Tidarfelagi.com

ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል

ዳሠሣ መጻሕፍት ዘወርሃ ግንቦት

ዛሬ የምነግራችሁ አማራን በመጥላትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ስለተጋውና ለዚህም ህልሙ መሳካት ጥለቻን በመጽሐፍ ከትቦ ለትውልድ ስላቆየው አውሮፓዊ ሮማን ፕሮቻዝካ እና ስለ መጽሐፉ ነው።”ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል” የመጽሐፉ ርዕስ ነው።በባሩድ በርሜል ፍንዳታ ትፈራርስ ዘንድ ስለተፈረደባት ሃገር ኢትዮጵያ በመርዝ ጭስ ታፍኖ ይሞት ዘንድ ስለተበየነበት አማራ በዝርዝር የመጥፊያውን መንገድ ይናገራል።ደራሲው ኢትዮጵያ ላይ ካለው የመረረ ጥላቻ በመነሳት ኢትዮጵያ የምትባል ሃገርና አማራ የሚባል ህዝብ እንዲጠፉ ሃገሪቱ በዘር በቋንቋ በሃይማኖት ተከፋፍላ ብትንትኗ ካልጠፋ ለአውሮፓውያን የመስፋፋት መንገድ እንቅፋት እንደሆነች አበክሮ ይመክራል።ለዚህም የክፉ ሰው ሽንት ፍሬ አፍርቶ ዘር ተክቶ አብቦና ጎምርቶ እንደ ታይም ቦምብ በየቦታው እየፈነዳ እያየነው ነው። የግብር ልጆቹም ህገ መንግስት በተሰኘ የተንኮል ድርሳናቸው ለጥላቻው መልክና ድርሳን ጽፈውለት አይዞህ አለንልህ በማለት ተባባሪነታቸውን ገልጸውለታል።
.
ከቅድመ ጣሊና ወረራ ጀምሮ ድሩን ያደራው ይህ ክፉ ሰው በኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ደህንነት ላይ ታሴራለህ ተብሮ ከኢትዮጵያ እስከ ተባረረበት እስከ 1934 እአአ ድረስ በአዲስአበባ በሚገኙ የተለያዩ ዲፕሎማቲክ ስብሰባወችና በአውሮፓውያን የቆንስላ ልዩ ፍርድ ቤቶች እየተገኘ መርዙን ሲዘራ የኖረ ቀሳጢ ነው።መጽሐፉ በተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች ተተረጉሟል።የመጀመሪያ ስራው በ1935 እአአ በጀርመንኛ ቋንቋ ተጽፎ በዚሁ ዓመት የእንግሊዝ ዓለማቀፍ የዜና አገልግሎት በእንግሊዘኛ ቋንቋ “ABYSSINIA :THE POWDER BARREL –A BOOK ON THE MOST BURNING QUESTION OF THE DAY” በሚል ርዕስ ተርጉሞ በ94 ገጽ ወስኖ አቀረበው።የእኛው እውቁ ከያኒ ደበበ እሸቱም ዓለም በእኛ ላይ ምን ሲሴር እንደነበር ትውልዱ ያውቅ ዘንድ ለነገም ይጠነቀቅ ዘንድ መጽሐፉ ከተጻፈ ከ65 ዓመት በኋላ በ2007 ዓ.ም “ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል- የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ” በሚል ርዕስ ተርጉሞ በ54 ገጽ ወስኖ አቀረበው።

ዘረኛው ጠበቃ ሮማን ፕሮቻዝካ መጽሐፉን በሦስት ምዕራፍ ከፍሎ አራተኛ ላይ የማጠቃለያ መርዙን አክሎ ይጨርሳል።

ምዕራፍ 1 ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምንድን ነው” በሚል ርዕስ ተነስቶ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል።ስለ ሃገሪቱ መልክዓ ምድራዊ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነት ሲደሰኩር ከቆየ በኋላ ቅኝ ተገዥ ከሆነው ከሌላው ዓለም ህዝብ የሚያገኙትን ክብርና ታዛዝነት እትዮጵያ ውስጥ ማጣታቸውን ደራሲው ሳይደብቅ ይነግረናል።”ይህንን ኩራታቸውን አደብ ካላስገዛንና በቸልታ ከታለፈ ወደ ሌሎቹ አዋሳኝ የአፍሪካ ሃገሮች ተሸጋግሮ ዋጋ ያስከፍናልና መፍትሔ ያሻዋል” በማለት ለአውሮፓውያን ይመክራል።አክሎም “የአማራ ብሔር ለውጭ ሃይሎች ያለው ጥላቻ ለሁሉም የውጭ መንግስታትና ዜጎች አሳሳቢ ሆኗል።የኢትዮጵያ ህዝቦችና ነገዶች በዘር በቋንቋ በባህል ከኢትዮጵያ ገዥዎች ጋር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ ገና ዱሮ የኢትዮጵያዊነትን አስኳል ከውስጣቸው እጥተው በጣሉ ነበር።ሁኔታው ግን ከዚ የተለዬ ነው።ከአውሮፓውያን ተሰሚነትና ተራማጅ አስተሳሰብ በተቃራኒ ለራሳቸውና ለሃገራቸው ሊያስገኝላቸው ከሚችለው ጥቅምና ግንዛቤ አራርቀው በተጽዕኖ እየገዟቸው ነው።” በማለት አዛኝ ቅቤ አንጓቹ ጠበቃ እርስ በርስ የምንባላበትን አጀንዳ ይነግረናል።ይህች ሥልጣኔ ያላያት እድገት የምትጠላ ሃገር ወደ ዓለም ማኅበር ሌግ ኦፍ ኔሽን ልትገባ አይገባትም በማለት የጥላቻውን ጥግ ይነግረናል። ደራሲው ከግብር ልጆቹ የሚለየው በአንዲት ነገር ብቻ ነው።ለግርማዊነታቸው አፄ ኃ/ሥላሴ መጠነ ሰፊ ጥላቻ ቢኖረውም አፄ ሚኒልክን ግን “ልባሙ ንጉሥ” በማለት በተደጋጋሚ መልካም ነገራቸውን እየጠቀሰ ያወድሳቸዋል።

ምዕራፍ 2 “ጥቁር መጽሐፍ የኢትዮጵያውያን የጥቃት ስንዘራ” በሚል ርዕስ ተነስቶ ነጮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጡ የሚገጥማቸውን መከራና ሰቆቃ በመዘርዘር ያለቃቅሳል።ለውጭው ዓለምም ለጥቁር አሜሪካውያን ሳይቀር ኢትዮጵያ ማለት ለእንግዳ ክብር የማትሰጥ የምድር ሲዖል እንደሆነች አድርጎ ይስላል።በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ዜጎች ጋር የተደረጉ ግላዊ አለመግባባቶችን ሃገራዊ አጀንዳ አስመስሎ በማቅረብ መርፌዋን እንደ ግመል በማሳበጥ ሃገሪቱን የተቀረው ዓለም አክ እንትፍ ብሎ እንዲተዋት የውሸት ድርሰቱን ከጥቂት እውነት ጋር አጋኖ በማቅረብ የሃገሪቱን ጠባሳ ያሰፋዋል።

ምዕራፍ 3 “ኢትዮጵያና ሌላው ዓለም” በሚል ርዕስ ተነስቶ የውጭው ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ግንኙነትና በነሱ ጉዞ ላይ ስለሚፈጥረው መሰናክል ስለ ሃገሪቱና ሌግ ኦፍ ኔሽን ስለ መሆኗ ተጽዕኖ ሃገሪቱ ጦርነት ለማከናወን ስላላት አቅምና ስለ ሃገሪቱ መንግስት የመረዳት መጠን የራሱን ውስጠ ምርዛዊ ትንታኔ በመስጠት ኢትዮጵያ አፍሪካ በምዕራባውያን እዝ ስር ሆኖ እንዳይሰለጥን የተቀመጠች ደንቀራ መሆኗን በማጠቃለያው ገልጾ አውሮፓውያን ሃገሪቱን ልክ እንዲያስገባት መክሮ መጽሐፉን ይደድማል።
ካነበብሁት ዓመታት ቢቆጠሩም እንደገና ተመልሸ በእኛ ላይ ማን ምን እያሴረ እንደሆነና እንደነበረ ታውቁና ታስቡ ዘንድ ስለ መጽሐፉ ነገርኋችሁ።ታነቡት ዘንድ ወንድማዊ ምክሬ ነው። መጽሐፉ በአማረኛ ገበያ ላይ ይገኛል።በእንግሊዘኛ የሚፈልግ ካለ ደግሞ በሶፍት ኮፒ ከእኔ ጋ ስለሚገኝ መጠየቅ ይቻላል።
.
ማንበብ ጎደሎ ያደርጋል።
ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም
 አፄ እንደልቡ

One Comment

  • fbekele660@gmail.com'
    fikru bekee commented on June 2, 2022 Reply

    መፅሐፉ ገበያ ላይ የለም በpdf ብትወጡትስ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...