Tidarfelagi.com

እምቢ እሺ አይደለም…እሺ ብቻ ነው እሺ

ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከጓደኞቼ አንዱ የሚያሰቅቅ ነገር ላከልኝ።
አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ በመቶ የሚቆጠሩ ወንድም ሴትም ተማሪዎችን ያሳተፈ ጥናት ውጤት ነው። ጥናቱ ስለ አስገድዶ መድፈር ነው።
የመጠይቁ ብቸኛ ጥያቄ ይሄ ነው፤ ‹‹አስገድዶ መድፈር ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው በእንዴት ያለ ሁኔታ ነው?››
ምርጫዎቹ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።
ሰውየው ልጅቷ ላይ ብዙ ገንዘብ ካጠፋባት::
በፍጹም ስሜቱን መቆጣጠር ካቅተው::
ልጅቷ ከእሱ በፊት ከሌሎች ወንዶች ጋር ግንኙነት ከነበራት ::
ልጅቷ ከሰከረች ወይም አደንዛዥ እፅ ከወሰደች።
ከወገቧ በላይ እንዲነካት ፈቅዳለት ከነበረ።
መጀመሪያ የምትፈልግ መስላ ከዚያ ደግሞ ሃሳቧን ከቀየረችበት።
ካሳሳተችው።
በጓደኝነት ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተው ከሆነ።

እውነቱን እንናገር ከተባለ፤ በእኛም ሀገር ከእነዚህ ምርጫዎች ውስጥ ለአስገድዶ መድፈር በወንዶች በሰበብነት የሚቀርቡ፣ በሴቶችም ተቀባይነት ያላቸው ጥቂት አይደሉም።
አብሶ፣ እነ ‹‹ለምን በማታ ወጣች?››.፣
እነ ‹‹ማን አባቷ አጭር ቀሚስ ልበሺ አላት?››፣.
እነ ‹‹መጀመሪያውኑ ምን ፊት አሰጣት?››፣
እነ ‹‹ጓደኛዋ ከሆነ ምናለበት? ›› እና
‹‹ወንድ እኮ ራሱን መቆጣጠር አይችልም…ምን ያድርግ?››ን ለምደናቸዋል።
የዚህ ጥናት ውጤትም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው። ሴቶችም ወንዶችም እነዚህ ሁኔታዎች አስገድዶ መድፈርን በትንሹም ቢሆን ትክክል ያደርጉታል ብለው ያምናሉ።

እንደኔ እንደኔ ፤ አስገድዶ መድፈር በ‹‹ማርች ኤይት ሰልፍ›› እና በነ እንትና ኤን ጂ ኦ ‹‹ወርክሾፕ››፣ ‹‹ሲምፖዚየም››፣ ‹‹ኮንፍረንስ›› እና ‹‹ፈንድ ሬይዚንግ ፓርቲ›› ሊቆም ያልቻለበት ቀንደኛ ምክንያት ይሄው ነው።
በ‹‹ ሴት እህትህ፣ እናትህ፣ ሚስትህ ናት›› ዲስኩር የማይቀንሰው ለዚህ ነው።
በ ‹‹አሪፍ ወንድ ሴትን አይደፍርም!›› ብልጣብልጥ ዘመቻዎች ጋብ የማይለው ለዚህ ነው።
አስገድዶ መድፈር ከሌሎች ወንጀል በተለየ ተጠቂዋን ሴት ወንጀለኛ አድርጎ የሚያስቀምጥ ብቸኛ ወንጀል ሆኖ የቀረው እነዚህን ሰበቦች እንደ ተገቢ ምክንያት አድርገን ስለምንቀበላቸው ነው።
በግልፅ ተናገሩ ብንባል ፤ የአስገድዶ መድፈር ዜና የጋዜጦቻችን ቋሚ አምድ እስኪመስል በዝቶ ስናየው የማያስደነግጠን ውስጥ ውስጡን በነዚህ ሰበቦች ስለምናምን ነው።
ሴት ልጅ ‹‹ሚኒ ስከርት›› ከለበሰች ‹‹ድፈረኝ› ማለቷ ነው ብለን ስለምናስብ ነው።
ሴት ልጅ ጓደኛ ለመያዝ ከተስማማች ወሲብ ለመፈፀም ተስማምታለች ብለን ስለምንደመድም ነው።
በልባችን፣ አንድ ወንድ አንዲትን ልጅ ደጋግሞ እራት ከጋበዛት ወደደችም ጠላችም ፤ በልዋጭ ‹‹ያን ነገር›› ልትሰጠው ይገባል ብለን ስለምንወስን ነው።
ከሁሉም በላይ ግን፤ ሴት ልጅ ለወሲብ ጥያቄ ‹‹እምቢ›› ስትል ‹‹መግደርደሯ ነው እንጂ ‹‹እሺ›› ማለቷ ነው›› በሚለው አባባል ስለምንስማማ ነው።
‹‹የሴት ልጅ እምቢ እምቢ ነው›› ብለን መቀበል ስለሚያቅተን ነው።
እንደኔ፤ አስገድዶ መድፈር ፍጹም የማንቀበለው እና የሚያንገፈግፈን ነገር የሚሆነው፤
‹አስገድዶ መድፈር ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው በእንዴት ያለ ሁኔታ ነው?›› ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው ብቸኛ መልስ የሚከተለው ሲሆን ብቻ ነው።
‹‹በምንም ሁኔታ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም!››

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...