Tidarfelagi.com

እኛ፣ሾፌሩና አውቶብሱ

‹ዛጎል› ልቦለድ ውስጥ የምናገኘው ዮናስ የተባለው ገጸ ባሕርይ እንደሚከተለው ያስባል፤ያምናል፤ይናገራልም!

‘በእኛ ፈቃድ አይደለም ነገሮች የሚከወኑት። እግዜራችን ነው ሾፌር። እሱ ነው ፈላጭ ቆራጭ! እሱ ነው የእኛ ሃይል። በየትኛው ጊዜ – በየትኛው ቦታ – እኛን ከመኪናው ማውረድ እንዳለበት የሚወስን። እኛ ‘ወራጅ አለ’ ስላልን ፍሬኑን አይዝም፤ እሱ ሲፈቅድ እንጂ! እናስ?! እኛ ምንድነን?! ሰው ማለት ምንድነው፤ ‘ምድር’ በምንላት መንገድ፤ ‘ጊዜ’ በምንለው አውቶብስ ውስጥ እንዲሳፈርና አምላክ በሚለው ሾፌር ፈቃድ እንዲቀላቀል የተፈረደለት ወይም የተፈረደበት እንጂ!! እንሄዳለን – ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር እንግባባለን – እንላመዳለን – አዳዲስ ተሳፋሪዎች ይቀላቀሉናል። እያንዳንዱ ተሳፋሪ የራሱ የሆነ ተልዕኮ፣ የራሱ የሆነ ተውኔት አለው። ተልዕኮውን ግን አጥርቶ አላወቀውም። ተውኔቱን አላነበበውም። አንዴ መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ ግን እግዜር አፉ ላይ ቃላት ያኖርላታል። እየኖረ እያለ ነው ምን እየሰራ እንደሆነ የሚያውቀው። ‘ንቁ’ ከሆነ ነው፣ እግዜር ምን እየሰራበ(ለ)ት እንደሆነ የሚገባው. . .

‘እና – እያንዳንዱ ተሳፋሪ ያለ ምክንያት አንተ በተሳፈርክበት የጊዜ አውቶብስ ውስጥ አይሳፈርም። አንድ ነገር ሊነግርህ ነው፤ አንዳች ነገር ሹክ ሊልህ ነው የተላከ። እሱም ካንተ የሚቀበለው ነገር አለ። ዕጣው አንተ በተሳፈርክበት የጊዜ አውቶብስ እንዲሳፈር ያደረገው ስትገነባ የቆየኸውን እምነት ለመናድ ይሆን ይሆናል – ማን ያውቃል። ትሄዳለህ፤ ትከንፋለህ፤ የምትመሰጥባቸው ዜናዎችን እንድታዳምጥ ትገደዳለህ። አፍንጫህ ዘንድ ባይደርሱ የምትመርጣቸው ጠረኖች ያውኩሃል። ግን – ‘ወራጅ አለ’ ብትል የሚሰማህ የለም። አንተ አይደለህም፤ የራስህን ህይወት የምታበጀው። ትኖራለህ – ሰዓታት ያልፋሉ – ቀናት ይወልዳሉ – ወራት ይመጣሉ። ዐመታትን ይጠራሉ።

‘በተሳፈርንበት የጊዜ አውቶብስ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ታቦት ተሸክሞ ይዞራል። የውበት ታቦት – የፍቅር ታቦት . . . ብዙ አይነት ታቦቶች።

‘ታያለህ – የምትወደውን ትከተላለህ – ተከታይም ታፈራለህ – የጊዜ አውቶብስ ይከንፋል፤ ከልካይ የለውም። የትራፊክ መብራት አይዘውም – መቆም ሲፈልግ በየፌርማታው ይቆማል። እያንዳንዱ ፌርማታ ማህፀንና መቃብር አለው። አዳዲስ ተሳፋሪዎችን ይወልዳል። ከአውቶብስ እንዲወርዱ የታዘዙት ይቀብራል።

‘አውቶብሱ ውስጥ ሁለቴ መሳፈር አይቻልም። ከአውቶብሱ የወረደው ተሳፋሪ፤ ከጎንህ ስታጣው፤ አንዳች ነገር እንደጎደለብህ ይታወቅሃል። ታለቅሳለህ። ወዮ ወዮ ትላለህ፤ ይረብሽሃል ወይ ደግሞ ‘ተገላገልኩት’ ትላለህ – ግን ቀጣዩ ፌርማታ ላይ፤ ማን ‘ውረድ’ ተብሎ እንደሚገደድ አታውቅም።

……

‘ሲኦልህንም ገነትህንም በምትሳፈርበት አውቶብስ ውስጥ ፈልገው። አብረውህ ባሉ ሰዎች ልብ ውስጥ ያንተ ጥልቅ ደስታ አለ – ጥልቅ ሀዘንም ጭምር! . . . በማን በኩል ምን እንደተላከልህ አሰላስል። ለምሳሌ እኔ፣ ፍቅረኛዬ በተሳፈረችበት አውቶብስ ውስጥ ራሴን አገኘሁት። የኔን ገነት በእሷ በኩል አገኘሁት – ፍቅርን ሰጠቺኝ። ገነቴን ሸለመቺኝ። ገነቴን ከብዙ ስቃይ በኋላ አገኘሁዋት። ግን አንድ ሰው በአንድ ሰው በኩል ገነቱን ብቻ አያገኝም – ሲኦሉንም ጭምር እንጂ!

‘በየራሳችን ልቦና ውስጥ ስቃይና ደስታ አለ። ገነትን ራሴ ውስጥ ፈለግሁት። ስዕል ስዬ በማገኘው ሀሴት ውስጥ አገኘሁት። እውነቱን ለመናገር በፍቅረኛዬና በሰዓሊነቴ በኩል የማገኘው ስሜት ገነታዊ ብቻ አይደለም፤ ገሀነማዊ ሲኦሌም ገነቴም። ሁለቱ – የብርሃንና የጨለማ ያህል እየተፈራረቁ በስሜት ይነዱኛል . . .’

/እንዳለጌታ ከበደ፣ዛጎል፣2000ዓ.ም/

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...