Tidarfelagi.com

‘’ኤልያስ መልካ-ኒዝም’’

እመነኝ ጥበብን አታሳድጋትም ፤ በጥበብ ውስጥ ግን አንተ ታድጋለህ። የፈላስፋነት እና ፍልስፍና ትርጉምም ‹‹ምላሽ መፈለግ›› ነው። ኤልያስ መልካም በጥበብ ፍለጋው የ‹‹ለምን›› ጥያቄዎች አጭሮ ታገኘዋለህ። የቤትሆቨንም ምክር ይህ ነው፡- ‹‹Don’t only practice your art, but force your way into its secrets›› ስለሚልህ፤ ታዲያ በጥበብ ጣሪያ ስር ደረጃ እና መስፈርት ስታወጣም የኤልያስን ከፍታ በሙዚቃ ስራዎቹ ውስጥ ታገኘዋለህ። ምሳሌዎች ልስጥህ – በቡድን ስራዎች ምናልባትም ከደርግ ዘመን አብዮታዊ እና የቡድን ዝማሬዎች በኋላ በእነ ‹‹ማፍቀር መሰልጠን ነው ፣ አፍሪካ ፣ መላ በሉ፣ አይዞሽ ኢትዮጵያየ፣ አለፈ ( ሓሊፉ ) ከሙዚቃ ስራነታቸው በላይም ችኮ ሳይሆኑብህ መልዕክቶቹ እያዝናኑ ይደርሱሀል።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ እንደስትሪ እድገትም በ3ተኛ ትውልድ ተደማጭ የሚሆኑ ድምፃዊያንን በጥሩ ስራ እንካ አድምጣቸው ሲልህ ፣ ብቃት ያላቸውንም ሲያስተዋውቅህ፣ በቅንብር የተዋጣላቸው እና በአካባቢያዊ አጥር ስር የሆኑትን popular ሲያደርግ ስታይ እና ስትሰማ በታሪክ ማህደር ላይ ቅርስ እንደተወልህ በእነ ቴዲ አፍሮ ፣ ዘሪቱ ከበደ ፣ ማህሌት ገ/ጊዮርጊስ ‹‹በይነይ ተሪፈ›› ( በትግረኛ ስልተ-ምት ላይ ከተለመደው ወጣ ባለ Experimental music ሂደትን የተከተለ ሳፍያ አፅብሃንም በ‹‹ዋኒነይ›› የሙዚቃ ስራ ያስከተለ አድርጎልሀል ) ፣ ኪዳነ ኃይለ ‹‹ኦማኒንዳ ጉዳ›› ቅንብር አንዳች ነገር ትገነዘባለህ – ምርጥ ድምፅ አለኝ ብለህ በብዙዎች ያስመሰከርክ ድምፃዊ ከሆንክ ደግሞ ኤልያስ ከቀጠናህ ( comfort zone ) አስወጥቶ አዲስ ፈተና ያቀርብልሃል። ጌቴ አንለይን ካየህ በ Contemporary Music ትርክት በ modernism ፍልስፍና ውስጥ ብዙ ጥያቄዎችን ታነሳበታለህ ፤ አብረው የሚሰሩትን ድምፅ እና ባህሪ መረዳትን ደግሞ በእዮብ መኮንን ኢንደስትሪው ከለመደው ውጪ ፣ ገበያው ከደራበት ባፈነገጠ አቀራረብ ይዞ መምጣቱም አድማጭንም በ comfort zone መፈተኛ ሲያደርገው በኤልያስ ፍልስፍና የተጠመቀው እዮብም ጭምር ‹‹ጨለምተኝነትን፣ ክፋትን›› እንደማይሰብክ ይነግረሃል ፤ በቂ ካልሆነልህ የድፍረት ጥጉ ማሳያ ደግሞ ‹‹ ቤሪ ›› ላድርግልህ፤ ‹‹ ግን ለመሆኑ ኢትዮጵያዊት ናት?፣ ‹‹ፈረንጅኛ ትመስላለች?›› ብለህ እንድትጠይቅ ሲያስገድድህ የ Pentatonic እና Diatonic scale ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለቱም ስለመኖራቸው ጥያቄን ያጭርብሀል።

እንደ ‹‹ህሊና›› ባለ የሙዚቃ ስራ ላይ ደግሞ ፍሬድሪች ኒቸ የቀመረውን ናዚንም በግርድፉ ባሳሳተው ግን ደግሞ አባዜው በገሀዱ አለም አሁንም የምታየውን ‹‹ Master–slave morality ›› የምትንድበትን ሃሳብ ያቀርብልሃል በትልቁ ግን theological concepts ወደ ጭንቅላትህ እንዲመጣ ይነግርሃል። – የዘለቀ ገሰሰን የመጨረሻ አልበም ካደመጥክ ደግሞ ከአጋር ሙዚቀኞች እና ባለሙያዎች ያለውን ልዩነት ታያለህ ( የትዕግስ በቀለን፣ ታደለ ሮባ፣ ናትናኤል ኃይሌ፣ግርማ ተፈራ፣ ኃይልየ ታደሰ፣ ዘሩባቤል ሞላ ልመርቅልህ) ፤ በዘለቀ ገሰሰ አይዞን አልበም ሀገሬ ነጠላ ሙዚቃ ( music video ጥቅም ላይ በዋለው audio ) ገበያውን ሲፈትሽ / market test / ያሳይህ እና በአልበሙ ውስጥ ላይ ለማዳመጥ ስትሄድ ደግሞ ለየት ባለ Intro ታገኘዋለህ ግን ደግሞ በኤልያስ መልካ ስራ ነግሰው ( ቅንብር፣ ዜማ እና ግጥም ድርሰቶች ) ድጋሜ በሙዚቃው አለም በሙሉ አልበም ስራ ለመከሰት ያልታደሉ ድምፃውያንን ስታገኝ እንዳትገረም ? እነዚህ ድምፃውያን በኤልያስ ከፍታ የተቀመጡ ከቻልክ ደግሞ ጥሩ ስራ ፈላጊዎች ልትላቸው ትችላለህ ! ትዕግስት በቀለ፣ እዮብ መኮንን፣ ሚካያ በኃይሉ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ኃይሌ ሩትስ ፣ ቤሪ ፣ ጌቴ አንለይ ፣ ሀብታሙ እንግዳ፣ ሞኒካ ሲሳይ፣ መዝሙር ዩሀንስ … ( አንዳንዶቹ ሁለተኛ አልበም ለማውጣት በትንሹ 9 እና 10 ዓመት ሲወስድባቸው በድንገት ከዚህ አለም የተለዩም ታገኛለህ … / ምናልባት ግን የእነዚህ ድምፃዊያን ከሙዚቃው መራቅ በሌላ ምክንያት ልትሞግተኝ ትችል ይሆናል ፤ እኔም ግን የአመክንዮ ጥያቄ በማሳያነት በማንሳት ልመልስልህ እሞክራለሁ ፤ ምልከታየን ውድቅ የሚያደርገው ቢኖር የድምፃዊያኑ እውነተኛ ምላሽ ብቻ ያደርገዋልና።

በመጨረሻም የእነ ፍሬድሪች ኒቸ ፣ ፍሬድሪች ሸሊግ፣ ኢማኑኤል ካንት በሙዚቃ ላይ ያላቸውን ፍልስፍና Ralph Blumenau ሊነግርህ ሲንደረደር የሙዚቃ ፍልስፍና (philosophy of music) ስታጠና የሙዚቃ ትርጉም ፣ ሙዚቃ ከአእምሮ ጋር ስላለው ዝምድና ፣ እንዴት ሙዚቃ ስሜቶችን እና አስተሳሰብን እንደሚነካ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ ሊሰጥህ እንደሚችል ሲነግርህ ፣ Noah Potvin ደግሞ በኦክስፎርስ ዩኒቨርስቲ ድረ-ገፅ ስለ Music and spirituality at the end of life ሲያስረዳ ሙዚቃን ወደ እምነት ስትወስደው ከራስህ ዛቢያ ጋር እንደምትገናኝበት ይጠቁምሀል ( musical encounters are infused with spiritually-based beliefs and practices to provide individuals connections with themselves and others in uniquely powerful ways.)

ኤልያስ መልካም በቅንብር፣ በዜማ እና በፍልስፍናዊ ግጥሞቹ በእነዚህ ሁሉ መንገድ እየተጓዘ ምላሽን እየፈለገ ፤ ጥያቄን እያነሳ ፣ በጥበቡ ሲያድግ ከላይ በነገርኩህ እና በሌሎች ድምፃዊያን አንደበት ታገኘዋለህ። ጆሮ ስጠውና ደጋግመህ አድምጠው፤ በዛውም ግጥሙን የዜማ አወቃቀሩንም ለብቻ ፣ ግጥሙ ከዜማው ጋር በምን ያክል ደረጃ እንደተዋሀደ እያመላለስክ አጥና፤ በስተመጨረሻም ሙዚቃውን እንድትሰማ የሚያደርግህ ድምፅ ከድምፃዊው አግኝቻለሁ ወይ ብለህ ጠይቅ ? የኤልያስ ልዩነት ታገኝበታለህ፤ ጥበብን አሳድጋለሁ ከሚልህ ይልቅ ጥበብን እየፈለገ ያለውን በልዩነት ታደንቃለህ።
ታዲያ ግን የኔ ትውልድ ሆይ! የኤልያስ መልካን አካላዊ ገፅታ እያየህ አትደናገጥ፤ የ’ሱ መብራት የደበዘዘው የሌሎቹን ሲያደምቅ ነው!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...