Tidarfelagi.com

እግዜርን እሰሩት !!

ከስሩ ታድሞ ትውልድ ይማከራል ‹‹እናምፅ ›› እያለ
ቁረጡት ያን ዝግባ ምናባቱ ቆርጦት ለህዝብ ጥላ ጣለ!?
ወንበር ሊገረስስ ላገር ጣይ ሊያወጣ ጥላው ስር ተቀምጦ ህዝብ ከመከረ
ዝግባ አሸባሪ ነው በግንደ ልቦናው ሳጥናኤል ያደረ !
እሰሩት !!

ይጨፍጨፍ ባህር ዛፍ ምን ቅብጥ አድርጎት
ማገዶ እየሆነ እንጀራ አበሰለ
ስንቴ እየገደልነው የሞተ ግንዱ ላይ
ሌላ ነብስ ፀደቀ እልፍ ሁኖ በቀለ ?
እንጀራ በወጡን በልቶ እየጠገበ
‹‹ስራ ፈት ሰልፈኛ ››መንገድ ካጣበበ
ሽብር ነው ባህር ዛፍ ፅድና ግራሩ
ከየበቀሉበት እየተለቀሙ
የዛፍ ዘር በሙሉ ከ,ሳት ይወርወሩ !

ስሩ እየተማሰ ቅጠላ ቅጠሉ እየተበጠሰ
ለህዝብ ጤና ሰጠ
በመሃበር ስናብድ ጤነኛ በቅሎብን
መንጋው ተናወጠ
ከዚህ በላይ ሽብር ከዚህ በላይ ረብሻ
አላፊ አግዳሚውን ስለምን ይንከሰው ‹እውነት› እንደውሻ ?
ማን አብዶ ማን ሊቀር …. አናብድም ምትሉ ?
አርፋችሁ እበዱ ‹ሽብርተኞች› ሁሉ !
መንጥሩት ቅጠሉን ከተቀበረበት ስራስር ይመዘዝ
‹‹መድሃኒት ነኝ›› የሚል ይወገር ይሰቀል በደቦ ይወገዝ !
የታባቱ !

እሰሩት በሬውን ! እኛ ሳንፈቅድለት ምድር እያረሰ
ስጋውን ጀብቶ ጥሬውን ከብስል ህዝብ እያጋበሰ
ህዝበ በላተኛ በየበረንዳው ላይ በሚስለው ቢላ
ይበላው ያጣ ቀን እኛን እንዳይበላ
ራብን ይጥገባት ከዳቦ በስተቀር እንዳያስብ ሌላ
ሳሩን እጨዱና በሬውን እሰሩት
መደለብ ሽብር ነው የደለበን ቀንዳም
ጮማውን ትታችሁ ..እርሻውን ትታችሁ ውጊያውን አግንኑት !
እሰሩት !!

ንፋሱን እሰሩት ! ማንን አስፈቅዶ እንዳሻው ነፈሰ
ህዝቡስ ካለፍቃድ ለምን ተነፈሰ ?
እሰሩት አየሩን መታፈን ነው ደጉ
የታፈነ ትውልድ ጩኸት አያበዛም በየጥጋጥጉ !
‹‹ሽ አመት ንገስ ›› የሚል ምድሩን ይፈንጭበት
‹‹ ለምን ›› ባዩን ማቶ ‹‹እንዴት ›› ባዩ ‹በጥባጭ ›
ይቆምበት ይጣ ‹ቅድስት› ምድራችን እሳት ይሁንበት !!
ሰቅዞ ይዞናል የራሳችን ድግስ የራሳችን ተስካር
መድረሻህን ፈልግ ‹ሰላማዊ ስካር›
እሰሩት !

እ….ዛ ላይ …….
ድንገት ሳይደፋብን የአብዮት ዝናብ የብጥብጥ መና
ከሰማየ ሰማይ ተገፎ ይታጎር ይቅፍደድ ደመና
በዚች ‹ቅድስት› አገር እንኳን ያአመፅ ጥሪ እንዳይኖር ትንታ
ከስር ያመለጠች የዝናብ ዘለላ የውሃ ኮለልታ
እንጦሮጦስ ትውረድ በፍኝ ተጠራቅማ በፎሌ ተሞልታ
ድንጋይ ትበሳለች ላይን አትሞላም ብለን የናቅናት ጠብታ !
ጀርባዋ እስኪገጠብ ትሞሽለቅ ጨረቃ
እንጦሮጦስ ትጣል ፀሃይ ምድር ወርዳ
ነገ ሳትፈጀን እልፍ እሳቶች ወልዳ
ትታሰር !!

ሰማይ ባዶ ይሁን
ከ,ኛ እግር በስተቀር ማንም እንዳይረግጠው
‹ፀሃይ የት ደረሰች ጨረቃ የት ገባች ›
የሚል ጠያቂ ነፍስ መቸም እንዳይገልጠው !
ይከደን ሰማዩ ጨለማ ይዋጠው !

በጨለማው ሰማይ በድቅድቁ ህዋ የተጠራቀመ
ይታሰር ኮከቡ አንድ ባንድ በነቂስ እየተለቀመ !

መሬቱም ይታሰር አዳሜ ሚረግጠው
ሽብርተኛ ደም ነው ሲጠጣ የኖረው አፈሩን ብትገልጠው
ይመስልሃል እንጅ የስጋጃ ምንጣፍ
ሸፍኖት ሳር ቅጠል ሸፍኖት አበባ
ነገ ቀን ሲከዳ በቁምህ የሚውጥ
ክፉ መቃብር ነው ካፈር የሚያሚያስገባ
እሰረው …. !!

እንደውም ……
ሰማዩም ይታሰር … ተጠቅልሎ ይግባ እንደሰሌን ምንጣፍ
ቀና እንዳይል ህዝቡ የነፃነት ምኞት በላዩ እንዳይፃፍ !
ሰማይ ሸቤ ሲወርድ እግዜር ለዙፋን ቦታ ሲቸግረው
ይወድቃል ከጃችን በደረቅ እንጨት ላይ ግራ ቀኝ ቸንክረው !
በቃ !

ምድርን ከቀፈደድክ እግዜሩን ካሰርከው
ህዝብህና ህዝቤን ‹‹ኢትዮጲያ እጆቿን …›› እያልክ ስበከው
የታሰረች አገር ወዳሰርነው አምላክ እጇን ብትዘረጋም
ይሄን ሁሉ ደክመን ያቆምነው ጨለማ በቀላሉ አይነጋም !!

One Comment

  • ማማው አያሌው commented on January 27, 2018 Reply

    አሌክስ ክበርልኝ እውነትህ አይሰረዝ
    የታሪክ ገፅ ላይ ሰርክ አብራ በመቅረዝ !!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...