ ጆንያ ነበርኩና ለካ?! አንዴ እዚህ ነኝ በይኝና የወናነቴን ጥልቀት ታዘቢ! … “ለዚሁ ነበር?” ብለሽ አፊዢብኝ

ምኑ ሞኝ ነበር ግን!
መንገዱን በአሜኬላ የሚያጥር፣ እግሩን ቆርጦ የሚጥል ተገዢ አለ? …ቤተመቅደሱን የሚያቃጥል ጳጳስ አለ? …መስኪዱን የሚያፈርስ ሼህ…? አዎ! እሱ እኔ ነኝ!
አቤት ንፁህ ነብስሽ እንዴት ትታዘበኝ፣ እንዴት ታዝንብኝ ይሆን ግን? ይሄው የበደለኝነት ጥፍር ነብሴን እየቧጠጣት ነው፣ ደምቶ ያለቀው ልቤን እያደማው ነው! … ይቅርታሽን ያላገኘሁት ንስሃዬ ከበቂው በታች ሆኖ ነው? ወይስ በደሌ በልጦ? ምን ላድርግ ይቅርታሽን ለማግኘት? ግራ ገባኝ እኮ ዓለሜ! ዓለሜ ሁሉ ጨለመ፡፡ እባክሽ ቶሎ ነይልኝ?!
እባክሽ?!
እባክሽ?!
እባክሽ?!….

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...