Tidarfelagi.com

‘እዬዬ ሲደላ ነው’ ይላሉ

‘እዬዬ ሲደላ ነው’ ይላሉ።
ተረቱን ያመጣሁት፤ ደንባራ የሆነ የባዕድ ባህል ቅጂ ምን ቦታ እንደሚከተን ሳስብ እያለሁ፤ ‘ሙሾ አውራጆች የኋላ ቀር ባህል እሴቶች እንደሆኑ’ ሊነግረን የሚጥር፣
በምርምር ያልተደገፈ፣
ጥልቅ በሆነ ፍልስፍና ሞትን፣ ሃዘንና ኪነትን እንድንረዳ ለደቂቃ እንኳን ያልጣረ፣
ለስሙ ‘ለኪነ ጥበብ ተሟጋች ነኝ’ ባይ
የፖለቲካ ልምድ አለኝ’ ባይ፣ አሌክስ ባህሩ በተባሉ ሰው የሆነ ግምት (እሳቸው ‘ሃሳብ’ የሚሉት) ሲሰነዘር ትዝ ብሎኝ ነው።
ይቅር ልንለው የማንችል የእኚህ አምደኛ ትልቅ ድክመት፤ ለቅሶን ተዘርቶ ካበበበት ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባሕላዊ አውድ በማላቀቅ ለብቻው ሊረዱት መጣራቸው ነው።

አቀራረባቸው ሁሉን አቃፊ (Holistic) አይደለም ። የሚገርመው፤ አውድ ባይጠቅሱም አውዱን ያመጡት አይተነውና ኖረነው ከማናውቀው የሰለጠነ ካሉት የባዕድ ሀገር ነው።

ለመሆኑ፤ ቢያንስ ቢያንስ ይሄ ልማዳችን እስከዛሬ ድረስ ፀንቶ መቆየቱ ነገር ቢኖር ነው ብለን እንድንጠረጥር አያደርግም?
ጋሼ አሌክስ፤ በሌላ ነገር የሚነዘንዙን ይበቃልና እስኪ ሬሳችንን ለቀቅ፣ ዕንባችንን ተወት ያድርጉልን።

የሰው ልጅ ይወለዳል፣ ይኖራል፣ ይሞታል። በዚህ ጎዳና የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ማንም ነፍስ ያለው ፍጡር ያልፋል። ታላቁ ፈላስፋ ሚጌል ደ ኡናሙኖ (The Tragic Sense of Life in men and people, 1954) ባለው መፅሀፉ ሃይማኖቶችን ሞትን ለመረዳትና ተፈጥሮአዊ ግዴታ መሆኑን ለመቀበል የሰው ልጅ የፈጠራቸው ማሕበራዊ አመለካከቶች ናቸው ይላል። ሮበርት ካስተንባውም እና ባለቤቱ ወይዘሮ ቢትሪስ (Encyclopedia of Death, 1954) በተባለው የአጠቃላይ የዕውቀት መፅሐፍቸው ውስጥ ለቅሶ በአጠቃላይ ሶስት ዓላማዎች እንዳሉት ፅፈዋል።

አንደኛው፤ የሞተው ሰው ገላ የጤና ጠንቅ እንዳይሆን በስልት ከማሕበረሰቡ ጆኦግራፊያዊ አካባቢ በማሸሽ (ይሄም መቅበር) ሲሆን ሁለተኛው የሚቀርቡት ሃዘንተኞች ከሟቹ ገላ ጋር እንዲተያዩና ያሉበትን ሁኔታ እንዲረዱ የሚያደርግ ነው። ሶስተኛው ደግሞ ሰዎች ከኮሚዩኒቲያቸው ወይም ከማሕበረሰቡ አንድ አባላቸው በመጉደሉ በመጠኑ ከተለወጠውና ከጎደለበት ስብስብ ተገናኝተው መጉደልን የሚረዱበትና ይሄን ጉድለት የሚገነዘቡበት ነው።

በዚህ አከፋፈል የተለያዩ ማሕበረሰቦች አንዱን ወይም ሁለቱን ወይንም ሁሉንም በተለያየ ደረጃ አጥብቀው ሊይዙ ይችላሉ። ይሄም አንዱ ከአንዱ ይበልጣል ማለት አይደለም። እነዚህ ልማዶች ሰዎች ሞትን በማሰብ ወይም የሞት ሃሳብ ላይ በመቆዘም በሕይወት እያለን ላለንበት ማሕበረሰብ እንድናስብና ከውስጥ የተሸሸገውን ጥሩ የማድረግ ስሜታችንን እንዲቀሰቅስ ያደርጋሉ።

በቅዱስ መፅሀፍ ውስጥ ያለው መፅሐፈ መክብብ ሙሾ ነው። የዳዊት መዝሙር ከሲሶው በላይ ሙሾ ነው። እንደ ኤርሚያስና ኢሳያስ ዓይነት ታላላቅ ነቢያት በሙሾ የሚፅፉት አልቃሻ ሆነው ወይም ኋላቀር ሆነው ሳይሆን ሙሾ የተፈጥሮ ማሕበራዊ ግዴታ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። ዛሬም ዘመናዊ ፈረንጆች ሙታንን ቆመው በንባብ፣ በግጥም፣ በንግግርና በሙዚቃ ይዘክራሉ። በአጭሩ ለቅሶ የአገራችንን ብቻ ሳይሆን የዓለም ስራ ነው።

ሙሾ አውራጆች የሚሰሩት፤ ነጠላ ወይም ግላዊ ጉዳይን ማሕበራዊ ፍቺ ለመስጠት ነው። ከግል ጉዳይ ውስጥ ማሕበራዊ ትርጉም የመፈልቀቅ ጥረት ነው። በቋንቋና በድራማ ጥልቀት የመስጠት ነው። ይሄ የኪነት አንዱ ባህርይ ነው . . . የገብረክርስቶስ ደስታ ግጥሞች ሙሾ አይደሉም እንዴ? ብዙ ወጣቶች ዛሬ የሚገጥሟቸው አራቶችና መንቶዎች ሙሾ አይደሉም እንዴ?

የጥንት ግብፃውያን የሙታን መፅሐፍ (hail to you, lords of eternal repetition founders of eternal sameness! Do not take my heart from me) ይላል አንዱ ለሞት በሚልኩት ግጥማቸው። የአኒ ፓፒረስ የቲቤታውያን የሙታን መፅሐፍና በአገራችንም ልፋፈ ፅድቅ የሞትን ሁለንተናዊነት የተለያየ መግለጫ፣ ማሳያና መቀበያ መንገዶችን የሚያስተምሩን ናቸው።

በሕይወት የነበሩ ግለሰቦች በተለያየ መልክና ደረጃ ማሕበራዊ ተሳትፎ ያደርጋሉ። በገጠሩ አገራችን፤ ሰንፎ የሚቀመጥ የለም። ትንሽ ልጅ እረኛ ነው። አንድ ሰው በመጉደሉ የማይመች ሁኔታ ይፈጠራል። ሰርግ ሲሆን ዘፋኙ ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት ወይም የሰፈር ሰው ነው። ለቅሶም እንደዛ ነው።
መኮራረፍ ቢኖር እርቅ መፍጠሪያ ነው። በባህላችን ጠላት ጠላቱን ይቀብራል። ቀብር መታረቂያ ቦታ ነው።

ምናልባት እነ አቶ አሌክስ ባይኖሩ የሚጎድልብን አይኖርም። ወሬኛ አያጎድልም። አያድርገውና ቢሆን፣ አሉባልታ የነፉለትና ያስደሰቱት አይጠፋምና እንቀብርዎታለን። የምንቀብርዎት ዝነኛ ፖለቲከኛ ስለሆኑ አይደለም።
እዚህ መሬት ላይ አብረውን ስለነበሩ ነው . . .”

#የስንብት_ቀለማት

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...