Tidarfelagi.com

እኔና አንቺ

“አንተ ሴሰኛ አይደለህም።” ትዪኛለሽ። ሴሰኝነት ‘ስሜ’ መሆኑን አንቺም፣ እኔም፣ ከጎኔ የሚሻጡት ሴቶችም፣ እኔን የሚያውቁኝም ሁሉ እናውቃለን።

ለራሴ ‘ያለማወቅሽን እና የዋህነትሽን’ ነገርኩት። ላንቺ ግን ዓይኖቼንም ልቤንም የጠለፈውን ህልም የመሰለ ውበት ያለው አካልሽን እያየሁ ጥርሴን ለመግለጥ ከንፈሬን አሸሸሁልሽ …….. ሚስጥር አዘል ወጋገን ያለው ፈገግታሽን መለስሽልኝ።

“አንተ የእኔ በመሆንህ እድለኛ ነኝ::” አልሽኝ የሳምኩሽ እለት…….. በልቤ ሳቅኩብሽ….. በጥርሴ ሳቅኩልሽ …..

“አንተ ከንቱ ሱሰኛ አይደለህም::” አልሽኝ አስረኛ ሲጋራዬን እየተቀበልሽኝ ……. የሙሉ ጊዜ ስራዬ ሱስ መሆኑን ካንቺ በላይ የሚያውቅ አልነበረምና ግራ አጋባሽኝ።

“አንተ እኮ ታታሪ ሰራተኛ ነህ። እንደማውቃቸው ሰዎች ሰነፍ አይደለህም። ለምን ስራ አትሰራም?” ያልሽኝ ቀን
‘ትፎግራለች እንዴ?’ አልኩኝ ለራሴ …… በአንድ ዓይነት የትምህርት ዘርፍ ተመርቀን አንቺ ቤተሰብሽን ስታስተዳድሪ እኔ ቤተሰቤን ሳሳርር ዓመት እንዳለፈን ካንቺ በላይ እማኝ የለኝም።

ከቋመጥኩለት ገላሽ ጋር መውደቅ አጓግቶኝ እንዳንቺ የወደድኳት ሴት ያለመኖሯን ምዬ ተገዝቼ ስነግርሽ

“አምንሃለሁ። እኔን የምትዋሽበት ምክንያት አይኖርህም!!” ብለሽ ውሸታምነቴን አገዘፍሽብኝ።

ማንም ወንድ ያልዘለቀው ገላሽን ስዘልቀው ………………. እድለኛነቴን ሳይሆን ‘ስላፈቀርሽኝ ራስሽን አሳልፈሽ በመስጠትሽ’ እድለኛነትሽን ነገርሽኝ እና ከደስታዬ ይልቅ ራስምታቴን አበዛሽው ………….

አብሬሽ ሆኜ ከሌሎች ብዙዎች ጋር አብሬያቸው መሆኔን ታውቂያለሻ !……….. ለቁጥር የሚታክቱ ጊዚያት ብልግናዬን ደርሰሽበታላ !……… ለተገለጠ ስድነቴ ብዙ ሰበብ ስደረድርልሽ

“ምክንያትህ አንተን ካሳመነህ ለኔ አትንገረኝ::” ብለሽ ምንም ያልበደልኩሽ ያህል ከረሳሽው ቀናቶች ብቻ ናቸዋ ያለፉት!!

አንቺ በህይወቴ እስከተከሰትሽበት ጊዜ ድረስ ሴት ልጅ …………. ልብ፣ ነፍስ፣ አዕምሮ፣ ስሜት ……..( ከሚታየው የሰውነት ክፍሏ ውጪ ያሉት የ’ሰው’ነት መለኪያ) አብሯት ስለመኖሩ አስቤ አላውቅም። የሴት ፍቺው – እኔጋ የሌለው የሴትነት አካሏ ነበር። …..

የተናገርኳቸው ቃላትም ሆነ ያደረግኩት ድርጊት ሁሉ የተለመደ ……. ቁጥራቸውን ለማላስታውሳቸው ሴቶች ሁሉ ያልኩትና ያደረግኩትን ነበር።

ከመቼ ወዲህ ነው የሴት ልጅ ነፍስ ይናፍቀኝ የጀመረው? መቼ ላይ ነው የሴት ልጅ ከንፈር ከመሳም አልፎ የሚያፈልቀው ቃል ይርበኝ የጀመረው? …… ለስንተኛ ጊዜ አካልሽኝ ከተዋሃድኩት በኋላ ነበር ነፍስሽን የተዋሃድኳት?………..……… በሆነ በኔና ባንቺ ቀናት ውስጥ በአንዱ ቀን ወይም በሁሉም ቀን ነበር እንደዛ የተሰማኝ።

መቼ ነው አንቺ ነህ የምትዪኝን እኔነቴን እየወደድኩት፣ የሆንኩት ራሴ እያስጠላኝ የመጣው? የትኛው ቀን ላይ ነው አንቺን ለማማለል ሳይሆን ትክክለኛ ስሜቴን ማውራት የጀመርኩት? ምን ካልሽኝ በኋላ ነው ራሴን ማረም እና ንግግሬን መቀባባት፣ ድርጊቴን መደበቅ ሳያስፈልገኝ ራሴን አሳይሽ የጀመርኩት? …….. የትኛው ቀን ላይ አንቺ ነህ ያልሽውን ሰው ለመሆን መወሰኔን አላውቅም። ከራሴ መማከሬም ትዝ አይለኝም።

ብቻ…………… እግሮቼ ስራ ፍለጋ ሲኳትኑ፣ እጆቼ ሱሳቸውን ላለመከወን ሲታገሉ፣ ምላሴ ላለመዋሸት ከህሊናዬ ጋር ሲጣላ፣ ከሌላ ሴት ተኝቼ ይሰማኝ የነበረው ደስታ በበዛ ፀፀት ሲተካ………… ራሴን በቃልሽ ሳበረታ አገኘሁት።

ክንዴ ሌላ ሴት አንተርሶ ሳለ ደወልሽልኝ። ‘የት መሆኔን’ ስትጠይቂኝ ለመዋሸትም ያለሁበትን ለመንገርም ቃል ከከንፈሬ አልወጣ አለኝ። ……

“ መጣሁ ህይወቴ የት ነሽ?” ነበር ያልኩሽ ……

በስምሽ የጠራሁሽ ልቤ ውስጥ መከመርሽን የሚያሳንሱብኝን ቃላት ላለመጠቀም ነበር። …….ማሬ፣ ፍቅሬ፣ እናቴ ፣ውዴ…… ሁሉንም ቁልምጫዎች ለሌላ ሴት ብያቸዋለሁ …………….

“ስትጨርሽ ደውልልኝ!!” ማለትሽ ለቸኮለች ነፍሴ አልገባትም።

“ መጣሁ!!” ስልሽም በአካሌ ብቻ አልነበረም ….. በሁለንተናዬ እንጂ

“ከኔ ጋር ሆነህ ሌላ ሴት ትቀጥራለህ? ….. ስድ ነህ!!!” ብላ እንደብራቅ ጮኸችብኝ ካንቺ ጋር ሳወራ ነፍሴ መሳቋ የገባት ሴት …..

“ከዛሬ በኋላ ስድ አልሆንም!!” ብዬ የመለስኩላት እውነቴን ነበር። ……

ካንቺ ውጪ ለመጨረሻ ጊዜ የተኛኋት ሴት መሆኗን ለራሴም እያረጋገጥኩለት ነበር። ……. ልቤም እግሬም አንቺጋ ለመድረስ ተጣድፈው ሸሚዜን እየቆላለፍኩ የሆቴሉን ክፍል ለቅቄ ስወጣ ነበር ሩቅ በማይባል ቦታ ተቀምጠሸ ያየሁሽ ………… ካልሺኝ ሁሉ በጉልህ የሰማሁት ንግግርሽ

“መቼም የማትሻሻል ሴሰኛ ነህ!!” የሚለውን ነው።

ላስረዳሽ አልሞክርም። አንቺ ነህ ካልሺኝ በላይ የትኛውን መሆኔን ራሴም እርግጠኛ መሆን አልቻልኩማ ………

★ ★ ጨርሰናል!!! ★ ★

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...