Tidarfelagi.com

እህል ወይስ አረም ?

አሁን ባለንበት ዘመን ያለን የኢትዮጵያ ትውልድ የሀገራችንን ታሪክ፣ የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትና የመሪዎቻችንን ሁኔታ ስንነጋገርና ስንጽፍ በአብዛኛው አሉታዊውን ነገር ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ፣ ጥላቻ እንዲበቅል፣ ቂም እድሜ እንዲያገኝ፣ ልዩነት እንዲሰፋ፣ ጠብም ሥር እንዲሰድ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይታያል፡፡ ርግጥ ነው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ የመስተጋብር ችግሮች ሁሉ በኛም ሀገር ተፈጥረዋል፡፡ በኛ ሀገር የተፈጠሩትም በሌሎች ይገኛሉ፡፡ በዓለም ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ የኩራትም የውርደትም፣ የፍቅርም የጠብም፣ የሰላምም የጦርነትም፣ የእኩልነትም የጭቆናም፣ የመረዳዳትም የመጠፋፋትም፣ የሥልጣኔም የስይጣኔም ታሪኮች አሉ፡፡ እንኳን በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያየ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ እምነትና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቀርተው በተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባሕልና የኑሮ ደረጃ የሚገኝ የአንዲት ሀገር አንድ ወጥ ሕዝብ እንኳን በውስጡ ጽጌረዳም እሾህም አለው፡፡

የሚገርመው ነገር ኢትዮጵያን ከዓለም የተለየች የሚያደርጋት ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያኮ ሲኦልም አልነበረችም መንግሥተ ሰማያትም አልነበረችም፡፡ ሀገር ነበረች፣ አሁንም ሀገር ነች፡፡ ሀገር የሚገጥማት ፈተና ሁሉ ገጥሟታል፤ ሀገር የሚኖራት ጸጋ ሁሉ ታድሏታል፡፡ በአንዳንድ የታሪክ ምእራፏ ለመንግሥተ ሰማያት ጠጋ፣ በሌላው ምእራፏ ደግሞ ለሲኦል ጠጋ ብላ ይሆናል እንጂ፣ ፈጽማ ሲኦልና መንግሥተ ሰማያት ሆና አታውቅም፡፡ እኛ ልጆቿ ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት ጠጋ ማለት ብቻ ሳይሆን ምድራዊት መንግሥተ ሰማያት ብትሆንልን እንወዳለን፤ ለዚያም እንሠራለን፡፡ ወደዚያ በተጠጋችበት ታሪክም እንኮራለን፤ ወደ ሲኦል ለመውረድ አዘንብላ የነበረችበትንም ዘመን ስናስብ በልብ ስብራት እንመታለን፡፡
የታሪክ ሂደት ያመጣቸውን የትናንት ነገሮች ዛሬ አንቀይራቸውም፡፡ ሆነዋልና፡፡ ነገር ግን እንማርባቸዋለን፤ ከትናንት ወስደንም ለዛሬ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ የዛሬ ማንነታችን መገንቢያም እናደርጋቸዋለን፡፡ በተቃራኒውም ያለፉትን ዘመናት ጠባሳዎች እየነካካን ቂምን ማመርቀዝ፣ ጥላቻን ማጎንቆል፣ ልዩነትን ማስፋት፣ ፍቅርንም ማደብዘዝ እንችላለን፡፡ ሁለቱም በእኛ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ምርጫው ለእህሉ ወይስ ለአረሙ ትለፋለታለህ? የሚለው ነው፡፡

ታሪካቸውን ለዕድገታቸውና ለሰላማዊ መስተጋብራቸው የተጠቀሙት ግን ከአረሙ ይልቅ ለእህሉ ጊዜና ጉልበታቸውን ያፈሰሱት ናቸው፡፡ ገበሬ ዓመት በሙሉ የሚለፋው አረም ለማብቀል አይደለም፡፡ አረም ለመብቀል ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ጉልጓሎ፣ አያስፈልገውም፡፡ ወንፈልና ደቦ አይሰበስብም፡፡ ጉልበትና ጊዜውን አያባክንም፣ ወዝና ላቡን አያንጠፈጥፍም፡፡ ለአረም አንድ ነገር በቂ ነው፡፡ ስንፍና ብቻ፡፡ ገበሬ ከሰነፈ ምንም ሳይደክም አረም እርሻውን ከዳር ዳር ይወርስለታል፡፡ በሬ ሳይጠምድ፣ እርሻ ሳይውል፣ ሌሊት ሳይነሣ፣ ማታ ሳይገባ፣ ዝናብ ሳይመታው፣ ፀሐይ ሳይከካው፣ ብርድ ሳይገርፈው፣ ወላፈን ሳይጠብሰው አረም እንዲሁ ይበቅልለታል፡፡ ገበሬ ለአረም አይለፋም፡፡
የገበሬን ጥበብ፣ የገበሬን ድካም፣ የገበሬን ጉልበት፣ የገበሬን ማዳበሪያ፣ የገበሬን ትዕግሥት፣ የገበሬን ሐሞት፣ የገበሬን ልምድ፣ የገበሬን ጊዜ፣ የሚፈልገው እህሉ ነው፡፡ ወንፈልና ደቦ የሚሰበስበው ለእህሉ ሲል ነው፡፡ በሬ የሚጠምደው፣ ሞፈር የሚቆርጠው፣ ቀንበር የሚነድለው፣ ጎተራ የሚያዘጋጀው፣ አውድማ የሚለቅልቀው ለእህሉ ሲል ነው፡፡ አረም በስንፍና የሚበቅለውን ያህል እህል የሚበቅለው በጉብዝና ነው፡፡ እህል ያለ ገበሬው ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ጉልበትና መሣሪያ ከምድር አይወለድም፡፡ አረም ግን አዋላጅ አይፈልግም፡፡ አረም በራሱ ተወልዶ በራሱ ያድጋል፡፡

በታሪክ መስክ ላይ የተሠማራ ትውልድም ጊዜውን ማጥፋት፣ ጉልበቱን መሠዋት፣ ጥበቡን ማፍሰስ፣ ዕውቀቱን መከስከስ፣ ያለበት ለአረሙ አይደለም፡፡ ጥላቻው፣ ቂም በቀሉ፣ መቆራቆሱ፣ መናከሱ፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ይኼ የትውልድ አረም ነው፡፡ በስንፍና ብቻ ሊበቅል የሚችል፡፡ በታሪካችን ውስጥ በቅሎ የነበረው እህል ፍቅራችን ነበረ፣ አንድነታችን ነበረ፣ መዋለዳችን ነበረ፤ መዋሐዳችን ነበረ፤ ሥልጣኔያችን ነበረ፤ ጀግንነታችን ነበረ፤ ነጻነታችን ነበረ፡፡ ትኩረታችንን እህሉ ላይ ካደረግነው አረሙን እንቋቋመዋለን፡፡ መቋቋምም ብቻ ሳይሆን እናጠፋዋለን፡፡ አረሙን ማጥፋት ያለብን አረም ስላልነበረ አይደለም፣ አረምን ለመሸፋፈን ሲባልም አይደለም፡፡ አረም ስለማይጠቅመን ነው፡፡ በሀገራችን እንክርዳድ የተሰኘው አረም ሳይለቀም ቀርቶ ከስንዴ ጋር ገብቶ ጠላ የሆነ እንደሆነ ያሳብዳል፡፡ ለዚህም ነው፡-
እንክርዳድ እንክርዳድ የተንከረደደ
ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ
የተባለው፡፡

አሁን አሁን በሀገራችን ጉልበታችንን እየጨረስን ያለነው አረሙን ለማብቀል ይመስላል፡፡ አንዲት ጽጌረዳን ከማብቀልና ፈንድታ አበባዋ ሠፈሩን እንዲያውድ ከማድረግ ይልቅ አንድ ማሳ ሙሉ አረም ማብቀል በጣም ቀላል ነው፡፡ አረሙ ስንፍናን ብቻ ይጠይቃልና፡፡ ጽጌረዳዋን ለማብቀል ግን ከመሬቱ፣ ከሰማዩ፣ ከአየሩ፣ ከአራዊቱ፣ ከአላፊ አግዳሚው ጋር መጋደልን ይጠይቃል፡፡

በታሪካችን ውስጥ የነበረውን እህል ዘሩን አምጥተን መዝራት፣ ዘርተን መከባከብ፣ ተከባክበንም ማሳደግ ይገባን ነበረ፡፡ ጥበባችንን፣ ዕውቀታችን፣ ገንዘባችንንና ጉልበታችንን ለእርሱ ማፍሰስ ይገባን ነበረ፡፡ አሁን ግን ድርሰቶቻችንን፣ ሚዲያዎቻችንን፣ ሐውልቶቻችንን፣ ትርክቶቻችንን፣ ዲስኩሮቻችንን፣ ንግግሮቻችንን፣ የፖለቲካ ፕሮግራሞቻችንን የምናባክነው አረሙን ለማብቀል ሆኗል፡፡ አረምኮ ይህንን ሁሉ አይፈልግም ነበር፡፡ አረምን ለማብቀል ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ፣ ዩኒቨርሲቲ መገንባት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ማደራጀት፣ ሚዲያ መዘርጋት፣ ብዕርና ወረቀት ማባከን፣ ምስትርናና ዱክትርና መድረስ አያስፈልግም ነበረ፡፡ አረም እንዲሁ ይበቅላልኮ፡፡

የፖለቲከኞቻችን ብስለት፣ የምሁሮቻችን ብቃት፣ የትውልዱ ምጥቀት፣ የተቋሞቻችን ሥልጠት፣ የሐሳቦቻችን ጥልቀት፣ የሚዲያዎቻችን ፍጽመት፣ የሥልጣኔያችን ርቀት፣ የጥበበኞቻችን ልህቀት የሚታወቀው ባበቀልነው እህል እንጂ ባበቀልነው አረም ብዛት አይደለም፡፡ ለአረምማ እነዚህ ሁሉ አያስፈልጉትም፡፡ እነዚህ ያስፈለጉት ሲቻል አረሙን ቀድሞ ለመከላከል፣ ካልሆነም የበቀለውን አርሞ እህሉን አህል ለማድረግ ነበር፡፡ ለማስተማር እንጂ ለማደንቆር ምን ትምህርት ቤት ይሻል? ለማዳን እንጂ ለማሳመም ምን ሆስፒታል ያስከፍታል? ለፍትሕ እንጂ ለወንጀል ምን ዳኝነት ያስፈልጋል? ለመግባባት እንጂ ላለመግባባት ምን ቋንቋ ያስፈልጋል? ለልዕልና እንጂ ለውርደት ምን ኪነ ጥበብ ያሻል? ለዓለም ዓቀፋዊ እሴቶች እንጂ ለጎጠኝነት ምን ጥበብ መፍሰስ ያሻዋል? ለማጥገብ እንጂ ለማስራብ ምን ፖሊሲ ያስፈልጋል? ለሥልጣኔ እንጂ ለስይጣኔ ምን ፓርቲ ማቋቋም ያስፈልጋል? ለጽድቅ እንጂ ለኃጢአት ምን የእምነት ተቋም ያሻል?

የኛ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት አረም ላይ እየፈሰሰ ነው፡፡ የገበሬ ጉብዝና በአረም ብዛት እንደማይለካው ሁሉ የትውልድ ጉብዝናም በአረም አይለካም፡፡ ‹እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ› እንዲሉ እንኳንና የእኛ ጥበብና ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ተጨምሮበት አረም በራሱም ሀገር ያጠፋል፡፡
እንዲህ እርሻው ሁሉ አረም እስኪወርሰው
የለም ወይ፣ የለም ወይ፣ የለም ወይ ባገር ሰው
ተብሎ የለ፡፡
አረም አያዋለዱ ሀገርን ለማሠልጠን መመኘት፣ ተኩላን እያረቡ የበግ ሥጋን እንደመመኘት ያለ ነው፡፡
በገበሬዎቻችን ታሪክ ውስጥ በ16ኛው መክዘ በሀገራችን ተከስቶ በነበረው የሃይማኖት ጦርነት ጊዜ ከ20 ዓመታት በላይ ገበሬው ተረጋግቶ በእርሻ ላይ ስላልነበር አገሩን አረም ወርሶት ነበር ይባላል፡፡ በዚያ ጊዜ ከሀገራችን ገጽ የጠፉ የእህል ዓይነቶች አሉ፡፡ ለዘር ተብሎ የተቀመጠው ወይ በቀጠና ምክንያት ተበልቶ፣ አለያም ቤቱ ሲቃጠል ተቃጥሎ፣ ካልሆነም የተቀበረበት ቦታ በዘመን ብዛት ጠፍቶ ሳይተኩ የቀሩ የእህል ዘሮች አሉ፡፡ የካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔርን ኅብረ ብዕር ያነበበ ሰው ከሚያያቸው የእህል ዘሮች መካከል ብዙዎቹ ስማቸውን ትተው ጠፍተው የቀሩት እንዲህ ባሉ ዘመናት ነው ይባላል፡፡ አረሙ ግን አልጠፋም፡፡ እንዲያውም ተመችቶት ነበር፡፡

በታሪካችንም ውስጥ እየጠፉና እየመነመኑ የመጡ በጎ እሴቶች፣ ባሕሎች፣ ልማዶችና ወጎች አሉ፡፡ አገር ችግር ላይ ስትወድቅ እህሉን የሚያመርተው ሲያጣ፣ ዘሩ ይጠፋል፡፡ ያንን ዕድልም አረሙ ይጠቀምበታል፡፡ ምድሩም እህል ተዘርቶበት የማያውቅ ይመስላል፡፡
አሁን ለዚህ ትውልድ ጥያቄው አንድ ነው፤ ለአረሙ እንድከም ወይስ ለእህሉ? እህሉን በማምረት ብርታትህን ታሳያለህ ወይስ አረሙን በማብቀል ስንፍናህን? የኢትዮጵያ መልክ የሚቀየረው ለዚህ ጥያቄ በምንሰጠው መልስ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...