Tidarfelagi.com

‹‹እታባዬ…እታባዬ!›› 

ባለፈው ሰሞን አንድ ቀብር ሄጄ ነው። ሟች፣ እታባ ጠና ያሉ ሴት ነበሩ።

የእኛ ሰው ቀጠሮ የሚያከብረው ቀብር ሲሆን ብቻ አይደል? ምን ማክበር ብቻ? ቀድሞ ይጀምራል እንጂ! ያጣድፈዋል..ያዋክበዋል እንጂ! ስለዚህ ለስድስት ሰአት ቀብር መንገድ ተዘጋግቶብኝ እንዳላረፍድ ሰግቼ ከአምስት ሰአት በፊት ከቢሮ ወጣሁና አምስት ከሃያ ገደማ ቤተክርስትያኑ ደረስኩ።

ከእኔ ቀድመው መጥተው ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመውም ተቀምጠውም የአስክሬኑን መምጣት የሚጠባበቁ ሰዎችን አየሁ። ነጠላ አዘቅዝቀው የለበሱ ሴቶች፣ በጠራራ ፀሃይ የበረዶ ሃገር ሱፍ ካፖርት የደረቡ አዛውንት፣ ሚጢጢ ጥቁር ሻርፕ ጣል ያደረጉ ባለ ጅንስ ወጣት ሴቶች፣ ካናቴራ በጅንስ የለበሱ ወጣቶች ወንዶች……

የትልቅ ዛፍ ጥላ ሥር ካለ የድንጋይ አግዳሚ ወንበር ላይ አረፍ አልኩ።

እንደተቀመጥኩ ከእኔ ጀርባ እርምጃም ሳይርቁ ጥላ የሆነኝን ዛፍ ደገፍ ብለው ሹክሹክታም ጩኸትም በማይባል የድምፅ መጠን የሚያወሩ ጎልማሳ ወንድ እና ሴት ከእኔ በፊት የተጀመረ ወሬ ጆሮዬ ጥልቅ አለ።
>>>>>……>>>>>>

– እና ታዲያ…ጠዋት ቤት ሄደህ ነበር?
– እንዴ ምን ማለትሽ ነው…ምንም ዛሬ ነገሩ ቢበለሻሽ እታባ እኮ ነች…ሄጄ ነበር…
– ምፅ! እሱስ አዎ….! እንደው ልጆቹ እንዴት ናቸው? በተለይ ያች ትእግስት…እንደው እኔማ ንደሰማሁ ጉዷ ፈላ …ምን ይዋጣት ስል ነበር…ታመውም ስትባባ አልነበር?
– አዬ…ያዝ ለቀቅ እያደረጋት ቆየና ሲወስዳት….ያው ድንገት ሆነባቸው….የሚገርምሽ ግን ትእግስት እንኳን ደህና ነች…ይልቅስ የገረመኝ በዛችኛዋ ባሰ!
– በማ?
– ያቺ ያሳደገቻት ልጅ ናታ….የእህቷ ልጅ….
– ያቺ ቀይ ረጅሟ?
– እህ! ጸዳለ ነው ስሟ…እንዲያው የተወለደችው እያለች የእሷ ያዙኝ ልቁቁኝ ሰዉን ሁሉ ሲገርመው ነበር!
– ሆ…ሆ….! ምን ልሁን ነው ምትለው?
– እናጃላት…! ያው እንግዲህ ለዚያ መከረኛ ቤት ውርስ አትርሱኝ ይሆናላ!
– ተው ተው!
– ታዲያስ! አትርሱኝ…እኔም ልጅ ማለት ነኝ ለማለት ነው…ስለማትወለድ….
– አይ….ብቻ ካንጀቷም ሊሆን ይችላል…እንደ ልጅ ነው ያሳደጓት ሲሉኝ ነበር…እህታቸው ስትሞት…
– አዎ እሱማ ግን እንደው ብታያት ለሾው ይመስል ነበር…እምባ የሚባል ጠብ አይላትም…ግን ዝ…..ም ብላ ከጣራ በላይ ትጮሃለች….ሰው በገባ ቁጥር መሬት ትንፈራፈራለች…ቁርጠት እንደያዘው ሰው ያደርታል….ላይ ታች…ላይ ታች…..! ሰው መቼም ለዚህ ረጋፊ ጠፊ አለም እንዲህ ሲሆን ያሳዝናል…እታባን አያዩም? አንዱንም ሳትይዘው…አንድ ቀን ሳይደላት ይሄው ክትተት በላ….
– እሱስ ልክ ነህ አዎ…ሰዉ እሱን እየረሳ…ሞትን ይዘነው እየዞርን ለንብረት ላይ ታች ስንል ያሳዝናል..
– በጣም እንጂ…ሰው ሲያስመስል ደግሞ ይቀፋል…በጣም ይቀፋል…እንዴት ያለች ዱርዬ መሰለችሽ እኮ! አበሳዋን ነበር ምታሳያት! እሱ ይዞላት እንጂ በስተርጅና ስንት ዲቃላ ልታመጣባት ነበር…
– ልክ ነህ ብቻ….ይገርማል…ስታቃጥላቸው ኖራ ደርሶ አዛኝ ስትመስል አይደል? አይ ሰው!
– ታዲያስ !ብቻ ተያት…. ምናባቷ ታመጣለች! እሷ እንደ እምቧይ ብትፈርጥ ባለመብቷ ያቺ ናት…ትእግስት…!.እሷንም መድሃኒአለም ያለዘር አትቅሪ ብሎ በስተርጅና በስንት ምህላ የሰጣት ልጇ…
– አዎን…ዘር ጥሩ ነው…እንኳን ንብረታቸው ለባዳ ተበትኖ ያልቀረ….
– ታዲያስ! አሁንማ ቱስ ቱስ ባዩም ይበዛል…እኔም ያሰጋኝ እሱ ነው…
– ምኑ ነው ያሰጋህ?
– ቱስ ቱስ ባዩ መብዛቱ! ቤቱ ብዙ ዋጋ ያወጣላ! ባለፈው ስድሰት ሚሊዮን ዛሬ ልስጥሽ ስትባል እምቢ የልጄ ቅርስ ነው ብላ እኮ ነው አልሸጥም ያለችው…
– ስድስት ሚሊዮን?
– እህ!
– ባለፈው ታመው ልጠይቃቸው ሄጄ ነበርኮ…ትንሽ ቤት አይደለም እንዴ? ማነው ያበደ ያንን ስድስት ሚሊዮን ሚገዛው ባክህ?
– ትንሽማ ትንሽ ነው…ዛሬ ጠዋት እንኳን ስሄድ አምስት የማይሞላ ሰው ሳሎን ተቀምጦ እኔ ስገባ ጢም አይል መሰለሽ?
– እና ታዲያ እንዴት ይሄን ያህል ያወጣል?
– ቦታው ነዋ! ሎኬሽን ነው ዛሬ እኮ እናቴ!ሎኬሽኑ! ሃያ ሁለት አናት ላይ እኮ ነው ያለው!
– እሱስ አዎ…ጥሩ ነው ለልጅቱ…እሳቸውማ ከቤተክርስትያን መሳም ውጪ መች ያውቃሉ…ምስኪን!
– አዎ…እታባስ ክፉ መካሪው አላስኖር …እኛንም አሳቢ ዘመዶቿን አላስጠጋ ብሎ ከዘመድ አቃቃራት እንጂ እንጂ የዋህ ናት…ነበረች….ግን ምን ዋጋ አለው?
– እንዴት?
– ምን አለ በይኝ! ገና አርባዋ ሳይወጣ እንደ ዶሮ ገነጣጥለው ይሸጡታል! ወርም አያቆዩት….ብቻ ለሱም በተስማሙ!
– እህ..ምን የዛሬ ልጅ…ልክ ነህ! ግን …ግን ከትእግስት ውጪ ሰው አለ እንዴ? ማን ይካፈላታል?
– የእታባ ታናሽ ወንድም አለ…ይህችን ቀን ሲጠብቅ እዛው እኖረበት ቤት ያረጀ …አላገባ…አልወለደ…እዚያው ነው የኖረው….አምሳ አምስት አይሆነውም? የእናት አባታችን ቤት ነው ብሎ መካፈሉ አይቀርም!
– በስማም! ለንብረት ብሎ ነው እስኪያረጅ ያላገባው?
– ቢሆን ነዋ! እግሩን ላለማውጣት…ድሮ መተሃራ ይሰራ ነበር አሉ….እታባ መታመም ስትጀምር እሱም እግሩን ከዚያ ግቢ አልነቅል አለ!
– በስማም! ሰዉ እንዴት ተበላሽቷል….ሃጢያት አይፈራ…ገንዘብ ማሳደድ…!
– ምን ታረጊዋለሽሽ..ዘንድሮ ሁሉ ነገር በኪስ ሆነ…ክፉ ጊዜ ነው…ዝምድና ጠፋ…የእግዜር ሰው ጠፋ!
– አዬ!…በጣም እንጂ! የቁጣ ዘመን ነው…..ብቻ …ብቻ …ስድስት ሚሊዮን ካወጣ ጥሩ ይካፈሉታል…ምንም አይደል….
– አዎ እሱስ…ከደላላው ከምኑ ተርፎ ሁለት ተኩል ካገኘች ደህና ቤት ወጣ ብላ ትገዛለች….ብቻ…ግን ትእግስት የዋህ ናት ብታይ…የእግዜር በግ…ከትምህርት ትምህርት የላት…ኤለመንተሪም አልጨረሰች…..ወይ ብልጥ አይደለች…ስድስት ሚሊዮን ሲካፈል ለሁለት ሁለት ሚሊዮን ነው ቢላት እሽ ብላ ዞር የምትል አይነት ናት….
– ውይ! ተውንጂ!
– ሙች ! ከሰሞኑ ደግሞ የሆነ ባል ነኝ ባይ እንደ ጦስ ዶሮ ሲዞራት ነበር…ተካፍሎ እንዳይቀማት ፈርቻለሁ…
– አግብታለች እንዴ…?ማለቴ…ህጋዊ ጋብቻ አላቸው?
– እኔ ምናባቴ አውቄ…የሆነ ፀጉሩን ያቆመ ወጠጤ ብጤ ነው…ባልም አይመስል…
– አዬ! በሉ ምከሯት እንግዲህ
– ስትሰማ እኮ ነው….እሱ ላይ እንደተለጠፈች ነው…ይሄን ቀብር ሳይቀር የሚያዝበት እሱ አይደል…ለዚህ ሳይሆን ይቀራል እስካሁን የዘገዩት?
– አዬ…ዝርክርክ ነው ማለት ነው…እግዜር ይሁናት እንግዲህ!
– አዎ…ብቻ ኢንዲሲዥን ጥሩ አይደለም…አይመስልሽም?
– ኢንዲ- ምን?
– ኢንዲሲዥን…
– ማለት?
– አለመወሰን…
– እንዴት?
– ምልሽ አሁን የአዲስባ ነገር ..የፖለቲካው ሁኔታም አያስተማምንም…አንዱ መጥቶ የኔ ነው ቢልስ! ቶሎ ቀልጠፍ ብሎ ገንዘቡን እጅ ማስገባት ይሻላል…እስቲ እመክራታለሁ…እኔ ስለዚህ ቢዝነስ ብዙ አውቃለሁ….ከሰማችኝ…ብቻ እንዳልኩሽ ደንባራ ነገር ናት…ከእሱ ነጥዬ አገኛታለሁ እንጂ…እታባንም ስመክራት ደስ ያላላቸው ሰዎች ናቸው ያለ ስሜ ስም ሰጥተው ያራራቁን….ከሰማችኝ እነግራታለሁ…
– አዎ…ማድረግ አለብህ…አንተ እኮ አጎት ማለት ነህ….አግዛት.. እኔ ምለው..
– እ?
– ከእታባ ምን አጣላችሁ ግን? ቤቱን ሽጭው ብለሃቸው ነው እንዴ?
– አዬ…እሱ ረጅም ታሪክ ነው ልጄ…ብቻ ምን ዋጋ አለው….?እሷም ቀርታለች እንኳን ሌላው ነገር…
– እሱስ አዎ…ልጅቱን አግዛት እንግዲህ ….
– ለእታባ ስል አግዛለሁ እንግዲህ…ማለቴ…ምን ተቀያይሜ ብርቅም አሁን ልጅቷን ስትታለል ዝም ብዬ ባይ አጥንቷም ይወጋኛል …ጡር አለው….
– እህስ! ልክ ነህ…ደህና ያቋቁማታል…ስራም የላት ሲሉ ሰምቻለሁ
– አዎ…ከዚህ ውጪ ምን አላት? ሃጢያት ይሆንብኛል ገደል ስትገባ ባይ…እመክራታለሁ….
– አዎ…ለነገሩ….ለነገሩ እኮ ለአንተም ጥሩ ነው…ከመንግስት ስራ ከወጣህ ንብረት ማሻሻጥ ነው ምትሰራው አይደል አሁን?
– እ?
– የኮምሽን ስራ ጀምረሃል ብለው ሲሉኝ ነበር…..
– ….ውይ… መጡ! መጡልሽ…..ነይ…ነይ እንጂ ቶሎ! ……እናጅባት እስቲ….እናጅባት……እታባዬ እታባዬ! እታባዬ ለእኔ ይሁን…!ለእኔ ያርገው የኔ ደግ…!.ለእኔ ያርገው ….ለእኔ ያርገው ሰብሳቢያችን…እታባዬ…ሰብሳቢያችን….እታባዬ!

ጭንቅላቴ በወሬያቸው ተጣቦ ከበደኝ መሰለኝ ብዥ እያለብኝ በዝምታ አጀብኳቸው።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...