Tidarfelagi.com

እትት በረደኝ

“ጅላዋት ሆይ፣ ጮማ ክፋት ከመጣ ሰላሳ እግዜር፣ ሰላሳ አላህ አይመልሰውም።”

“….በዲሞክራሲ ስለማምን አይደለም። ምንድን ነው እሱ? ልግመኛ ቢሰበሰብ የአንዲት ጮጮ ክዳን አይከፍትም።

ፍትህ ፍትህ ፍትህ የምትባለዋም የነብር ቂንጥር ናት። በሥዕል ይህቺ ፍትህ የሚሏት ሴትዮ ቆማ አይቼአታለሁ፤ ሚዛንና ሰይፍ ይዛ። ሰይፉ አለ አዎ። ሚዛኑም አለ አዎ። አይኖቿን በጨርቅ ጋርዳለች አዎ፣ ጭንብሉ ግን ቀዳዳ ነበረው። ጠጋ ብላችሁ አይታችኋታል? ፊቷ ላይ ባለው የጨርቅ ሽንቁር አሾልቃ ስታይ? ረዥም ቀሚሷ ስር እግር የለም። የትም አትሄድም። ልሂድ ብትል እቆመችበት ሾኬ ተጠልፋ በተገለበ ቀሚሷ የእነአጅሬ ሆሆይ ነው። ከዛ ሩካቤ፣ ፈረሰኛው ይመሰክርልኛል፣ የሚወለደው ሞሳ፣ ሲሚንቶና ብረታብረት ነው። እግሯ ሰርቶላት ብትሮጥ አትደርስም፣ ብትደርስ አታደርግም፣ ብታደርግም ‘አደረገች’ አይባልም። እግር ኖሮኝ እሮጫለሁ። የደረስኩት እዚህ ነው። ዙሪያዬን ሳይ የተረፈኝ ነገር ቢኖር አፌ ብቻ ነው። እሱም እንደ አሞሌ ሳይሟሟ ጀባ ልበላችሁ፣ ያደገበት ወዙን ልቀባችሁ። መቅበሪያ ቦታ አለ ልቦናችሁ ውስጥ? በሆሆታ እንድትከቱኝ? ባያረካኝም…. ለጨዋታው፣ ለፌዙ፣ ጥርሴ ተንዶ ከማለቁ በፊት ትንሽ ባርኛ ልገልፍጥላችሁ… ሰበቡ….

***
መንገድ ተዳዳሪ ነኝ። መተዳደር ከባድ ቃል ነው። መተዳደር የሚለው ቃል በሀምሌ ብርድ ወፍራም ጋቢ ተከናንቦ አጃ መጠጣት ይመስላል። ግን እንዴት ነው መንገድ ላይ እየኖሩ ‘መተዳደር’?

ቃሉን ለመጠቀም ለሰው ልጅ የሚመጥን መኖሪያ ቦታና ዘመድ ያስፈልገዋል። ብዙ ጉዳይ ቸል ብዬ እንዳለፍኩ ይሄንንም ቸል ብዬ ልለፍላችሁ። በየመንገዱ ዳር መተኛት አደጋ ስለሆነብኝ፣ የተቀናበረ ዐሠሣ አድርጌ የማድረው በቤቶች መሀል ያለ ባዶ ቦታ አግኝቼ ነው። ዘበናዮች ክፍተት የምትሉት። ይክፈታችሁና የሚከፍት (እስካሁን ካልከፈታችሁ)።

እኔን የመሰሉ ሰዎች አይተው እንዳይመጡብኝ የት እንደማድር ለማንም እኔን መሰል ጎዳና ተዳዳሪ አልነግርም።

ምቀኝነት አይደለም።

ባዶ ቦታ እንደመከላከያ ወረዳ በሚስጥር የሚጠበቀው እዚህ ነፋስ ስልክ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ጊዮርጊስን።

እያንዳንዱ ዘመን የራሱ አይነት ክፋት የራሱ አይነት ቸርነት አለው። እከክ የሰጠ ጌታ ጥፍር አይነሳም። አባባሌ የሚገባው ይገባዋል። ነገር ከከበዳችሁ ይሄው ሰበቡን እዘፍናለሁ…. ሰበቡ…

***
አገሬን ነክተውብኝ ጮኼ የተነሳሁ ነኝ።

ምርምር አላደረግኩም። ተማርን እንደሚሉት አገሬን ነዝንዤ በፉክክርና በምቀኝነት ለጠላት አልሰጠሁም።

ጠላቷ እንዲደፍራት የእናቴን ቀሚስ ወደላይ አልሰበሰብኩም።

ደፋሪው የልጆቿን ታሪክ ሰምቶ ሲርበተበት፣ ሊደፍራት ሲፎክር ‘አይዞህ’ ብዬ የሱሪውን አዝራር አልፈታሁለትም።

እኔ የፊት በር ስዘጋ የጀርባ በር ከፍተው ጠላታቸውን አገራቸው እልፍኝ አስገብተው፣ እናታቸው ተከናንባ የተኛችበትን ቡሉኮ ገፈው ‘ይችትልህ’ እንዳሉት አጅሬዎች አይደለሁም።

ከርሞ ከርሞ መቆየት ደጉ፣ ጠላ እየጠጣሁ እዛ አለማያ ኮሌጅ የሚማሩ ለጋ ወጣቶች ሳይ፣ በልቤ ለመሆኑ ለእነሱ እግሬ እንደተሰነከለ አይኔ እንደጠፋ ሳንባዬ በብርድ እንደታመመ ይገባቸዋል? እላለሁ። ጎረምሶቹ ተምረው ጨርሰው ልጄን ንጋትን ከመሰሉ ኮረዶች ጋር ሲሄዱ፣ ሀብት አግኝተው ቢራ ተኮልኩለው ሲጠጡ፣ አሁንም ጠላ እየጠጣሁ አይቻቸዋለሁ። አንካሳ በመሆኔ በመንሸዋረሬ ኮራሁ። ምናልባት ዛሬ እዛ ብሄድ ‘ወደ መጣህበት ሂድ’ ይሉኝ ይሆን? ከገደል ይጥሉኝ ይሆን? ‘ምን አይነት ገደል?’ በሉኝ። ሜዳም ገደል አለው…ገደል ወንድሜ አጣጣል ነው። አወ’ራ’ወር። የመወ’ርወ’ር መንገዱ…

***
ጀግኖች አምባ ሲፈርስ ጓዶቼ በጋሪያቸው፣ በክራንቻቸውና በወሳንሳቸው ለባለስልጣን አቤት ሊሉ አዲሳባ ሲመጡ፣ ነገር በመጠኑ ተረድቼአለሁና እዚህ መንገድ ገባሁ። የማላውቀው ሀገር።

ካሸነፈኝ ወያኔና ሻቢያ ምህረት አገኛለሁ?

ጅላዋት ሆይ፣ ጮማ ክፋት ከመጣ ሰላሳ እግዜር፣ ሰላሳ አላህ አይመልሰውም።

***
የወጣለት ተንኮለኛ ሰው የባዴ ስታይል ያደርጋል አሉ። በጎዳና ተዳዳሪ አንደበት፣ የባዴ ስታይል አይገድልህም ግን ክብርህን እየዘረፈ ባዶ ያስቀርህና ከዛ ራስህን ትገድላለህ። ከዛ እኔ ሳልሆን እሱ ራሱን ገደለ ብሎ ጋዜጣ ላይ ማስወራት ባዴ ስታይል ነው። ማለት በጥይት ሳይሆን በውርደት መረሸን ነው አሉ። እንግዲህ ትክክል መሆኑ አለመሆኑ አይደለም ዋናው፤ ዲሞክራሲ እንዲህ ነው እኮ ብሎ ስም መስጠቱ ነው። ክብር የሚጠላ የለም። ግን አርበኛን ብቻ ክብር ወዳጅ አድርገው ያሙታል። ነው እንዴ?

***
እና መሳሪያ ሆነች አልሆነችም ሞትን አንዴ ሳይሆን ዘጠኜ አሸንፌያታለሁ። የተደበቀ ሞት አልወድም። ሞትን እንደ ወንድ ፊት ለፊት ማወቅ አለብኝ። ከስንት ሺህ ሚሊሺያ ነው በ69 ከዘመተ የተረፍኩት? ሞትን ደግሞ የማሸንፈው እየሸሸሁ አይደለም። እየተዘጋጀሁ ነው። እዚህ የጎዳና ጉድጓድ የገባሁት ፈርቼ የሚመስለው ይኖራል። አይደለም ክብሬንና ኩራቴን እስከመጨረሻው ላለመዘረፍ ነው። ከጥይትና ከፈንጂ የሚመጣ ሞት ሳመልጥ፣ ዘመዶቿን ብርድን ተስቦን የመሳሰሉትን ትልካለች። መኖር እንደተፈቀደለት ሰው ጤንነቴን እጠብቃለሁ። ለመኖር የፈለግኩ ይመስላቸዋል። አይደለም ሞትን ለማሳፈር ነው።

ብሞት እንኳን እግዜር ጋር መሄድ አልፈልግም። አዚችው አገሬ ላይ እንደ አየር መንፈስ ነው የምፈልገው። በአገራችሁ ቃላት ስትረገሙ ቃል ሆኜ በጆሮአችሁ መግባት፣ ፉከራችሁ ውስጥ ግጥም ሆኜ መብቀል እፈልጋለሁ።

***
ጠዋት ጠዋት ከአልጋዬ ስነሳ እዛችው አደርኩባት ስፍራ ሰባ ሰማንያ ፑሽአፕ እሰራለሁ። ለምን በሉ? ሁለመናዬን ለማጠንከር። አንዳንዴ ወደኔ የሚላከው የሞት አይነት ገና ሲያየኝ እንዲፈራኝ ነው። መሞቴ አይቀርም። የምሞታት ግን በክብር ነው።

ይሄ ሻምበል ጉተማ የአገሩን ጠላቶች እና አቃጣሪዎቻቸውን ኦጋዴን ምድረበዳ የቀበረ፣ እዚህ እርጥብ ጥቁር አፈር ላይ ገምቶ አይወድቅም። የክንዴ ጡንቻዎች ቀላል አይደሉም። ሞቼ ብቀበር የትሎች ጥርስ ስጋዬን መንጨት አይችልም። ልምድ ያላቸው ትሎች ያውቃሉ። ሽማግሌ ትሎች ያውቁኛል። ይሄኛው ያርበኛ ስጋ ነው በኛ ጥርስ አይቻልም ይላሉ። ነገ መጥተን ደግመን እንሞክረዋለን ብለው ተቃጥረው ሲሄዱ፣ ሟሙቼ አድራለሁ። ነግቶ ሲመለሱ፣ እንዴ ይሄው የዛ ያርበኛ ነገር ያልነው ሆነ። ምኑንም አይሰጥም። ምኔንም አልሰጥም። ምን ይጎላል? ቂጣ በልቼ ለማደር እግር ልላስ? ባዕድ ሀገር ልሰደድ? በረሀ ያለ አድራሻ ልውደቅ? በባዴ ነገር ልበድ? በራሴ ፍላጎት ብቻ በጎቼ ይግጡት የነበረው ሳር የተመለሰበትን አፈር እሆናለሁ። ሰበቡ ….

***
የስንብት ቀለማት

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...