Tidarfelagi.com

እልፍ አእላፍ እኛ!

ቅዳሴው ሰማዩን ሰንጥቆት አረገ ….
በደስታው ከበሮ ልብ አረገረገ
መሬት አደይ ሞላች ውሽንፍሩ አባራ
የቢራቢሮ አክናፍ እልፍ ቀለም ዘራ
የፀሃይ ብርሃን በመንደሩ በራ…..

እንዲህ ከጎረቤት እልልታ ያጀበው የዶሮ ወጥ ሽታ
የነጭ ልብስ ወጋገን የሰዎች ቱማታ
እንዲህ ወደማጀት የተከፋች እናት አይኗ የቦዘዘ
በነጋ መስከረም ባልነጋ ነፍሷ ውስጥ ዝናብ ያረገዘ
እንዲህ ወደጥጉ ማታ ያከሰመው የጉልቻ ፋና
አመድ ረቦበት ባዶውን የቆመ የምድጃ ኦና
እንዲ ወደዚህ ጋ ምንም የማልጠብቅ ከሚመጣው ቀኔ
የጎረቤት ድሎት ጠረኑ ቀስቅሶኝ የተቀመጥኩ እኔ
ያደረበት ስይት እራብ የሚነጨኝ
የመገፋት መድሎ እያነጫነጨኝ

አመትባል ነው ለካ ….አመት ባል ነው ዛሬ
የነማን ዶሮ ነው በጠረን እግሮቹ ቤታችን የመጣው
እነማን ጓዳ ነው ፈንድሻ ሚንጣጣው ….
እንዲህ እየሳበኝ የጎረቤት ጠረን
ካንዲት እናቴ ጋር በአጎራባች ድሎት ቤታችን ተከበን

እንዲህ ወደከሳት …ቀስ ብየ መሄድ እግሬ ወደመራብኝ ….
የእርሃብ ቁስል ያመረቀዘብኝ …
ከጎረቤት ግገን …ከበር ላይ መቆም
የተድላ ሽታውን ባይን መለቃቀም
ና ግባ እንዲሉ በከፊል መታየት
በከፊል መደበቅ
ከቀዩ ከነጩ ….ከአጥንት ከመረቅ
እያዩ መሳቀቅ …
እንዲያ እያጮለኩኝ
እግዜርን ታዘብኩት …ምነው እኛን ብቻ
በአምሮት ሰቀቀን ደጅ የምታቆመን
ምነው እኛን ብቻ የምኞት ስንክሳር ምታስቀምመን
ምነው እኛን ብቻ…. የረገፈ እጣ የምታስለቅመን
ብየ ሳልጨርሰው ከኋላየ ግድም ሲነካኝ ሰማሁ ሰው …..?
ዞር …..በድንጋጤ ….!

ለካስ ከኔ ኋላ እኔን የመሰለ ከሚበሉት ቃየ ተዘርቶ ነበረ ….
እልፍ አእላፍ ማቲ …ከሰሜን ጀምሮ ደቡብን የነካ
እልፍ አእላፍ ወጣት…ከፀሃይ መውጫ ጥግ …እስከመግቢያ አድማሷ
የሞሉ ደጆችን በአይኑ እያንኳኳ

እልፍ አእላፍ አእሩግ ….ምርኩዝ ተደግፈው ማምሻቸው እንዳይመሽ የሚውተረተሩ
እልፍ አላፍ ቀነኞች ማዳቸውን ከበው ወደኛ ማይዞሩ
እልፍ አእላፍ እኛ ቁመናል ከግገን
ግማሽ እዩን እያልን ግማሽ ተሸሽገን !!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...