Tidarfelagi.com

አፍረን ቀሎ እና የአቡበከር ሙሳ ገድል (ክፍል ሁለት)

የአቡበከር ሙሳ የኪነ-ጥበብ ስጦታ በጣም ይደንቃል። ራሱን በአንዱ የጥበብ ዘውግ ሳያጥር ሁሉንም ያዳርሳል። በአንድ ወቅት ዓሊ ቢራ ቃለ-ምልልስ ሲደረግለት “ፊሎሶፈር ነበር” ብሏል። አቡበከር ከጻፋቸው ዘመን አይሽሬ ድርሰቶች መካከል ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንጥቀስላችሁ።

ሐሚዶ መሐመድ ድሬ ዳዋ ካፈራቻቸው የአፍረን ቀሎ ቡድን ዝነኛ ተጫዋቾች አንዱ ነበር። ይህ ሐሚዶ እስከ አሁን ድረስ የማትረሳ አንዲት ውብ ዘፈን አለችው። የሚገርመው ነገር ብዙዎች የዘፋኙን ስም አያውቁትም። ይሁንና ዘፈኑን በዜማው ብቻ የሚያውቁት በርካቶች ናቸው። በተለይ በርካታ የሙዚቃ ተጫዋቾች የዘፈኑን ግጥም ባያውቁትም ዜማውን በደንብ እንደሚያውቁት ለመታዘብ ችያለሁ። አንዴ እንዲያውም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የማውቀው ልጅ ዜማውን በኦርጋን ሲጫወት ሰማሁና “ይህንን ዜማ እንዴት ልትጫወተው ቻልክ?” በማለት ጠየቅኩት። ልጁ “በሙዚቃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት” በማለት ጥያቄዬን ሲመልስልኝ በጣም ነበር የደነቀኝ። “ዘፈኑ እስከ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ድረስ ሊገባ የቻለው ሰዎችን የሚስብበት አንዳች ሚስጢራዊ ጉልበት ቢኖረው ነው” በማለትም ተደመምኩ።

ያንን ዘፈን በዜማው ላሳያችሁ አልችልም መቼስ! የዘፈኑ አዝማች ግን የሚከተለው ነው።
Haayaa nagayyatti
Lolaa mitii daddatti
Osoo jirtuu jaalalti
Eefa dhufte jibbanti

በአማርኛ እንሞክረው እንዴ? መቼስ ይህ የትርጉም ነገር ኦሪጂናሌውን ግጥም ከነነፍሱ ሊመልሰው እንደማይችል ደጋግሜ ገልጬአለሁ። ይሁንና የግጥሙን ሐሳብ ሊያንጸባርቀው ይችላል። እናም ወደ አማርኛ እንዲህ ቀይሬዋለሁ።
እስቲ በይ ደህና ሁኚ
በጥል ሳይሆን በሰላም ጥኚ
መፋቀርና መዋደድ እያለ
ጥላቻው እንዲህ ፊት ለፊት ከዋለ።

ዓሊ ሸቦን ታውቁታላችሁ አይደል? አዎን!… ከአንጋፋዎቹ የአፍረን ቀሎ ቡድን አባላት አንዱ ነው። ዓሊ ቢራ በአቡበከር ሙሳ ድርሰቶች ዝና ቢቀዳጅም በህጻንነቱ ሙዚቀኛ ለመሆን የተደፋፈረው የዓሊ ሸቦን አዘፋፈን በማየቱ ነው። ማለትም ትንሹ ዓሊ (ቢራ) ትልቁን ዓሊ (ሸቦ) ስላየ ነው ወደ ከያኒነት የገባው። ትንሹ ዓሊ ጊታርን እንዳሻው መጫወትን የተማረውም ከትልቁ ዓሊ ነው።

ዓሊ ሸቦን ብዙዎቻችሁ የምታውቁት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ዱምቡሼ ገላ”ን በሸጎዬ ስልት ሲጫወተው ነው። ይህንን ዘፈን ማን እንደጻፈው በትክክል አላውቅም። ስለዚህ የአቡበከር ሙሳ ድርሰት ነው ብዬ ከዚህ አልጽፍም። ነገር ግን አቡበከር ሙሳ ከጻፋቸው የዓሊ ሸቦ ድርሰቶች መካከል የሚከተለው ዝነኛ ዘፈን ይጠቀሳል።
Asheeta shumburaa loosha bishaan biraa
Azeeba timira jannatni sibiraa.
ይህ አዝማቹ ሲሆን በአማርኛ እንዲህ ሊፈታ ይችላል።
የሽምብራ እሸት የወንዝ ዳር ቄጤማዋ
የቴምር ቀንበጥ አንቺ ነሽ መስኖዋ።

“ሲሲ” በጣም ዝነኛና ተወዳጅ ከሆኑ የኦሮምኛ ዘፈኖች አንዱ ነው። ይህ ዘፈን በብዙ አርቲስቶች እየተመላለሰ የተዘፈነ በመሆኑ በአሁኑ ዘመን የህዝብ ዜማ እየመሰለ ነው። ሆኖም የ“ሲሲ” ኦሪጂናሌ ዘፋኝ ኢብራሂም ዩሱፍ ይባላል። ይህ ሰው ከዓሊ ቢራ ጋር ወደ አፍረን ቀሎ ቡድን ከተቀላቀሉ ታዳጊዎች አንዱ ነበር። ከዓሊ ቢራ ጋር የቀረበ ጓደኝነት የነበረውም እርሱ ነው። ታዲያ ብዙዎች እርሱን የሚያውቁት “ሂሜ” በተሰኘው ቅጽል ስሙ ነው። ሂሜ በአፍረን ቀሎ ቆይታው ልብ የሚነኩ ጨዋታዎችን ተጫውቷል። በጥበብ አፍቃሪዎች ዘንድ የማይረሳው ተወዳጅ ስራው ግን “ሲሲ” ነው። የ“ሲሲ” አዝማች የሚከተለው ነው።
Sihi sihi siitu tiyya
As gori gori gama khiyya
Boochistee onnee tiyya
Boochiste dhiiga khiyya
እነኝህ ስንኞች ወደ አማርኛ ቢመለሱ እንደሚከተለው ሊሆኑ ይችላሉ።
አንቺ ነሽ አንቺ ነሽ አንቺ ነሽ የኔ
ወዲህ ጎራ በይ ነይ ወደኔ
አስለቀስሽው ልቤ ዳመነ
ደም አስለቀስሽኝ ወይኔ ወይኔ።

በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ እነ ሙሐመድ ወርዲን ያቀፈ የሱዳን የሙዚቃ ቡድን ለልምድ ልውውጥ ድሬ ዳዋ ወርዶ ነበር። በመሆኑም ሱዳናዊያኑ ዘፋኞች ከአፍረን ቀሎ ቡድን አባላት ጋር ዝግጅታቸውን በአንድ መድረክ ላይ ለማቅረብ ችለዋል። ከዚህም አልፎ ዜማና ግጥም እስከ መለዋወጥ ደርሰዋል። ለምሳሌ አቡበከር ሙሳ ወደ ኦሮምኛ ከቀየራቸው የሙሐመድ ወርዲ ዜማዎች መካከል ሁለቱን ላሳያችሁ።

ሙሐመድ ወርዲ “ያ ኑረል ዐይን” የተሰኘ ውብ ዜማ አለው። አዝማቹ የሚከተለው ነው።
ያ ኑረል ዐይን.. ያ ኑረል ዐይን
ያ ኑረል ዐይን ኢንታ ኢንታ
ዌን ዌን
አቡበከር በጻፈው ግጥም ዓሊ ቢራ ዜማውን እንዲህ ነበር የተጫወተው።
Ofii rafaa bultaa hirriba mi’aawaa
Ani hirriiba dhabee naaf himi mee dawaa

“ሱድፋ” የተሰኘው የሙሐመድ ወርዲ ዜማም በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ብዙዎች ያለመሰልቸት ከሚያዳምጡት ዘፈኖች መካከልም አንዱ ነው። የ“ሱድፋ” አዝማች የሚከተለው ነው።
ሱድፋ ሱድፋ
ሱድፋ ወአጅመል ሱድፈና የውም ላቄታ
አስዓድ የውም የውሚል ሐዬታ
ኑረ ዐይነይያ ያ መሓቤታ።

አቡበከር ሙሳ ይህንንም ዜማ ወደ ኦሮምኛ ቀይሮት አንጋፋው ዓሊ ሸቦ ተጫውቶታል። የዘፈኑ አዝማች የሚከተለው ነው።
Sirbaa sirbaa
Sirbaa sirbaa
Sirbi armaan loohii khoottu gama khiyya
Loohee sirbe sirbee loohee
Gamas loohi gamas loohi
Loohii sirbii sirbii loohi
Ani gama khee dhufuu khiyya.
*****
አቡበከር ሙሳ ከብዙ በጥቂቱ ይህ ነበር እንግዲህ! ይህ ሰው ነው በድሬ ዳዋ ከተማ በታሪክ ዘወትር የሚታወሰውን የአፍረን ቀሎን የኪነ-ጥበብ ቡድን የመሰረተው።

በ1958 የአፍረን ቀሎ ቡድን እንቅስቃሴውን በማስፋት በሌሎች የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞችም ዝግጅቱን ማቅረብ ጀመረ። ሆኖም እንቅስቃሴው በዘመኑ ገዥዎች ስላልተወደደለት ከፍተኛ እመቃ ይደረግበት ጀመር። በተለይም ቡድኑ በ1959 በዘመኑ ገንኖ በወጣው የመጫና ቱለማ ማህበር መሪዎች ተጋብዞ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ከተማ በማቅረቡ ገዥዎቹ ጥርሳቸውን ነከሱበት። በመሆኑም ያለ አንዳች ጥፋት የእገዳ ውሳኔ ተላለፈበት። ከቡድኑ አባላት መካከል የሚበዙት ወደ ሶማሊያና መካከለኛው ምስራቅ ተሰደዱ። ዓሊ ቢራና ጥቂቶች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ተፈናቀሉ። አቡበከር ሙሳ ግን ለጥቂት ዓመታት እዚያው ድሬ ዳዋ ውስጥ አደፈጠ።

በ1966 መጨረሻ ላይ የሀረር ሬድዮ ጣቢያ የኦሮምኛ ቋንቋ ስርጭት ሲጀምር አቡበከር ሙሳ በጣቢያው በፕሮግራም አዘጋጅነት ተቀጥሮ ነበር። በቦታው ላይ ለሶስት ዓመታት ከሰራ በኋላ ግን በሀምሌ ወር 1969 ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተገድሏል። ያ ሰው ሲሞት ሰላሣ አምስት ዓመት እንኳ አልሞላውም ነበር። በዚያች ትንሽ ጊዜ ውስጥ ነው በድሬ ዳዋ ከተማ የማይሞት ስሙን ጥሎ ያለፈው። ዛሬ አቡበከር ሙሳ የድሬ ዳዋን የኪነ-ጥበብ ጉዞ ከስረ-መሰረቱ ከቀየሩት ባለ ተጽእኖዎች አንዱ ሆኖ ይዘከራል።

(ማስታወሻ፡ ይህ ታሪክ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ዳዋ” ከተሰኘው የኔ መጽሐፍ የተቀዳ ነው)።

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...