Tidarfelagi.com

“ኢትዮጵያ ደግሞ… አጉል ትመፃደቃለች!”

ይሄ ለስራ የመጣሁበት አፍሪካዊ ሃገር የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበር።
መቼ እለት ነው… የዚህ አገር ዜጋ ከሆኑ የስራ ባልደረቦቼ ጋር ሻይ-ቡና ስንል የ‹‹በቃ›› ወይም ” #No More›› ንቅናቄ በወሬ ወሬ ተነሳና ብዙ ነገር ሲያስመዝዘን አመሸ።

በዚያ ሰሞን የበቃ ንቅናቄ ጀማሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ፣‹‹እንደውም ለምን እኛ ብቻ…? ድፍን አፍሪካ አዲሱን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አሻፈረኝ ማለት አለበት‹‹ ብለው ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ከፍ ሲያደርጉት እዚሁ ነበርኩ።
በዚህ ጥሪ ግን ከዚህ አገር ጓደኞቼ መሃከል ደስ ያላላቸው ነበሩ።

ያበጠው ይፈንዳ ብለው በግልፅ፣ ‹‹ኤጭ! ኢትዮጵያ ደግሞ አጉል ትመጻደቃለች….›› ያሉኝምነበሩ።
አንዳቸው ለአንዳቸው ተደርበው፣
‹‹እርግጥ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ናት። ኩዋሜ ንክሩማ ሳይቀር ‹‹ትነሳለች›› ብሎ በቅኔ የተነበየላት…የምንኮራባት ሃገር…›› ብለው ጀመሩ።
ቅቤ መቀባቱ ግን አልዘለቀም።
ወዲያው፣
‹‹ግን እውነቱን አፍርጪው ካልሽን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንኳን አፍሪካን ለአዲስ ነፃነት የማነቃነቅ ጉልበት፣ የራሷን አንገትም መሸከም ያቃታት ሃገር ናት። ጭራሽ እኛን እንዲህ ሁኑ፣ እንዲህ አድርጉ የማለት የሞራል ልእልና የላትም…በእርግጥ ያኔ እናንተ ሳትገዙ እኛ ተገዝተን ሊሆን ይችላል። ግን አሁን ነፃ ነን.. እናንተ ግን ዛሬ እርስ በርስ እየተባላችሁ ነፃ ነን ማለት ትችላላችሁ? ›‹ እያሉ በብዙ ቃላት፣ ለብዙ ደቂቃዎች አንጀቴን አቆሰሉት።

ሃገሬ ለአፍሪካ እና ለጥቁር ህዝብ የዋለችውን ውለታ፣ትሩፋቷን ልዘረዝርላቸው የሚገባ አይነት ሰዎች አይደሉም። የተማሩ፣ የነቁ እና በንባብ ብቻ ሳይሆን በጉዞ መሃይምነታቸውን ያከሙ ናቸው።
ስለዚህ ጊዜያዊ ችግራችንን አይተው የዘመናት ችሮታችንን ማሳነሳቸው፣ በአደባባይ እናታችን በሚሏት ሃገር ላይ በየሻይ ቤቱ መሳለቃቸው፣ የአንበሳነት ታሪካችንን በፍጥነት ለመሰረዝ መሽቀዳደማቸው ፣ እኛማ አሁን ነፃ ነን ብለው መመፃደቃቸው ግን ነደደኝ።
ያኔ ነው….በንዴቴ መሃል…የምለውን እያሰላሁ፣ ለመልስ ምት ስዘጋጅ ካፍቴሪያው ውስጥ ተከፍቶ ከነበረው ቲቪ ላይ አይኔ የተሰካው።
ከመጣሁ ጀምሮ ሱስ የሆነብኝን የሃገሩን ተወዳጅ ተከታታይ ድራማ እያሳየ ነበር።
ታሪኩ የጠበቆች ነው። በዚያች ደቂቃ ይታይ የነበረው ትእይንት ደግሞ ምን ነበር? እንግሊዛዊያን ከሃምሳ አመታት በፊት ቅኝ ግዛታቸውን ጣጥለው ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ትተውት የሄዱትን ጠበቆችና ዳኞች ችሎት ሲታደሙ የሚያጠልቁት ወርቃማ ዊግን ያጠለቁ ጥቋቁር ሰዎች።
ይሄ ዊግ ዝነኛው የእንግሊዝ ንጉስ ጆርጅ ሶስተኛውን ጨምሮ ይሄን ሃገር ጠፍንገው ሲገዙ የነበሩ እንግሊዛውያን የህግ ሰዎች ለዘመናት ፍርድ ቤት ሲያጠልቁት የነበረ ከፈረስ ጠጉር እንደ ሹሩባ ተገምዶ የተዘጋጀ የኮፍያ ዊግ ነው።
እንደሰማሁት ፣ ምቾት ከመንሳቱ የተነሳ እንግሊዞቹ ራሳቸው ከአመታት በፊት ትተውታል።
ወርቃማው ዊግ ግን ዛሬ ድረስ፣ ነፃ ወጥተናል በሚሉ የቀድሞ ቅኞቻቸው የህግ ሊቆች ጥቁር ራስ ላይ በኩራት ተቀምጦ ይገኛል።
እነዚህ ሰዎች ናቸው ‹‹እኛ ነፃ ወጥተናል። ኢትዮጵያ መጀመሪያ ለራሷ ትሁን›› ብለው ረጅም ስር እና ታሪክ ያላትን ሃገሬን የሚሰድቡት።
ያቺን ሰአት እና ያንን ትእይነት ያገጣጠመ የኢትዮጵያ አምላክ ክብር ምስጋና ይግባውና፣ ስድባቸውን ከዊጉ አያይዤ ‹‹እስቲ መጀመሪያ ይሄንን ዊግ አውልቁ›› አልኳቸው። ለነጻነት የሞቱት አያቶቻቸው ይሄን ቢያዩ ምንኛ እንደሚያፍሩባቸው እስከ ፑንት ድረስ ነገርኳቸው።
ከሁሉ የቆጨኝ ግን ይሄን ሁሉ ሃተታ ትቼ በሚገባቸው ቋንቋ፣
‹‹የጎባጣ አሽከር ጎንበስ ብሎ ይሄዳል
ምነው ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል ይላል››
ማለት አለመቻሌ ነው።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • binhus1234@gmail.com'
    ባንጃዉ! commented on January 14, 2022 Reply

    እናትሽ ወልዳሻለች

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...