Tidarfelagi.com

አይዳ ለምን ከግቢ እንዳትወጣ ተከለከለች ?

አባ በድሉ ‹‹ድግምተኛ ናቸው ››!!
ይቅርታ ‹‹ድግምተኛ ናቸው እየተባለ ይወራል !!

እኛ ሰፈር ስትመጡ በጎሚስታው ጋ ወደቀኝ ታጥፋችሁ ፒስታ መንገዷን (አሁን ኮብል ስቶን ተነጥፎበታል) እሷን ይዛችሁ ወደላይ ትንሽ እንደሄዳችሁ …. ዙሪያውን በግንብ የታጠረ የግንብ አጥሩ ደግሞ ሙሉውን ነጭ ቀለም የተቀባ ድርጅት የሚመስል ቤት ካያችሁ እሱ ድርጅትም ት/ቤትም ሆስፒታልም አይደለም ….የአባ በድሉ ቤት ነው !

(እኒህ ስማቸው ለማቀናጣት የማይመች ሰውየ) በነገራችን ላይ አባ በድሉ ሁሉ ነገራቸው ነጭ ነው ! ቤቱ ነጭ ልብሳቸው ነጭ ሚስታቸው ነጭ (ማለቴ ሁልጊዜ ነጭ ልብስ ነው የሚለብሱት) …መኪናቸው ነጭ በጎቻቸው ( ሰባት በጎች አሏቸው ከድሮ ጀምሮ ሰባት ናቸው አይሞቱ አይወልዱ ) ነጫጮች ‹‹ ያሰሩት ድግምት ጥላ አይወድም ቦጌ ነገር ነው›› ይባላል ! እንደውም ሌሊት ሌሊት ቤታቸውን ሰባት ነጫጭ ጅቦች ይከቡታልም ይባላል ! እንግዲህ ሰይጣናቸውም ነጭ መሆኑ ነው የሚወራው ! ‹‹ምንድን ነው እንዳባ በድሉ ንብረት ነጣህ ›› ይባላል ከናባባሉ !

ከህፃንነታችን ጀምሮ ወደትልቁና ዙሪያውን በግንብ ወደታጠረው ግቢያቸው ድርሽ እንዳንል እየተመከርን ስላደግን ከአጥሩም በላይ ‹‹ድግምቱ›› እያስፈራን እዛች ግድም አንደርስም ነበር ! ደግሞ ለክፋቱ በአጥሩ ላይ ተንዘርፍፎ እና ፍሬው የከበደው ቅርንጫፉ መሬት እስኪነካ አጎንብሶ ምራቃችንን የሚያስውጠን የኮክ ዛፍ አለ ! እኔማ ኮኩን በአይኔ ጭምቅ ሳደርገው ትሙክ ትሙክ ሲል ይሰማኛል አይኔ እጅ የሆነ ይመስለኛል ….እንደውም አንዳንዴ ፍሬው በራሱ ረግፎ መንገዳችን ላይ እንደጠጠር ይበተናል ( ሰይጣን ሲፈትነን ተመልከቱ )

አባ በድሉ ትልቅ ሆቴል ፣የላም እርባታ እና ከብት ማድለቢያ፣ ጭነት መኪናወች አሏቸው ወፍጮ ቤትም አላቸው ያውም ሁለት ! ከነዚህ ሁሉ ድርጅቶች በላይ ግን በድሉ ስጋቤትን ማንም ያውቀዋል ! እራሳቸው ከእርባታቸው የሚያመጧቸውን ሰንጋወች ስለሚያርዱ ኪሎ ብለው የሚሸጡት ስጋ ኪሎ ከተኩል ይሆናል …. እሳቸው ልኳንዳ ስጋ መግዛት ማለት ቅርጫ እንደመቃረጥ ይቆጠራል …. ግን ሰው ሁሉ እንዲህ አትረፍርፈው ቢሸጡለትም ስጋቸውን ብስል ከጥሬ ሰልቅጦ ጥግብ ሲል ‹‹ ሰላቢ ናቸው ›› ይላቸዋል !

አንድ ቀን ታዲያ እናቴን ጠየኳት
‹‹ ሰላቢ ከሆኑ ለምን ከሳቸው ስጋ ትገዣለሽ ? ››
‹‹ አትርፈው ከሚዛን በላይ ነው የሚሰጡት ኪሎ ብለሃቸው ኪሎ ከግማሽ ይሰጡሃል ግማሹን ቢሰልቡት ዋናው ይቀራል …ቢሆንም ስጋው እንደማንም ስጋ አንጆ እንዳይመስልህ ጠፍ ያለ ነው ›› እንግዲህ አዳሜ ጥሬ ከብስል የሚራኮትለት የአባ በድሉ ስጋ ሂሳቡ ይሄው ነው ! እኛ ኢትዮጲያዊያን እኮ አንዳንዴ ‹ፊዚክስ› የሆነች የስጋ ቀመር አለችን ! እስቲ አሁን ሰላቢ የሆነ ባለልንኳንዳ እና ሰላቢ ያልሆነ ባለልኳንዳ እንዲህ በቀመር አወዳድሮ ጥራትን እንደውጤት ቁጭ ማድረግ ማን አስተማረን ? ያውም ስልብናን የሚያስንቅ አንድ ኪሎ ጠፍ ያለ ጥራት !!

ታዲያ አባ በድሉ ድግምተኛ በመሆናቸው የማይፈራቸው ሰው የለም…. እንኳን የመንደሩ ሰው ከሩቅ ሰፈር ዝናቸውን የሰማ ሁሉ በግቢያቸው በር ሲያልፍ አረማመዱን ፈጠን አድርጎ ከአካባቢው ብን ብሎ ነው የሚጠፋው ! አንዳንዱ እንደውም አማትቦ ነው የሚያልፈው ! መቸም ከእግዚአብሄር ይልቅ ህዝቡ ሰይጣንን ‹‹በፍርሃት ስም ›› የሚያከብር ይመስለኛል ! እንዴት ማለት ጥሩ ነው …

እንግዲህ አባ በድሉ ቤት አጥሩን አልፎ መንገዱ ድረስ የተንዘራፈፈውን አስጎምጅ የኮክ ፍሬ ወድቆ ይበሰብሳል እንጅ አንድ ሰው ንክች አያደርገውም …አለፍ ብሎ የቄስ ለይኩን ቤት አለ (አባ ለይኩን ሀ ሁ ያስቆጠሩን የብዙወቻችን ቤተሰቦች የንስሃ አባት ) ትንሽ የኮክ ዛፍ አለቻቸው አጥራቸውን እየተንጠላጠልን እንጨፈጭፈዋለን ….ደግሞ እኮ እቤታቸው ድረስ ‹‹መስቀል እንሳለም›› በሚል ሰበብ ሂደን ነው ተሳልመን ስናበቃ ኮክ የምንሰርቀው !

ይህ ድርጊታችን ያስመረራቸው ወላጆቻችን ወደአባ ለይኩን ቤት እንዳንሄድ ሲከለክሉን ታምራት የሚባል ጓደኛችን ከየት እንዳመጣው እንጃለት ወላጆቻችን ላይ ቦንብ የሆነ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅስ አጣቀሰባቸው ‹‹ ህፃናትን ወደእግዚሃር ቤት እንሂድ ሲሉ አትከልክሏቸው …ከከለከላችኋቸው ግን እያንዳንድሽ ወላ እናት ወላ አባት ወላ አክስት (አክስቱ ጋር ነበር የሚያድገው) ሲሆል ትወረወሪያለሽ ልጀ አድነኝ ብትይ መስሚያችን ጥጥ ነው …..ማቲወስ ወንጌል …ምእራፍ ….ቁጥር…›› ወላጆቻችን በታምራት አፍ እግዜር የተናገራቸው ነበር የመሰላቸው !
‹‹ታዲያ የግዚሃር ቤት የት ነው ቤተስኪያን መስሎን …?›› አሉ በፍርሃት
‹‹ እንዴ ያው መስቀሉ ያለበት የትም መንፈሱ አለ ሁሉም ቦታ ቤቱ ነው …በተለይ ያባ ለይኩን ግቢ …›› ተከራከረ ጓደኛችን ታምራት አሸነፈ!
‹‹ መሄዱን ሂዱ ኮክ የሚባል ነገር ግን ትነኩና ዋ ….›› ተብለን እንድንሄድ ተፈቀደልን ! አባ ለይኩን ግቢ ስንገባ ጉዳዩ የአዳምና ሂዋን አይነት ሆነብን ‹‹ ወደግቢው ግቡ ከዛች የኮክ ዛፍ የነካችሁ ቀን ግን ወዮላችሁ …….››› ምን ዋጋ አለው እባብ የሆነ አምሮታችን ያሳስተናል ! ሌላም ቀን ያው ነው ፡፡

አባ ለይኩን ታዲያ ኮካቸው መጨፍጨፉን ለወላጆቻችን ቢናገሩ ለፖሊስ ቢናገሩ ማን ይፍራቸው…. ቢጨንቃቸው ‹‹ ከዛሬ የካቲት 27 ቀን ጀምሮ ይችን ኮኬን የሚነካ ገዝቸዋለሁ ይሄው በለተ ቀኑ ማልኩ መድኃኒያለምን ›› አሉ … ወይ ፍንክች !! እንደውም ባሰብን ! አባ ለይኩን አጥራቸውን ለማስከበር ድግምተኛ አይሆኑ ነገር ቢቸግራቸው ከእግዜር ከምጣላ ብለው ኮኩን ከስሩ በመጥረቢያ ቆርጠው ማገዶ አደረጉት ! አዘንን ! መንገድ ላይ ካላጋጠሙን ቤታቸው ድረስ ሂደን መስቀል መሳለሙንም ተውነው ! ታዲያ እናቴ አንዳንዴ ነገር ስትፈልገኝ ከንፈሯን ሸርመም አድርጋ ፊቷ ላይ ሊፈነዳ የተዘጋጀ ሳቅ ደመናውን አዝሎ ….እንዲህ ትላለች

‹‹ አቡቹ ምነው ህፃናት ከእግዚአብሄር ቤት ቀሩ ? ››
‹‹እ ›› እላታለሁ እንዳልሰማ
‹‹ ….እግዜር የኮክ ዛፍ የሆነበት ትውልድ በረከቱ ጎደል ሲልበት ድራሹ ነው የሚጠፋው … ሂሂሂ ›› እናቴ ታበሳጨኛለች እግዚአብሄርን እወደዋለሁ ኮክንም የፈጠረው እራሱ እግዚአብሄር ነው አይደል እንዴ … ታዲያ ……..እያልኩ ለብቻየ አስባለሁ …ደግሞ እግዚአብሄር …ምንድን ነበር ስሙ ………………አዎ ‹‹እፀ በለስ ሲፈጥር›› የፈለጋችሁትን ብሎ ከዚች ዛፍ ፍሬ ብቻ እንዳትበሉ ነበር ያለው …..እኛ ሰፈር ግን ካባ ለይኩን ግቢ ኮክ እንዳትበሉ ተባልን …ከአባ በድሉ ግቢም ኮክ እንዳትነኩ ተባልን እዛ ታች ሰፈር እማማ ያምሮት ግቢ ደግሞ ኮክ አለ ግን እንኳን ግቢው ጋ ደርሰን ገና ከቤታችን ሳንነሳ የሚጮሁብን አደገኛ ሶስት ውሾች አሏቸው !(እስኪ አሁን ሶስት ውሻ ምን ይሰራላቸዋል )

አባ በድሉ በቁንጅና (((ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ))) የሆነች ውብ ልጅ አለቻቸው (አይዳ ነው ሰሟ) ….ግን ከግቢ አትወጣም ‹‹…አይዳ ከግቢ ከወጣች ሃብታቸው ሁሉ እንደጤዛ ይተናል ቢሞቱ ከግቢ አያስወጧትም …አስደግመውባታል ! ›› እየተባለ ይወራል እንደውም የሰፈሩ ሰው ሁሉ ቁንጅና የሚለካው በአይዳ ነው …..‹‹ ቁንጅና ይብቃ ይከተት በአይዳ በድሉ ›› ይባላል ! ታዲያ ይህች አይዳ ድሮ ተረት ትመስለኝ ነበር ሲቆይ ግን የእውነትም ከቤት እንዳትወጣ የተፈረደባት ውብ ልጅ መሆኗን አረጋገጥኩ ….

እንደውም አንድ ቀን የአባ በድሉ ነጭ መኪና ልትገባ የግቢው ብረት በር ሲከፈት እኔ እግር ጥሎኝ በዛ ሳልፍ አይዳ ጋር አይን ለአይን ተገጣጠምን በስስስስስስስስስስስስስስስስስስማም ውበት ! በዛች ቅፅበት የግቢ በር ለመኪና ተከፍቶ እስከሚዘጋ ባለች ቅፅበት ልብ ላይ መታተም የሚችል ውበት ያላት ብቸኛ ሴት ሳትሆን አትቀርም አይዳ (ወይስ ሰው የተደበቀ ነገር ስለሚያጓጓው ) … አይዳን ከዛ በኋላ ለድፍን ሁለት አመታት አላየኋትም !

ከሁለት አመታት በኋላ ግን እኔ እና አይዳን በቅርበት በጣም በቅርበት የሚያገናኝ ነገር ተፈጠረ !! በዚህ አጋጣሚ አይዳን ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርበት ለማናገር የቻልኩ የውጭ ወንድ እኔ ብቻ ነኝ ! እድሌ ይገርመኛል ….ባ,ንድም በሌላም አጋጣሚ ‹‹ክልክል›› የተባለ ቦታ ላይ መገኘት ለምን እጣ ክፍሌ እንደሆነ አይገባኝም ! ገና የአንደኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ለተማሪ ፈፅሞ የተከለከለ የሚባል የአስተማሪወች ልብስ መቀየሪያ ክፍል ውስጥ እግር ጥሎኝ ተገኝቸ ወላጅ ጠርቻለሁ …..

አንድ ቀን ደግሞ ኳስ እያሳደድኩ ሰፈራችን የሚገኝ አንድ ታላቅ ባለስልጣን ግቢ ውስጥ በአጥር ዘልየ ገባሁ ….ባለስልጣኑ በረንዳ ላይ ተቀምጠው ጋዜጣ እያነበቡ ነበር ….እኔን የሚያክል ልጃቸው በጭቃ የጨቀየ የጨርቅ ኳሴን እንደአንዳች ተአምር እያያ ቁሟል ጭራሽ አመዴ ቡን ያለ ጭቃ በጭቃ የሆንኩ እኔ በአጥር ዘልየ መየመአዘኑ ዛኒጋባቸው ላይ መትረየስ ደግነው የቆሙ ጥበቃወችን አልፌ ባለስልጣኑ ፊት ቆምኩ ….ቱታ እና ሰንደል ጫማ ነበር የለበሱት…. ባለስልጣኖች ሲወለዱ ጀምሮ እስከሚሞቱ ሱፍ የሚለብሱ ነበር የሚመስለኝ ገረመኝ …ታዲያ እኒህ ባለስልጣን ሰውየ በግርምት ተመለከቱኝና

‹‹ ማሙሽ ምን እግር ጣለህ ›› ሲሉ ፈገግ ብለው ወደተቀመጡበት ጠሩኝ ሄጀ አጠገባቸው ቆምኩ እየሳቁ ጨበጡኝ ከዛም ነጭ ሽርጥ ያሸረጠች ሴትዮ ጠሩና ለስላሳ እንድታመጣልኝ ነገሯት ደስ ብሎኝ ጠጣሁ ….ልጃቸውም ጋር ልባችን እስኪጠፋ ጭቃ በነካችው የጨርቅ ኳሴ ተራገጥን ……ቆይቸ ሲበቃኝ ባለስልጣኑ ሁልጊዜ ቅዳሜ እየመጣህ ተጫዋቱ ብለው ፈቀዱልኝ …በቃ ከሰኞ እስከአርብ ኢትዮጲያዊ ሁኘ ቅዳሜ ………አስከብዙ ጊዜ ድረስ ቤተኛ ሁኘ ነበር …….. ዛሬም ድረስ ልጃቸው ጋር አልፎ አልፎ እንደዋወላለን !

ይሄው ዛሬ ደግሞ የፖለቲካ ሳይሆን ሰይጣናዊ ስልጣን አላቸው እየተባሉ የሚፈሩት አባ በድሉ ቤት …..ጣለኝ …….እጣ ፋንታየ !!

3 Comments

 • bekilegesse10@gmail.com'
  ቤኪ ለገሰ commented on November 6, 2016 Reply

  አረ አሌክሶ suspense አደረከው

 • Sifenmamo@gmai.com'
  ሲፈን ማሞ commented on December 12, 2017 Reply

  ምነው ምነው ሌቤን እንዲሀ አንሳፈክ አስቀረከው እኔ ምንም አልልም ፈጣሪ ይይልክ !!!

 • solomon215mekonnen@gmail.com'
  ሰለሞን መኮንን commented on September 4, 2018 Reply

  ሁሌ ፅሁፎችህ መጨረሻቸው ያናድዳሉ፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...