Tidarfelagi.com

እድሜዬ እና የኢትዮጲያ እርምጃ!

ሰላም ነው ጋይስ!

እንግዲህ ቅዳሜ እለት በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ ያለፈውን የ 35ኛ አመት የልደት በአሌን በማስመልከት ብዙዎች ” እድሜህ ስንት ነው?” በማለት በጠየቃችሁት መሰረት ስለ እድሜዬ የሚከተለውን መግለጫ ለመስጠት ተገድጃለሁ። ግና ለአንባቢ የተወለድኩበትን ዓመተ ምህረት በቀጥታ ከመናገር ይልቅ እስከዛሬዋ እለት ድረስ ያለፍኩባቸውን “ወሳኝ” ሀገራዊ ኩነቶች በመዘርዘር አንባቢ የራሱን ግምት እንዲወስድ መርጫለሁ…..

እንግዲህ አንዲ ማኛ የተወለደችው ከበርካታ አመታት በፊት “የቀይ ኮከብ አብዮታዊ ሁለገብ ዘመቻ” በከሸፈበት እና የኮ/ል መንግስቱ ፊት ከነሃሴ ሰማይ የበለጠ በከበደት በወርሃ ነሃሴ የመጀመሪያው ሳምንት ሲሆን ቦታው በባሌ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ ዶዶላ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው። የዛሬን አያድርገውና ያኔ ላልተሳካው ዘመቻ የወጣው 2 ቢሊዮን ብር የት ገባ ተብሎ ቆራጡ መሪ ኮ/ል መንግስቱ እነ ኮ/ል ውብሸት ማሞን ጨምሮ በበርካቶች ላይ የማያወላውል እርምጃ እየወሰዱ የነበሩበት ወቅት በመሆኑ ባለስልጣናቱ መሬት ተከፍታ እንድትውጣቸው ሲመኙ አንዲ ማኛ ገና በእናቷ ማህጸን ሆና ትሰማ ነበር……በእርግጥ ያኔ ላይ ከአመታት በኋላ በዚህች ደሃ ሀገር 77 ቢሊዮን ብር ጠፍቶ አጥፊው ላሽ የሚባልበት ጊዜ እንደሚመጣ ብታውቅ ኖሮ አንዲ ማኛም እንደ አቤ ጉበኛ “አልወለድም” ብላ ከእናቷ ማህጸን በኦፕራሲዮን ሁላ ባልወጣች ነበረ!

ከላይ ባለው የታሪክ ፍንጭ ጊዜውን ላልተረዳ ጸረ ደርግ አንባቢ ተጨማሪ ፍንጭ ለመስጠት ያህል .. የተጸነስኩበት እና የተወለድኩበት አመት ኦ.ነ.ግ የትግል ማኒፌስቶውን ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽ ያደረገበት አመት ነበር። የትግሉ አላማም “የጸረ ቅኝ ግዛት ትግልን በማካሄድ እራሷን የቻለች ነጻ የኦሮሚያ ሪፐብሊክን ማቋቋም” እንደሆነ አሳውቆ የነበረ ሲሆን ከብዙ አስርት አመታት በኋላ በተመሳሳይ ወር በልደቴ ሰሞን ጥያቄው በመጠኑ ቅርጹን ለውጦ “በኦሎምፒክ መድረክ ኦሮሚያ የእራሷን አትሌት መላክ አለባት” በሚል የቀደመው ጥያቄ በመጠኑ ተዋዝቶ አግኝቼው ፈገግ አስብሎኛል። በአንጻሩ በዚሁ አመት ህ.ወ.ሃ.ት ከደርግ ጋር የነበረውን ቀጣይ የውጊያ አቅጣጫ በተመለከተ አረጋዊ በርሄ “የቁንጫዎች ጦርነት” (ዋር ኦፍ ዘ ፍሊ)(ወይም “ንጸላኢ ብድወ.….(ትግርኛው ጠፋብኝ) (ብቻ “ጠላትን በቁሙ ማሸነፍ” ነው ሃሳቡ) ….ቁንጫዎች በውሻ ጸጉር ውስጥ ተሰግስገው እንደሚያሸንፉት ሁሉ ደርግን በዚህ መልኩ የመዋጋት ስትራቴጂ) በማለት የሰየመውን የውግያ ስትራቴጂ ሲጽፍ በዛው አመት ስዬ አብርሃ ደግሞ “የኮንቬሽናል ዋር” አስፈላጊነትን የሚያትተው ጽሁፉን አጠናቆ ለፓርቲው አባላት ለውይይት አብቅቷል……የዛሬን አያድርገውና እንደዚህ አይነት ሁለት የተለያዩ ጽንፎችን አቻችሎ እና አማርጦ ይታገል የነበረ ፓርቲ ዛሬ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ትቶ የተለየ ሃሳብ ያፈልቁ የነበሩትን አባላቱን በተለያየ ምክንያት ከሀገር አባሮና አስሮ ከትንሽ እስከትልቁ ሃሳብ “ከታላቁ መሪ የወረደ ነው” ብሎ ግለሰብ ወደ ሚያመልክበት ጊዜ ላይ ሲደርስ አይታ አንዲ ማኛ “አይ ጊዜ!” በማለት በለውጡ ተደምማለች…..

ያው በ9 ወር መወለድ አይቀርም ተወለድኩ። እንደ አብዛኛው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ እንደ ተወለደ ህጻን አንዲ ማኛም በ7 ቀኗ ተገርዛ በ40 ቀኗ ክርስትና ተነሳች።

ያው አስተዳደጓም ቢሆን እንደ ማንኛውም ልጅ ነበረ። አንዲ ማኛ ገና በአፍላ እድሜዋ በሀገራችን አስከፊ ድርቅ ተከስቶ አንድ ኩንታል ጤፍ 450 ብር ሲገባ እና “ጉድ ጉድ!”ሲባል ትዝ ይላታል (ዛሬ በ 450 ብር አራት ሰዎች ምሳ ጠግበው አይበሉም!)….ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በ19 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ(በእርግጥ “ከቼኮዝላቫኪያ እቃው መጥቶ ሲገጣጠም” ማለት ይቀላል) “አይ የመንግስት ጭካኔ! ድፍን 19 ሚሊዮን ብር ለአንድ ፋብሪካ!!” ተብሎ ደርግ መወያያ ሲሆን ያየችው አንዲ ዛሬ እድሜ ሰጥቷት 19 ሚሊዮን ብር የሰረቀ የአንድ ፕሮጀክት ዳይሬክተር በሙስና ሲታሰር ህዝቡ “አሁን በፖለቲካ ተጣልተው እንጂ 19 ሚሊዮን ምን አላት?” ሲልም ለመመልከት በቅታለች።

“እንደ አብዛኛው የገጠር ልጆች አንዲ ማኛ እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ በእረኝነት ተሰማራች” የሚል ትራጀዲ አትጠብቁ….ይልቁንም ጥቂት የማይባሉ ጄነራሎች በኮለኔሉ ላይ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት ባደረጉበት አመት አንዲ አንደኛ ክፍል ተመዘገበች….አንዲ ማኛ ገና ከጥዋቱ አእምሮዋ ለትምህርት እጅግ ክፍት የነበረ በመሆኑ አመቱ ሲጠናቀቅ ከአንደኛ ክፍል በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ክፍል ተዘዋወረች ።በዛው ሰሞን ጄነራል ፋንታ በላይ መፈንቅለ መንግስቱ ሲከሽፍባቸውና ኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው ሲያዙ

“ፔፒሲና ሚሪንዳ በከተማው ጠፍቶ
ፋንታ ተገኘ አሉ በኮንቴነር ሞልቶ……..”

እየተባለ ከተማው ውስጥ ሙድ ሲያዝ አንዲ ማኛ በጊዜው ቅኔው ሳይገባት ስቃለች።ዛሬም ይህ አመሏ ቀጥሎ “እገሌ ተያዘ…. እገሌ ታሰረ” ሲባል እንደ አብዛኛው አበሻ ዋናውን ነገር ረስታ በሰውየው አያያዝ ወይም ወሰደ በተባለው የገንዘብ መጠን ላይ ትሳለቃለች።

አንዲ ከትምህርቷ ውጪ መጻፍ ማንበብና እግርኳስ መጫወት በተለይ ደግሞ እግርኳስን በራዲዮ መከታተል ያስደስታት ነበር።(ቲቪ ከሌለ ታዲያ ምን ታድርግ!?)። ከምንም በላይ ትወደው የነበረው ብሄራዊ ቡድኗ ከአንዲ ማኛ ህይወት አብዛኛውን እድሜ ለሚሸፍኑት አመታት ከአፍሪካ ዋንጫ ርቆ የቆየ በመሆኑ አዝናለች።በረኛችን ተካበ ዘውዴ ሶስት ፔናሊቲ አድኖ ዋንጫ ስንበላ በደስታ እንዳልሰከረች ሁሉ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሚሊዮን በጋሻው ሞሮኮ ላይ ፡ፍሰሃ በጋሻው ሱዳን ላይ ፔናሊቲ ሲስቱ በፊሊፕስ ራዲዮና አዳምጣ እርር ድብን ብላለች….በ1957 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጪ ሀገር ለጨወታ ሄዶ በዛው ጠፍቶ ከቀረው እስማኤል ገሪላ ጀምሮ አስከ 1993 እነ ሁሴን ሰማን አርጀንቲና ላይ ጠፍተው እሰከቀሩበት ጊዜ ድረስ ከስድሳ በላይ ተጫዋቾች በየሀገሩ ለጨዋታ ብለው ወጥተው በዛው ጠፍተው ሲቀሩ በራዲዮኗ ሰምታ በሀገሯ ችስታነት ተማራ ገና በልጅነቷ ቆዝማለች።ለጎረቤት ውሃ ቀድታ በብላክ ኤንድ ዋይት ቲቪ የአፍሪካን ዋንጫ በመታደም የግብጹን አቡዚያድ ፡የአይቮሪኮስቱን ትራወሬ፡ የካሜሮኑን ሮጀር ሚላ፡ የጋናውን አቤዲ ፔሌ የናይጄሪያውን ያኪኒ ፡የዛምቢያውን ቡዋሊያ ፡በቅርብ ደግሞ የግብጹን መላጣውን ሆሳም ሀሰን እና ደቡብ አፍሪካውያኑን ማካርቲ እና ባርትሌትን ግሩም ጎሎች አይታ ፈንድቃለች…..

በዚህች እድሜዋ በሀገሯ አውሮፓን ያስደመመ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተደርጎ ተሸናፊው አራት ኪሎ ቤተመንግስት ሲገባ አሸናፊው ቃሊቲ ወህኒ ቤት ሲዶልም አይታለች……

“አባይ …አባይ… የአገር አድባር… የአገር ሲሳይ” እየተባለለት ሲዘፈን የምታውቀው አባይ ሊገድብ ነው ሲባል ህዝቡ ደስታ ፈንቅሎት “አባይ ይገደብ!” እያለ ሲጮህ ባየችበት አይኗ በጥቂት አመታት ውስጥ ጥያቄው” ከአባይ ይገደብ ወደ አባይ ይታሰር “ሲቀየርም አይታለች……….

መሪ ሀገር ጥሎ ሲሰደድ፡ መሪ ሞቶ ሲቀበር፡ በውኑም በህልሙም መሪ ሆናለው ብሎ አስቦ የማያውቅ አስተማሪ መሪ ሲሆን ሁላ አይታለች!…..ብቻ ምን ያላየችው ነገር አለ……..!
አሁን ዋናው ጥያቄ “የዚህች ሰውዬ እድሜ ስንት ነው?” የሚለው ነው

መልሱ ምንም ይሁን ምን…..ብቻ ሁላችሁም

ይመቻችሁ

One Comment

  • Kassahailu6@gmail.com'
    ጀማሉዲን ሚፍታ፡፡ commented on December 18, 2017 Reply

    አንዲ በርታ!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...