Tidarfelagi.com

ኤሊቱ ብዙ ነው መዓቱ

ኤሊቱ ኤሊቱ
ብዙ ነው መዓቱ

እኔ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ ቀሪዎቹም ኤሊቶች የኦሮሞን ሕዝብ ይጠሉታል የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረስኩ ቆይቻለሁ። የሚገርመው እንደሚጠሉት አያውቁም ወይም መቀበል አይፈልጉም።
የራስህን ሕዝብ ካልጠላኧው በቀር፣ በድህነት መዶቀሱን እንደሌለ እውነታ እየከለልክ እንዴት የብሔር ጉዳይ ላይ ብቻ ቸንክረህ አሻግሮ እንዳያይ ትጋርደዋለህ? ካልጠላኧው እንዴት ደህና ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት እስከዛሬ በስሙ ለማቋቋም ሰንፈህ፣ ላንተ የቆመ ሚዲያ እያልክ ከመቀነቱ ገንዘብ እየፈታህና እራስህን ዲታ እያደረክ ኑሮው ላይ፣ አሻግሮ ማየቱ ላይ ትቆማለህ?

እንዴት እንደ ጠንቋይ ቀላቢ «ደም ይፈሳል» እያልክ ሰርክ ልቡ ላይ የስጋት እና የፀብ ስሜት እንዲፈላ ታደርጋለህ? አንተ ሁለትና ሶስት ቋንቋ አቀላጥፈህ እየተናገርክ እንዴት አንድ ቋንቋ ላይ ቆሞ የሚቀርነትን እድል ትሰብካለህ? ሰፊ ዓለም አይቶ፣ ለዓላማህ ከመሮጥ እንዳያመልጥህ አይደለም?
·
ጃዋርም በለው ሌላው ሕዝብ ወዳጅ መስሎ ቢቀርብ አትመን። ራሳቸውን ነው የሚወዱት! አዳሜ በኦሮምኛ ጥናታዊ ፅሁፉን አይፅፍም። ለምን? ገንዘብ እንደሚፈለገው አይሰራማ። ዞር ብሎ ቋንቋችን ይልሃል፤ የተጨነቀው ለቋንቋው ሳይሆን ነገ ከነገ ወዲያ ከሱ የዝመት ትእዛዝ ወጥተህ ሌላ አይነት ሶሻላይዜሽን ውስጥ ገብተህ እንዳትጠፋ ነው። ምክንትያቱም እንደዛ ከሆንክ ለቅፈላ አትመችም። ስለሚጠሉህ ወይም በራሳቸው የጥቅም መነፅር ስለሚያዩህ አሁን ካለህበት ፈቅ እንድትል አይሹም። ሁሌ የገቢ ምንጫቸው፣ ሁሌ የምትታለብ ላም ሆነህ እንድትዘልቅ ነው የሚፈልጉት።
·
ደም ይፈሳል ይሉሃል። እንደውነቱ ከሆነ ያንተ ደም ምናቸውም አይደለም። ስለዚህ በደምህ ለመደራደር ይፈልጋሉ። ሲልም ደምህን ወጥተህ እንድታፈስ ግፋ ይሉሃል። ከራሳቸው ወይ ከዘመዳቸው ደም ግን ጠብታ አይፈስም። ያልጠላኧውን ሕዝብ ፀብ ባለበት ሁሉ ስለመማገድ ትቆዝማለህ?
እንጮሃለን ይሉሃል እንጂ በጩኧትህ ሰዓት ከነቤተሰባቸው ሀገር ውስጥ የሉም። እንሞታለን ይሉሃል እንጂ ሙቀቱ ሲቀየር ድራሻቸው ጠፍቷል። እንቆስላለን ይሉሃል እንጂ አይመቱልህም።
·
በዚህ ሁሉ ውስጥ፣ ተበላህ እያሉ ሌላ ሕይወትህ ላይ እንዳታተኩር ቸንክረው ይይዙሃል። የኢኮኖሚ፣ የፆታ፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የስራ ሁኔታ አያሳስባቸውም። በነጠላ ችግር ላይ ሰቅዘው አምጣ አምጣ እያሉ ከኪስህ ኪሳቸውን ይሞላሉ። አንተ ጀግኖቻችን ትላለህ። ለነሱ ግን የገንዘብ ምንጫቸው ነህ። «ለኛ ብለው» ትላለህ እነሱ ግን ለራሳቸው ብለው ከሆነ ቆይቷል!
.
የሰሞኑን የቋንቋ ነገር ብቻ አንሳ። ካጠሩልህ አጥር እንዳትሻገር ስለሚፈሩ አይሆንም ይሉሃል። ምንድነው ችግሩ ብትል በውል አይነግሩህም። ችግሩ ከቅንፋቸው እንዳትወጣ ነው። ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝማችን ይሉሃል እንጂ፣ የሚጨነቁት የገቢ ምንጫቸው ከመሆን እንዳታመልጥ ነው።
·
በትምህርታቸው ሰቃይ የሚባሉት ፊንላዶችን ሂድና እይ። ስንት ተጨማሪ ቋንቋዎች እንደሚማሩ አየት አየት አድርግ። ከመጠቀም አልፈው፣ ትምህርት ማለት እንዲህ ነው ተባለላቸው እንጂ ማንነታቸውን አላጡም። ሲጀምር ማንነት ቋንቋ ብቻ አይደለም። ግን ቋንቋው ላይ ካልተቸነገርክ ወደ ሌላ ነገር ታነጣጥራለህ ብለው ስለሚሰጉ ቀድመው ይጋርዱሃል።
·
ወገን በግልፅ እናውራ ካልን አማርኛ ቋንቋ ሀገራችን ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች በላይ በደንብ ታስቦበታል። እኛ እሱን በማወቃችን ፕሪቪሌጅድ ነን። ጉዳዩ ቋንቋውን እየለመዱ ሌሎቹንም ቋንቋዎች ወደዚህ ደረጃ ማምጣት መሆን ሲገባው አትድረሱብን አንደርስባችሁም ይባላል። ለምን ብለህ ጠይቅ!
·
ጥያቄያቸው ከዚህ በፊት ቃል እንደተገባው በአማራ ክልልም ኦሮምኛ ይሰጥ እኛም ጋር ከታች ጀምሮ አማርኛ ይሰጥ አይሉህም። ጭንቀታቸው ቋንቋ አይደለማ! ኦሮምኛው አደገ አላደገ አይደለም ጉዳያቸው። ተቀባይነታቸው እንዳያንስ፣ ኪሳቸው እንዳይጎድል ነው። ሌሎች ቋንቋዎችን አውቀህ እየተዋሃድክ ተነጥለህ ዝመት ስትባል አለመገኘትህ ነው የሚያሰጋቸው።
·
ይደግ የሚለው ላይ እንድታተኩር አይፈልጉም። እንትን ይነሳልን፣ እንትን ቋንቋ እንዳይጫንብን የሚለው ላይ እንድትቸነከር ነው የሚፈልጉት። ስጋት ካልተሰማህ ለመታዘዝ አትመችማ። ልትዋጥ ነው ካልተባልክ ለዓላማቸው አትቀባበልም።
·
ልብ አድርገህ ስማ። ተወረሃል ወይ ልትወረር ነው ብለው ነው የሚነግሩህ። የሰጋ ሕዝብ ለመቀፈልም status quo ለማስቀጠል ሸጋ ግብዓት ነዋ! እንጂ ያንተም ቋንቋ ሌላ ቦታ ስለሚያድግበት ነገር ቢያወሩ/ ቢደራደሩ ምን ክፋት አለው? ነገ ከነገ ወዲያ የስራ አክሰስህን ያሰፋልና የራስህንም ሳትለቅ እዚህም ላይ በርታህ ሊሉህ ለምን ጠሉ? የምክንያታዊነትህን ቡቃያ ሁሉ ገርዘው ካልጨረሱት ጠርጥር!
.
.
.
የሆነስ ሆነና አዳም ረታን አንብበሃል?

*ማሳሰቢያ፣ ለጊዜው ባለው ሙቀት የአንድ ብሔር ኤሊቶች ላይ አተኮርን እንጂ፣ የተባለው ሁሉ ለሌሎች ብሔር ኤሊቶችም ይሰራል!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • temushashe15@gmail.com'
    temsgen gabrie commented on August 15, 2021 Reply

    በጣም ሚያስማማ ነገር ነው እኛ አገር ያስቸገረን
    ብሄርተኛ መሆናችን ነው ቋንቋ ደግሞ መግባቢያ ነው
    እንጂ አንተ ለምን አማርኛ አወራ ለምን ኦሮምኛ አወራ ብለን ምንጨራረስበት አይደለም

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...